ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች እንደ ፈውስ፥ በልሳን መናገር፥ ቁሳዊ ሀብት፥ መንፈሳዊ ያደርጉናል ብለው በሚያስቧቸው መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ሲያተኩሩ፥ ወይም በሐሰት ትምህርት ሲወሰዱ ምን ይከሰታል? በዚህ ጊዜ ክርስቶስን ሳይሆን ሰዎችን (ራሳቸውን ወይም ሌሎች)፥ ወይም የዓለምን ነገሮች ይመለከታሉ። የቆላስይስ ክርስቲያኖች አንዳንድ ስዎች ጠቃሚዎች ናቸው ያሏቸውን ነገሮች ይመለከቱ ነበር። አንዳንዶች የተወሰኑ ሕግጋትን ወይም ደንቦችን መጠበቃቸው ወሳኝ እንደሆነ ይነግሯቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሊያውቁት የሚገባቸው ልዩ መንፈሳዊ ምሥጢር እንዳለ ይነግሯቸዋል። የቆላስይስ አማኞች እነዚህን ሁሉ የሐሰት ትምህርቶች እያደመጡ ክርስቶስን ከመመልከት ታቀቡ። የመንፈሳዊ ሕይወታችን ሚዛን የሚጠበቀው እርሱን ብቻ ለመምሰልና ለማስከበር በማሰብ ወደ ክርስቶስ የተመለከትን እንደሆነ ነው። የቆላስይስ ክርስቲያኖች በቀጥታ ከሐሰተኛ መምህራን ስለተማሩና በተዘዋዋሪ ደግሞ ጠቃሚ ባልሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር ስለጀመሩ፥ ክርስቶስን እንደሚገባቸው ሊያከብሩት አልቻሉም ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ በሕይወታቸው ዋናው ነገር ክርስቶስ እንደሆነ ያስተምራቸዋል።
ክርስቶስ ምን ያህል ታላቅ ነው? ኖስቲኮች ወይም የይሖዋ ምስክሮች እንደሚያስተምሩት ከእግዚአብሔር ያነሰ አምላክ ነውን? ወይስ ከእግዚአብሔር አብ የተለየና እኩል የሆነ የሥላሴ አካል ነው? ጳውሎስ ክርስቶስ ከአብ ጋር እኩል እንጂ የማይተናነስ መሆኑን ያስረዳል።
ጳውሎስ የሚገልጻቸውን ነገሮች ቀጥለን እንመልከት።
ሀ. ክርስቶስ የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። ጳውሎስ በዚህ ዐረፍተ ነገር ሁለት ዐበይት እውነቶችን ያስተላልፋል። በመጀመሪያ፥ ወልድ ከአብ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ያስረዳል። ከእግዚአብሔር አብ ጋር የመንትያ ዓይነት ተመሳሳይነት አለው ልንል እንችላለን። (ከዕብራውያን 1፡3 ተመሳሳይ አገላለጽ መመልከት ይቻላል።) ኢየሱስን ማየት እግዚአብሔር አብን እንደ ማየት ነው ( ዮሐ 14፡9)። ሁለቱም በባሕርይ፥ በኃይል፥ በአሳብ፥ በስልጣን ተመሳሳይ ናቸው። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ምንም እንኳን አብ ለሰዎች ባይታይም ወልድ የሚታይ መሆኑን ያስረዳል። ስለሆነም የሚታየውን ክርስቶስን መመልከት የማይታየውን እግዚአብሔርን እንደ ማየት ነው። ከውስን ሰብአዊ እይታችን የተነሣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ክርስቶስ በምናነብበት ጊዜ የቀድሞዎቹ ሐዋርያትም በተመለከቱት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል በግልጽ እንረዳለን (ዮሐ. 1፡18፥ 14፡9)።
ለ. ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው። «በኩር» የሚለውን ቃል መረዳት ያለብን ዛሬ ቃሉን በምንገነዘብበት መልኩ ሳይሆን አይሁዶች በሚረዱበት መንገድ ሊሆን ይገባል። የይሖዋ ምስክሮች ይህን ጥቅስ በመጠቀም ኢየሱስ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ፍጥረት እንደሆነና በዚህም ምክንያት ከአብ እንደሚያንስ ያስተምራሉ። ነገር ግን ይሄ ቃል የመጣው ከብሉይ ኪዳን ነው። በአይሁድ ባሕል በኩር የሚለው ቃል ልዩ የክብር ስፍራ ማግኘትን ያሳያል። በቤተሰብ ውስጥ ልዩ ክብር የሚያገኘው መጀመሪያ የተወለደው ልጅ ነበር። እስራኤል የእግዚአብሔር በኩር ተብላ ትጠራ ነበር። ይህም ከሌሎች የዓለም አገሮች የተለየ ስፍራ እንደነበራት ያመለክታል (ዘጸ. 4፡22)። የእሰይ የመጀመሪያ ልጅ ያልነበረው ዳዊት ከሌሎቹ አይሁዶች የተለየ የክብር ስፍራ ስለነበረው በኩር ተብሏል (መዝ 89፡27)። ጳውሎስ ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ ገዢና የበላይ መሆኑን ለማሳየት ይፈልጋል። እርሱ ከፍጥረት ሁሉ የቀደመ ስፍራ አለው። ታላቅነቱም የፍጥረት ሁሉ ጀማሪ በመሆኑ ተረጋግጧል።
ሐ. ክርስቶስ የተፈጠረው ነገር ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ በሰማይ የመላዕክት በምድር ደግሞ የእንስሳት፥ የዕፅዋትና የሰዎች ምንጭ ነው። እርሱ ሰዎች የሚያዩዋቸውንና የማያይዋቸውን ነገሮች የፈጠረ አምላክ ነው። እዚህ ላይ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የኖስቲኮችን አስተሳሰብ በመሠረታዊነት እየተጠቀመ ነው ይላሉ። ኖስቲኮች ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ስለ አማላጆች ወይም ትናንሽ አማልእክት ያስተምር ነበር። እነዚህንም አማልእክት «ጌትነት፥ አለቅነት፥ ሥልጣናት» ሲሉ ይገልጻሉ። ጳውሎስ እንደዚህ ዓይነት ትናንሽ አማልእክት አሉ ብሎ አያምንም። ቢኖሩ እንኳ በክርስቶስ የተፈጠሩ ስለሚሆኑ ከክርስቶስ ማነሳቸው አይቀርም። ነገር ግን ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የተጠቀመው ስለ መላዕክት ለመናገር ይመስላል። ሰብአዊ ሠራዊቶች የሥልጣን ደረጃ (ኮሎኔል፥ ጄኔራል፥ ወዘተ.) እንዳላቸው ሁሉ፥ የእግዚአብሔር መላዕክትም የሥልጣን ደረጃዎች አሉዋቸው። እነዚህንም ጳውሎስ ዙፋናት፥ ኃይላት፥ ጌትነትና ሥልጣናት ሲል ይገልጻል። ነገር ግን መላዕክት ምንም ያህል ታላቅ ቢሆኑም ክርስቶስ ፈጣሪያቸው በመሆኑ ይበልጣቸዋል።
መ. ክርስቶስ ከፍጥረት ሁሉ ቀዳሚ ነው። ዮሐንስ 1፡1 ክርስቶስ ሁልጊዜም ከእግዚአብሔር ጋር የኖረ ዘላለማዊ አምላክ እንደሆነ ተገልጾአል። ስለሆነም ከማንኛውም ነገር በፊት እርሱ ነበር።
ሠ. ፍጥረታትን ሁሉ ያያያዘው ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ሁሉን ነገር መፍጠር ብቻ ሳይሆን እንዳይጠፋም ይጠብቃል። አንድ መካኒክ መኪና አገልግሎት መስጠቷን እንድትቀጥል እንደሚያደርግ ሁሉ ክርስቶስ ዓለም ጉዞዋን እንድትቀጥል ያስችላታል።
ረ. ክርስቶስ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱ የቤተ ክርስቲያን መሪና ጠባቂ ነው። ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው።
ሰ. ክርስቶስ ከሙታን በኩር ነው። መጀመሪያ በአዲስ የትንሣኤ አካል ከሞት የተነሣው እርሱ ነው። በሙታንም ላይ ሥልጣን ያለው እርሱ ነው። ሙታንን ከሞት የሚያስነሣቸውም እርሱ ነው።
ሽ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር ሙላት ሁሉ አለው። ጳውሎስ ይህን ሲል ክርስቶስ የእግዚአብሔር ባሕሪያት፥ ኃይላት፥ ሥልጣን፥ ችሎታ፥ ወዘተ… እንዳሉት መግለጹ ነው። እግዚአብሔር ያለው ሁሉ ክርስቶስም አለው። አንዳንድ ኖስቲኮች ያስተምሩ እንደነበረው እርሱ ከትናንሽ አማልእክት አንዱ አልነበረም።
ቀ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዕቅዶች ፍጻሜ ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የሚፈጽማቸው ሁለት ዓላማዎች እንደ ነበሩት ይናገራል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ የበላይ ይሆናል። ይህም ክርስቶስ የነገሮች ሁሉ ገዢና ጌታ እንደሚሆን ያሳያል። በፊልጵስዩስ 2፡10-11 አንድ ቀን በሰማይና በምድር የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ በክርስቶስ ፊት ተንበርክከው እንደሚሰግዱና እንደሚያከብሩት እንመለከታለን። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች ለማስታረቅ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። ሰይጣንና የሰው ልጆች በኃጢአት መውደቃቸው በሰማይና በምድር ላይ ተጽዕኖ አስከትሏል። እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት በፍጥረታት ላይ የደረሰውን ይህንኑ መለያየት ለማስወገድ ክርስቶስን ለመሣሪያነት ተጠቅሟል። በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ምክንያት ዕርቅ በመርሕ ደረጃ ተከናውኗል። ኖስቲኮች እንደሚያስተምሩት የክርስቶስ ሰብአዊ አካል ክፉ ሳይሆን ስረከት ነበር። እግዚአብሔር የነገሮችን የመጨረሻ ዕርቅ ተግባራዊ ለማድረግ ክርስቶስን ይጠቀማል።
ከዚያም ጳውሎስ ይህ የዕርቅ ሥራ በቆላስይስ ክርስቲያኖች ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያስከትል ያብራራል። የተመረጠው የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ባለመሆናቸው ምክንያት አሕዛብ፥ ከእግዚአብሔር መንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ የራቁ ነበሩ። አሕዛብ በአስተሳሰባቸውና በተግባራቸው በእግዚአብሔር ላይ ያምፁ ነበር። ነገር ግን ከክርስቶስ አካላዊ ሰውነትና በመስቀል ላይ ከመሞቱ የተነሣ የሚያምኑ አሕዛብ በእግዚአብሔር ፊት ቅዱሳን፥ እንከን የሌላቸውና ከክስ የነፁ ነበሩ። ነገር ግን ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ፍርድ በሚያስከትሉ የስሕተት ትምህርቶችና ተግባራት እንዳይጠመዱ ያስጠነቅቃቸዋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ ማን እንደሆነና ምን እንዳደረገልን በግልጽ መረዳቱ ጠቃሚ የሚሆንባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) ስለ ክርስቶስ የተገለጹ ዘጠኝ ነጥቦች እያንዳንዳቸው ዛሬ በሕይወታችን ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያስከትሉ ግለጽ። ለእያንዳንዱ ነጥብ አንድ ምሳሌ ልጥ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)