ጳውሎስ መልእክቱን ለማን ጻፈ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮ. 1፡2 እንብብ። ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈው ለማን ነበር? ለ) ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዴት ነው የገለጻት? ሐ) ይህንን ከሮሜ 1፡7 ጋር አነጻጽር። ይህ ጳውሎስ የሮሜን ቤተ ክርስቲያን ከገለጸበት ሁኔታ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰልና እንደሚለያይ አብራራ። መ) የሐዋ. 18፡1-11ን አንብብና ቤተ ክርስቲያኒቱ መጀመሪያ እንዴት እንደተመሠረተች ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

ጳውሎስ የጥንታዊ ደብዳቤዎችን አጻጻፍ በመከተል ጸሐፊነቱን ከገለጻ በኋላ ደብዳቤውን ለማን እንደሚጽፍ ጠቅሷል። ጳውሎስ፥ «በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት» ብሏል። ከዚህ ገለጻ አራት ነገሮችን ልንመለከት እንችላለን።

  1. ደብዳቤው የተጻፈው ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ነበር። ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቃል ስንሰማ ሰዎች ስለሚያመልኩበት ሕንፃ እናስባለን። ለዚህም ነው በአማርኛ ቋንቋ «ቤተ ክርስቲያን» (የክርስቲያን ቤት) የሚባለው። ሌሎች ደግሞ «የጸሎት ቤት» ይሉታል። በባሕላችን፥ የቤተ ክርስቲያኑ አስፈላጊነት የሚለካው በቤቱ ትልቅነት ነው። ለዚህም ነው የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎቻቸውን ሁሉም ሰው ሊያይ በሚችልባቸው ደብሮች ላይ የሚሠሩት። የሕንጻዎቹ ማማርም የቤተ ክርስቲያኑን አስፈላጊነት ያጎላዋል ብለው ያስባሉ። ወንጌላውያን ክርስቲያኖችም በሕንፃ ላይ ያተኩራሉ። በቤት ወይም ከቤት ውጭ በመጠለያ ውስጥ ተሰባስቦ ማምለኩ የትንሽነት ስሜት የሚያሳድር ይመስላቸዋል። ይህ ደግሞ መሬት አግኝተው የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እስኪገነቡ ድረስ ለጊዜው ብቻ የሚጠቀሙበት አማራጭ ነው። የሣር ቤት ካለን ወደ ቆርቆሮ ቤት ለመለወጥ ጥረት እናደርጋለን። ሕንፃው ትልቅ በሚሆንበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑም የበለጠ አስፈላጊ ይመስለናል። እንደዚህ ሲሆን ሰዎች ለአምልኮ ይመጣሉ ብለን እናስባለን።

በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግን እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ አልነበረም። «ቤተ ክርስቲያን» ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል የትኛውንም ዓይነት የሰዎች ስብስብ ያመለክታል። መንግሥት ሕዝቡን በሚሰበስብበት ጊዜ ስብሰባው «ቤተ ክርስቲያን» ተብሎ ይጠራ ነበር። ስለሆነም፥ እንደ ጳውሎስ ያሉ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ይህን ቃል የሚጠቀሙት የክርስቶስን ተከታዮች ለማመልከት ነበር። የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች የተሠሩት ክርስቶስ ከሞተና ከተነሣ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ በመሆኑ፥ የጥንት ክርስቲያኖች የሚሰባሰቡት በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ነበር።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ «ቤተ ክርስቲያን» የሚለው ቃል በሦስት ዐበይት መንገዶች ይተረጎማል። በመጀመሪያ፥ የአንድ አካባቢ አማኞች በግለሰቦች ቤት ውስጥ ይሰባሰቡ ነበር። በሮሜ 16፡5 ጳውሎስ በጵርስቅላና አቂላ ቤት ውስጥ ስለምትሰባሰብ ቤተ ክርስቲያን ጽፎአል። ሁለተኛ፥ በአንድ አካባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ይባሉ ነበር። ምንም እንኳ በቆሮንቶስ የሚገኙ ክርስቲያኖች በተለያዩ ቤቶች እየተሰባሰቡ ያመልኩ የነበረ ቢሆንም፥ ጳውሎስ ለሁሉም ባስተላለፈው መልእክት «ለቆሮንቶስ» ሰዎች የሚል አገላለጽ ተጠቅሟል። ሦስተኛ በዓለም ውስጥ የሚገኙትን አማኞች በሙሉ ያመለክታል። ይህም አንዳንድ ጊዜ «ዓለም አቀፋዊው ቤተ ክርስቲያን» የሚባለው ነው (ኤፌ. 1፡22)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ኢትዮጵያውያን ለአምልኮ ጥሩ ሕንፃ ያስፈልጋል ብለው የሚያስቡት ለምንድን ነው? ለ) ይህንን አመለካከት ከአዲስ ኪዳን ዘመን ሁኔታ ጋር አነጻጽር። ሐ) ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ መፈለጋችን ጥሩ ይመስልሃል ወይስ መጥፎ? መልስህን አብራራ።

  1. የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን። ለጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የግለሰብ፥ የክርስቲያኖች ቡድን ወይም የቤተ እምነት ሳትሆን የእግዚአብሔር ናት። ቤተ ክርስቲያንን በክርስቶስ ደም የገዛት እግዚአብሔር ነው። ክርስቲያኖችን የሚጠራቸው እግዚአብሔር ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ ወደ አማኞች ኅብረት ውስጥ ይጨምራቸዋል። ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቤተ ክርስቲያን የእነርሱ ንብረት እንደሆነች ያስባሉ። «ቤተ ክርስቲያኒቱ በእኔ መሬት ላይ ነው የቆመችው። ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ገንዘብ ሰጥቻለሁ» ይላሉ። መሪዎች አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የእነርሱ እንደሆነችና ያሻቸውን ሊያደርጉባት የሚችሉ ይመስላቸዋል። ባለቤቷ ለሆነው ለክርስቶስ የሚሠሩ መጋቢያን ብቻ የመሆናቸውን እውነታ ይዘነጋሉ። እርሱም ቤተ ክርስቲያኑን ስላስተዳደሩበት ሁኔታ አንድ ቀን ይጠይቃቸዋል። መሪዎች ቤተ እምነታቸው ብዙ ክብር እንዲያገኝ ይጥራሉ። ቤተ እምነታቸው የፈለጉትን ያህል ክብር ሳያገኝ ሲቀር ወይም አባሎቻቸው የሌላ ቤተ ክርስቲያን አባላት በሚሆኑበት ጊዜ ይቀናሉ። ጳውሎስ ግን የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ሲመሠርታትም እንኳ የእርሱ ንብረት እንዳልሆነች ያውቅ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ ሙሉ ለሙሉ የእግዚአብሔር ንብረት ስለሆነች፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ሊያስከብር ይገባል። ለግል ወይም ለቤተ እምነት ክብር መሥራት አያስፈልጋቸውም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ሳትሆን የእኛ ናት ብለን የምናስበው ለምንድን ነው? ለ) የየትኛውም ቤተ እምነት ተከታይ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ የእግዚአብሔር እንደሆነ ብናስብ አመለካከታችን እንዴት ይቀየራል?

  1. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በክርስቶስ ተቀድሰዋል። ጳውሎስ በኃላፊ ጊዜ ግስ እየተናገረ መሆኑን አጢን። ጳውሎስ ወደፊት እንደሚቀደሱ ሳይሆን ቀደም ሲል እንደተቀደሱ ገልጾአል። ጳውሎስ የሚጽፍላቸው እነዚህ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ሕይወት ይኖሩ ነበር? ትክክለኛውን የቅድስና ፍች የሚያንጸባርቅ ሕይወት ይመሩ ነበር? አልነበረም። የወሲብ ኃጢአት፥ ክፍፍል፥ የጌታን እራት አግባብነት በጎደለው ሁኔታ የመመገብ ኃጢአቶች ነበሩባቸው። እንዲያውም አንዳንዶች በጌታ እራት አወሳሰድ ላይ በፈጸሙት ጥፋት የሞትና የሕመም ቅጣት ደርሶባቸው ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ በራስ ወዳድነት ተሞልታ ነበር። ይህም ሆኖ፥ ጳውሎስ «ተቀድሰዋል» ብሏል። ለምን? ምክንያቱም መቀደስ ማለት መለየት ማለት ነው። እግዚአብሔር በቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ መካከል ልጆቹ እንዲሆኑለት መርጧቸዋል። እንደ ልጆቹ ተመላለሱም አልተመላለሱ፥ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ከዓለም የተለዩ ልጆቹ ናቸው።
  2. ቅዱሳን ለመሆን ተጠርተዋል። ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች ከብዙ ችግሮች ጋር ቢታገሉም፥ እግዚአብሔር በሕይወታቸው ለመሥራት የሚፈልግበት ዓላማ ነበረው። ጳውሎስ እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ በቅድስና እንዲኖሩ የሚፈልግ መሆኑን ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ገልጾላቸዋል። ቢቀደሱ ኖሮ ክፍፍላቸው፥ የወሲብ እርኩሰታቸው፥ ራስ ወዳድነታቸው፥ ወዘተ… ይለወጥ ነበር። ጴጥሮስ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ፥ እኛም በቅድስና እርሱን እንድንመስል ጠይቆናል (1ኛ ጴጥ. 1፡15–16)። መቀደስ ማለት ኃጢአትን አለመሥራት ማለት ብቻ አይደለም። መቀደስ ማለት መለየትና ልዩ መሆን ማለት ነው። ይህም በአመለካከታችን፥ በዓላማችን፥ በባሕሪያችንና በተግባራችን ከዓለም መለየታችንን ያሳያል። ይህ ክርስቶስን የምንመስልበትና እንደ እርሱ የምንመላለስበት ሕይወት ነው። እግዚአብሔር ከልጆቹ ሁሉ የሚፈልገው ይህንን ነው። አንድ ሰው አማኝ ነኝ እያለ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያሳይ በተከታይ በኃጢአት ውስጥ የሚመላለስ ከሆነ፥ ድነቱን (ደኅንነቱን) ልንጠራጠር እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር አንተን ከጠራባቸው ምክንያቶች አንዱ እርሱን እንድትመስልና እንድትቀደስ ነው። ሀ) ክርስቲያን ከሆንህ በኋላ ክርስቶስን ለመምሰልና ለመቀደስ የለወጥሃቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) በተግባርህና በአስተሳሰብህ አሁንም ክርስቶስን እንዳትመስል የሚከራከሩህ ያልተቀደሱ ነገሮችህ ምንድን ናቸው? አሁን ጊዜ ወስደህ እነዚህን ኃጢአቶች ተናዘዝና መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን ትመስል ዘንድ እንዲለውጥህ ጠይቀው።

የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ተመሠረተች? ጥንታዊቷ የቆሮንቶስ ከተማ ምን ትመስል ነበር? በሐዋርያት ሥራ 18 እንደተገለጸው፥ ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኛነት (ሚሲዮናዊ) ጉዞው ወደ ቆሮንቶስ ከተማ ሄደ። በዚያም ለ18 ወራት ሲሰብክና ቤተ ክርስቲያን ሲተክል ቆየ። ቆሮንቶስ ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኛነት ጉዞው ወቅት የቆየባት ዐቢይ ከተማ ነበረች። በዚህ ጊዜ ነበር እግዚአብሔር ጳውሎስ ብዙ አይሁዶችንና አሕዛብን፥ በተለይም ግሪኮችን ወደ ክርስቶስ እንዲመልስ የተጠቀመበት። አብዛኞቹ ግሪኮች በግሪክ ፍልስፍናና ትምህርት ይደነቁ ስለነበር፥ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ጥበብ ጋር ሲነጻጸር የዓለም ጥበብ ሞኝነት እንደሆነ ገለጸላቸው (1ኛ ቆሮ. 1፡18–2፡16)። ነገር ግን አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ከሀብታሞች ወይም ከተማሩት ወገን የመጡ ሳይሆኑ፥ ድሆች፥ ያልተማሩና ምናልባትም ባሮች ነበሩ (1ኛ ቆሮ. 1፡26-28)። በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኛነት ጉዞው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ተመልሶ 3 ወራት በዚያ አሳልፎአል።

ጳውሎስ ወንጌልን በሰበከበት ወቅት የወንጌሉ ንጹሕነት ከሰዎች የክፋት ሥራ ጋር ግጭት ሊፈጥር ችሏል። ቆሮንቶስ በሮሜ የእካይያ ክፍለ ሐገር ዋና ከተማ ነበረች። ቆሮንቶስ በአያሌ ነገሮች የታወቀች ከተማ ነበረች።

ሀ. ትልቅ ከተማ ነበረች። በከተማዪቱ ውስጥ 250,000 ነፃ ሰዎችና 400,000 ባሪያዎች ይኖሩ እንደነበረ ይገመታል።

ለ. ዋነኛ የንግድ ከተማ ነበረች። ቆሮንቶስ ሁለት ውኃማ አካላትን በምትከፍል አነስተኛ ሰርጥ ውስጥ የተመሠረተች ከተማ ነበረች። በስተምሥራቅ ወደ እስያና መካከለኛው ምሥራቅ የሚወስድ የኤጂያን ባሕር ነበር። በስተምዕራብ የአድሪያቲክ ባሕርና ወደ ሮም የሚወስድ መንገድ ነበር። ይህም የሮም ግዛት እምብርት ነበር። ከሮም ወደ ምሥራቅና እስያ የሚሄዱ ነጋዴዎች ሁሉ በቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ ይገናኙ ነበር። ብዙውን ጊዜ ባለመርኮበች አደገኛ በሆነው የብስ ዙሪያ ከመጓዝ ይልቅ ዕቃዎቻቸውን በቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ ያራግፉ ነበር። ዕቃው ወደ ሌላው የመሬቱ ሰርጥ 8 ኪሎ ሜትሮች ያህል ከተጓዘ በኋላ በሌላ ጀልባ ይጫናል። ይህም ቆሮንቶስ የንግድ ቀጠና እንድትሆን አድርጓታል።

ሐ. ቆሮንቶስ የፍቅር ጣዖት የሆነችው የአፍሮዳይት አምልኮ እምብርት ነበረች። ምንም እንኳ በከተማዪቱ ውስጥ ቢያንስ ሌሎች 11 ቤተ ጣዖታት የነበሩ ቢሆኑም፥ አፍሮዳይት ከሁሉም የላቀ ዝና ነበራት። በተራራው ጫፍ ላይ ታላቅ ቤተ ጣዖት ተሠርቶላት ነበር። ሰዎች ይህችን የፍቅር ጣዖት የሚያመልኩት እንዴት ነበር? ከቤተ ጣዖት ጋለሞታዎች ጋር ወሲብ በመፈጸም ነበር የሚያመልኳት። በቤተ ጣዖቱ ውስጥ ከ1000 የሚበዙ ጋለሞታዎች ይገኙ እንደነበር ይገመታል።

መ. ቆሮንቶስ እንደ አቴና ዓይነት የዩኒቨርስቲ ከተማ ባትሆንም፥ ፈላስፎችና የተማሩ ሰዎች አዳዲስ ፍልስፍናዎችን የሚወያዩበት ከተማ ነበረች።

ሠ. ምንም እንኳ ሰዎች ሁሉ ክፉዎች ቢሆኑም፥ ብዙ ሰዎች በሚሰባሰቡበት ጊዜ ክፋት ይጨምራል። በንግድ እምብርት ውስጥ ደግሞ ክፋት ገደቡን የሚያጣ ይመስላል። ቆሮንቶስ በሮም ግዛት ሁሉ ዋነኛ የክፋት ተግባራት መዲና ሆና ትታወቅ ነበር። እንዲያውም፥ አንድ ሰው የተበላሸ ወሲባዊ ባሕርይ በሚያሳይበት ጊዜ ሰዎች «ቆሮንቶሳዊ» ብለው ይጠሩት ነበር። በዚህች የክፋት ከተማ ነበር ወንጌሉ ሥር የሰደደው። ጳውሎስ አብዛኞቹ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንደ ሌላው ቆሮንቶሳዊ ሁሉ ጣዖትን በማምለክ፥ ግብረሰዶማዊነትን በማካሄድ፥ ወንድና ሴት የቤተ ጣዖታት ጋለሞታዎች በመሆን፥ በመስረቅ፥ በመስከር፥ ወዘተ. ኃጢአቶችን ያደርጉ እንደነበረ ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 6፡9-11)። የሚያሳዝነው ዛሬ ብዙ ሰዎች ክፉዎች ከሚመስሉ ሰዎች ይርቃሉ። ለመመስከር የምንፈልገው ለተከበሩት ሰዎች ብቻ ነው። ይህም የወንጌሉ ኃይል ሰዎችን ከሁሉም ዓይነት ክፋት ነፃ እንደሚያወጣና ክርስቶስም መንፈሳዊ በሽታ ያለባቸውን እንጂ ጤነኞችን ለመርዳት እንዳልመጣ መዘንጋታችንን ያሳያል (ማቴ. 9፡12)።

ጳውሎስ አብረውት የሚሠሩትን ሁለት ባልደረቦቹን (ጢሞቴዎስንና ሲላስን) በፊልጵስዩስና ተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ትቶ ወደ ቆሮንቶስ ሲሄድ ጵርስቅላና አቂላ የተባሉትን ሁለት አይሁዶች አገኘ። ብዙውን ጊዜ ጳውሎስ አገልግሎቱን የሚጀምረው በምኩራብ ውስጥ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን አይሁዶች በጳውሎስ ላይ በተቃውሞ በመነሣታቸው ምኩራቡን ትቶ በኢዮስጦስ ቤት ውስጥ ማገልገል ጀመረ። የአይሁድ የምኩራብ አለቃ የነበረውን ቀርስጶስ ጨምሮ አንዳንድ አይሁዶች ወደ ክርስቶስ ተመለሱ። በጃስተስ ቤት ውስጥ እያለ በአገልግሎቱ ላይ ለውጥ ተከሰተ። በዚህ ጊዜ በአሕዛብ ላይ ትኩረት በማድረጉ ብዙ ሰዎች ወደ ክርስቶስ መጡ። ይህ ለጳውሎስ ቀላል ጊዜ አልነበረም። ተስፋ በመቁረጡ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም እግዚአብሔር እንደሚጠብቀው በመግለጽ እዚያው ተግቶ እንዲያገለግል የሚያበረታታ ልዩ መልአክ ልኮለታል (የሐዋ. 18፡9-10)። ጳውሎስ ለ18 ወራት በቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ ቆይቶ ሲመሰክር፥ ሲያስተምርና ቤተ ክርስቲያንን ሲመሠርት ሰነበተ። ቤተ ክርስቲያኒቱ እያደገች ስትሄድ የአይሁዶችም ቁጣ እንዲሁ ተጠናከረ። ጋሊዮስ በተባለ ገዢ ፊት ጳውሎስን ከሰሱት። ጋሊዮስ ፖለቲካዊ ያልሆነ ክስ ለመመርመር ባለመፈለጉ አይሁዶችን ከችሎቱ አስወጣቸው።

ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ሁለተኛውን የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞውን ፈጸመ። ጳውሎስ በኢየሩሳሌምና አንጾኪያ ሳለ አጵሎስ የተባለ የንግግር ችሎታ ያለው ግለሰብ ከኤፌሶን ወደ ቆሮንቶስ መጣ። አጵሎስ በኤፌሶን ሳለ ከጵርስቅላና አቂላ በተሰጠው ምስክርነት በክርስቶስ አምኖ ነበር። እግዚአብሔር በቆሮንቶስ እጵሎስን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቀመበት። የሚያሳዝነው ሰይጣን ሰዎች ስጦታውን ከሰጠው እግዚአብሔር ይልቅ በተቀበለው በአጵሎስ ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ቀልባቸውን ነጠቃቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች ለሁሉም ስጦታዎችን ከሚሰጠው ክርስቶስ ይልቅ ከፍተኛ ስጦታ ባላቸው መሪዎች ወይም ዘማሪዎች ላይ ዓይኖቻቸውን የሚጥሉት እንዴት ነው?

አንዳንድ ምሁራን ጴጥሮስም (ኬፉ) ወደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ለአጭር ጊዜ እንዳገለገለ ያስባሉ። ለዚህ ነበር በዚያ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የፈለጉት። ነገር ግን ጳውሎስ ወይም የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ የነበረው ሉቃስ እንዲህ ዓይነቱን ጉብኝት ሳይጠቅሱ ስለማያልፉ ትክክለኛ ግምት አይመስልም።

አጵሎስ በቆሮንቶስ ከሰበከ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፥ ጳውሎስ ሦስተኛውን የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞውን ጀመረ። ጳውሎስ በሦስተኛው ጉዞው በእስያና ኤፌሶን አካባቢ ትኩረት አድርጎ ለሁለት ዓመታት (አንዳንድ ምሁራን ከሞላ ጎደል ሦስት ዓመት ነበር ይላሉ) ሠርቷል። ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የመልእክት ልውውጥ ጀምሮ ነበር። እጵሎስና ምናልባትም ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ አይመስልም። ጠንካራ አመራር ባለመኖሩ ምክንያት ችግሮች ተከሰቱ። ቤተ ክርስቲያኒቱም መከፋፈል ጀመረች። ጳውሎስ ከኤፌሶን ሆኖ ደብዳቤ በመጻፍ ችግሮቹን ለማስተካከል ሞከረ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

3 thoughts on “ጳውሎስ መልእክቱን ለማን ጻፈ?”

  1. ተባረኩ በጣም እየተጠቀምኩነው በዚህ ድህረ ገፅ ሌሎች አዳዲስ መልከሰቶች በምን ያህል ጊዜ ይለቀቃሉ

    1. ወንድሜ ሃብታሙ፣

      የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ ለአዳዲስ አማኞች የሚሆን የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች፣ ለሰነበቱ አማኞች የሚሆን የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛዎች፣ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጽሐፎችን ያካተተ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማቴሪያሎችን፣ ለተለያዩ መንፈሳዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርህ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትህን ማካሄድ ትችላለህ፡፡

      የወንጌል በድረገጽ ዌብ ሳይት ተከታታይ (follower) ለመሆን የምትሻ ከሆነ የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት ዌብ ሣይት (https://ethiopiansite.com/) የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በመሄድ፣ በስተቀኝ ባልው ክፍት ሣጥን ውስጥ የኢ-ሜይል አድራሻህን በመጻፍና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ቁልፍ በመጫን የዌብ ሣይቱ ተከታይ (follower) መሆን ትችላለህ፡፡ ይህን ስታደርግ በዌብ ሣይቱ ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲጫኑ፣ በኢ-ሜይል አድራሻህ የማንቂያ መልእክት (notification) የምታገኝ ይሆናል፡፡

      ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖርህ በሚከተለው ኢሜይል ልትልክልኝ ትችላለህ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡

      የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከአንተና ቤተሰብህ ጋር ይሁን። አሜን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: