ጋብቻን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች ጳውሎስ የሰጠው መልስ (1ኛ ቆሮ. 7፡1-40)

እያንዳንዱ ባሕል በጋብቻና ወሲባዊ ግንኙነቶች ላይ የተለያየ አመለካከት አለው። የምዕራባውያን ባሕል በወሲባዊ ፍቅር ስለሚደመደም፥ ይህንኑ ወሲባዊ ፍቅር ከሁሉም እንደ ላቀ ደስታ ይቆጥረዋል። ለምዕራባውያን ወሲባዊ ፍቅር የሚያተኩረው ራስን በማስደሰት ላይ ነው። የአፍሪካ ባሕል ጋብቻንና ወሲባዊ ግንኙነቶችን ልጆችን ለመውለዱ ዓላማ ይጠቀማል። ብዙ ልጆች ለመወለድ ሲባል ብዙ ሚስቶች ማግባትንም የሚፈቅዱ አንዳንድ ባሕሎች አሉ። ከጳውሎስ ዘመን ጀምሮ እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ ወሲባዊ ግንኙነቶችና ጋብቻ ትክክል አለመሆናቸውን የሚያስረዱ አመለካከቶች ተንጸባርቀዋል። መንፈሳዊ የሆነ ሰው ብቻውን ወይም በገዳማት ከወሲባዊ ግንኙነቶች ርቆ መኖር እንዳለበት ይታሰባል። ይህ ወሲባዊ ግንኙነት መጥፎ ነው የሚለው አመለካከት በዓለም ውስጥ በብዙ ባሕሎች ውስጥ ይታያል። ስለ ወሲባዊ ፍቅር ሚዛናዊ አመለካከት ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን መመልከት ይኖርብናል። ጥሩና መጥፎ ስለሆነው ነገር መመሪያዎችን የሚሰጠው ሰዎችንና ወሲባዊ ግንኙነቶችን የፈጠረው እግዚአብሔር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን።

  1. እግዚአብሔር ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ በአምሳሉ ፈጥሯል። ሔዋንን ለአዳም እንደ እኩል አጋሩ አድርጎ ሰጥቷል። እኩልነታቸውንና ፍቅራቸውን ይገልጹ ዘንድ ወሲባዊ ፍቅርን ሰጥቷቸዋል። ይህንንም ሁሉ «መልካም ነው» ብሏል። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔርን የፍጥረት አሠራር ከተከተልን ወሲባዊ ፍቅር መልካም ነው (ዘፍጥ. 1-2)። የመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ እግዚአብሔር በባልና ሚስት መካከል ያለውን ፍቅር እንደሚቀበል ያሳያል።
  2. ሌላው እግዚአብሔር ወሲባዊ ፍቅርን የሰጠበት ምክንያት ሰዎች እንዲበዙ ነበር። ሰዎች ልጆችን በመውለድ እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን ምድር እንዲሞሉ ታዘዋል (ዘፍጥ. 1፡22)።
  3. ወሲባዊ ግንኙነት በባልና በሚስት መካከል ብቻ መፈጸም ይኖርበታል። ሰዎች ከመጋባታቸው በፊትም ሆነ የትዳር ጓደኞቻቸው ካልሆኑት ሰዎች ጋር የሚፈጽሙት የትኛውም ዓይነት ከጋብቻ ውጭ የሆነ ወሲብ እግዚአብሔር ያልፈቀደው ነው።
  4. የጋብቻ ግንኙነት እስከ ሞት ድረስ የጸና መሆን አለበት። ስለሆነም፥ በምዕራቡ ዓለም ተስፋፍቶ የሚታየው ፍች ኃጢአት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፍች ሊካሄድ የሚችለው የማያምን የትዳር ጓደኛ ያመነውን ትቶ ሲሄድ ወይም ከተጋቢዎቹ አንዱ የማያቋርጥ ዝሙት ከሌላ ሰው ጋር የሚፈጽም እንደሆነ ብቻ ነው (ማቴ. 5፡31-32)። የተሻከሩ ባልና ሚስት በይቅርታ ታድሰው ትዳራቸውን ሊቀጥሉ ስለሚችሉ ዝሙት የግድ እንዲፋቱ ማድረግ የለበትም።
  5. የእግዚአብሔር የጋብቻ ዓላማ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት፥ አንዲት ሴት ከአንድ ወንድ ጋር እንዲጋቡ ነው። ለዚህም ነው እግዚአብሔር አዳምን ለሔዋን ሔዋንን ደግሞ ለአዳም የፈጠረው። ስለሆነም፥ የአንድ ወንድ ብዙ ሴቶችን ማግባትም ሆነ በአንዳንድ ባሕሎች እንደሚታየው የአንዲት ሴት ብዙ ወንዶችን ማግባት ትክክል አይደለም።
  6. እግዚአብሔር ወሲባዊ ፍቅርን እንደ ውብ፥ አስደሳችና ጠቃሚ የጋብቻ አካል አድርጎ ስለፈጠረ፥ ሰይጣን ሁልጊዜም ሊያበላሸው ይሞክራል። ይህንንም የሚያደርገው በብዙ የተለያዩ መንገዶች ነው። ሰይጣን ያገቡም ሆነ ያላገቡ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ወሲብን እንዲፈጽሙ ያበረታታቸዋል። ወንዶች ብዙ ሚስቶችን ማግባታቸውንም ያበረታታል። ወንዶች ሴቶች እኛን ለማርካት የተፈጠሩ መሣሪያዎች ናቸው ብለው እንዲያስቡ ወይም ወሲባዊ ፍቅር ክፉ ነው እንዲሉ ይገፋፋቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ኢትዮጵያውያን እግዚአብሔር በጋብቻ ውስጥ ያስቀመጠውን ወሲባዊ ፍቅር ያበላሹባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ምን ያህል ክርስቲያኖች ስለ ጋብቻና ወሲባዊ ፍቅር የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳላቸው ግለጽ።

ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1-16 እርሱን ሊጎበኙ የመጡት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለነገሩት ችግሮች መልስ መስጠቱን አቁሞ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በደብዳቤ የጠየቁትን ጥያቄዎች ወደ መመለሱ ይሻገራል። (1ኛ ቆሮ. 7፡1 አንብብ።) ጳውሎስ እየተናገረ ያለውን አሳብ ለመረዳት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተጋፈጧቸውንና የጳውሎስን ማብራሪያ የጠየቁባቸውን ጉዳዮች መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል። አንዳንዶቹ ጉዳዮች ግልጽ ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ግን ግልጽ አይደሉም። እንዲሁም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ውስን ጉዳዮች ከሰጣቸው መልሶች ምን ያህሉን ከዛሬው ሁኔታችን ጋር ማዛመድ እንዳለብን በመግለጹ ረገድ ክርስቲያኖች በአሳብ ይለያያሉ። ከነዚህም መካከል ዝርዝር ጉዳዮችን ሳይሆን ከጳውሎስ ትእዛዛት በስተጀርባ የሚገኙትን የተወሰኑ መርሆች መከተል አለብን የሚሉ አሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮ. 7ን አንብብ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስለ ጋብቻ የተጠቀሱትን የተለያዩ መርሆች ዘርዝር። ለ) ጳውሎስ በላጤነት መኖር መልካም ስለመሆኑ የሰጣቸውን ምክንያቶች ዘርዝር።

ጳውሎስ ስለ ወሲባዊ ርኩሰት እየገለጸ በመሆኑ፥ አቅጣጫውን ቀይሮ ስለ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ማስተማሩ ተገቢ ነበር። ቆሮንቶሶች ለጳውሎስ ሁለት ጥያቄዎችን ያቀረቡለት ይመስላል። በመጀመሪያ፥ መበለቶች፥ ወንደ ላጤዎችና ሴተ ላጤዎች ክርስቲያኖች ማግባት ወይም ሳያገቡ መኖር እንዳለባቸው ጠይቀዋል (1ኛ ቆሮ. 7፡1)። ሁለተኛ፥ ልጃገረድ ሴቶች (ደናግልት) ማግባት ወይም በላጤነት መኖር እንዳለባቸው ጠይቀዋል (1ኛ ቆሮ. 7፡25-26)።

የጳውሎስን ዝርዝር ትእዛዛት ከመመልከታችን በፊት ጳውሎስና ሌሎችም በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጻፉትን መረዳት ይኖርብናል። ጳውሎስ ጋብቻን እንደማይቃወምና ዝቅ አድርጎ እንደማይመለከት ግልጽ ነው። በኤፌሶን 5፡22-33 ጳውሎስ በባልና ሚስት መካከል ያለው ጋብቻና ፍቅር ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ያሳየውን ፍቅር በምሳሌነት እንደሚያብራራ አስረድቷል። እንዲያውም ጋብቻን መከልከል የተሳሳተ የመጨረሻው ዘመን ምልክት እንደሆነ አስረድቷል (1ኛ ጢሞ. 4፡1-3 አንብብ።) ዕብራውያን 13፡4 ጋብቻን እንድናከብር ያስተምረናል። ይህም ጳውሎስም ሆነ ሌሎች የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ጋብቻን እንደማይቃወሙ ያሳያል።

በ1ኛ ቆሮንቶስ 7፥ ጳውሎስ ጋብቻንም ላጤነትንም ያከብራል። ከዚህ በታች የክርክር አሳቡ ጠቅለል ብሎ ቀርቧል።

ሀ. ሰው ሳያገባ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። ይህም የወንድና ሴት መበለቶች፥ እንዲሁም ገና ያላገቡትንና ደናግሎችን ይመለክታል። ጳውሎስ ስላላገባ ራሱን በምሳሌነት አቅርቧል። አንድ ሰው ከተቻለ ሳያገባ መኖር ያለበት ለሦስት ምክንያቶች ነው።

በመጀመሪያ፡ ከጊዜው «ችግር» የተነሣ በላጤነት መቆየት ከብዙ የልብ ስብራት ያድናል (1ኛ ቆሮ. 7፡26)። ጳውሎስ ስለ የትኛው ችግር እንደሚናገር አናውቅም። ምናልባትም ጳውሎስ የሮም መንግሥት በክርስቲያኖች ላይ እንደሚያመጣ ስለሚጠባበቀው ስደት መናገሩ ይሆናል። ወይም ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች እየታሰሩና እየተገደሉ ለስደት ስለሚዳረጉ፥ ሳያገቡ መኖሩ ባል፥ ሚስት ወይም ልጆች በሚለዩዋቸው ጊዜ በኃዘን ከመጎሳቆል እንደሚያድናቸው መናገሩ ይሆናል።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ክርስቶስ በቶሎ ስለሚመለስ የእግዚአብሔርን አገልግሎት ለማካሄድ ብዙ ጊዜ እንደማይኖር አስረድቷል። ስለሆነም፥ ክርስቲያኖች እየተጋቡ በምድር ላይ የተለመደ ሕይወት ለመምራት ከመሞከር ይልቅ እግዚአብሔርን በማገልገሉ ተግባር ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። በቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ጳውሎስም ክርስቶስ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደሚመለስ ተስፋ አድርጎ ነበር። ስለሆነም፥ ከዚህ ዓለም ሕይወት ይልቅ በመጭው የክርስቶስ መንግሥት ላይ አጽንኦት ሰጥቶ ነበር።

ሦስተኛው፥ ከጋብቻ በኋላ በባልና ሚስት ላይ ብዙ ኃላፊነቶች ይወድቃሉ። ይህም የአገልግሎት ጊዜያቸውን ስለሚሻማ ላጤነቱ ተመራጭ ይሆናል። ላጤነት እግዚአብሔር ለአንዳንድ ሰዎች የሚሰጣቸው ስጦታ ነው (1ኛ ቆሮ. 7፡7)። ያላገባ ሰው ብዙ ጊዜውን እግዚአብሔርን በማገልገሉ ተግባር ላይ ሲያውል፥ ያገባው ግን ሌሎች ኃላፊነቶች ይኖሩታል። እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ለማገልገል ቢፈልጉም፥ ጊዜያቸውና ትኩረታቸው እግዚአብሔርንና ቤተሰቦቻቸውን በማገልገሉ መካከል ይከፋፈላል። ያገቡ ሰዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ጥሩ ሥራ መያዝ ይኖርባቸዋል። ቤት፥ የልጆች ትምህርት፥ ወዘተ… እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበትን ጊዜ ይወስድባቸዋል። በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔር ብዙ ሰዎችን፣ ላጤ ሚሲዮናውያንንም፥ ሳያገቡ እንዲኖሩ ጠርቷቸዋል። እነዚህ ሰዎች ባልተከፈለው ልባቸው አብዛኞቹ ያገቡ ሰዎች በማይችሏቸው መንገዶች ለቤተ ክርስቲያንና ለወንጌሉ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ለዚህ እንደጠራው በማወቅ ሳያገባ የኖረ ሰው ታውቃለህ? ለ) ይህ ሰው አሳብን ከሚሰርቁ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ርቆ ከአብዛኞቹ ባለትዳሮች በላቀ መንገድ እግዚአብሔርን ለማገልገል የቻለበትን ሁኔታ ግለጽ።

ለ. አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ማግባት ይፈልጋሉ። ለዚህም አንዱ ምክንያት ከዝሙት ራሳቸውን ለመጠበቅ ነው። በጋብቻ ሁለቱ አንድ ስለሆኑ፥ እያንዳንዱ አጋር ለገዛ ሰውነቱ መብት አይኖረውም። የባል ሰውነት ሚስቱ ትደሰትበት ዘንድ የራሷ ሰውነት ይሆናል። የሚስት ሰውነት ባል ይደሰትበት ዘንድ የራሱ ሰውነት ይሆናል። በጸሎት ላይ ለማተኮር በጋራ ተስማምተው ለተወሰነ ጊዜ ወሲባዊ ግንኙነቶችን እስካላቋረጡ ድረስ፥ ወሲባዊ ፍቅር ሁልጊዜም ሊቀጥል የሚገባውና ለሁለቱም እርካታ የሚበጅ ነው። ባል ወይም ሚስት ወሲባዊ ግንኙነት ለመፈጸም የማይፈቅድ ከሆነ ሰይጣን በግንኙነታቸውና በትዳራቸው ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር መፍቀዳቸው ነው።

ሐ. ከተቻለ፥ ሁሉም እግዚአብሔር ድነትን (ደኅንነትን) ባገኙ ጊዜ በጠራቸው ሁኔታ ሊኖሩ ይገባል። ካላገቡና ወሲባዊ ፍላጎት ካላየለባቸው ሳያገቡ መኖር አለባቸው። ያገቡ ሰዎች ግን መለያየትም ሆነ መፋታት የለባቸውም። በዚህ ክፍል፥ ጳውሎስ እግዚአብሔር በግልጽ የተናገረውን (ይህን ጌታ እንጂ እኔ አይደለሁም–1ኛ ቆሮ. 7፡10) እና ራሱ የተሻለ ነው ብሎ ያሰበውን (ይህን እኔ እንጂ ጌታ አይደለም- 1ኛ ቆሮ. 7፡12) ለይቶ ያቀርባል።

ጳውሎስ ባሉበት ሁኔታ የመቆየትን መርህ ለሌሎችም ሁኔታዎች ተጠቅሟል (1ኛ ቆሮ. 7፡17-24)። በመጀመሪያ፥ ከድነት (ደኅንነት) በኋላ ባሕላቸውን ወይም ራሳቸውን ለመለወጥ እንዳይሞክሩ አሳስቧል። በጳውሎስ ዘመን ክርስትናን የተቀበሉትን ጨምሮ አይሁዳውያን በግርዘት ላይ ያተኩሩ ነበር። መገረዝ የአይሁዳዊነት ምልክት ነበር። አንድ አሕዛብ ሲገረዝ፥ እንደ አይሁዳዊ ተቆጥሮ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ለመከተል ይገደድ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የአሕዛብ ክርስቲያኖች መገረዝ ሳያስፈልጋቸው በቀድሞው ሁኔታቸው እንዲኖሩ ነግሯቸዋል። የተገረዙት የአይሁድ ክርስቲያኖች ደግሞ ወዳለመገረዝ መመለስ አያስፈልጋቸውም ነበር። መገረዝም ቢሆን ለእነርሱ የተሳሳተ ተግባር አልነበረም። መገረዝ በደኅንነታቸው ላይ የሚጨምረው ወይም የሚቀንሰው ነገር አልነበረውም። አለመገረዝም የሚያመጣው ለውጥ አልነበረውም።

ሁለተኛ፥ ወደ ክርስትና የመጡት ባሪያዎች ነጻነታቸውን ለማግኘት መዋጋት አያስፈልጋቸውም ነበር። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባሪያዎች ነበሩ። ወንጌሉ በፍጥነት የተስፋፋው በእነዚህ ባሪያዎች መካከል ነበር። ባርነት አሳፋሪ የበታችነት ደረጃ ነው። ጳውሎስ ግን ክርስቲያን ባሪያዎች በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ነፃ የወጡ ልጆች ስለሆኑ ሊያፍሩ ወይም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሊመለከቱ እንደማይገባ አበረታቷቸዋል። ባሪያዎች ነጻነታቸውን መቀዳጀታቸው መልካም ቢሆንም፥ ክርስቲያን ባሪያዎች ስለ ባርነታቸው ሊጨነቁ አይገባም። ባሪያዎች ያልሆኑት ደግሞ ሊመኩ ወይም ባሪያዎችን ሊንቁ አይገባም። ምክንያቱም ነፃ የሆኑ ክርስቲያኖች ባሪያዎችም ነበሩ። ደግሞም የክርስቶስ ባሪያዎች ነበሩ።

ሦስተኛ፥ ከዚህ በፊት ያላገቡት «ደናግል» ማግባት አያስፈልጋቸውም። ጳውሎስ ይህን ምክር የሰጠው ከእግዚአብሔር ባገኘው ጥበብ እንጂ በቀጥታ ከእግዚአብሔር ያልታዘዘ መሆኑን ገልጾአል።

አራተኛ፥ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛው ክርስቲያን ካልሆነች በደኅንነቱ አመካኝቶ ሊፈታት አይገባም። ያላመነች ሚስቱ ልትፈታው እስካልፈለገች ድረስ ክርስቲያኑ አብሯት ሊኖር ይገባል። ከክፍሉ ዓውደ ንባብ እንደምንመለከተው፥ ጳውሎስ የተፋታ ክርስቲያን ብቻውን ሊኖር እንደሚገባ ቢመክርም፥ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግን የተፈታው ክርስቲያን ሌላ ሚስት ለማግባት ነፃ መሆኑን የሚናገር ይመስላል። ያመነ ሰው ካላመነው ጋር በትዳር ተሳስሮ መቆየት ያለበት ለምንድን ነው? ይህ በትዳር ውስጥ ተጨማሪ ውጥረቶችንና ሥቃዮችን ያስከትል የለምን? ጳውሎስ ሁለት ምክንያቶችን ይሰጣል።

በመጀመሪያ፥ አማኙ የማያምን የትዳር ጓደኛውን ይቀድሰዋል። ጳውሎስ ይህን ሲል የክርስቲያኑ እምነት የትዳር ጓደኛውን እንደሚያድን መግለጹ አይደለም። ነገር ግን አማኙ በየቀኑ ወንጌሉን የመስማት ዕድል ስለሚያገኝ፥ በክርስቶስ አምኖ ሊድን ይችላል። ይህም ሁለቱም ዓለማውያን ከሚሆኑበት ሁኔታ የተሻለ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ «መቀደስ» የሚለው ቃል «ከሌሎች ገጠመኝ የተለየ» የሚል ፍች ይኖረዋል።

ሁለተኛ፥ የባለትዳሮቹ ልጆች ይቀደሳሉ። አንድ ክርስቲያን ዓለማዊ የትዳር ጓደኛውን ከፈታ፥ ዳኛው ልጆች ከዓለማዊው ጋር እንዲያድጉ ሊፈርድ ይችላል፡፡ ይህም ልጆቹ ወንጌሉን ሰምተው የሚድኑበትን ዕድል ያጠብበዋል። በመሆኑም ልጆቹ ስለ ክርስቶስ የሚሰሙበት ዕድል የጠበበ ስለሚሆን እንዳይቀደሱ ያደርጋቸዋል። ነገር ግን ክርስቲያን ከዓለማዊ የትዳር ጓደኛው ጋር አብሮ መኖሩን ሲቀጥል፥ ለልጆቹ ለመመስከርና ወደ ክርስቶስ ለመመለስ መልካም ዕድል ይኖረዋል። እነዚህ ልጆች ስለ ክርስቶስ የመስማት ሰፊ ዕድል በማግኘታቸው ምክንያት ከዓለማውያን ልጆች የተለዩ የተቀደሱ ናቸው። ከወላጆቻቸው አንዱ ክርስቲያን በመሆኑ ብቻ ልጆቹ ከመቅጽበት ክርስቲያኖች አይሆኑም። ሁለቱም ወላጆቹ ክርስቲያኖች ቢሆኑም እንኳ እያንዳንዱ ልጅ በግሉ በክርስቶስ ለማመን መወሰን አለበት። እምነት ከመቅጽበት ከወላጆች ወደ ልጆች አይፈስም። ነገር ግን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ወንጌሉን ስለሚሰሙ፥ የእምነት እርምጃ መውሰዱ አይከብዳቸውም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች 80 በመቶ ያህሉ በልጅነታቸው ማለትም ዕድሜያቸው 16 ከመሙላቱ በፊት በወላጆቻቸው ምስክርነት ያመኑ መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ራሳቸው አማኞች በመሆናቸው ልጆቻቸውም አማኞች እንደሆኑ የሚመስላቸው ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ልጅ ድነትን (ደኅንነትን) በግልጽ እንዲረዳና ክርስቶስን ለመከተል እንዲወስን ቤተ ክርስቲያን ምን እያደረገች ነው?

መ. 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡36-38 ሁለት ዐበይት አተረጓጎሞች አሉት። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ምሁራን ይህ ልጃገረድ ለማግባት ስላጨ ሰው ይናገራል ይላሉ። ያ ሰው ያግባ ወይስ አያግባ? ጳውሎስ ሰውዬው ለራሱና ለልጃገረዷ የመወሰን መብት እንዳለው ይናገራል። ማግባት አለብኝ ብሎ ካሰበ ወይም ያጫትን ልጃገረድ ባለማግባቱ ስሜቷን የሚጎዳ መስሎ ከተሰማው፥ ሊጋቡ ይችላሉ። የጋብቻ ሕይወት መልካም ነው። ነገር ግን ሰውዬው በላጤነት ለመኖርና የትዳር ኃላፊነት ሳይጫነው እግዚአብሔርን ለማገልገል ከፈለገ፥ ያለማግባት ነጻነት አለው። ጳውሎስ ይህንን የተሻለ ውሳኔ ነው ይላል።

ሁለተኛ፥ ሌሎች ምሁራን ይህ ምንባብ እንዲት ልጃገረድ ስላለችው አባት የሚናገር ነው ይላሉ። ለዚህች ልጅ ባል ይፈልግላት ወይስ ይተው? አሁንም ጳውሎስ ሰውዬው ለእግዚአብሔር መንግሥትና ለልጁ የሚሻለውን እንዲወስን ምርጫውን ትቶለታል።

ሠ. የጋብቻ ፍጻሜ ሊሆን የሚገባው ሞት ብቻ ነው። ስለሆነም የትዳር ጓደኛው የሞተበት ሰው እንደገና ለማግባት ወይም በላጤነት ለመኖር ነፃ ነው።

ረ. ክርስቲያን ከክርስቲያን ውጭ ሊያገባ አይችልም። እንግዲህ፥ የጳውሎስ መርሆች ከዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው? በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ከተጋባን በወሲባዊ ፍቅር እንደተገለጸው እንዳችን የሌላውን ፍላጎት በማሟላት የደስታን ድባብ መፍጠር እንዳለብን ገልጾአል። ወሲባዊ ፍቅር ክፉ ነገር ሳይሆን እግዚአብሔር ባለትዳሮች ደስ ይሰኙበት ዘንድ የሰጣቸው በረከት ነው። ሁለተኛ፥ ዋናው ነገር መጋባት ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነው። እግዚአብሔር አንድ ሰው በላጤነት እንዲኖር ከመራው፥ ሌሎች ክርስቲያኖች ሊሳለቁበት ወይም እንዲያገባ ጫና ሊያሳድሩበት አይገባም። ሙሉ ጊዜያቸውን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ስለመረጡ፥ ውሳኔያቸውን ማክበሩ ተገቢ ይሆናል። ያላገቡ ሰዎች ደግሞ ትዳርን ባለመመሥረታቸው ከማማረር ይልቅ እግዚአብሔርን በበለጠ ትጋት ለማገልገል ተጨማሪ ጊዜያቸውን ሊጠቀሙ ይገባል። ሦስተኛ፥ መፍታት ተገቢ አይደለም። ጋብቻ አንደኛው የትዳር ጓደኛ እስኪሞት ድረስ የሚቀጥል ነው። ወሲባዊ ፍቅር አንዱ ለሌላው ራሱን መስጠቱን የሚገልጽበት ስለሆነ፥ በትዳር ሕይወት ውስጥ ብቻ ሊካሄድ ይገባዋል። አራተኛ፥ አማኝ ከዓለማዊ ጋር መጋባት የለበትም። አምስተኛ፥ ክርስቲያን ከዓለማዊ ሰው ጋር ተጋብቶ በሚኖርበት ጊዜ በፍቅር ሕይወትና በመልካም ቃል ወደ ክርስቶስ ለመመለስ ሊማር ይገባል። ስድስተኛ፥ ወላጆች ልጆቻቸው በግላቸው በክርስቶስ እንዲያምኑ በጥንቃቄ ሊያስተምሯቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከትዳር ይልቅ ሳያገቡ መኖር የበለጠ ሥቃይና መከራ የሚያስከትልባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎችን ጠቃቅስ። ለ) እንደ ወንጌላዊ ላለ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ላጤ መሆን እንዴት እንደሚጠቅም በምሳሌ አብራራ። ሐ) ለሙሉ ጊዜ ከርስቲያን አገልጋይ የትዳር ሕይወት ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው መቼ ነው? መ) ጳውሎስ ስለ ጋብቻና ወሲባዊ ፍቅር ምን ዓይነት አመለካከት እንደነበረው በራስህ አገላለጽ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ይህ ከዛሬው አመለካከታችን የሚለየው እንዴት ነው? ሀ) እነዚህን ከ1ኛ ቆሮንቶስ 7 የተወሰዱትን መርሆች ለከርስቲያኖች ማስተማሩ ለምን ይጠቅማል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “ጋብቻን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች ጳውሎስ የሰጠው መልስ (1ኛ ቆሮ. 7፡1-40)”

  1. ተባረኩ በብዙ ከዚህም በላይ የእውነትን ቃል በመግለጥ እግዚአብሔር እውቀቱን ጥበቡን ያብዛላችሁ።

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading