Site icon

የዕብራውያን መልእክት ዓላማ

የውይይት ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ። ዕብ. 1፡1-4፤ 3፡3፤ 6፡9፤ 7፡7፤ 19፥22፤ 8፡6፤ 9፡23፤ 10፡34፤ 11፡16፥35፥ 40፤ 12፡24። የዕብራውያን መልእክት ክርስቶስ ካምን ከምን እንደሚበልጥ ይናገራል?

የመጀመሪያ ዓላማ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ዘመን ታላቅ ነው ብለው ከሚያስቡት ነገር ሁሉ እንደሚበልጥ ለማሳየት።

አይሁዶች ረዥም ዘመናት ውርሳቸውና በብሉይ ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር በነበራቸው ልዩ ቃል ኪዳን ምክንያት ከፍተኛ የትምክህተኝነት ስሜት ይሰማቸው ነበር። የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያረፈበት ቃልና ኪዳናት ነበሩዋቸው። አይሁዶች በመላእክት የተጎበኙ፥ ከሙሴ ሕግን የተቀበሉና እግዚአብሔር ባዘዛቸው መንገድ አምልኮአቸውን የሚያካሂዱ፥ ወዘተ… በመሆናቸው ይኩራሩ ነበር። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በተለይ ከወገኖቻቸው ስደት በተነሣ ጊዜ በእነዚህ ነገሮች ላይ አጽንኦት ወደ መስጠቱ አቅጣጫ ለመመለስ እየተፈተኑ ነበር። ጸሐፊው ለዚህ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት አይሁዶች ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ መንገድ ቢመለሱ፥ በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ማመናቸውን እንደ ካዱ ያስረዳል። ክርስቶስ ታላቅ ሰው ነው ብሎ ቢያስቡም እንኳን፥ ወደ ብሉይ ኪዳን መመለሱ የክህደት ተግባር ነበር። ለኃጢአታቸው መሞቱን ጭራሽ እንዳልተፈጸመ ታሪክ ከንቱ ማድረጋቸው ነበር። የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ባለመቀበላቸው ሌላ የመዳን መንገድ አያገኙም ነበር። እግዚአብሔር የእንስሳት መሥዋዕቶችን የድነት (ደኅንነት) እና የይቅርታ መንገድ አድርጎ የሚቀበልበት ጊዜ አልፎ ነበር።

ጸሐፊው የክርስቶስን ታላቅነትና እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ያቀደው ነገር ሁሉ ፍጻሜው መሆኑን ያስረዳል። ብሉይ ኪዳን እንደ ጥላ ሲሆን፥ እውነታው ክርስቶስ ነበር። ክርስቶስ የሚገልጣቸውን ነገሮች በተምሳሌትነት አሳይቷል። ጸሐፊው ለምን አይሁዳውያን ክርስቶስ ላይ ዓይኖቻቸውን መትከል እንዳለባቸውን ወደ ይሁዲነት መመለስ እንደሌለባቸው ሲገልጽ፥ የሚከተሉትን ነጥቦች አብራርቷል። ክርስቶስ ከሚከተሉት ሁሉ እንደሚበልጥ፥ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ እንመለከታለን፡

ሀ) ክርስቶስ እግዚአብሔር ከገለጣቸው ቀደምት መገለጦች፥ እንደ ኢሳይያስ ካሉት ነቢያትም የሚበልጥ ነው። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ቃሉን የሰጠው በደካማ የሰው ልጆች በኩል ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ግን አምላክ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነበር። እርሱም በአካል ተገኝቶ በሰዎች መካከል ያደረና እግዚአብሔርን በታላቅ አኳኋን የገለጸ አምላክ ነው (ዕብ. 1፡1-4)።

ለ) ክርስቶስ አይሁዶች፥ ከሚያከብሩአቸው የብሉይ ኪዳን መላእክት በላይ ነበር። ጸሐፊው መላእክት እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲያገለግሉ የሚልካቸው መናፍስት መሆናቸውን ይናገራል። መላእክት የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነበሩ። ክርስቶስ ግን አምላክና ሰዎች እንዲሁም መላእክት የሚሰግዱለት መሆኑን ተመልክቷል (ዕብ. 1፡3-2፡18)።

ሐ) ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ታላቅ ሕግ ሰጪ ከነበረው ከሙሴ በላይ ነው (ዕብ. 3፡1-6)። ሙሴ ምንም ያህል ታላቅ ቢሆንም፥ የቤቱ አካል ወይም የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ነበር። ክርስቶስ ግን አምላክ እንደ መሆኑ፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ በላይ ነበር። እርሱ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቤት ንድፍ እንደሚያወጣና እንደሚቆጣጠር ዕቅድ ነዳፊ ነበር።

መ) ክርስቶስ ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ይበልጣል (ዕብ. 5፡1-10)። አሮንና ከእርሱ በኋላ የነበሩት ሊቀ ካህናት በሙሉ ኃጢአተኞች በመሆናቸው፥ ለራሳቸው ኃጢአቶች መሥዋዕቶችን ማቅረብ ያስፈልጋቸው ነበር። አሮን ሰው በመሆኑ በሞት እንደ ተሸነፈና ሌሎች (ብዙዎች መንፈሳዊያን ያልሆኑ የሊቀ ካህናትነት አገልግሎቱን እንደተቀበሉ ተገልጾአል። ክርስቶስ በብዙ መንገድ ከአሮን ይበልጣል። ክርስቶስ ካህንም ንጉሥም በመሆኑ ከአሮን ይበልጣል። ኃጢአት የሌለበት እና ፍጹም በመሆኑ ከአሮን ይበልጣል። ሰውም አምላክም በመሆኑና ከዚህም የተነሣ ሰውንና እግዚአብሔርን ለመወከል በመቻሉ ከአሮን ይበልጣል። አሮን አገልግሎቱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ለማረፍ ያልተፈቀደለት ሲሆን፥ ክርስቶስ የመሥዋዕትነት አገልግሎቱን ስላጠናቀቀና እንደገና መድገም ስለማያስፈልገው በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጧል። በአሮንና በሊቀ ካህናት ዘመን ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዳይቀርቡ የሚከላከል መጋረጃ በቤተ መቅደስ ውስጥ ነበር። ክርስቶስ በሞተ ጊዜ ግን መጋረጃ ው ከላይ እስከ ታች ተቀዷል፤ በመሆኑም አማኞች በድፍረት ወደ ጸጋው ዙፋን ሊቀርቡ ይችላሉ)።

ሠ) ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች የበለጠ መሥዋዕት ነው (ዕብ 9፡11-14)። እንስሳት ጊዜያዊ የኃጢአት ይቅርታ ከማስገኘት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም፡፡ እንስሳት እንደ መሆናቸው፥ ለሰዎች ኃጢአቶች ምትክ ሆነው ሊሞቱ አይችሉም። ክርስቶስ ግን ሰውም አምላክም በመሆኑ፥ የበለጠ ታላቅ መሥዋዕት ሆኗል። የብሉይ ኪዳን እንስሳት ባለማቋረጥ መሠዋት የነበረባቸው ሲሆን (በቀን ብዙ እንስሳት፥ በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠር)፥ የክርስቶስ አንድ መሥዋዕት ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻው ግለሰብ ያሉትን ሰዎች ኃጢአት ለማንጻት ችሏል። የእንስሳት መሥዋዕቶች ከፊልና ጊዜያዊ የኃጢአት መሸፈኛ ነበሩ። የክርስቶስ መሥዋዕት ግን ዘለቄታዊ በመሆኑ፥ በእርሱ የሚያምኑትን ለዘላለም ያነጻቸዋል።

ረ) ክርስቶስ በላቀ ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገለግላል ( ዕብ. 9፡1-10)። ሰብአዊ ካህናት የሰማያዊቱ ቤተ መቅደስ ነጸብራቅ በሆነ እና ፍጹምነት በጎደለው የመገናኛ ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ ውስጥ አገልግለዋል። (ይህ ልጆች የሚሰሩት የቆርቆሮ መኪና ከእውነተኛ ትልቅ መኪና እንደሚያንስ ማለት ነው።) ክርስቶስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሆነችው መንግሥተ ሰማያት ውስጥ ያገለግላል። ምንም እንኳን ክርስቶስ በምድር ላይ ቢሞትም፥ እግዚአብሔር በሚቀበለው መንገድ ኃጢአት ይቅርታ የሚያገኝበትን መንገድ ለማቅረብ ደሙን (ሕይወቱን የሠዋው) በሰማይ ነበር።

ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንና የአይሁዶች የአምልኮ ሥርዓት ማዕከላት ከሆኑት ነገሮች ሁሉ ስለሚበልጥ፥ ከክርስቶስ ርቆ ፍጹም ወዳልሆነ፥ የአምልኮ ሥርዓት መመለሱ ሞኝነት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንደ ክርስቶስ ታላቅ ሳይሆኑ ዛሬ ክርስቲያኖችን የሚማርኩ የሚመስሉትን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝር። በሕይወትህ ውስጥ የሚማርኩ፥ ዳሩ ግን በዘላለም ዘመን አንጻር ሲታዩ መልካም ያልሆኑና እምነትን ሊያወድሙ የሚችሉ ነገሮች መኖራቸውን ለማወቅ ሕይወትህን መርምር። እነዚህን ነገሮች ለእግዚአብሔር ተናዘዝና ከጊዜያዊ ነገሮች ይልቅ ወሳኝ የሆኑትን ለመከተል ቁረጥ።

የውይይት ጥያቄ፡– ዕብ. 2፡1-4፤ 3፡12-14፤ 4፡1-2፤ 5፡11-6፡8፤ 10፡26-31 አንብብ። በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ ለክርስቲያኖች የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ምን ምን ናቸው?

ሁለተኛ ዓላማ፡ አማኞች ከስደት ለማምለጥ ብለው በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዳይክዱ በጽኑ ለማስጠንቀቅ። ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዳይክዱ የሚያሳስቡ እጅግ ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎች በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ይገኛሉ። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ከአይሁዳውያን ወገኖቻቸው የሚመጣውን ስደት ፈርተው ነበር። ብዙዎቹ እምነታቸውን ለመደበቅ፥ ወይም እምነታቸውን ክደው ወደ ይሁዲነት ለመመለስ እያሰቡ ነበር።

የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ እምነታቸውን ከመካድ ይልቅ በድፍረት ስደትን እንዲቀበሉ ይመክራቸዋል። የአይሁድ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ብዙ ካወቁ በኋላ እምነታቸውን ሲክዱ፥ ዘላለማዊ ቅጣቶች ይከተሏቸዋል። ሌላ የመዳን መንገድ አያገኙም። ስለሆነም ወደ ኋላ ከመመለስ ይልቅ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደ ነበሩትና ከጊዜያዊ ችግሮች አሻግረው የሰማይን በረክቶች እንደ ተመለከቱት የእምነት ጀግኖች መሆን ያስፈልጋቸው ነበር። ሊቀ ካህናችን የሆነው ክርስቶስ ደግሞ ትግላችንን ስለሚያውቅ እነዚህን ፈተናዎች እንድናሸንፍ ይረዳናል፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ብዙ አማኞች እምነታቸውን የካዱት ለምንድን ነው? ለ) እንደ እነዚህ ዓይነት ውሳኔዎች ስለሚያስከትሏቸው ዘላለማዊ ውጤቶች የዘነጉት ነገር ምንድን ነው? ሐ) ሰዎች እምነታቸውን መካድን እንደ አማራጭ እንዳይወስዱ ቤተ ክርስቲያን እንዴት በተሻለ ሁኔታ ልታስተመራቸው ትችላለች?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version