የ1ኛ ቆሮንቶስ ልዩ ባሕርያት፣ መዋቅር እና ርእሰ ጉዳዮች

፩. የ1ኛ ቆሮንቶስ ልዩ ባሕርያት

  1. አብዛኛው የ1ኛ ቆሮንቶስ ክፍል የተለመደው ዓይነት ደብዳቤ ሳይሆን ችግሮችን የሚያንጸባርቅ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለሆነም፥ ከዳር እስከ ዳር ጎልቶ የሚታይ ጭብጥ ከመያዝ ይልቅ (የሮሜ መልእክት በድነት ላይ እንደሚያተኩር)፥ የቆሮንቶስ መጽሐፍ በቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮችና ጥያቄዎች ላይ ያተኩራል።
  2. 1ኛ ቆሮንቶስን ማንበብ አንድ ሰው በስልክ ሲነጋገር እንደ መስማት ነው። ከአጠገባችን ያለው ሰውዬ የሚናገረውን ልንሰማ ብንችልም፥ ከሌላኛው የስልኩ ጫፍ ያለው ግለሰብ የሚያነሣቸውን ጥያቄዎች ወይም ሃሳቦች ልንሰማ አንችልም። ስለሆነም፥ የዚያ ሰውዬ ጥያቄዎችና የነበረበት ሁኔታ ምን ዓይነት እንደሆኑ መገመት ይኖርብናል። በ1ኛ ቆሮንቶስ፥ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ችግሮች የሰጣቸውን መልሶች ብንመለከትም፥ ችግሮቹ የተነሡባቸውን ዝርዝር ሁኔታዎች ግን አናውቅም። ለምሳሌ፥ ጳውሎስ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን እንዳይናገሩ ወይም ራሶቻቸውን እንዲከናነቡ ያዘዘው ለምን ነበር? ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አንድ ችግር እንደነበረ ቢያሳይም፥ በትክክል ምን እንደሆነ አናውቅም። ጳውሎስ ምላሽ የሚሰጠው ለእንደነዚህ ዓይነት በጊዜው ለተከናወኑ ዝርዝር ጉዳዮች በመሆኑ፥ ይህን ክፍል በምንተረጉምበትና ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር በምናዛምድበት ሁኔታ ላይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ዛሬ የምንጋፈጣቸው ችግሮች ከቆሮንቶስ የተለዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ፥ የጳውሎስ ዝርዝር ትምህርቶች ከዛሬው ሁኔታችን ጋር እንደሚስማሙ ከመገመት ይልቅ መርሆችን መፈለግ ይኖርብናል። ለምሳሌ፥ ዛሬ ሴቶች ጸጉራቸውን መሸፈናቸው የተለየ ዓላማ ካለውና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ዓይነት ሁኔታ የማያስከትል ከሆነ፥ ዛሬም ይህንኑ ደንብ መከተል አለብን? ብዙ ክርስቲያኖች የለብንም ይላሉ።

፪. የ1ኛ ቆሮንቶስ መዋቅር

የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ሊጎበኙት ከመጡት ሰዎች የሰማቸውን ጉዳዮች በማስመልከት ከምዕራፍ 1-6 ያለውን አሳብ ጽፎአል። ጳውሎስ ከዚህ ቃላዊ ዘገባ ተነሥቶ ስለ ክፍፍል፥ በጥበብ ላይ ስለሚደረግ የተጋነነ ትኩረት፣ ስለ ራሱ ሐዋሪያዊ ሥልጣን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚታይ ወሲባዊ እርኩሰትና ስለ አማኞች መካሰስ ምላሽ ሰጥቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 1፡11፥ 19፤ 5፡1፤ 6፡1፤ 7፡1፤ 8፡1፤ 11፡3፤ 12፡1፤ 15፡1፤ 16፡1 አንብብ፡ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የዘገባና የደብዳቤ ምላሽ በመስጠት ያነሣቸውን ጉዳዮች ዘርዝር።

ሁለተኛ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 7-16 የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ባቀረቧቸው የተወሰኑ ጥያቄዎች ላይ ያተኩራል። (1ኛ ቆሮ 7፡1 አንብብ።) ጳውሎስ አዲስ ጉዳይ በሚጀምርበት ጊዜ «ስለ . . .» የሚል መስተዋድድ ስለሚጠቅም (1ኛ ቆሮ. 7፡1፥ 25፤ 11፡3፤ 12፡1፤ 16፡1)፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥያቄዎችና መልሶች በቀላሉ መለየት ይቻላል። ጳውሎስ በምላሹ ስለ ጋብቻ፥ ለጣዖት የተሠዋን ሥጋ ስለ መብላት፥ ስለ ሴቶች አለባበስ፥ ስለ ቅዱስ ቁርባን፥ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ ስለ አማኞች ትንሣኤና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ድሆች ስለሚሰጠው እርዳታ አብራርቷል።

፫. የ1ኛ ቆሮንቶስ ርእሰ ጉዳዮች

I. መግቢያ (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9)

II. ክፍል አንድ፤ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳሉ የተገለጹ ችግሮች (1ኛ ቆሮ. 1፡10-6፡20)

  1. የመጀመሪያው ችግር፤ የቤተ ክርስቲያን ክፍፍል (1ኛ ቆሮ. 1፡10-4፡21)

ሀ. ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ክፍፍል የመኖሩን እውነታ ያስተዋውቃል (1ኛ ቆሮ. 1፡10-17)

ለ. ስለ ዓለማዊ ጥበብና በክርስቶስ መስቀል በተገለጠው የመንፈሳዊ ጥበብ መካከል ያለውን ልዩነት ጥርት አድርጎ አለማወቅ ክፍፍልን ያስከትላል (1ኛ ቆሮ. 1፡18-2፡14)

ሐ. የተለያዩ ሰዎችን ከመከተል የሚመጣው ክፍፍል መሪዎችን እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች የሚያበረክቱትን ድርሻ በተሳሳተ መንገድ እንድንረዳ ያደርጋል (1ኛ ቆሮ. 3)

መ. የሐዋርያነትን ምሳሌነት በመከተል ክፍፍልን ማሸነፍ (1ኛ ቆሮ. 4)

  1. ሁለተኛው ችግር፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተ የሥነ ምግባር ብልሹነት (1ኛ ቆሮ. 5፡1-12)
  2. ሦስተኛው ችግር፤ የአማኞች በችሎት ፊት መካሰስ (1ኛ ቆሮ. 6፡1-8)
  3. ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚከሰት ወሲባዊ ኃጢአት ያቀረበው ተጨማሪ ትምህርት (1ኛ ቆሮ. 6፡9-20)።

III. ክፍል ሁለት፤ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጥያቄዎች የሰጣቸው መልሶች (1ኛ ቆሮ. 7፡1-16፡4)።

  1. 1ኛ ጥያቄ፡- ክርስቲያን ሊያገባ ወይስ ብቻውን ሊኖር ይገባል? (1ኛ ቆሮ 7)
  2. ሁለተኛ ጥያቄ፡- ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ሊበላ ይገባል? (1ኛ ቆሮ. 8-11፡1)

ሀ. የመብላት ነጻነት ለሌሎች ክርስቲያኖች ባለን ፍቅር መወሰን አለበት (1ኛ ቆሮ. 8)

ለ. ጳውሎስ ነጻነትን ስለ መገደብ ከራሱ ሕይወት የሰጠው ምሳሌ (1ኛ ቆሮ. 9)

ሐ. ከብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን ታሪክ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (1ኛ ቆሮ. 10፡1-13)

መ. በምግብ አማካኝነት የጣዖት አምልኮ ተካፋይ እንዳይሆኑ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (1ኛ ቆሮ. 10፡14-22)።

ሠ. ክርስቲያን ለሌላው ክርስቲያን ካለው ፍቅር የተነሣ ከምግብ ለመታቀብ ወይም ምግብ ለመብላት ስለሚኖረው ነጻነት ጳውሎስ የሰጣቸው ዝርዝር መመሪያዎች (1ኛ ቆሮ. 10፡23-11፡1)።

  1. ሦስተኛ ጥያቄ፡- ወንዶችና ሴቶች በአምልኮ ስብሰባ ላይ ምን ዓይነት ልብስ መልበስ ይኖርባቸዋል? (1ኛ ቆሮ. 11-14)
  2. አራተኛ ጥያቄ፡- በቅዱስ ቁርባን ላይ ሊኖር የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)።
  3. አምስተኛ ጥያቄ፡- የመንፈሳዊ ስጦታዎች፥ በተለይም የልሳን ዓላማ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 12-14)።

ሀ. ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የሚሰጡ የተለያዩ ስጦታዎች አሉ (1ኛ ቆሮ. 12)።

ለ. መንፈሳዊ ስጦታዎችን የምንጠቀምበት ዓላማ ፍቅርና ለሌሎች ክርስቲያኖች ማሰብ ሊሆን ይገባዋል (1ኛ ቆሮ. 13)።

ሐ. ትንቢት በልሳን ከመናገር ለምን እንደሚሻል (1ኛ ቆሮ. 14፡1-12)።

መ. ስለ ልሳን፥ ትንቢትና በጉባዔ ውስጥ ስለሚደረግ የሴቶች ንግግር የተሰጠ መመሪያ (1ኛ ቆሮ. 14፡13-40)።

  1. ስድስተኛ ጥያቄ፡- አንድ አማኝ ከሞተ በኋላ ሥጋው ምን ይሆናል?(1ኛ ቆሮ. 15)
  2. ሰባተኛ ጥያቄ፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አይተዋቸው ለማያውቋቸው የአይሁድ ክርስቲያኖች ገንዘብ መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 16፡1-4)

IV. መደምደሚያ፡- (1ኛ ቆሮ. 16፡5-21)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d