Site icon

በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ምግባረ ብልሹነት ነበር (1ኛ ቆሮ. 5፡1-13)

መሪዎችን ጨምሮ ክርስቲያኖችን በተደጋጋሚ ከሚያውኩ ኃጢአቶች አንዱ ወሲባዊ እርኩሰት ነው። ከጋብቻ ውጭ ወሲብ የሚፈጽም ባል ወይም ሚስት፥ ወንድ ወይም ሴት ወጣት እግዚአብሔርን በጽኑ ያሳዝነዋል።

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከብዙ ሰዎች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ተቀባይነት ባገኘበት ማኅበረሰብ ውስጥ ይኖሩ ነበር። የቆሮንቶስ ሰዎች ከጋብቻ ውጭ ከሚፈጽሟቸው የወሲብ እርኩሰቶች በተጨማሪ፥ እንደ ግብረ ሰዶማዊነት ያሉትን ያልተለመዱ ወሲባዊ ተግባራት ያከናውኑ ነበር። በዚህ ባሕል ውስጥ የነበሩት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይህን ችግር እንዴት መቋቋም እንዳለባቸው አላወቁም ነበር። ስለሆነም አክራሪ ጫፍ ይመዙ ጀመር። አንዳንዶች ሁሉም ወሲባዊ ግንኙነቶች ክፉዎች ስለሆኑ መጋባት ለክርስቲያኖች አስፈላጊ እንዳልሆነ ይናገሩ ጀመረ። ሌሎች ደግሞ ሁሉም ዓይነት ወሲባዊ ግንኙነቶች ተቀባይነት እንዳላቸው አስተማሩ። እነዚህ ወገኖች የእግዚአብሔር ጸጋ ለኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ በሥጋ የሚሠራው ኃጢአት መንፈሳዊ ሕይወትን እንደማይነካ ገለጹ። ስለሆነም፥ ጳውሎስ እነዚህን ሁለት የተራራቁ አመለካከቶችን በማማከል መናገር ነበረበት። በ1ኛ ቆሮንቶስ 7 ስለ ጋብቻ ይናገራል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 5-6፥ ከጋብቻ ውጭ ስለሚካሄዱ ወሲባዊ ግንኙነቶች ክርስቲያኖች የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ያብራራል።

ሁለተኛውና የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለጳውሎስ ሪፖርት ያደረጉት ችግር ግልጽ የሆነ ወሲባዊ እርኩሰት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መከሰቱ ነበር። ጳውሎስን ያስደነቀው ወሲባዊ እርኩሰት መፈጸሙ ሳይሆን የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና መሪዎች ለዚህ ኃጢአት የነበራቸው አመለካከት ነበር።

  1. ሁኔታው (1ኛ ቆሮ. 5፡1)፡- በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ከአባቱ ሚስት ጋር ዝሙት የሚፈጸም ሰው ነበረ። ይህች ሴት እናቱ ሳትሆን የእንጀራ እናቱ ነበረች። ሴቲቱ ለኃጢአቷ መቀጣት እንዳለባት የሚያመለክት አሳብ ስላልተጠቀሰ፥ ሴትዮዋ አማኝ ያልነበረች ይመስላል። ቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ያላት በምእመኖቿ ላይ ብቻ ስለሆነ፥ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በኃጢአት የሚመላለሱ ምእመኖቿን እንዴት ማረም እንዳለባት ያስረዳል። መሪዎቹ ግለሰቡን ከመገሠጽና የቤተ ክርስቲያን የቅጣት ደረጃዎችን ተከትለው ከመሥራት ይልቅ ሁኔታውን በቸልተኝነት ይመለከቱ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ኃጢአት እየቀጠለ እንዲሄድ መፍቀዳቸው ለተፈጸመው ጥፋት ተቃውሞ የሌለበት ምላሽ እንዳላቸው ያሳያል። ጳውሎስ ራሱ ኃጢአት ሲበዛ የእግዚአብሔር ጸጋ ከዚያ በላይ እንደሚገለጥ አስተምሮ የለም? ሊሉ አሰቡ (ሮሜ 5፡20-21)።
  2. የጳውሎስ ውሳኔ (1ኛ ቆሮ. 5፡2-5)፡-

ሀ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰት ኃጢአት አስደሳች ወይም በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን ኃዘንን የሚያስከትል ነው።

ለ) ይህን ኃጢአት የሚፈጽመው ግለሰብ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት መውጣት አለበት። ጳውሎስ ይህንኑ ግለሰቡን ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የማስወጣት ሂደት ሰውዬውን «ለሰይጣን አሳልፎ መስጠት» ሲል ይጠራዋል። የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ስብሰባና ኅብረት ውስጥ ስለሚኖር ስፍራው ድነት (ደኅንነት) የሚገኝበትና ክርስቶስ የሚገዛበት በመሆኑ የሰይጣን ኃይል የተዳከመበት እንደሆነ ያምኑ ነበር። ነገር ግን ከክርስቲያኖች ኅብረት ውጭ ሰይጣን በንጉሥነት እንደሚገዛ ያምኑ ነበር። ስለሆነም አንድን ሰው ከኅብረቱ ማስወጣት ማለት ወደ ሰይጣን ግዛት መመለስ ማለት ነበር። በዚህ ጊዜ ሰይጣን ግለሰቡን በተለያዩ መንገዶች ሊያጠቃው ይችላል። ግለሰቡን ከቤተ ክርስቲያን ማስወጣታቸው ክርስቲያን ወዳለመሆን እንደተመለሰ አያሳይም። ቀዳሚ ዓላማውም ቅጣት አልነበረም። ይህ የግለሰቡ የኃጢአት ባሕርይ እንዲጠፋና መንፈሱ በጌታ ቀን እንድትድን ታስቦ የተደረገ የመማሪያ ገጠመኝ ነበር። ሰውዬው ከሚወዳቸው ምእመናን ተለይቶ ሲወጣ በሚሰማው ኃፍረትና በሚደርስበት የሰይጣን ጥቃት ምክንያት ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለስ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ ነበር። (የዚህን አሳብ ተጨማሪ ማብራሪያ ከ1ኛ ጢሞ. 1፡20 አንብብ።)

ጳውሎስ ግለሰቡ በኃጢአቱ እየገፋበት መሆኑንና ይህም በምእመናን ሁሉ ዘንድ መታወቁን ገምቷል። ይህ አንድ ሰው ስለ ሌላው የሚያቀርበው ወቀሳ ወይም ጉምጉምታ ሳይሆን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ጥናት አድርገው ለጳውሎስ የጻፉት ጉዳይ ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአት በሚኖርበት ጊዜ ሽማግሌዎች በማቴ. 18፡15-17 የተሰጠውን ደረጃ መከተላቸው ጠቃሚ ነው። ይህን ከፍተኛ ቅጣት መስጠት የሚቻለው ከዚያ በኋላ ብቻ ነው።

  1. ይህ ከፍተኛ ቅጣት የተሰጠበት ምክንያት (1ኛ ቆሮ. 5፡6-8)፡- ኃጢአትን በትኩረት ተከታትለን የቤተ ክርስቲያን ቅጣት እንዲሰጥበት ካላደረግን ጥቂት እርሾ ጠቅላላውን ሊጥ እንደሚያቦካ ሁሉ፥ ኃጢአት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መስፋፋቱ የማይቀር ነው። ጳውሎስ ከብሉይ ኪዳን የአይሁዶች የፋሲካ ልምምድ ተነሥቶ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል። ከፋሲካው በዓል ቀደም ብሎ እያንዳንዱ አይሁዳዊ ቤተሰብ እርሾ ያለበትን ነገር ሁሉ ያስወግድ ነበር። ይህም ክፋትን የማስወገድ ተምሳሌት ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም የትኛውንም ዓይነት ያፈጠጠና ንስሐ ያልተገባበትን ኃጢአት ከቤተ ክርስቲያን ለማስወገድ ነቅተው ሊሠሩ ይገባል። ጳውሎስ፥ «በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም» ሲል ለወሲባዊ እርኩሰት ብቻ ሳይሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ስላለ ሥነ ሥርዓትም ጭምር ነበር። ስለሆነም፥ ንስሐ ያልተገባበትና የዓመፃ ኃጢአት ሁሉ እልባት ሊሰጠው ይገባል። ጳውሎስ ራሷን በንጽህና የምትጠብቅ ቤተ ክርስቲያንን «የቅንነትና የእውነት ዳቦ» ይላታል።

በተጨማሪም፥ ጳውሎስ ፍርዱ በክርስቲያኖች ፊት በይፋ መሰጠት እንዳለበት አመልክቷል። ይህ ኃጢአት ለፈጸመው ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኖች ሁሉ የመማሪያ ገጠመኝ ይሆናል። ኃጢአት ከፈጸሙ በኋላ ንስሐ በማይገቡት ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ቅጣት በመመልከት ክርስቲያኖች በተመሳሳይ ኃጢአት ላለመውደቅ ይጠነቀቃሉ። በማቴዎስ 18፡15-17 የተጠቀሰውን ሂደት ከተከተሉ በኋላ ክፍፍል እንዳይፈጠር ሽማግሌዎች ፍርዱን ለክርስቲያኖች ሁሉ ማሳወቃቸው አስፈላጊ ነው። ይህም መከፋፈል እንዳይፈጠር ያደርጋል። ስለተፈጸመው ኃጢአት ሰዎች ሁሉ ከሰሙ በኋላ ከዋናው ጋር ሲስተያይ የሽማግሌዎችን ውሳኔ በይፋ አለማሳወቁ፥ ሰይጣን የወሬ ጉምጉምታዎችን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎችን እንዲከፋፍል በር ይከፈታል። በተጨማሪም፥ እነዚህ በማቴዎስ 18፡15-17 የተጠቀሱትን ምስክሮች በምንመርጥበት ጊዜ እድልዎአዊ አቅጣጫ የማይዙትን ሰዎች መጠቀም እንዳለብን ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ጳውሎስ የሰጠው ዓይነት ፍርድ ሲበየን አይተህ ታውቃለህ? እንደዚህ ከሆነ፥ የተከሰተውን ሁኔታ አብራራ። ለ) ቤተ ክርስቲያን በዓመፃ ኃጢአቶች ላይ ብዙም ይፋዊ ፍርድ የማትሰጠው ለምን ይመስልሃል? ይህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአት እንዲስፋፋ የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐ) በሽምግልና ተመርጠህ በምታገለግልበት ጊዜ ሁለት የኳዬር መዘምራን ዝሙት እንደሚፈጽሙ ሰማህ እንበል። ማቴዎስ 18፡15-17 እና በዚህ ክፍል ጳውሎስ ያስተማረውን አሳብ በመከተል፥ ለዚህ ኃጢአት መፍትሔ መጠቆም ያለብህ እንዴት ነው? መ) «እነዚህን ሰዎች ብናጋልጥ እነርሱና ቤተሰቦቻቸው ቤተ ክርስቲያናችንን ጥለው ይወጣሉ። እነዚህ ሰዎች ስለሚጠቅሙን በዚህ መንገድ ልናሳፍራቸው እንችልም?» የሚል አሳብ ለሚያቀርብ ሽማግሌ ምን ምላሽ ትሰጠዋለህ?

  1. ጳውሎስ ቀደም ሲል ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን ትእዛዝ አብራራ (1ኛ ቆሮ. 5፡9-11)፡- ጳውሎስ ስለዚህ ወይም ስለ ሌላ ወሲባዊ ኃጢአት ቀደም ሲል የሰማና ክርስቲያኖች ጭፍን ዝሙት ከሚፈጽሙና በእግዚአብሔር ላይ ከሚያምፁ ሰዎች ጋር ኅብረት እንዳያደርጉ የሚያሳስብ መልእክት የጻፈላቸው ይመስላል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ትእዛዛት በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ከዓለማውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳያደርጉ የከለከላቸው መሰላቸው። ጳውሎስ ግን የተቀደሰ አኗኗር ሳይከተሉ እንደ ዓለማውያን ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች እየተናገረ መሆኑን ገልጾላቸዋል። አሁንም ጳውሎስ ስለ ወሲባዊ ርኩሰት ብቻ እየተናገረ አለመሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ስለ ራስ ወዳዶች፥ ነጣቂዎች በክርስቶስ እናምናለን እያሉ የቤተሰቦቻቸውን ወይም የማኅበረሰቡን ፍርድ በመፍራት የድሮ አምልኮአቸውን የሚያካሂዱትን ጭምር ይዘረዝራል።

ጳውሎስ ክርስቲያኖች ያፈጠጠ ኃጢአት ከሚፈጸሙ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት እንዳያደርጉ የከለከለው ክፉ መንገዳቸውን አይተው በንስሐ እንዲመለሱ ለማገዝ ነበር። በአንጻሩ ግን ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በኃጢአት ከሚኖሩት ከዓለማውያን ጋር ኅብረት በማድረግ እንደሚመሰክሩላቸው አሳስቧል። እግዚአብሔር ክርስቲያኖችን የጠራቸው ዓለምን እንዲተዉና ራሳቸውን ከዓለማውያን እንዲለዩ አይደለም። ነገር ግን እርሱ ባስቀመጠን ማኅበረሰብ ውስጥ እየኖርን ንጹሐንና ቅዱሳን እንድንሆን ጠርቶናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሆን ብለው ኃጢአትን ከሚፈጽሙ ክርስቲያኖች ጋር ያለንን ግንኙነት እምብዛም የማናቋርጠው ለምን ይመስልሃል? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች በክርስቲያናዊ ድርጅቶች ውስጥ ለመሥራት ሲሉ ሥራቸውን የሚለቁት ወይም ከክርስቲያኖች ጋር ለመጎራበት የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ጳውሎስ እንዲህ ያለውን ምክንያት የሚቀበል ይመስልሃል?

  1. ጳውሎስ ኃጢአት የሚሠሩትን ክርስቲያኖች እንደ ዓለማውያን ለምን መፍረድ እንደሌለብን ያብራራል (1ኛ ቆሮ. 5፡12-13)። በዓመፀኝነት መንፈስ ግልጽ ኃጢአት የሚፈጽሙትን ክርስቲያኖች መቅጣትና መፍረድ ያለብን እግዚአብሔር ከሰጠን የፈራጅነት ሥልጣን የተነሣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የመፍረድ ሥልጣን እንዳላቸው ይናገራል። (ማቴ. 19፡28 አንብብ።) ስለሆነም አሁን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳችን በሌላችን ላይ የመፍረድ ብቃት አለን። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በዓለማውያን ላይ እንዲፈርዱ ሥልጣን አይሰጣቸውም። ይህ የእግዚአብሔር ኃላፊነት ሲሆን፥ በመጨረሻው ዘመን ዓለማውያንን በዘላለማዊ ሞት ይቀጣቸዋል። (ራእይ 20፡11-16 አንብብ።)

ክርስቲያኖች ክርስቶስ በማቴዎስ 7፡1-5 ያስተማረውን አሳብ ጳውሎስ በዚህ አሳብ ከገለጻው ጋር ለማስታረቅ ይቸገራሉ። ክርስቶስ በማቴዎስ 7፡15-20 ተከታዮች ሰዎች በአኗኗራቸው (በፍሬአቸው እንዲፈርዱ እንዲገመግሙ) ነግሮአቸዋል። ክርስቶስና ጳውሎስ ሁለት ዓይነት ፍርድ እንዳለ እያስተማሩ ነበር። ለክርስቲያኖች ያልተፈቀደው የመጀመሪያው ዓይነት ፍርድ የሌላውን ክርስቲያን ስውር አመለካከቶችን እና የመነሣሻ ዓላማዎችን መገምገም ነው። ለምሳሌ ያህል «እገሌና እገሌ መንፈሳዊ አይደሉም። መዝሙር በሚዘምርበት ጊዜ አያጨበጭብም። እገሌና እገሌ የእኔን ጎሳ አይወዱም። እገሊት የራሷ ዘር የሆነውን ሰውዬ ምሳ ስትጋብዝ እኔን ግን ኦልጋበዘችኝም» የሚሉ ዓይነት ፍርዶችንና አሳቦችን መስጠት ለክርስቲያኖች አልተፈቀደም።

ለክርስቲያኖች የተፈቀደው ሁለተኛው ዓይነት ፍርድ የእግዚአብሔርን ቃል በግልጽ የሚጥሱትን ክርስቲያኖች ተግባራትና የአኗኗር ስልቶች መመዘን ነው። የእግዚአብሔር ቃል «አታመንዝር» ሲል በግልጽ ተናግሯል። ጳውሎስ ክርስቲያኖች ይህን ትእዛዝ በሚጥሱበት ጊዜ ይህንኑ ኃጢአት የመቃወምና በቤተ ክርስቲያን የቅጣት ደንብ መሠረት ፍርድ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለብን ያስረዳል። እንደ መዋሸት፥ መስረቅ፥ መስገብገብና የመሳሰሉት ኃጢአቶችም በሌላው ክርስቲያን ላይ ፍርድን የሚያሰጡ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር ባልፈቀደላቸው መንገድ በሌሎች ክርስቲያኖች ላይ እንደሚፈርዱ የሚያሳዩ አምስት ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) እግዚአብሔር ክርስቲያኖች በሌሎች ክርስቲያኖች ላይ እንዲፈርዱ የሚጠብቅባቸውን አምስት ምሳሌዎች ስጥ።

ጳውሎስ እርስ በርሳችን የመፍረድ ኃላፊነት እንዳለብን ማብራራቱን የቋጨው፥ «ክፉውን ግለሰብ» ከመካከላችሁ አውጡት» የሚል ፍርድ በመስጠት ነው። ከአያሌ ወራት በኋላ ጳውሎስ ይህ በኃጢአተኛው ግለሰብ ላይ የተሰጠው ቅጣት ፍሬ ማስገኘቱን ሰምቷል። በ2ኛ ቆሮንቶስ፥ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ንስሐ የገባውን ክርስቲያን ወደ ኅብረቱ እንዲመልሱ ጠይቋል (2ኛ ቆሮ. 2፡6-11)። ይህም የመፍረድና ከኅብረት የማስወጣት (የመገዛት) ዓላማው ክርስቲያኖች ንስሐ ገብተው ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱና የተቀደሰ ሕይወት ለመምራት ከቁርጥ ውሳኔ ላይ እንዲደረሱ ለማገዝ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version