ከጳውሎስ ልማዶች አንዱ ስለ አንድ ጉዳይ እየጻፈ ሳለ ሌላ ነገር ሲነገረው ርእሰ ጉዳዩን ወደ አዲሱ መረጃ የማዞር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በኤፌሶን 3፡1 ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ስለ መጸለዩ የሚናገር ይመስላል። ነገር ግን ለአሕዛብ መታሰሩን ማስታወሱ አሳቡን ስላላስለወጠው ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ስለ መጸለይ ያነሣውን ጉዳይ ከማብራራቱ በፊት (ኤፌ. 3፡14) ወንጌል ለአሕዛብ ስለ መሰበኩ ብዙ ማብራሪያ ሰጥቷል። በዚህ ስፍራም ጳውሎስ የጀመረውን የዝሙት ጉዳይ አቋርጦ (በ1ኛ ቆሮ. 6፡9-20 የሚቀጥል) ክርስቲያኖች በሌሎች ክርስቲያኖች ላይ በመፍረድ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸውን ያስረዳል።
ጳውሎስ አንዳንድ ክርስቲያኖች በሀብት ጉዳይ ሌሎች ክርስቲያኖችን ፍርድ ቤት እንደሚያቆሟቸው የሰማ ይመስላል። ምናልባት አንድ ክርስቲያን ለሌላው አንድ ንብረት ወይም ከብት ከሸጠለት በኋላ ገዢው የተታለለ መስሎ ሳይሰማው አልቀረም። ስለዚህም እንደ ዓለማውያን ክርክራቸውን በፍርድ ቤት ለመቋጨት ፈለጉ። ክርስቲያኖች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ክርስቲያን ባልሆነ ዳኛ ፊት መቆማቸው ጳውሎስን አስቆጣው። ይህ ክርስቲያኖች የመፍረድ ሥልጣናቸውን እንዳልተጠቀሙበት የሚያሳይ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ የማያምኑ ሰዎች ወደሚገኙበት ችሎት መውሰድ እንደሌለባቸው በመግለጽ የሚከተለውን ብሏል።
- ክርክሮችን ወደማያምኑ ዳኞች (ችሎት ወይም የጎሳ ሽማግሌዎች) የሚወስዱ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የሰጠንን ሥልጣን አልተገነዘቡም። በመጨረሻ ከክርስቶስ ጋር በማያምኑ ሰዎች ላይ እንፈርዳለን። (ማቴ. 19፡28፤ 2ኛ ጢሞ 2፡12፤ ራእይ 20፡4 አንብብ።) በመላእክትም ላይ እንፈርዳለን። ይህ ምናልባትም በወደቁትና አሁን የሰይጣን መላእክትና እጋንንት ሆነው በሚሠሩት መላእክት ላይ ክርስቶስ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ እኛም እንደምንሳተፍ የሚያሳይ ይሆናል። (2ኛ ጴጥ. 2፡4-9፤ ይሁዳ 6 አንብብ።) እግዚአብሔር ወደ ፊት ለክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ሥልጣን የሚሰጣቸው ከሆነ፥ አሁን እንደ ንብረት ያሉትን ጥቃቅን ጉዳዮች የመዳኘት ሥልጣን እንዳለን ግልጽ ነው። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመዳኘት ሥራ የሚሠሩትን ሰዎች መምረጡ ቀላል እንደሆነ በምፀታዊ ድምፀት ይናገራል። ጳውሎስ ይህን ሲል፥ «ትምህርትና ስጦታ ያላቸውን ሽማግሌዎች ተዉአቸው። ትምህርት የሌላቸውን ሽማግሌዎች ውሰዱ። እነዚህ ሰዎች በኋላ በታላላቅ ጉዳዮች ላይ ፍርድ የሚሰጡ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ ችግሮችን ለማስተካከል ይችላሉ» ማለቱ ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ በክርስቲያኖች መካከል የሚነሣውን አለመግባባት የሚፈታ አስተዋይ ሰው የለም እንደ ማለት ነበር።
- ክርስቲያኖች ችግሮቻችንን ወደ ዓለማውያን መውሰዳችን እርስ በርሳችን ለመዳኘት አለመቻላችንን ያሳያል። ይህም ምስክርነታችንን ከማበላሸቱም በላይ የክርስቶስን ስም ያስነቅፋል። ይህም በዋናው ጉዳይ ላይ ሽንፈት እንደገጠመን ያሳያል። ክርስቲያናዊ ስማችንና የክርስቶስ ስም ከየትኛውም የግል ጉዳይ የበለጠ ነው።
- በጠብና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ የክርስቶስንና የክርስቲያኖችን ስም ከማጉደፍ ይልቅ ተበዳዩ ተበድሎም እንኳ ቢሆን ጉዳዩን መተው ነበረበት። የራሳችን ለሆነው ንብረት በመፋለም የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ስም ከማጉደፍ ይልቅ መበደሉ የተሻለ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ችግሮቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊፈቱ ሲችሉ እንዴት ወደ ዓለማውያን እንደሚወስዱ ግለጽ። ለ) ከእነዚህ ልምምዶች የሚመነጩ አሉታዊ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) በክርስቲያኖች መካከል ስለተፈጸመ አንድ ክፍፍል ግለጽ። ጳውሎስ ባስተማረው መሠረት እግዚአብሔር ክርስቲያኖች ችግሮቻቸውን እንዴት አድርገው እንዲፈቱ የሚፈልግ ይመስልሃል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)