የ1ኛና የ2ኛ ተሰሎንቄ ማን ጻፈው፣ ለማን ተጻፈ፣ የትና መቼ ተጻፈ

የ1ኛና የ2ኛ ተሰሎንቄ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ተሰ. 1፡1 እና 2ኛ ተሰ. 1፡1 አንብብ። ሀ) የእነዚህ ሁለት መጻሕፍት ጸሐፊ ማን ነው። ለ) እነዚህ መግቢያዎች የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ሐ) በዚህ ክፍልና በገላ. 1፡1 ጸሐፊው ራሱን የገለጸባቸው መንገዶች የሚለያዩት እንዴት ነው? መ) እነዚህ መልእክቶች የተጻፉት ለማን ነበር? የመልእክቶቹ ተቀባዮች የተገለጹት እንዴት ነው?

የ1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች የሚጀምሩት በተመሳሳይ መንገድ ነው። የመጽሐፉ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ ራሱንና ሁለት የቅርብ ባልደረቦቹ የሆኑትን አገልጋዮች (ሲላስና ጢሞቴዎስ) ያስተዋውቃል። ሲላስና ጢሞቴዎስ መልእክቱን ጽፈዋል ማለቱ ተገቢ አይሆንም። እነርሱ ከጸሐፊው ከጳውሎስ ጋር አብረው የሚሠሩ አገልጋዮች ነበሩ።

መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነበር?

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 17፡1-9 አንብብ። ሀ) በተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተመሠረተች ግለጽ። ለ) ከዚህ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ያለውን ካርታ ተመልከት። ተለሎንቄ የት ትገኛለች? በአሁኑ ዘመን በየት አገር ውስጥ እንደምትገኝ ግለጽ።

የተሰሎንቄ ከተማ ከፊልጵስዩስ በስተደቡብ ምዕራብ 50 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ስትሆን፥ የሮም አውራጃ የሆነችው የመቄዶንያ ርእሰ ከተማ ነበረች። ተሰሎንቄ ከእስያ ተነሥቶ በግሪክ በኩል ወደ ሮም የሚሄድ ታላቅ የንግድ ጎዳና የሚያቋርጣት ወሳኝ ከተማ ነበረች። በተጨማሪም ተሰሎንቄ የባሕር ወደብና በግሪክ፥ ብሎም በመቄዶኒያ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ከተማ ነበረች። 200,000 ሕዝብ የሚኖርባት ተሰሎንቄ በመቄዶኒያ አውራጃ ውስጥ ምናልባትም በሕዝብ ብዛትና በብልጽግና ተወዳዳሪ ያልነበራት ሳትሆን አትቀርም።

የተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በሁለተኛው የጳውሎስ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ወቅት ነበር። በዚህ ጉዞው ጳውሎስ ወንጌልን ወደ መቄዶኒያ እንዲወስድ መንፈስ ቅዱስን እንደመራው ታስታውሳለህ። ጳውሎስ ያገለገለባት የመጀመሪያዋ ታላቅ ከተማ ፊልጵስዩስ ነበረች። ጳውሎስ እዚያ ከታሠረ በኋላ ከሲላስና ጢሞቴዎስ ጋር በመሆን ሁለት ትናንሽ ከተሞችን አቋርጦ በክልሉ ውስጥ ወደምትገኝ ወደ ሌላዋ ትልቅ ከተማ አመራ። እርሷም የተሰሎንቄ ከተማ ነበረች። ጳውሎስ በተሰሎንቄ ውስጥ መጀመሪያ በምኩራብ ውስጥ ለሚገኙ አይሁዶች፥ ከዚያም ሊሰሙት ለፈቀዱት ሰዎች ሁሉ ወንጌልን ሰብኳል። በዚህ ጊዜ ጥቂት አይሁዶችና አሕዛብ በክርስቶስ በማመናቸው የተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ በእነዚህ ጥቂት አማኞች ላይ ስደት ተነሣ። ከፊልጵስዩስ በተቃራኒ ስደቱ መጀመሪያ የተነሣው ከአሕዛብ ሳይሆን ከአይሁዶች ነበር። እነዚህ አይሁዶች ሀብታም አሕዛብን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ወንጌልን በመቀበላቸው በቅንዓት ተነሣሡ። ጳውሎስና ሲላስን ለመያዝ በመሻት የሕዝብ ሁከት እንዲቀሰቀስ አደረጉ። ሕዝቡ ግን የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነውን እያሶንና የአካባቢውን ክርስቲያኖች ብቻ ነበር የያዙት። እነዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በገዢዎች ፊት ቀርበው በመንግሥት ላይ ክህደት ፈጽመዋል በሚል ተከሰሱ። ገዢው የቀረበውን የሐሰት ክስ ከመረመረ በኋላ አማኞቹን በነፃ አሰናበተ።

ጳውሎስና ሲላስ በተሰሎንቄ ከተማ ምን ያህል ጊዜ እንደቆዩ አልተገለጸም። ምናልባትም ለአንድ ወር ያህል ቆይተው ይሆናል። የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ጳውሎስና ሲላስ ለተጨማሪ ችግር እንዳይጋለጡ በማሰብ ከከተማይቱ ፈጥነው እንዲወጡ አድርገዋል። ምንም እንኳ ጳውሎስ በተሰሎንቄ ከተማ ብዙ ጊዜ ሊቆይ ባይችልም፥ ወንጌሉን ለመስበክና እነዚህን አዳዲስ አማኞች ለማስተማር ብዙ ተግቶ ሠርቷል። ነገር ግን ከነበረው አጭር ቆይታ የተነሣ የሚፈልገውን ያህል እውነት ሁሉ ሊያስተምራቸው አልቻለም። ከዚህም የተነሣ ወደ በኋላ በአማኞች መካከል ግራ መጋባት ተከሠተ። ይህም በተለይ የአማኞችን ትንሣኤና የክርስቶስን ዳግም ምጽአት የሚመለከት ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ እነዚህን አስተምህሮዎች ለማብራራት ሲል የ1ኛና የ2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶችን ለመጻፍ ተገደደ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በስደት ወይም በመከራ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ዓላማና ፍቅር የሚጠራጠሩባቸውን መንገዶች አብራራ። ለ) በእነዚህ ጊዜያት አማኞች የእግዚአብሔርን ፍቅር ማስታወሳቸውና ክርስቶስ እውነታቸውን እንደሚጠብቅ መገንዘባቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ዮሐ 10፡38 እና ሮሜ 8፡31-38 አንብብ። ለአማኞች የተሰጡት የተስፋ ቃሎች ምን ምንድን ናቸው? ስደትና መከራ በሚደርስብን ጊዜ እነዚህ የተስፋ ቃሎች እንዴት ያበረታቱናል?

ሁለቱም መልእክቶች የተጻፉት ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ነው። እነዚህ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ከስደት ጋር የሚታገሉ አዳዲስ አማኞች ነበሩ። ስለሆነም ጳውሎስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታላላቅ እውነቶች አንዱን በማቅረብ ሊያበረታታቸው ፈለገ። እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት የእግዚአብሔር አብና የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰቦች ሆነው ነበር። ቤቶቻቸውን፥ ሥራዎቻቸውን ሊያጡ፥ ወደ ወኅኒ ቤት ሊወረወሩና ለሞት ሊዳረጉ ቢችሉም፥ እግዚአብሔር አልተለያቸውም ነበር። እነርሱ የእግዚአብሔር ውድ ንብረቶች ነበሩ። ክርስቶስ ተስፋ እንደገባው፥ ማንም ከእጁ ሊነጥቃቸው አይችልም (ዮሐ 10፡28-29)። ጳውሎስ እንደ ገለጸው ደግሞ፥ ማንም ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለያቸው አይችልም (ሮሜ 8፡31-39)። ከሚጋፈጧቸው ችግሮች ባሻገር የተሰሎንቄ አማኞች በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ አስተማማኝ ዋስትና ነበራቸው።

የ1ኛ ና 2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች የትና መቼ ተጻፉ?

ጳውሎስና የአገልግሎት ተባባሪዎቹ ከተሰሎንቄ ተነሥተው በደቡብ አቅጣጫ ወደ ቤሪያ አቀኑ። በቤሪያ ጳውሎስ በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ፍሬያማ አገልግሎት በማከናወኑ ቤተ ክርስቲያን ልትመሠረት ቻለች። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ አይሁዶች ከተሰሎንቄ መጥተው ሁከት ይፈጥሩ ጀመር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በስተደቡብ ወደ አቴና ሲያመራ ሲላስና ጢሞቴዎስ በቤሪያ ማገልገላቸውን ቀጠሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጳውሎስ ጢሞቴዎስና ሲላስ ወደ አቴና እንዲመጡ መልእክት ላከባቸው። ከዚያም ጳውሎስ፥ በተሰሎንቄ የነበሩት ማኅበረ ምእመናን በኃይለኛ ስደት ውስጥ እንዴት እየተመላለሱ እንዳሉ ያስብ ጀመር (1ኛ ተሰ. 3፡1-5)። ስለሆነም ጢሞቴዎስን ወደ ተሰሎንቄ መልሶ ከላከው በኋላ (ምናልባትም ሲላስ ወደ ፊልጵስዩስ ሄዶ ይሆናል)፥ ጳውሎስ ወደ አቴናና ከዚያም ወደ ቆሮንቶስ አመራ። በኋላ ሲላስና ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር በቆሮንቶስ ከተማ ሲገናኙ (1ኛ ተሰ. 3፡6)፥ ጢሞቴዎስ ስለ ተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ማብራሪያ ሰጠ። የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ጳውሎስን ይወዱትና ያከብሩት፥ ክርስቶስንም በታማኝነት ሊከተሉት ይፈልጉ ነበር። ጢሞቴዎስ ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን አመለከተ። ከእነዚህም ችግሮች መካከል ወሲባዊ ኃጢአቶችና ቀደም ሲል የሞቱት አማኞች በሕይወት ካሉት አማኞች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚመለከቱ ውዝግቦች ነበሩ። ጳውሎስ የ1ኛ ተሰሎንቄን መልእክት የጻፈው በ51 ዓ.ም አካባቢ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ወቅት ከቆሮንቶስ ከተማ ነበር። ደብዳቤውን ለጢሞቴዎስ ሰጥቶ ወደ ተሰሎንቄ ከመለሰው በኋላ እዚያው በቆሮንቶስ ከተማ ማገልገሉን ቀጠለ።

በዚህ ዓይነት ሁኔታ አያሌ ወራት ከተቆጠሩ በኋላ፥ ጳውሎስ ከጢሞቴዎስ ይሁን ወይ ከሌላ ግለሰብ በተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን አንዳንድ ዕልባት ያላገኙ ጉዳዮች መኖራቸውን ሰማ። አንዳንዶች ኢየሱስ በቶሎ እንደሚመለስ በማሰብ ሥራቸውን አቆሙ። የሆነ ሰው ደግሞ በጳውሎስ ስም የክርስቶስን መመለስ የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር። ይህም ደብዳቤ በመካከላቸው ውዝግብን አስከተለ። ስለሆነም ጳውሎስ ይህን የ2ኛ ተሰሎንቄ መልእክት የጻፈው የተሰሎንቄ አማኞች ስለ መጨረሻው ዘመን የነበሯቸውን አንዳንድ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ለማረም ነበር። ይሄኛው መልእክት የተጻፈው የመጀመሪያው መልእክት ከተጻፈ በኋላ ከ3-6 ወራት ባሉት ጊዜ ውስጥ ነው። የመጀመሪያው መልእክት የቆሮንቶስ ከተማ ከ51-52 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ ይታወቃል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: