የተቀደሰ ሕይወት ሳይኖሩ ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ አይቻልም። መቀደስ ማለት መለየት ማለት ነው። ስለሆነም፥ እኛ ከዓለም አሠራር ወይም አስተሳሰብ የተለየን ነን። ከኃጢአት የተለየን ነን። እንዲሁም ለእግዚአብሔር የተለየን ነን። ይህ ማለት በምናደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ማክበር አለብን። ጳውሎስ በዚህ የኤፌሶን ክፍል በቅድስና ላይ በማተኮር የሚከተሉትን እውነቶች ገልጾአል።
ሀ. መቀደስ ማለት ከዓለማውያን በተለየ መንገድ ማሰብ ነው። ቅድስና የሚጀምረው ከአስተሳሰባችን ነው። አእምሯችን የሕይወታችን፥ የባሕርያችንና የተግባራችን ምንጭ ነው። ያልታደሰ አእምሮ ዓለም የምታተኩርባቸውን ነገሮች በአስፈላጊነት ይገነዘባል። ስለሆነም፥ ዓለማዊ አእምሮ ስለ ወሲባዊ እርኩሰት፥ ጎሰኝነት፥ በትምህርት መኩራራት፥ ራስ ወዳድነትና የመሳሰሉት ያስባል። እግዚአብሔርን የሚያስደስት አእምሮ በቤተ ክርስቲያን በአንድነት ስለ መኖር፥ ስለ ምስክርነት፥ የተቸገሩትን ስለ መርዳትና ስለ ሌሎችም እግዚአብሔርን ደስ ስለሚያሰኙ ነገሮች ያስባል።
ለ. መቀደስ ማለት እግዚአብሔርን የማያስከብሩትን ነገሮች ለማስወገድና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚያንጸባርቁትን ነገሮች ለመልበስ መቁረጥ ነው። ጳውሎስ ይህንን ምርጫ ከልብስ ጋር ያነጻጽረዋል። የአንድ ሰው ልብስ በሚያድፍበት ጊዜ ያወልቅና ንጹሑን ይለብሳል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ተግባራችን፥ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን በኃጢአት በሚጎድፍበት ጊዜ አውጥተን በመጣል የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን በሚያሳዩ አዳዲስና ንጹሕ ባሕርያት እንለውጣቸዋለን። እነዚህ ልንለብሳቸው የሚገቡን ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?
- ውሸትንና በሌሎች የመጠቀምን ሁኔታ አስወግደን እውነትን እንናገራለን። እውነተኛ ተግባራትንም እናከናውናለን።
- ከሰዎች ጋር መልካም ግንኙነቶች ይኖሩናል። በሰዎች ላይ በምንቆጣበት ጊዜ በፍጥነት ቁጣችንን አስወግደን በኑዛዜና ይቅርታን በመጠየቅ ነገሮችን እናስተካክላለን።
- ከመስረቅና ከትጉሕ ሠራተኝነት ከመሸሽ ይልቅ በታማኝነትና በትጋት እንሠራለን። (መስረቅ የተለያዩ መልኮች አሉት። ከሥራ ቦታ እስክሪብቶ እንሥተን ስንጠቀም፥ በሰዓት ከሥራ ገበታችን ላይ ሳንገኝ ስንቀር ወይም ሰዓቱ ሳይደርስ ስንሄድና ሙሉ ክፍያ ስንቀበል እንሰርቃለን።) ግን ለምን እንሠራለን? ሀብታም ለመሆን ነው? ጳውሎስ ለሌላቸው ሰዎች የምናካፍለው እንዲኖረን መሥራት አለብን ብሏል።
- ሌሎችን ሰዎች ማማትና ስለ ወሲባዊ ርኩሰቶች መነጋገር ትተን ሰዎችን ስለሚያንጹና ስለሚያከብሩ ነገሮች ብቻ እንነጋገራለን። ለራሱ ለግለሰቡ የማንናገረውን ነገር ለሌሎች ልንናገርበት አይገባም። ስለ ሌላ ሰው ምንም ባንናገር መልካም ነው። ያውም ለምናማው ሰው ልንናገር የማንችለውን። የምንናገረው ሰሚውን የማያንጽ ከሆነም አለመናገሩ ይመረጣል።
- ከመራርነት፥ ቁጣ፥ ጠብ ወይም ስድብ የራቁ መንፈሳዊ ባሕርያት ይኖሩናል። ቸሮችና ርኅሩኆች በመሆን የሚጎዱንን ይቅር እንላለን። የይቅርታ ምሳሌያችን በክርስቶስ በኩል ኃጢአታችንን እግዚአብሔር ይቅር ማለቱ ነው።
- ከወሲባዊ ኃጢአቶች ሁሉ እንርቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ ከትዳር ጓደኛችን ጋር ብቻ ወሲብን እንድንፈጽም ያስተምረናል። ያላገቡ ሰዎች ከማግባታቸው በፊት ወሲብን መፈጸም የለባቸውም። ያገቡትም ከትዳር ጓደኞቻቸው ውጭ መሄድ የለባቸውም። እግዚአብሔር ከወሲብ ኃጢአት የማይመለሱትን ሰዎች እንደሚቀጣ ተናግሯል።
ሐ. እንቀደስ ዘንድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። ጳውሎስ ክርስቲያኖች እምነታቸውን የሚያንጸባርቅ የተቀደሰ ሕይወት መምራት እንዳለባቸው ካስተማረ በኋላ፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ባላቸው ግንኙነት ሊያደርጓቸው የሚገቧቸውን አያሌ ነገሮች ጠቅሷል። እግዚአብሔርን የሚያስከብር የተቀደሰ ሕይወት የምንኖርበትን ኃይል የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ከሆነ፥ በቀረበ መንፈሳዊ መንገድ ከእርሱ ጋር መዛመዳችን እጅግ አስፈላጊ ነው። (እነዚህ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተሰጡን ጥቂት ትእዛዛት ሁለቱ ናቸው። ብዙውን ጊዜ አዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ስለሚፈጽመው ተግባር እንጂ ከእርሱ ጋር በአግባቡ ለመዛመድ ምን ማድረግ እንዳለብን አይናገርም።)
አንደኛ፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ እንዳናሳዝን ይናገራል (ኤፌ. 4፡30)። መንፈስ ቅዱስን የምናሳዝነው እንዴት ነው? በቀዳሚነት መንፈስ ቅዱስን የምናሳዝነው ባልተናዘዝንባቸው ኃጢአቶች እንደሆነ ከዓውደ ንባቡ እንረዳለን። ጳውሎስ ከላይ የዘረዘራቸው ዓይነት የተሳሳቱ ተግባራትና አመለካከቶች በሕይወታችን ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ በውስጣችን የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስ እናሳዝናለን። መንፈስ ቅዱስን ካሳዘንነው፤ ኃጢአትን የምናሸንፍበትንና የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር የምንችልበትን ኃይል አይሰጠንም።
ሁለተኛ፥ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ አዞናል (ኤፌ. 5፡18)። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ እንዴት እንደምንሞላ ወይም በመንፈስ ቅዱስ መሞላት በሕይወታችን ምንን ሊያመጣ እንደሚችል አልተናገረም። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ስለምን ዓይነት መሞላት እንደሚናገር ለመረዳት ዓውደ ንባቡ ሳይረዳን አይቀርም። ጳውሎስ አጽንኦት የሰጠው እንደ ልሳን ወይም ተአምራት ባሉት አስደናቂ ነገሮች ላይ ሳይሆን፥ የተቀደሰ ሕይወት በመኖርና እግዚአብሔርን በማምለክ ላይ ነው። በቅድስና ስንመላለስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንኖራለን። እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ልንኖር የምንችለው መንፈስ ቅዱስ ከረዳን፥ ከሞላን፥ ብሎም የኃጢአትን ተፈጥሮ የምናሸንፍበትን ኃይል ከሰጠን ብቻ ነው። በመንፈስ ቅዱስ በምንሞላበት ጊዜ በቅድስና መመላለስ ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድም እናመልካለን። እነዚህ ሁለቱ በዚህ ስፍራ በሚያስገርም ሁኔታ ተያይዘዋል። የተቀደሰ ሕይወት እስካልኖርን ድረስ እግዚአብሔርን የሚያስደስት አምልኮ ልናካሂድ አንችልም። በመንፈስ ቅዱስ መሞላት አምልኳችንንም ሆነ አኗኗራችንን ያግዘዋል። አኗኗራችን ወይም አምልኳችን ከወንጌሉ ጋር ካልተጣጣመ፥ በልሳን ብንናገር ወይም ተአምራት ብንሠራም በመንፈስ ቅዱስ አልተሞላንም። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት ምን ማድረግ እንዳለብን ያልተናገረው ምናልባትም በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት የሚያስፈልገው ብቸኛው ቅድመ-ሁኔታ ለእግዚአብሔር የተገዛና በቅድስና የተሞላ ሕይወት ስለሆነ ይሆናል። ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት እንድንጸልይ እልተነገረንም። ነገር ግን ኃጢአታችንን ከተናዘዝን፥ ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ከተገዛንና መንፈስ ቅዱስን ከታዘዝን፥ ይሞላናል፥ ይቆጣጠረናል፥ ኃጢአትን እንድናሸንፍና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንድንኖር ኃይልን ይሰጠናል። ኃጢአትን በምንሠራበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ አልተሞላንም ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት ከተሰጡት ገለጻዎች አንዱ «በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ክርስቲያኑ በተግባርና በባሕርይ ክርስቶስን ይመስል ዘንድ በሕይወቱ ውስጥ ለሚሠራው ለመንፈስ ቅዱስ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥበት ልምምድ ነው» የሚል ነው።
ማስታወሻ፡— በአዲስ ኪዳን ውስጥ፥ ሦስት የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ዓይነቶች የሚታዩ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት መንፈሳዊ ብስለት ላለው ሰው የተሰጠ አገላለጽ ይመስላል። ለዚህም ምክንያቱ ግለሰቡ አብዛኛውን ጊዜ ለመንፈስ ቅዱስ በመታዘዝ መኖሩ ነው ( የሐዋ. 6፡3)። ምንም እንኳ ሁሉም ክርስቲያኖች በዚህ ዓይነት ሕይወት ባይኖሩም፥ እግዚአብሔር ከሁላችንም ይህንኑ ይጠብቃል። ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡18 ስለ መንፈስ ቅዱስ ሙላት የተናገረው ከዚህ አንጻር ነው። ሁለተኛ፥ አዲስ ኪዳን አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለአንድ ሰው የሚሰጠውን የተለየ የሕይወት ዘመን አገልግሎት ለማመልከት በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን ይጠቅሳል። መጥምቁ ዮሐንስ ለነቢይነት አገልግሎቱ ከተወለደ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላ ተነግሮለታል (ሉቃስ 1፡15-17)። ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ይሆን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላ ተገልጾአል (የሐዋ. 9፡17)። ሦስተኛ፥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ማለት አንድ ሰው ድንገተኛ ሁኔታን ለመቋቋም እንዲችል መንፈስ ቅዱስ ሲያስታጥቀው ማለት ሊሆንም ይችላል። ተግባሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ይሄ ማስታጠቅ ይወሰዳል። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በአብዛኛው ያገለገለው በዚህ መልኩ ነው። ጴጥሮስ በሃይማኖት መሪዎች ፊት በቆመ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ነበር። እስጢፋኖስ ቀደም ሲል በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞላ የተገለጸ ሲሆን፥ ሊሠዋ ሲልም እንደገና ተሞልቷል። ጳውሎስ በምትሐተኛው ላይ የተግሣጽ ቃል በተናገረ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላ ተገልጾአል (የሐዋ. 4፡8፥ 31፤ 7፡55፤ 13፡9)።]
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ብዙ ክርስቲያኖች በቅድስና ለመኖር ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች የሚቸገሩት በየትኞቹ አካባቢ ነው? ለ) አንተስ? ሐ) መንፈስ ቅዱስ በሕይወትህ እርሱን የሚያሳዝን ነገር ካላ እንዲያሳይህ ጠይቀው። መንፈስ ቅዱስ ይቅር እንዲልህና በሕይወትህ የሚገኙትን መጥፎ ልማዶች፥ ጥሩ ያልሆኑ አስተሳሰቦችና ኃጢአቶች የምታሸንፍበትን ኃይል እንዲሰጥህ ጠይቅ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)