Site icon

የገላትያ መልእክት መግቢያ

በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፥ «ድነትn (ደኅንነት) ለማግኘትና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ከፈለግህ መገረዝ አለብህ፥ በክርስቶስ ማመኑ ብቻ በቂ አይደለም» ይሉ ነበር። ዛሬም አንዳንድ ወንጌላውያን፥ «የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ከፈለግህ መጠጥ ማቆምና ሁለተኛ ሚስትህን ማባረር ይኖርብሃል፥ በክርስቶስ ማመኑ ብቻ በቂ አይደለም» ይላሉ። ወንጌል ምንድን ነው? አንድ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርበታል? ከዳንን በኋላስ እምነታችን ከታዛዥነት ሕይወታችን ጋር እንዴት ይዛመዳል? እነዚህ ሰዎች በታሪክ ሁሉ ያነሷቸው ጥያቄዎች ናቸው። «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» የሚለው ጥያቄ እንድ ሰው ሊያነሣ የሚችለው እጅግ አስፈላጊ ጥያቄ ነው። ይህ ወደ መንግሥተ ሰማይ ወይም ወደ ሲኦል መግባታችንን የሚወስን ጥያቄ ነው። ጳውሎስ በወንጌሉ ላይ ብንጨምር ወይም ብንቀንስ የዘላለም ጥፋት ሊደርስብን እንደሚችል በመግለጽ ያስጠነቅቃል (ገላ. 1፡8-9)። ስለሆነም ለሁሉም ክርስቲያን ስለ ወንጌሉ ግልጽ ግንዛቤ ማግኘቱ አስፈላጊ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ የማይቀበላቸው ሚዛናቸውን ያዛቡ ሁለት ጫፎች (አክራሪ አቋሞች) አሉ። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት አንዳች በጎ ተግባር መፈጸም አለብን የሚል አክራሪ አቋም አለ። በጳውሎስ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ይህ ማለት መገረዝ ወይም የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መጠበቅ ነበር። ዛሬ ደግሞ፥ አለመጠጣት፥ የተወሰኑ ልብሶችን አለመልበስ፥ የመሳሰሉት በዝርዝሩ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። እነዚህ ሁሉ አመለካከቶች የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በክርስቶስ ማመንና ተጨማሪ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። ሰዎች በወንጌሉ ላይ ሌሎች ነገሮችን የመጨመር ዝንባሌ አላቸው። በገላትያ መልእክት ውስጥ በወንጌል ትምህርት ላይ የሚጨምረው ትምህርት ተዳሷል። ሁለተኛ፥ የተወሰኑ እውነቶችና በክርስቶስ ላይ እምነት እስካለን ድረስ እንዳሻን ልንኖር እንችላለን የሚል ሌላ አክራሪ አቋም አለ። እነዚህ ሰዎች፣ እምነት እንዳሻን እንድንኖር ነፃ በማውጣት ያድነናል ይላሉ። ጳውሎስ ግን በእውነት ከዳንን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መመላለስ እንደሚገባን በአጽንዖት ያስገነዝባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ከእነዚህ የተራራቁ አቋሞች አንዱን ሰያስተምሩ የተመለከትኸው እንዴት ነው? ለ) ድነትን (ደኅንነትን) በተመለከተ የእምነትና የበጎ ተግባር ግንኙነት ምንድን ነው?

የገላትያ መጽሐፍ ሕግጋትን በመጠበቅና በድነት (ደኅንነት) መካከል ስላለው ግንኙነት መልስ ይሰጣል። ይህን በጣም ጠቃሚ መልእክት ሰምታነብበት ጊዜ ይህን ጥያቄ በአእምሮህ ያዝ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ገላትያ አንብብና ጸሐፊውን፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን፥ እንዲሁም መልእክቱን በተመለከተ የቀረቡትን አሳቦች ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን መዝገበ ቃላት በማንበብ ስለ አካባቢው፥ በዚያ ስለነበሩት ሰዎች፥ ስለ ሃይማኖታቸው፥ ወንጌሉ እዚያ እንዴት እንደደረሰ፥ ወዘተ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

  1. የገላትያ መልእክት ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ገላ. 1፡1-2 አንብብ። ሀ) የዚህ መልእክት ጸሐፊ ማን ነው? ለ) ጸሐፊው እንዲህ ዓይነት መልእክት ለመጻፍ የነበረውን ሥልጣን እንዴት ገለጸ? ይህንን ከ2ኛ ቆሮ. 1፡1 ጋር በማነጻጸር ምን ዓይነት ተመሳሳይነቶችንና ልዩነቶችን እንደምትመለከት አስረዳ።

የጥንት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአዲስ ኪዳን መልእክቶችን ፈር በሚያስይዙበት ጊዜ የጳውሎስን መልእክቶች ሁሉ በአንድ አካባቢ አስቀምጠዋቸዋል። የጳውሎስን ረዣዥም መልእክቶች (ከሮሜ እስከ 2ኛ ቆሮንቶስ) መጀመሪያ ካስቀመጡ በኋላ አጫጭሮቹን አስከተሉ። በዚህ መሠረት አራተኛው መልእክት የገላትያ መልእክት ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ጳውሎስ የጻፈው የመጀመሪያው መልእክት ሊሆን ቢችልም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከቀረቡት ሌሎች ሦስት የጳውሎስ መልእክቶች አጠር ስለሚል ከ2ኛ ቆሮንቶስ ቀጥሎ ሰፍሯል።

በሁሉም መልእክቶቹ እንደሚያደርገው ጳውሎስ ራሱን «ሐዋርያ» ሲል ይጠራል። ጳውሎስ እንደ ሐዋርያ በልዩ ሁኔታ የተመረጠ የእግዚአብሔር ወኪል ሲሆን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን አማካኝነት ይሠራል። ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ በመልእክቶቹ ውስጥ ሐዋርያነቱን ብቻ ገልጾ ያልፋል። ለገላትያ በጻፈው መልእክቱ ግን ጳውሎስ ስለ ሐዋርያነቱ አንዳንድ ነገሮችን ይናገራል።

በመጀመሪያ፥ ሐዋርያነቱ ከሰዎች እንዳልመጣ፥ 12ቱ ሐዋርያትም ሆኑ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያ አድርጋ እንዳልመረጠችው ይናገራል።

ሁለተኛ፡ ጳውሎስ ሐዋርያነቱ ከ«ሰው» እንዳልመጣ ገልጾአል። ምናልባትም ጳውሎስ ይህን ሲል የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መሪ የነበረው ጴጥሮስ እንዳልሾመው መግለጹ ይሆናል። እንደ ዛሬው ዘመን ሁሉ፥ በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ከዝነኛ ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት መሠረት ግለሰቦችን የመቀበል ወይም ያለመቀበል ዝንባሌ ነበር። ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያልነበራቸውና የድጋፍ ደብዳቤ ያልያዙ ሰዎች ይጠረጠሩ ነበር። ጳውሎስ የድጋፍ ደብዳቤ ስላልነበረው አንዳንድ ሰዎች ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ይጠራጠሩ ነበር። ዛሬም ምንም እንኳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር መልካም የሥራ ግንኙነት መመሥረቱ ጠቃሚ ቢሆንም፥ የቤተ ክርስቲያን መሪነት ከምናውቃቸው ሰዎች ወይም ከምርጫ እንደማይመነጭ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። በሥልጣን ማገልገል ካለብን ምንም እንኳ ጥሪውን ለማጽደቅ በሰዎች ሊጠቀም ቢችልም፥ እግዚአብሔር እንደጠራን ማስታወስ አለብን።

ሦስተኛ፥ ጳውሎስ ሐዋርያነቱና የወንጌልን ምንነት የመወሰን ሥልጣኑ ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደመነጨ ገልጾአል። እግዚአብሔር አብና ወልድ ጳውሎስ ሐዋርያ እንዲሆን መርጠውታል። እግዚአብሔር ለአገልግሎት መጥራቱን ለማጽናት ሌሎች ሰዎችን ሊጠቀም ይችላል። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የተወሰነ ተግባር እንድንፈጽምላቸው ሊቀጥሩን ይችላሉ። ነገር ግን አንድን ተግባር ለማከናወን እግዚአብሔር በቀጥታ እንደጠራን ካላወቅን፥ እግዚአብሔር እንደሚፈልግብን አድርገን ልናገለግል አንችልም። ሰዎች ምን እንደሚናገሩና እንደሚያስቡ፥ ደመወዛችንን የተወሰኑ ግለሰቦች እንዴት እንደሚቆጣጠሩ በማሰብ ልንፈራ እንችላለን። የአገልግሎታችንን ሥልጣን ከሌሎች እንደተቀበልን ብናስብ እውነትን በመናገር ሌሎች ሰዎች ኃጢአትን በሚሠሩበት ጊዜ ለትክክለኛው ነገር ልንቆም አንችልም። ብዙውን ጊዜ በራስ ወዳድነትና በግል ጥቅም ላይ ተመሥርተን ልናገለግል እንችላለን። የኋላ ኋላም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወይም አገልግሎቱን ልንጎዳ እንችላለን። ነገር ግን እግዚአብሔር ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ በእርግጠኝነት ካወቅን የእርሱን ብርሃን ተከትለን ትእዛዛቱን ልንጠብቅ እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን ሠራተኞች (ወንጌላውያን፥ መጋቢያን፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ የወጣቶች መሪዎች) የሚያገለግሉት እግዚአብሔር በቀጥታ ጠርቶናል ብለው ስለሚያስቡ ነው ወይስ ሰዎች ስለመረጧቸው ወይም ሥራ ስለተሰጣቸው? ለ) አንድ ሰው እግዚአብሔር ጠርቶኛል በሚል እምነት የሚያበረክተው አገልግሎት፤ በመመረጡ፥ ሥራ በማግኘቱ ወይም ደመወዝ በመቀበሉ ምክንያት ከሚሰጠው አገልግሎት እንዴት ይለያል?

  1. ጳውሎስ የገላትያን መልእክት ለማን ጻፈ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በገላትያ 1፡2፥ የመልእክቱ ተቀባዮች እነማን ናቸው? ለ) የሐዋ. 13፡13-14፡25 አንብብ። በጳውሎስና በርናባስ የመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ አብያተ ክርስቲያናት የተመሠረቱባቸውን ከተሞች ዘርዝር።

ጳውሎስ የገላትያን መልእክት የጻፈው በገላትያ ለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ነበር። «ገላትያ» የሚለው ቃል ሁለት የተለያዩ ነገሮችን ሊያመለክት በመቻሉ ምክንያት ምሁራን በዚህ አሳብ ላይ ብዙ ይከራከራሉ። ቃሉ በሰሜን ማዕከላዊ ቱርክ የሚገኙትን የገላትያ ሰዎች ወይም በትንሹ እስያ ውስጥ የነበረችውን የሮም እውራጃ ሊያመለክት ይችላል።

ጳውሎስ ለሰሜን ገላትያ እንደጻፈ የሚያስቡ ምሁራን፤ ሉቃስ በግልጽ ባይጠቅስም ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት እንደመሠረተ ያስባሉ። በሐዋርያት ሥራ 16፡6 ላይ ሉቃስ፥ «በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ» ይላል። ምሁራኑ በዚህ ቃል ላይ በመመሥረት፥ ጳውሎስ የደቡብ ገላትያን አብያተ ክርስቲያናት ከጎበኘ በኋላ ወደ ሰሜን ገላትያ ተጉዞ ሌሎች ከተሞችን እንደ ጎበኘና አብያተ ክርስቲያናትን እንደ መሠረተ ይናገራሉ። እነዚህ ምሁራን ጳውሎስ በትንሹ እስያ ሰሜን ማዕከላዊ አካባቢ የሚገኙትን «የገላቲያ» ጎሳዎች ለማመልከት ሲል «ገላትያ» የሚለውን ቃል እንደ ተጠቀመ ያስባሉ።

ሌሎች ብዙ ምሁራን ደግሞ ጳውሎስ በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ለመሠረታቸው የደቡብ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደጻፈ ያስባሉ። እነዚህ ምሁራን በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን በመሠረተበት የሮም አውራጃ የሚገኘውን ስፍራ ለማመልከት ገላትያ የሚለውን ቃል እንደተጠቀመ ይናገራሉ። ሉቃስ በሰሜን ገላትያ አብያተ ክርስቲያናትን መመሥረታቸውን ስለማይጠቅስ ይህ ትክክለኛው ምርጫ ይመስላል።

ጳውሎስ መልእክቱን ከመጻፉ ከ400 ዓመታት በፊት ከጥቁር ባሕር በስተሰሜን (በከፊል የአሁኑ ሩሲያ አካባቢ) የሚገኝ አንድ ጎሳ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች መፍለስ ጀመረ። አብዛኞቹ ወደ አውሮፓ ሲሄዱ፥ ጥቂቶቹ ደግሞ ወደ ሰሜን ማዕከላዊ የትንሹ እስያ ክፍል አመሩ። ግሪኮች እነዚህን ሰዎች ገላታይ ይሏቸዋል። የሮም መንግሥት በትንሹ እስያ ሲስፋፋ፥ እነዚህ ሰዎች የሮሜዎቹ አጋሮች ሆኑ። በ25 ዓ.ም ሮማውያን ከዚሁ የትንሹ እስያ ክፍል የተወሰነውን አንድ ላይ አድርገው ገላትያ ሲሉ ሰየሙት። ከተለያዩ ዘሮች የተሰባሰቡት እነዚህ የገላትያ ሰዎች በብዙ አማልእክት የሚያምኑ ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ። ጳውሎስና በርናባስ በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዟቸው (47-49 ዓ.ም) ወደ ገላትያ አውራጃ ደረሱ። ምክንያቱን ባናውቅም በፍጥነት ወደ ሊሲያ፥ ጵንፍልያና ከገላትያ አውራጃ ዐበይት ከተሞች አንዱ ወደነበረችው ወደ ጲስድያ አንጾኪያ አመሩ። በዚህ ስፍራም የመጀመሪያይቱን ቤተ ክርስቲያን መሠረቱ። ቤተ ክርስቲያኒቷ ሥራዋን ከጀመረች በኋላ ጳውሎስና በርናባስ በሮሜ በስተምሥራቅ የሚገኙትን ዋና መንገዶች በመያዝ በኢቆንዮንና በልስጥራን አብያተ ክርስቲያናትን ተከሉ። ከዚያ በመቀጠልም ጳውሎስ ያደገባትን የጠርሴስ ከተማ የምትገኝበትን የኪልቂ ክፍለ ሐገር በማቋረጥ በደርቤን ቤተ ክርስቲያንን መሠረቱ። በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጥቂት አይሁዶች ቢኖሩም፥ አብዛኛዎቹ አሕዛብ ነበሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አሕዛብ ከአይሁዶች በቁጥር ልቀው ተገኙ። የአይሁዶችና አሕዛብ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማምለክ ጳውሎስ በገላትያ መልእክት ውስጥ ያነሣቸውን ችግሮች አስከተለ።

ጳውሎስ አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ የአይሁድ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም የሚገኙ ሐዋርያት ልከውናል ብለው መጡ። በእግዚአብሔር ዘንድ እውነተኛ ተቀባይነት ለማግኘት ግርዛትን ተቀብለው ወደ አይሁድነት በመለወጥ የሙሴን ሕግጋት ሊጠብቁ እንደሚገባ አስተማሩ። ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ብዙዎች ትምህርታቸውን መከተል ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ለመሠረታቸው የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት የመጀመሪያ መልእክቱን ጻፈላቸው። ጳውሎስ ክርስቲያኖቹ ከእርሱ ከሰሙት ንጹሕ ወንጌል ወደ ሐሰተኛ ወንጌል እንዳይመለሱ ያስጠነቅቃቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህ የገላትያ ክርስቲያኖች አዳዲስ ክርስቲያኖች ነበሩ። ሀ) አዳዲስ ክርስቲያኖች በቀላሉ ግራ ተጋብተው ወደ ሐሰተኛ ትምህርት የመግባታቸው ጉዳይ በአንተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት ይታያል? ለ) አዳዲስ ክርስቲያኖች እምነታቸውን አውቀው በሐሰት ትምህርቶች ከመወሰድ እንዲጠበቁ ቤተ ክርስቲያንህ ምን ልታደርግ ትችላለች?

ጳውሎስ የገላትያን መልእክት የጻፈበት ዘመንና ስፍራ ጳውሎስ የጻፈው በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ለመሠረታቸው ሰሜናዊ የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት ከሆነ፥ መልእክቱ የተጻፈው ምናልባትም በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ወቅት ከኤፌሶን ከተማ ሊሆን ይችላል (53-57 ዓ.ም)።

ነገር ግን ጳውሎስ ከመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው በኋላና ከሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው በፊት ለደቡብ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት የሚጽፍ ይመስላል። የገላትያ መልእክት የተጻፈው ከኢየሩሳሌሙ ጉባኤ በፊት (የሐዋ. 15) ከሆነ፥ ከ48-49 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተጽፎአል ማለት ነው። የተጻፈው ከኢየሩሳሌም ጉባዔ በኋላ ከሆነ ግን ምናልባት ከ49-51 ዓ.ም ተጽፎ ይሆናል። ይህም ከጳውሎስ ሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ትንሽ ቀደም ብሎ ማለት ነው። የገላትያ መልእክት የተጻፈው ከሶርያ አንኪያ ሲሆን፥ ጊዜውም ጠቃሚው የኢየሩሳሌም ጉባኤ ሊካሄድ በተቃረበበት በ49 ዓ.ም ይመስላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version