ሙላቱ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አባል ሲሆን፥ በመልካም መንፈሳዊ ሕይወቱ ይታወቃል። ዲያቆን ሆኖ የሚያገለግለው ይህ ወንድም የቤተ ክርስቲያኒቱ ዕለታዊ ተግባራት በትክክል መከናወናቸውን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የታማኝነትን አገልግሎት ያበረክታል። በየእሁድ ቤተ ክርስቲያኑን ለማጽዳት፥ ወንበሮችን ለማስተካከል፥ ወዘተ… በማለዳ ከቤተ ክርስቲያን ግቢ ይደርሳል። ሙላቱ ቤተሰቡን አፍቃሪ፥ ተንከባካቢና በመልካም ሥነ ሥርዓት የሚያስተዳድር ሰው ነበር። በሥራ ቦታም እውነተኛ ሰው በመሆኑ ተለይቶ ይታወቃል። አንድ ቀን ከሽማግሌዎቹ አንዱ ወደ እርሱ መጥቶ በሽምግልና ለመመረጥ ፈቃደኛ ይሆን እንደሆነ ጠየቀው። ሙላቱ ለዚህ ጥያቄ ምን እንደሚመልስ አላወቀም ነበር። ቀደም ሲል በትሕትናቸው የሚያውቃቸው መሪዎች በሙሉ ይህን ሥልጣን ካገኙ በኋላ በትዕቢት ሲነፉ ታዝቧል። በመሪነት አገልግሎት ውስጥ የሰዎችን ባሕሪ የሚያበላሽ አንድ ችግር እንዳለ ተገንዝቧል። በመሆኑም ለእግዚአብሔር የነበረውን ታላቅ ፍቅር የሚያበላሽ ሁኔታ እንዲፈጠር እልፈለገም። በሽምግልና ተመርጦ እያገለገለ ንጹሕ ሕይወት ሊመራ ይችል ይሆን? ሙስናን በሚያይበት ጊዜ ሌሎችን ሽማግሌዎች ቢቃወምስ? የቤተ ክርስቲያኒቱን ምእመናን በራስ ወዳድነት ፍላጎት ተነሣስቶ እንደሚያገለግል በማሰብ ስሙን ያጠፉበት ይሆን?
የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሽምግልና ከተመረጡ በኋላ መንፈሳዊ ባሕርያቸውን፥ አገልጋይ ሆነው የመሥራት ፍላጎታቸውንና ለሌሎች ሰዎች የነበራቸውን አክብሮት የሚያጡበትን ሁኔታ የሚያስረዱ ምሳሌዎች ስጥ። ለ) በአመራር ስፍራ ላይ ከመሆን ይልቅ ንጹህ ባህሪና መልካም ስም ይዞ መኖር የበለጠ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ብዙውን ጊዜ ሥልጣንን ማግኘት መሪዎችን ወደ ትዕቢት የሚመራቸው ለምንድን ነው?
እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሪነትን ልክ ዓለማውያን በሚመለከቱበት መንገድ ይገነዘባሉ። መሪ ወይም ሽማግሌ መሆን ተጨማሪ ክብርና ጥቅማ ጥቅሞችን ያስገኛል። ከዚህም የተነሣ ብዙ ሰዎች ለራስ ወዳድነት ዓላማዎች ሲሉ መሪነትን ይፈልጋሉ። ይህንኑ የመሪነት ሥልጣን ካገኙ በኋላ ወንበራቸውን ይዘው ለመቆየትና ሰዎችን በአምባገነንነት ለማዘዝ ይፈልጋሉ። የዚህ ዓይነቱ አመራር ደግሞ ለሥልጣን የሚደረጉ ሽኩቻዎችን፥ የገንዘብ ስርቆትን፥ ሙስናንና የምእመናንን ክብር ማጣትን ያስከትላል። ከዚህም የተነሣ ብዙ ሰዎች እንደ ሙላቱ ያለኝን መልካም ሕይወት ያበላሽብኛል በሚል ከአመራር ይሸሻሉ።
አዲስ ኪዳን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ መሪነት ከዓለማዊ አሠራር የተለየ መሆን እንዳለበት ያስረዳል። አመለካከታችን ሌሎችን እንጂ ራሳችንን ወይም ቤተሰቦቻችንን ወይም የጎሳ አባሎቻችንን በማገልገሉ ላይ አጽንኦት ሊሰጥ አይገባም። ብቃቶቻችንም ከዓለም የብቃት መለኪያዎች የተለዩ መሆን አለባቸው። በመሆኑም ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው በትምህርት ላይ ሳይሆን በመንፈሳዊነት ላይ ሊሆን ይገባል። የክርስቲያኖች የአመራር መንገድም መለየት ይኖርበታል። ይኸውም ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ እንዳልሆነች በመገንዘብ በትሕትና መከናወን አለበት። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንደ አሕዛብ ተከታዮቻቸውን እንዳይመሩ አዟቸዋል። አሕዛብ በጭፍሮቻቸው ላይ ጌቶች ለመሆን ይፈልጉ ነበር (ማር. 10፡35-45)።
የ1ኛና የ2ኛ ጢሞቴዎስ እንዲሁም የቲቶ መልእክቶች ስለ አመራር ብዙ ነገሮችን ያስተምራሉ። እንደውም የመጋቢነት ትምህርቶች በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ መልእክቶች ጳውሎስ ለሁለት የቅርብ ጓደኞቹ ማለትም ለጢሞቴዎስና ቲቶ የነበረውን የመጋቢነት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፥ መጋቢያን እንዴት ቤተ ክርስቲያናቸውን ሊንከባከቡ እንደሚገባ ያስተምራሉ። እነዚህ መልእክቶች የተጻፉት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለነበሩ ግለሰቦች እንጂ ለአብያተ ክርስቲያናት አልነበረም።
የውይይት ጥያቄ፡- ስለ 1ኛና 2ኛ ጢሞቴዎስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ መልእክቱን ስለሚቀበሉት ሰዎችና ስለ መልእክቶቹ ዓላማ ከመዝገበ ቃላቱ ያገኘኸውን ጠቅለል አድርህ ጻፍ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)