የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ

አንዳንድ ክርስቲያኖች «እንደ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ብንሆን መልካም ነበር። ክርስቲያኖች ታላቅ ፍቅርና አንድነት፥ እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወት ነበራቸው፥ አስደናቂ ተአምራት ይደረጉ ነበር። ወደ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን መመለስ ይኖርብናል። ያኔ እግዚአብሔር ያለ ጥርጥር ይባርከናል ይላሉ። እውን እነዚያ ጊዜያት ከእኛ ዘመን የተሻሉ ነበሩ? አዲስ ኪዳንን በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን የሚያውኩ ችግሮች በቀድሞዪቱም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደነበሩ እንገነዘባለን። ግብዝነት፥ ክፍፍል፥ ዝሙት፥ የሐሰት ትምህርትና እግዚአብሔርን ለማስደሰት ከነበራቸው ፍላጎት የሚመነጩ የሕግ አጥባቂነት አመለካከቶች ይታዩ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን በመሰልን እያሉ ሲመኙ የሰማኸው መቼ ነው? ለ) ከላይ የተጠቀሱትን የጥንት ቤተ ክርስቲያን ችግሮች ተመልከትና፥ ዛሬ ከእነዚህ መካከል የትኞቹ ችግሮች ቤተ ክርስቲያኖቻችንን እንደሚያውኩ ግለጽ። ለእነዚህ ለእያንዳንዳቸው ችግሮች ምሳሌዎችን ስጥ።

የሮሜ መልእክት ከጳውሎስ መጻሕፍት ሁሉ ረዥም በመሆኑ፥ ከሐዋርያት ሥራ ቀጥሎ በቀዳሚነት ቀርቧል። ይህ መጽሐፍ ሰው እንዴት እንደሚድን፥ እንደዳነ፥ ሰው ኃጢአትን እንዴት እንደሚያሸንፍና የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚወርሱት ተስፋ በመግለጽ ሥነ መለኮታዊ የድነት (ደኅንነት) ጉዳዮችን ያብራራል። ከጳውሎስ መልእክቶች በርዝመቱ የሁለተኛነቱን ደረጃ የያዘው የቆሮንቶስ መልእክት ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ የተጻፈው በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩትን የተወሰኑ ችግሮች ለመቅረፍ ነበር። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ችግሮች ዛሬ በየቤተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ ይገኛሉ። ስለሆነም፥ ለክርስቲያኖች የ1ኛ ቆሮንቶስን ትምህርት በግልጽ መረዳት ጠቃሚ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ 1ኛ ቆሮንቶስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደ ተመሠረተች፥ የቆሮንቶስ ከተማ ምን እንደምትመስል፥ የመጽሐፉ ደራሲ ማን እንደሆነ፥ የመጽሐፉ ዓላማ ምን እንደሆነ ወዘተ. ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) ይህ መጽሐፍ ከዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን እውነቶች ይይዛል ብለህ የምታስብባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር።

የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ

ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡28-29 በሐዋርያነት አገልግሎቱ ያጋጠማቸውን ችግሮች ሲገልጽ፥ «የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው፡፡ የሚደክም ማን ነው? እኔም አልደክምምን? የሚሰናክል ማን ነው? እኔም አልናደድምን?» ብሏል። እግዚአብሔር በሮም ግዛት ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ለመመሥረት በጳውሎስ ተጠቅሟል። ጳውሎስ ግን ቤተ ክርስቲያን በመመሥረቱና የተወሰኑ ሰዎች ለጸሎትና አምልኮ ሲሰባሰቡ በማየቱ ብቻ የሚረካ ሰው አልነበረም። እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቷ እንድትበስል ይፈልግ ነበር። በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ጸሎቶች ብንመለከት፥ ጳውሎስ አማኞች በእውቀት፥ በአንድነትና በብስለት እንዲያድጉ ከልብ መሻቱን እናያለን። (ለምሳሌ፥ ኤፌ. 1፡14-21፤ 3፡14-21)። ጳውሎስ እጅግ አጥብቆ ለሚወደው ለክርስቶስ አማኞችን እንደ ንጽሕት ሙሽራ አድርጎ ለማቅረብ ይፈልግ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡2)። ክርስቲያኖች እንደ እግዚአብሔር ልጆች የሚገባቸውን ዓይነት ሕይወት ሳይኖሩ በሚቀሩበት ጊዜ ጳውሎስ በፍቅርና አንዳንዴም በቁጣ ወደ ትክክለኛው ስፍራ ሊመልሳቸው ይተጋል። ከእግዚአብሔር መንገድ ሾልከው የሚወጡ ልጆች በሥጋ የወለዷቸውን ሰዎች ስሜት በእጅጉ እንደሚጎዱ ሁሉ፥ ጳውሎስም መንፈሳዊ ልጆቹ ከእውነት ፈቀቅ በሚሉበት ጊዜ በጽኑ ይቆስል ነበር። ጳውሎስ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለመመለስ ብቻ ሳይሆን በእምነታቸው እንዲያድጉ ለመርዳት ጭምር የተሰጠውን ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ተመለከተ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለቤተ ክርስቲያንህ በማሰብ ምን ያህል በጽኑ እንደተጎዳህ ግለጽ። ለ) አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለቤተ ክርስቲያናቸው ምእመናን መንፈሳዊ ዕድገት አጥብቀው በማሰባቸው ምክንያት እንደ ጳውሎስ የሚጎዱ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ሐ) ብዙ ሰዎች እየዳኑ ቢሆኑም፥ ብዙዎች ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን እየወጡ ናቸው። ይህ አማኞች ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱና በእምነታቸው እንዲያድጉ መሪዎች የሆንን ሰዎች ተግተን አለመሥራታችንን የሚያሳየው እንዴት ነው?

ምናልባትም የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በጳውሎስ ላይ ከፍተኛ ሥቃይና ሕመም ሳታስከትል አልቀረችም። በመሆኑም ከሌሎች ሁሉ በላይ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ብዙ መልእክት ጽፎአል። ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች ችግሮቻቸውን ተቋቁመው በእምነታቸው እንዲያድጉ በማበረታታት 1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስን ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ መልእክቶችን የጻፈ ቢሆንም፥ ጠፍተዋል።

ጳውሎስ በቆሮንቶስ 18 ወራትን ስላሳለፈ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱንና ክርስቲያኖቹን በደንብ ያውቃቸው ነበር። ስለሆነም፥ እንደ ሮሜ መልእክት አጠቃላይ እውነቶችን ከማብራራት ይልቅ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባጋጠማት የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading