- መንፈሳዊ መሪ ሰዎች አምነው የሚድኑበትን ዕድል ለመስጠት ሲል በመከራ ይታገሣል (2ኛ ቆሮ. 6፡3-13)።
ጳውሎስ በሕይወቱና በአኗኗሩ ምክንያት ማንም ሰው ከወንጌሉ እንዲያፈገፍግ አልፈለገም ነበር። የሚያከናውነው ተግባር ሁሉ ሰዎች ከክርስቶስ ፊታቸውን መልሰው የኋላ ኋላ ለኩነኔ እንዲጋለጡ የሚያደርግ ሳይሆን፥ ለማመን ሁኔታዎችን የሚያመቻችላቸው እንዲሆን ቆርጦ ነበር። ከዚህም የተነሣ፥
ሀ) ጳውሎስ ሰዎች ወንጌልን ይሰሙ ዘንድ አስፈላጊ የሆነውን መከራ ሁሉ በትዕግሥት ለመቀበል ወሰነ። ይህም ቀጥተኛ ስደትን ወይም የሕይወትን ሸካራ ገጽታዎች (ድካም፥ እንቅልፍ ማጣት፥ ረሃብ፥ ማጣትና የመሳሰሉትን) ያካትት ነበር።
ለ) ማንም ንጹሕ ልብ የለውም ብሎ እንዳይከስሰው ሕይወቱ ሙሉ በሙሉ ንጹሕ እንዲሆን ወሰነ።
ሐ) ጳውሎስ እንደ ቆሮንቶስ ያሉ አንዳንድ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ቢረዱትም፥ የእግዚአብሔር ባሕርያት የሆኑትን ትዕግሥትን፥ ፍቅርን ጽድቅንና እውነትን ይዞ ዘልቋል።
መ) በሕይወቱ ያለፈውን የእግዚአብሔርን ኃይልና በእርሱ በኩል የተከናወኑትን ተአምራቶች በግልጽ እንዲታዩ አድርጓል።
ሠ) ጳውሎስ ሰዎች አገልግሎቱን በሚቀበሉበት ጊዜ (ክብርና፥ መልካም ዘገባ ሲቀርብበት)፥ ወይም በተቃውሞ ተነሣሥተው አገልግሎቱን በሚያጥላሉበት ጊዜ (ውርደት፥ መጥፎ ዘገባ ሲቀርብበት፥ እንደ ግብዝ ሲታይ፥ እንዳልታወቀ ሰው ሲቆጠር) በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል።
- መንፈሳዊ መሪ ከማያምኑ ሰዎች ጋር ባለመተባበር በንጽሕና ለመመላለስ ይወስናል (2ኛ ቆሮ. 6፡14-7፡1)፡፡
ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች የሚከሰቱት ጥቂት ሰዎች ብዙዎችን የመበረዛቸው ውጤት ነው። የቆሮንቶስም ቤተ ክርስቲያን ችግር ይኼ ነበር። ጥቂት የሐሰት አስተማሪዎችና ፍላጎታቸው ባለመሳካቱ የተበሳጩ ሰዎች አሉታዊ ተጽዕኖ አሳደሩባቸው። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። ለእርሻ እንደ ተዘጋጁ በሬዎች እግዚአብሔርን ከማይከተሉ ሰዎች ጋር መጠመድ አያስፈልጋቸውም ነበር።
በመጽሐፍ ቅዱs ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከማያምኑ ወይም መንፈሳዊ ካልሆኑ ክርስቲያኖች ጋር ከመጠን ያለፈ ግንኙነት እንዳያደርጉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። የዚህ ክፍል ትምህርት የሚያመለክተው ክርስቲያኖች ከዓለማውያን ጋር መጋባት፥ የቅርብ የንግድ ሽርክና መፍጠር ወይም የዓመፅ ሕይወት ከሚመሩ ሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የቅርብ ጓደኝነት መመሥረት እንደሌለባቸው ነው። ከእነዚህ ነገሮች አንዱ በሚከሰትበት ጊዜ ክርስቲያኖች ሌሎችን መንፈሳዊ ሕይወት እንዲመሩ ከማበረታታት ይልቅ እንደ ዓለማውያኑ መኖር ይጀምራሉ። ይህም የክርስቲያኑን ምስክርነትና የአገልግሎት ዕድል ያጠፋል።
ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ እንደ ዓለማውያኑ እየኖሩ ለክርስቶስ ለመመስከር ሲሉ ጓደኝነት ይመሠርታሉ። የዚህ ዓይነቱ እርምጃ ግን ፍሬያማ አይደለም። ክርስቲያኖች እንደ ዓለማውያን በሚመላለሱበት ጊዜ የማብራት ኃይላቸውን ያጣሉ። ጳውሎስ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የሚኖርባቸው ቤተ መቅደሶች መሆናቸውን አመልክቷል። ከዓለማውያን ጋር ሽርክና መፍጠር የተቀደሰውን ነገር እግዚአብሔር ከሚጠላው ጋር እንደማደባለቅ ይሆናል። ክርስቶስን የማይከተሉ ሰዎች የቤልሆር (የሰይጣን ሌላ ስም) ናቸው።
ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከዓለማውያን አካባቢ ፈጽመው እንዲርቁ እያሳሰበ አለመሆኑን መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ይህ ለክርስቶስ የመመስከርን ዓላማ ያጠፋዋል። ነገር ግን እሴቶቻቸው፥ ተግባሮቻቸውና የቅርብ ጓደኝነቶቻቸው ከዓለማውያን እንዲለዩ ይፈልጋል። በዚህ ጊዜ ለክርስቶስ መልካም ምስክሮች ይሆናሉ። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሥጋቸውንም ሆነ ነፍሳቸውን ከሚያጎድፉ ነገሮችና ሰዎች እንዲያነጹ ጠይቋቸዋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ከማያምኑ ሰዎች ጋር “ሲጠመዱ” ያየህባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ይህ በክርስቲያኑ ሕይወት ላይ ምን አስከተለ? ሐ) ክርስቲያኖች በማያምኑ ሰዎች አመለካከቶችና አኗኗሮች ሳይበረዙ እንዴት መልካም ጓደኝነት ሊመሠርቱ እንደሚችሉ ግለጽ።
- ጳውሎስ በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መለወጥ መደሰቱን ገለጸ (2ኛ ቆሮ. 7፡2-16)፡፡
ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማስተካከል ይፈልግ ነበር። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሥራች ሆኖ ሳለ ክርስቲያኖቹ አግልለውት ነበር። ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና በእምነታቸው እንዲያድጉ ለማገዝ መሰጠቱን ከገለጸ በኋላ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የአለመተማመንና የጥርጣሬ አመለካከታቸውን አስወግደው እንደገና እንዲወዱትና እንዲያከብሩት ጠይቋል።
በ2ኛ ቆሮንቶስ 7፡5 ጳውሎስ የ2ኛ ቆሮንቶስን መልእክት ከመጻፉ በፊት በቲቶ በኩል ደብዳቤ በጻፈላቸው ጊዜ ከተከሰተው ሁኔታ (2ኛ ቆሮ. 2፡13) ይቀጥላል። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን በተመለከተ ቲቶን ለማነጋገር ወደ መቄዶንያ ሄዶ ነበር። ቲቶ በመጨረሻ ላይ ጳውሎስን በመቄዶንያ ባገኘው ጊዜ የቆሮንቶስ ሰዎች ንሥሐ የመግባታቸውን ዜና አበሰረው። ጳውሎስ ክርስቲያኖቹ ከእርሱ ጋር ለመታረቅ በወሰዱት የፍቅርና የንስሐ እርምጃ ከመጠን በላይ ተደሰተ። ይህም ጳውሎስና ቲቶ ቀደም ሲል በነበረው ሸካራ ግንኙነት ምክንያት ከደረሰባቸው ኀዘን እንዲጽናኑ አደረጋቸው። ጳውሎስ አዝኖ በጻፈው መንፈሳዊ ጠንካራ የማሳመኛ ደብዳቤ አማካኝነት እግዚአብሔር የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ንስሐ እንዲገቡ፥ ከጳውሎስ ጋር እንዲታረቁና፥ ይህም ደግሞ ደስታን እንዲፈጥር አድርጓል። በጳውሎስና በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መካከል እውነተኛ እርቅ ተካሄደ።
በክርስቲያኖች መካከል የአሳብ አለመግባባት መከሰቱ የማይቀር ነው። ነገር ግን አማኞች ለእውነተኝነት፥ ለፍቅርና ለአንድነት ሲተጉ፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ በመፍራትና ለቃሉ በመታዘዝ በሚመላለሱበት ጊዜ፥ አለመተማመናቸውን አስወግደው በዕርቅና በሰላም ሊኖሩ ይችላሉ። ይህም እግዚአብሔር ሰዎችን የማስታረቅ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ጠንካራ ምስክርነት ይሆናል።
ይህ ዕርቅ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደቻለ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። ዕርቁ የተገኘው ጳውሎስ የሕዝቡን ኃጢአት ሸፍኖ «ሁሉም መልካም ነው» በማለቱ አልነበረም። እውነትን በመደበቅና ኃጢአትን በመሸፋፈንም አልነበረም። ነገር ግን ጳውሎስ የመንገዳቸውን ትክክል አለመሆን፥ የተሳሳቱ አመለካከቶቻቸውንና ተግባሮቻቸውን አሳያቸው። መንፈሳዊ ንስሐ ሁልጊዜም ሦስት ነገሮችን ያካትታል። ሀ) የተፈጸመው ነገር በእግዚአብሔር ፊት ስሕተት መሆኑን አምኖ መቀበል፥ 2) መሳሳታችንን በመናዘዝ የእግዚአብሔርንና የበደልነውን ሰው ይቅርታ መጠየቅና 3) በኃጢአታችን እንዳንቀጥል ተግባራችንን መቀየር። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ኃጢአት መፈጸማቸውን በአግባቡ ሳይገነዘቡ ዕርቅን ለማካሄድ ይጥራሉ። መርዙ እስካልወጣ ድረስ እንደማይፈወሰው ቁስል፥ የዚህ ዓይነቱ ዕርቅ ወደ ፈውስ አያመራም። ችግሩ እንደገና ተከስቶ ብዙ ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በክርስቲያኖች መካከል ስለተፈጸመ የአሳብ አለመግባባት ግለጽ። ለ) አንድ ሰው ኃጢአትን በመሸፋፈን ይህን አለመግባባት ለማስወገድ ሊሞክር የሚችልበትን መንገድ ግለጽ። ሐ) እግዚአብሔር የመሠረተውን መንገድ በመከተል ዕርቅን መፈጸም ስለሚቻልበት መንገድ ግለጽ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)