ጳውሎስ ለአይሁድ ክርስቲያኖች ስለሚሰጠው የገንዘብ ዕርዳታ ማብራሪያ ሰጠ (2ኛ ቆሮ. 8፡1-9፡15)

አይናለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረች ጊዜ በገንዘብ እጥረት ትቸገር ነበር። አሥራት መክፈል እንዳለባት ብታውቅም፥ «እኔ በጣም ድሀ ነኝ፤ ለመጻሕፍት መግዣና ለመተዳደሪያ ገንዘብ ያስፈልገኛል፤ ተመርቄ ሥራ ላይ ስሰማራ እከፍላለሁ» ትል ነበር። ከተመረቀች በኋላ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ሥራ ተሰጣት። የሚከፈላት ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ የቤት ኪራይ፥ የምግብና የልብስ ወጪ ለመሸፈን ትቸገር ነበር። ስለሆነም፥ «እስካገባ ድረስ መጠበቅ አለብኝ። ያን ጊዜ ከባለቤቴ ጋር ተደጋግፈን አሥራት ልንከፍል እንችላለን» ስትል አሰበች። ባገባች ጊዜ ቶሎ በማርገዟ ሥራዋን አቆመች። የባለቤቷ ገቢ ብቻ ወጪያቸውን ለመሸፈን ካለመብቃቱም በላይ ልጅ በመውለዳቸው ለተጨማሪ ወጪ ተጋለጡ። አሁንም፥ «ልጄ ሲያድግ አሥራቴን እከፍላለሁ» አለች። ነገር ግን ልጇ አድጎ ወደ ሥራዋ ከተመለሰች በኋላ እንኳ ለእግዚአብሔር ሥራ ለመስጠት የሚበቃ ገንዘብ ያላቸው አልመሰላቸውም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሁልጊዜም ለእግዚአብሔር አሥራታችንን ላለመክፈል ማመኻኛ ማቅረብ የሚቀልለን ለምንድን ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያንህ አባላት በሙሉ ለእግዚአብሔር ከገቢያቸው አንድ እሥረኛውን እጅ የሚከፍሉ ይመስልሃል? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች አሥራት የማይከፍሉት ለምንድን ነው? መ) ገንዘባችንን የምንጠቀምበት መንገድ ቅድሚያ ስለምንሰጣቸው ነገሮችና ለክርስቶስ ስለመታዘዛችን እንዴት ያሳያል?

ከገቢያችን ለእግዚአብሔር አንድ አሥረኛ እጅ መስጠቱ መቼም ቢሆን ቀላል አይሆንም። ብዙውን ጊዜ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለማድረግ የሚያስችል በቂ ገንዘብ አናገኝም። እግዚአብሔር ግን ከምናገኘው ገንዘብ ለእርሱ አንድ አሥረኛውን እንድንሰጥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ደንግጓል (ዘሌዋ. 27፡30-32)። ሁሉንም ነገር የሰጠንና ፍላጎታችንን የሚያሟላው እግዚአብሔር ነው። ለእነዚህ በረከቶች እግዚአብሔርን ማመስገናችንን ከምንገልጽባቸው መንገዶች አንዱ ለእርሱ የተወሰነውን ክፍል መልሶ በመስጠት ነው። አሥራትን አለመክፈላችን እግዚአብሔር ላደረገልን ነገር አመስጋኞች አለመሆናችንን ሊያሳይ ይችላል። እንዲሁም፥ ከራሳችን በቀር ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ሌሎች ሰዎች ፍላጎቶች የማናስብ ራስ ወዳዶች መሆናችንን ያሳያል (ማቴ. 6፡33)። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚደሰተው አሥራትን በመክፈላችን ብቻ ሳይሆን ስለ አሥራቱ ባለን አመለካከት ጭምር ነው። አሥራትን ልንከፍል የሚገባን በፈቃደኝነት፥ በልግስናና በምስጋና ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮንቶስ 8–9 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመላክ ያሰበው ስጦታ ዓላማ ምን ነበር? ለ) ስለ መስጠት፥ ማለትም እንዴትና በምን ዓይነት ልብ መስጠት እንዳለብን ጳውሎስ የጠቃቀሳቸው መርሆች ምን ምንድን ናቸው?

ቀደም ሲል ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ለመሄድና በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ድሀ ክርስቲያኖች ምጽዋት ሰብስቦ ለመውሰድ መዘጋጀቱን በመግለጽ በእስያና ግሪክ ለሚገኙ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት መልእክት አስተላልፎ ነበር። እነዚህ የአይሁድ ክርስቲያኖች ለምን እንደደኸዩ አናውቅም። አንዳንድ ምሁራን ተደጋጋሚ ረሀብንና ጽኑ ስደትን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ሌሎች ደግሞ ክርስቲያኖቹ ክርስቶስ በፍጥነት ይመለሳል ብለው በማሰብ ቤቶቻቸውን በመሸጥ፥ ሥራዎቻቸውን በማቆምና በኅብረት በመኖር ለድህነት እንደተጋለጡ ያስረዳሉ (የሐዋ. 2፡44-47)። እንዳሰቡት ክርስቶስ በፍጥነት ባለመመለሱ የገቢ ምንጭ አጥተው ደኸዩ። ጳውሎስ ከርኅራኄና በአይሁድና በአሕዛብ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት ለማሳየት ሲል ሀብታም የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ለድሆቹ የአይሁድ ክርስቲያኖች ዕርዳታ እንዲያደርጉ ጠይቋል። የሚያሳዝነው አንዳንድ ሰዎች ይህን አሳብ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ጳውሎስ ገንዘቡን ለራሱ ሊወስድ ነው ብለው አስቡ።

  1. ጳውሎስ የስጦታውን ዓለማና እንዴት መሰብሰብ እንዳለበት ገለጸ (2ኛ ቆሮ. 8፡1-9፡5)፡፡

ሀ. ስለ ስጦታው አሳብ ያቀረበው ጳውሎስ ብቻ አልነበረም (2ኛ ቆሮ. 8፡1-5)። ቲቶ የበፊቱን ደብዳቤ ይዞ ወደ ቆሮንቶስ በሄደ ጊዜ ለኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ገንዘብ ስለማሰባሰብ ነግሯቸው ነበር። የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት መጀመሪያ አሳቡን ከተቀበሉ በኋላ በመስጠቱ ላይ ሰነፉ። ምናልባትም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ስጦታው ዓላማ ግራ ሳይጋቡና ጳውሎስ ገንዘቡን ለተሳሳቱ ምክንያቶች ይጠቀምበታል ብለው ሳያስቡ አልቀሩም።

(ማስታውሻ ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምእመናን ነፃ ሆነው በደስታ እንዲሰጡ ለማድረግ ገንዘቡ ስለሚውልበት ዓላማ ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መርዳትና ገንዘቡን በሚቆጣጠሩ ሰዎች ሊተማመኑ ይገባል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሁለት ነገሮች ካልተሟሉ የእግዚአብሔር ሰዎች የሚገባቸውን ያህል አይሰጡም።)

ጳውሎስ ማንንም እንዳላስገደደና እንደ መቄዶንያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በራሳቸው ነፃ ፍላጎት ለመስጠት እንደመረጡ አመልክቷል። የመቄዶንያ ክርስቲያኖች ገንዘብ ለመስጠት የወሰኑት ጳውሎስ ስለ ኢየሩሳሌም ወንድሞችና እኅቶች ካብራራላቸው በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ይህም ጳውሎስ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ስጦታዎችን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲልኩ ለመጠየቅ እንዲነሣሣ አበረታታው። የመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት በገንዘብ ሀብታሞች አልነበሩም። ብዙ ሰዎች ክርስትናን በመቀበላቸው ምክንያት ተሰድደው ሥራቸውን አጥተው ነበር። ነገር ግን «በጸጋ» (በእግዚአብሔር መንፈሳዊ በረከቶች) የበለጸጉ በመሆናቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ከሌሎች ጋር ለመካፈል ፈለጉ።

ጳውሎስን ደስ ያሰኘው መስጠታቸው ብቻ ሳይሆን፥ ለዚሁ ተግባር ያነሣሣቸው አመለካከታቸው ጭምር ነበር። የመቄዶንያ ክርስቲያኖች መጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ በመስጠታቸው አመስግኗቸዋል። በዚህም ጳውሎስ በመስጠት ውስጥ ስላለው ጠቃሚ አመለካከት አስተምሯል። ጳውሎስ በግዴታ ወይም በልማድ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናችንን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ከሰጠን በኋላ ገንዘባችንን መስጠት እንዳለብን አመልክቷል። ሕይወታችንን በሙሉ ለእግዚአብሔር ከሰጠን፥ እኛ ብቻ ሳንሆን የእኛ የሆነው ሁሉ የእግዚአብሔር ይሆናል። ከዚህ በኋላ አሥር እጅ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ለማስደሰት ስንል ያለንን ሁሉ እንሰጠዋለን። ገንዘብን መስጠት እግዚአብሔርን ከምናከብርባቸው መንገዶች አንዱ ነው።

ለ. ጳውሎስ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ሳይጎዱ በፈቃደኝነትና በልግስና እንዲሰጡ ያበረታታል (2ኛ ቆሮ. 8፡6-15)። ቲቶ የመጀመሪያውን (አሳዛኝ ደብዳቤ) ይዞ ወደ ቆሮንቶስ በሄደ ጊዜ፥ ገንዘብ መሰብሰብ እንዲጀምር መመሪያ ሳይሰጠው አልቀረም። ጳውሎስ ይህ ትእዛዝ እንዳልሆነና ለቅዱሳን ሁሉ ፍቅራቸውን የሚገልጹበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አመልክቷል። የቆሮንቶስ አማኞች እንደ እውቀት ወይም እምነት ባሉት ሌሎች መንገዶች የታወቁ ነበሩ። አሁን በመስጠትም የሚታወቁበት ሁኔታ ገጥሟቸዋል። የራስ ወዳድነት መንፈስ እንዳያይልባቸው እግዚአብሔር ስለ መስጠት ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ሀብታምና የሰማያዊ በረከቶች ሁሉ ባለቤት የነበረው ክርስቶስ ለእኛ ሲል ድህነትን መርጧል። ቤት፥ አልጋ፥ ምድራዊ ሀብት የሌለው ድሀ ሆነ። መስጠቱ ብልጽግናውን ነጠቀው። በሌላ በኩል በመዳናችን፥ የዘላለምን ሕይወት በማግኘታችን፥ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን በእርሱ ልግስና እኛ ሀብታሞች ሆነናል (ፊልጵ. 2፡5-8)።

ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጀመሩትን ነገር እንዲፈጽሙ አበረታቷል። ለኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ገንዘብ መሰብሰብ ጀምረው ስለነበር ይህንኑ ተግባር መፈጸም ያስፈልጋቸው ነበር። ነገር ግን ጉዳዩን አበክረው በመያዝ ለራሳቸው እስኪደኸዩ ድረስ ለመርዳት መሞከር አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር የቤተሰቡ አባላት ያላቸውን በማካፈል ተገቢ የሆነ የሀብት ምጣኔ እንዲለማመዱ ይፈልጋል። እግዚአብሔር ሌሎችን ለማበልጸግ ስንል ለራሳችን እንድንደኸይ አይፈልግም። ቤተ ክርስቲያን ችግረኞች የሚረዱባትና እነርሱም ዓቅሙ በሚኖራቸው ሰዓት ሌሎችን የሚረዱባት ልትሆን ይገባል።

አሥራት ሀብታሙም ሆነ ድሀው አግባብ በሆነ መንገድ ለእግዚአብሔር የሚሰጥበት መንገድ ነው። አሥር እጅ መስጠቱ ሀብታሙንም ሆነ ድሀውን እኩል ዋጋ ያስወጣዋል። በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት፥ ድሀው ሰው ካገኘው እሥር ብር አንድ ብር ቢሰጥና ሀብታሙ ሰው ከአምስት መቶ ብር ገቢው አምሳ ብር ቢሰጥ፥ ካላቸው እኩል ሰጥተዋል። እግዚአብሔር የሚመለክተው ብዙ መስጠታችንን ሳይሆን ካገኘነው አንጻር ትክክለኛውን መጠን መስጠታችንን ነው። ለመስጠት እጅግ ድሃ የሆነ ማንም ሰው የለም። ሰዎች እግዚአብሔር የሆነ ነገር ባይሰጣቸው ኖሮ ለመኖር እንኳን አይችሉም ነበር። ስለሆነም፥ የሌሎችን ያህል ብዙ ገንዘብ የለንም ብለው ሳያፍሩ የሚችሉትን ያህል ለእግዚአብሔር ሊሰጡ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ሰዎች ችግረኞችን የሚረዱበት የልግስና አሰጣጥ መንፈስ አለ? ከሌለ ለምን? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ምእመኖቿን፥ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አባሎችንና ዓለማውያንን ለመርዳት ምን ልታደርግ ትችላለች? ሐ) በቤተ ክርስቲያን ከሚሰበሰበው ገንዘብ ለድሆች የሚሰጠው ምን ያህል ነው? ቀሪውስ ገንዘብ ምን ላይ ነው የሚውለው? ድሆችን ለመርዳትና የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት ለማካሄድ በሚውለው ገንዘብ መካከል ጥሩ ሚዛናዊነት ያለ ይመስልሃል? መ) የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ ለወንጌሉና ለድሆች ከማዋል ይልቅ በራስ ወዳድነት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ መገልገል ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው?

ሐ. ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን በጎበኘ ጊዜ እርሱና የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዳያፍሩ ቲቶ ገንዘቡን ለመሰብሰብ ተመልሶ እንደሚሄድ ገልጾአል (2ኛ ቆሮ. 8፡16-9፡5)። የገንዘብ አሰባሰቡ ጳውሎስን፥ የመቄዶንያን ወኪሎችና ራሳቸው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን በማያስፍር መልኩ እንዲጠናቀቅ በማሰብ፥ ጳውሎስ ቲቶንና ሌሎች ሁለት ወኪሎችን አስቀድሞ ልኳል። ጳውሎስ ጉብኝቱ አማኞችን በማስተማርና በማበረታታት ላይ እንጂ በገንዘብ አሰባሰቡ ላይ እንዲያተኩር አልፈለገም ነበር።

ጳውሎስ የገንዘብ አሰባሰቡና የስጦታዎች አሰጣጡ ሂደት በመተማመን ይሞላ ዘንድ ከቲቶ ሌላ ሁለት ሰዎች ወደ ቆሮንቶስ እንደሚሄዱ ተናግሯል። ከሁለቱ ሰዎች አንደኛው «ስለ ወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነ ወንድም» ነበር። ይህ ወንድም መጀመሪያ ወደ ቆሮንቶስ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ከጳውሎስ ጋር ስጦታውን ይዞ እንዲሄድ በእስያና መቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተመረጠ ነበር። ይህ ወንድም ማን እንደሆነ ባናውቅም፥ አንዳንዶች ሉቃስ እንደነበረ ይናገራሉ። ሌላም ስሙ ያልተጠቀሰ ክርስቲያን የገንዘብ አሰባሰቡን ለማገዝ ተልኳል።

ጳውሎስ የገንዘብ አያያዝ ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጾአል። ገንዘብ ከፍተኛ ፈተና ሊሆን ይችላል። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለጌታ ሥራ የተቀበሉትን ገንዘብ ለራሳቸው ጥቅም በማዋል ኃጢአትን ፈጽመዋል። ደካማ የገንዘብ አያያዝም የአንድን መሪ ስም ሊያጎድፍ ይችላል። ጳውሎስ ራሱ ገንዘቡን ባይወስድም እንኳ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ ሊፈጠር ችሎአል። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታውቃቸውንና ገንዘቡን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚያስረክቡ የምታምናቸውን ሰዎች እንድትመርጥ ጠየቀ። ጳውሎስ ራሱ ሰዎችን ያልመረጠው በገንዘቡ የፈለጋቸውን ያደርጉ ዘንድ የገዛ ወዳጆቹን መረጠ ተብሎ እንዳይታማ በማሰብ ነበር። ይህ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊከተሉት የሚገባው የአስተዋይነት መርሆ ነው። አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ብቻውን ገንዘብ መያዝ የለበትም። ይህ ብዙውን ጊዜ ወደ ፈተናና ወደ አለመተማመን ይመራል። የጋራ ኃላፊነት የሚወስዱ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም አብረውት ሊሠሩ ይገባል። ዓላማቸውም፥ «በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን ማድረግ ነው።»

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ አላግባብ በመጠቀም ፈተና ውስጥ ሲገቡ የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ምእመናን መሪዎች የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ አላግባብ እየተጠቀሙበት ነው ብለው በማሰብ መጠራጠር ሲጀምሩ የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) መሪዎች ገንዘቡን ለመውሰድ እንዳይፈተኑ ወይም ምእመናኑ የምጽዋት ገንዘብ እየተበላ ነው ብለው እንዳይጠራጠሩ ምን ዓይነት ለውጥ ሊደረግ ይገባል?

  1. ጳውሎስ ለእግዚአብሔር በምንሰጥበት ጊዜ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ አስተማረ (2ኛ ቆሮ. 9፡6-15)

«የምንዘራውን ያንኑ መልሰን እናጭዳለን» የሚለው መንፈሳዊ መርህ ከብዙ የሕይወታችን ክፍሎች ጋር ይዛመዳል። የአዘራራችን ሁኔታ (የሰጠነው መጠንና የነበረን አመለካከት) የምናጭደውን ፍሬ ይወስናል። በገላትያ 6፡7-10 የኃጢአት ባሕርያችንን ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን ከዘራን ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድን እንደምናጭድ ተነግሮናል። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ በምንዘራው ዘር መጠን ላይ ትኩረት ሰጥቷል። ትንሽ ከዘራን ትንሽ እንሰበስባለን። ብዙ ከዘራን ብዙ እንሰበስባለን። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ትንሽ ብቻ ከሰጡ አነስተኛ በረከት እንደሚያገኙ ገልጾአል። ነገር ግን በደስታና በልግስና ቢሰጡ፥ እግዚአብሔር ይባርካቸዋል።

በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር በልግስና በሚሰጡት ሰዎች ላይ ጸጋውን እንደሚያዘንብና ፍላጎታቸውን ሁሉ (መንፈሳዊ፥ ቁሳዊና ሥነ ልቡናዊ) እንደሚያሟላላቸው ቃል ገብቷል። ለጋሽ የእግዚአብሔር ልጆች በሰናይ ምግባራት የበለጸጉ ይሆኑ ዘንድ ሁልጊዜም በቂ ሀብት ይኖራቸዋል።

ጳውሎስ እግዚአብሔር ልጆቹ በተሻለ ሕይወት ደስ ይሰኙ ዘንድ በረከትን ለመስጠት ቃል ይገባል አለማለቱን ልብ ማለቱ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ «ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ብትሰጠው የበለጠ አድርጎ የመመለስ ግዴታ አለበት። 100 ብር ብትሰጠው 500 ብር ይመልስልሃል» ይላሉ። በዚህ ዓይነት ለእግዚአብሔር መስጠትን ወደ ራስ ወዳድነት ተግባር ይለውጡታል። ጳውሎስ የፈለገው ይህንን ለማለት አልነበረም። ጳውሎስ የጻፈው የእግዚአብሔር ሀብት መልካም አስተዳዳሪ ከመሆን አንጻር ነው። ለእግዚአብሔር በልግስና ብትሰጥ ለበለጠ የሀብት እንክብካቤ ይተማመንብሃል። እግዚአብሔር የበለጠ ትሰጥ ዘንድ ብዙ ሀብት ይሰጥሃል። ጳውሎስ የሚናገረው ቁሳዊ በረከቶችን ስለመቀበል ብቻ ሳይሆን፥ ስለ ጽድቅ መከር ጭምር ነበር። በቸርነት በምንሰጥበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ጉዞ እናድጋለን። እግዚአብሔርንና መንግሥቱን አስቀድመን ለመሻት እንችላለን። የእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ተካፋዮች መሆናችንን በመገንዘብ ጥልቅ ደስታን እናገኛለን። እነዚህ ሁሉ ለእግዚአብሔር በምንሰጥበት ጊዜ በምላሹ ከምናገኛቸው በረከቶች ጥቂቶቹ ናቸው።

ጳውሎስ አማኞች በልግስናና በደስታ ለእግዚአብሔር በሚሰጡበት ጊዜ ምን እንደሚከሰት አብራርቷል።

ሀ. መስጠት ለእግዚአብሔር ምስጋናንና ውዳሴን ያመጣል። በችግር ላይ ያሉት ሰዎች ስጦታውን በሚቀበሉበት ጊዜ ካንተ ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንደመጣ ይነዘባሉ። ለችግራቸው ስለ ደረሰላቸው እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል።

ለ. እምነትህ ወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ እንደሆነ ታሳያለህ። ጳውሎስ የክርስቶስን ወንጌል ከተቀበላችሁ በኋላ ለምታሳዩት ታዛዥነት ሰዎች እግዚአብሔርን ያከብራሉ ብሏል። እምነታችንን ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ለክርስቶስ ስለመኖር መናገሩ እንደሚቀል ሁላችንም እናውቃለን። በልግስናና በደስታ በምንሰጥበት ጊዜ በራስ ወዳድነት ወይም የዚህን ዓለም በረከት ለማግኘት እንደማንኖርና በሰማይ ለራሳችን መዝገብን እየሰበሰብን መሆናችንን እናረጋግጣለን (ማቴ. 6፡19-21)።

ሐ. ሌሎች ሊያስታውሱንና ሊጸልዩልን ይጀምራሉ። አንዱ ክርስቲያን ስለ ሌሎች ጉድለት በሚያስብበት ጊዜ የክርስቶስ አካል ይጠናከራል። አሕዛብ ክርስቲያኖች የአይሁድ ክርስቲያኖችን በሚረዱበት ጊዜ በመካከላቸው የነበረው ክፍፍል ይወገድ ነበር። የአይሁድ ክርስቲያኖችም በበኩላቸው ለአሕዛብ ክርስቲያኖች ይጸልዩላቸው ነበር። ክርስቲያኖች በጸሎት መደጋገፋቸው ደግሞ ፍቅርንና አንድነትን ያመጣል።

ጳውሎስ መስጠት ፍቅርን መካፈልና ለሌሎች ጸጋን ማሳየት እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጾአል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ዋነኛ የጸጋ መገለጫ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ «የማይነገር ስጦታ» ሊያስታውሰን ይፈልጋል። እግዚአብሔር ክርስቶስን የሰጠን በማመንታት አልነበረም። ትንሹን ነገር ሳይሆን ካለው ሁሉ የሚበልጠውን ክርስቶስን በደስታ ሰጥቶናል። እኛም በተመሳሳይ መንፈስ ካለን ሁሉ የሚበልጠውን በልግስናና በደስታ ልንሰጥ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስላለፈው ዓመት አስብ። እግዚአብሔር በሕይወትህ የተለያዩ ክፍሎች የልግስና ስጦታን ያሳየው እንዴት ነው? ለ) ለእግዚአብሔር መልሰህ የሰጠኸውን ነገር ግለጽ። ስጦታዎችህ የልግስና፥ የደስታና ከሁሉም የተሻሉ ነበሩ? ለእግዚአብሔር ሥራ ቢያንስ 1/10ኛ ትከፍላለህ? በጸሎት መንፈስ ሆነህ ስጦታዎችህን አስብና እግዚአብሔር አሥራትን እንድትከፍል የሰጠህን ትእዛዝ በደስታ አክብር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading