የ1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት እና አስተዋጽኦ

የ1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡- ጳውሎስ ከተሰሎንቄ ከተማ ብዙም ሳይቆይ በፍጥነት መውጣት ስለነበረበት አማኞቹን በእግዚአብሔር ቃል ለማስታጠቅ የሚበቃ ጊዜ አላገኘም ነበር። ከዚህም በላይ የተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ስደት ውስጥ ነበረች። በመሆኑም ጳውሎስ እነዚህ ጥቂት አማኞች ለክርስቶስ ታማኞች እንዲሆኑና በዚህ በጥላቻ በተሞላው አካባቢ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባቸው ለማስተማር ፈለገ።

ሁለተኛ ዓላማ፡- የተሰሎንቄ አማኞች ስለ መጨረሻው ዘመን ብዙ ያልተገነዘቧቸው ነገሮች ነበሩ። ጳውሎስ እነዚህን ነገሮች ሊያብራራቸው ፈለገ። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ የጻፈው መልእክት ስለ መጨረሻው ዘመን ቁልፍ አሳቦችን አካትቷል። ከዚህ የበለጡ ዝርዝር ጉዳዮችን በአዲስ ኪዳን ውስጥ የምናገኘው ከክርስቶስ ትምህርቶችና ከዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ነው። በተሰሎንቄ መልእክት ውስጥ ጳውሎስ ካነሣቸው ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።

ሀ) ጳውሎስ የሞቱት ክርስቲያኖች ምን እንደሚገጥማቸው ያብራራል። ምንም እንኳን የተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ብትሆንም፥ ከአባሎቻቸው አንዳንዶቹ በሞት የተለዩአቸው ይመስላል። ወይም ደግሞ የተሰሎንቄ አማኞች ጥያቄ ክርስቲያኖች በሚሞቱበት ጊዜ ምን ያጋጥማቸው ይሆን የሚለው ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ በሕይወት ያሉት አማኞች የሚያገኙዋቸውን በረከቶች ያጡ ይሆን? ጳውሎስ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በመመሥረት ለክርስቲያን ሞት ማለት ምን ማለት እንደሆነና የሞቱ ክርስቲያኖች ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ምን እንደሚያጋጥማቸው ያብራራል። ጳውሎስ አማኞች በታማኝነት በመመላለስ የክርስቶስን ምጽአት እንዲጠባበቁ ያበረታታቸዋል። ይህም ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ለሀፍረት እንዳይጋለጡ ይጠብቃቸዋል።

ለ) የሐሰት ትምህርቶችና ደብዳቤዎች በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይሠራጩ የነበረ ይመስላል። እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች ስለ ክርስቶስ ምጽአት የተሳሳቱ ሐሳቦችን ያስተላልፉ ነበር (2ኛ ተሰ. 2፡1-3)። የክርስቶስ ምጽአት እንደቀረበ በማሰብ አንዳንድ አማኞች ሥራዎቻቸውን አቁመው ይጠባበቁት ነበር። ጳውሎስ እነዚህ አማኞች ክርስቶስ የሚመጣበትን ጊዜ ከመገመት እንዲታቀቡ ይመክራቸዋል (2ኛ ተሰ. 2፡2)። ነገር ግን የጌታቸውን መመለስ በሚጠባበቁበት ጊዜ በታማኝነት ክርስቲያናዊ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉና የዕለት ተግባሮቻቸውን እንዲያከናውኑ ያበረታታቸዋል።

ሐ) አንዳንድ አማኞች ደግሞ ክርስቶስ ቀደም ብሎ እንደ ተመለሰና እነርሱ ግን ሳያገኙት እንደ ቀሩ ያስቡ ነበር። ለእነዚህ አማኞች ጳውሎስ የክርስቶስ ምጽአት በሚደርስበት ጊዜ ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉና ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ደግሞ ሐሳዊ መሢሕ መገለጥ እንዳለበት ይናገራል። ጳውሎስ ከየትኞቹም መልእክቶቹም በበለጠ ስለዚህ ክፉ መሪ በዚህ የተሰሎንቄ መልእክት ውስጥ በሰፊው ያብራራል። ጳውሎስ ይህንን መሪ የዐመፅ ሰው ሲል ይጠራዋል።

መ) ወንጌሉን ለመቀበል በማይፈልጉት ሰዎች ላይ አንድ ቀን የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚመጣ በመግለጽ ጳውሎስ በስደት ውስጥ የነበሩትን ክርስቲያኖች ለማበረታታት ፈለገ። በክርስቶስ ለማመን ለማይፈልጉና በአማኞች ላይ ስደትን የሚያመጡ ሰዎች አንድ ቀን ለዘላለማዊ ቅጣት ይጋለጣሉ። በታማኝነት የጸኑ አማኞች ግን ሽልማትንና የዘላለም ሕይወትን ያገኛሉ።

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህን እውነቶች ማወቅ ለክርስቲያኖች ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ሦስተኛ ዓላማ፡- አማኞች ከወሲባዊ ኃጢአቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማበረታታት? (1ኛ ተሰ. 4፡1-8)

አራተኛ ዓላማ፡- በተሰሎንቄ የነበሩት አይሁዶች ጳውሎስ ገንዘብን ብቻ እንደሚፈልግና ለተሰሎንቄ አማኞች ምንም ዓይነት ፍቅር እንዳልነበረው በመግለጽ ስሙን ያጠፉ የነበረ ይመስላል። እነዚህ ከሳሾች ጳውሎስ ምንም ዓይነት መለኮታዊ የሐዋርያነት ሥልጣን እንዳልነበረው ይናገሩ ነበር። ይህ አዳዲስ አማኞችን ግራ ሊያጋባቸው ስለሚችል በአንደኛ ተሰሎንቄ ውስጥ ስለ ሐዋርያዊ አገልግሎቱ እነርሱን ለማገልገል ስላነሣሣው ፍላጎት ያብራራል።

የ1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ ልዩ ባሕርያት

1) በ1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች ውስጥ ስለ መጨረሻው ዘመን ብዙ ትምህርቶችን እናገኛለን። እንዲያውም ከ2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች ውስጥ አንድ ሦስተኛው ክርስቶስ ሊመለስ ሲል ስለሚሆኑት ሁኔታዎች የሚያብራራ ነው።

2) እነዚህ ጳውሎስ ከጻፋቸው መልእክቶች ሁሉ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ምናልባትም ከእነዚህ መልእክቶች በፊት የተጻፈው የገላትያ መልእክት ሊሆን ይችላል።

የ1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች አስተዋጽኦ

1ኛ ተሰሎንቄ፡- ከሌሎቹ መልእክቶቹ በተለየ ሁኔታ ጳውሎስ በዚህ መልእክት ውስጥ መጀመሪያ አስተምህሯዊ ቀጥሎ ደግሞ ተግባራዊ አኗኗርን አላሰፈረም። ነገር ግን 1ኛ ተሰሎንቄ በሚከተሉት ሁለት ክፍሎች ተከፍሏል፡-

  1. ጳውሎስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖችን እምነትና ከእነርሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ይከልሳል (1ኛ ተሰ. 1-3)።

ሀ. ጳውሎስ ስለ ተሰሎንቄ አማኞች እግዚአብሔርን ያመሰግናል (1ኛ ተሰ. 1)።

ለ. ጳውሎስ አማኞቹ ምሳሌያዊ ሕይወት እንዲኖሩ ያሳስባቸዋል (1ኛ ተሰ. 2)።

ሐ. ጳውሎስ የጢሞቴዎስን ዘገባ (ሪፖርት) ከሰማ በኋላ ደስ መሰኘቱን ይገልጻል (1ኛ ተሰ. 3)።

  1. ጳውሎስ የተሰሎንቄ አማኞች የክርስቶስን ምጽአት እየተጠባበቁ እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ ያሳስባቸዋል (1ኛ ተሰ. 4-5)።

ሀ. ጳውሎስ አማኞች የተቀደሰ የፍቅርና የሰላም ሕይወት እንዲመሩ ያሳስባቸዋል (1ኛ ተሰ. 4፡1-12)።

ለ. ክርስቶስ በድንገት ሲገለጥ የሞቱ አማኞች ምን እንደሚሆኑ ያብራራል (1ኛ ተሰ. 4፡13-5፡12)።

ሐ. ጳውሎስ አማኞች መሪዎቻቸውን እንዲያከብሩ ይመክራቸዋል (1ኛ ተሰ. 5፡12-28)።

2ኛ ተሰሎንቄ፡-

  1. ጳውሎስ አሳዳጆቻቸው ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ፍርድን እንደሚቀበሉ በመግለጽ በመከራ ውስጥ ያሉትን አማኞች ያበረታታቸዋል (2ኛ ተሰ. 1)

2.ጳውሎላ የዐመፁ ሰው ሳይገለጽ ክርስቶስ እንደማይመለስና እማኞች በታማኝነት ሊኖሩ እንደሚገባ ያብራራል (2ኛ ተሰ. 2)።

  1. ጳውሎስ አማኞች የክርስቶስን መመለስ ሲጠባበቁ ክርስቶስን በትጋት እንዲያገለግሉ ያሳስባቸዋል (2ኛ ተሰ. 3)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: