Site icon

የ2ኛ ቆሮንቶስ መዋቅር እና አስተዋጽኦ

የ2ኛ ቆሮንቶስ መዋቅር

የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ከአንዱ ወደ ሌላው ርእሰ ጉዳይ ቢያመራም፥ በሦስት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል።

  1. ጳውሎስ የሚደግፉትን አብዛኛዎቹን የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያመሰግናቸዋል (2ኛ ቆሮ. 1-7)። ጳውሎስ በዕቅዱ መሠረት ለምን ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣ ያብራራል። የክስተቶችን ቅደም ተከተል በመስጠት ቆሮንቶስን በቁጣ ለመጎብኘት ወይም በተቃወሙት ጊዜ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ለመጠቀም እንዳልፈለገ ያስረዳል። ንስሐ ገብተው የእርሱን ሐዋርያነት መቀበላቸው እንዳስደሰተውም ይገልጻል። ከኃጢአቱ ንስሐ የገባውን ወንድም ወደ ኅብረቱ እንዲቀበሉት ይጠይቃል። ጳውሎስ እግዚአብሔር ደካማ ሰዎችን የዕርቅ መሣሪያዎቹ አድርጎ የሚጠቀምበትን አስደናቂ ምሥጢር ያካፍላቸዋል። እግዚአብሔር የሚፈልገው የተማሩትንና ኃያላንን ሳይሆን እርሱን ለመታዘዝ ራሳቸውን የሰጡትን ተራ ሰዎች ነው።
  2. ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ገንዘባቸውን አሰባስበው ለኢየሩሳሌም ድሆች እንዲልኩ ያበረታታቸዋል (2ኛ ቆሮ. 8-9)።
  3. ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ አይደለም ለሚሉት የሐሰት አስተማሪዎች ምላሽ ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 10-13)። ጳውሎስ በሐዋርያነቱ ስለከፈለው የስደት መሥዋዕት ገልጾአል። ዋናው ነገር ግን በጳውሎስ ድካም ውስጥ የተገለጸው የእግዚአብሔር ኃይል ነበር። ጳውሎስ ንስሐ ካልገቡ እንደ ሐዋርያ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደሚያመጣባቸው አመልክቷል።

የ2ኛ ቆሮንቶስ አስተዋጽኦ

  1. መግቢያ (2ኛ ቆሮ. 1፡1-11)
  2. ጳውሎስ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች በዕቅዱ መሠረት ለምን እንዳልጎበኛቸው ያብራራል (2ኛ ቆሮ. 1፡12–2፡13)።
  3. ጳውሎስ የሐዋርያነት አገልግሎቱን በመከላከል ለመንፈሳዊ መሪዎች ምሳሌነትን ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 2፡14-7፡16)።

ሀ. መንፈሳዊ መሪ በአዲሱ ኪዳንና በእግዚአብሔር የማስቻል ኃይል ላይ ያተኩራል (2ኛ ቆሮ. 2፡14–3፡18)።

ለ. መንፈሳዊ መሪ የወንጌሉ መዝገብ የሚገኘው በእግዚአብሔር ኃይል በንጹሕ ልብ በሚያገለግሉ ደካሞች ውስጥ መሆኑን ይገነዘባል (2ኛ ቆሮ. 4፡1-12)።

ሐ. መንፈሳዊ መሪ የወደፊቱን ዘላለማዊ ሽልማት እያሰበ በአገልግሎቱ ይጸናል (2ኛ ቆሮ. 4፡13-5፡10)።

መ. መንፈሳዊ መሪ ሰዎችንና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ የሚሻ የክርስቶስ አምባሳደር ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡11-6፡2)።

ሠ. መንፈሳዊ መሪ ከማያምኑ ሰዎች ጋር ባለመቀላቀል በንጽሕና ለመኖር ይወስናል (2ኛ ቆሮ. 6፡14-7፡1)፡፡

  1. በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የአመለካከት ለውጥ የጳውሎስ መደሰት (2ኛ ቆሮ. 7፡2-26)፡፡
  2. ጳውሎስ ለአይሁድ ክርስቲያኖች ስለሚሰጠው ምጽዋት ማብራሪያ ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 8-9)፡፡

ሀ. ጳውሎስ የስጦታውን ዓላማና እንዴት መሰብሰብ እንዳለበት ያብራራል (2ኛ ቆሮ. 8፡1-9፡5)፡፡

ለ. ጳውሎስ ለእግዚአብሔር በምንሰጥበት ጊዜ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ያስረዳል (2ኛ ቆሮ. 9፡6-15)፡፡

  1. ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያነቱን የሚያረጋግጡ ነጥቦችን በማቅረብ ይከራከራል (2ኛ ቆሮ. 10-13)፡፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version