የዕብራውያን መግቢያ

ከጥንት ዘመን ጀምሮ፥ ከሁሉም ባህሎች ውስጥ ማለት ይቻላል የእንስሳት መሥዋዕት የአምልኮ አካል ነበር። እግዚአብሔር የአዳምና የሔዋንን እርቃን ለመሸፈን እንስሳትን ከገደለበት ጊዜ አንሥቶ (ዘፍጥ. 3፡21)፥ የእንስሳት መሥዋዕቶች የአምልኮ አካል ነበሩ። ሰይጣን ሰዎች ሐሰተኛ አምልኮ እንዲያካሂዱ ለማድረግ የእንስሳት መሥዋዕትን ያበረታታል። ይህ ሐሰተኛ ልምምድ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገለጸውን እውነተኛ አምልኮ በመኮረጅ የሚከናወን ነው።

ለመሆኑ በእንስሳት መሥዋዕትና በአማኝ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ዛሬም መሥዋዕቶቹ አስፈላጊ ናቸው? አማኞች የእንስሳትን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ጠንቋዮችን ወይም የተለዩ ካህናትን መጠቀማቸው ስሕተት ነውን? የዕብራውያን መጽሐፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምን መልስ ይሰጣል? አይሁዶች በክርስቶስ ካመኑ በኋላም ሳይቀር የእንስሳት መሥዋዕት ሥርዓታቸውን ለመቀጠል ይፈልጉ ነበር። የዕብራውያን ጸሐፊ የእንስሳትን መሥዋዕት ለኃጢአት ይቅርታ (ወይም የመናፍስትን ቁጣ ለማብረድ፥ ለፈውስ ወይም ከእርግማን ለመከላከል) መጠቀሙ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ላይ ያላንን እምነት የሚቃረን መሆኑን ያስረዳል። ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ከማግኘታቸው በፊት በእንስሳት መሥዋዕትነት፥ በካህናት የሚያገኟቸውን ነገሮች በሙሉ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተበት ጊዜ እንደፈጸመልን የዕብራውያን ጸሐፊ ያስገነዝባል።

በመሆኑም እነዚህን ጥንታዊ ሥርዓቶችና የእንስሳት መሥዋዕት መጠቀሙ ግለሰቡ በክርስቶስ ላይ ሕያው እምነት እንደሌለው ያመለክታል። የክርስቶስ ሞት ሌሎችን መሥዋዕቶች ሁሉ አላስፈላጊ አድርጓችዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የዕብራውያን መልእክት ርእስ ምንድን | 1 ነው? የመጽሐፉ ጸሐፊ ማን ነው ይላል ?

አጠቃላይ መልእክቶች

ምንም እንኳን በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዕብራውያን መጽሐፍ ርእስ የጳውሎስን ጸሐፊነት ቢያሳይም፥ ይህ ርእስ በጥንታዊ መዛግብት ውስጥ አይገኝም። መጽሐፉ ራሱ በማን እንደ ተጻፈ አይናገርም። (ስለ ዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ በምንነጋገርበት ክፍል ስለዚሁ ጉዳይ ሰፋ አድርገን እንመለከታለን።) ስለሆነም የጥንት አማኞች የዕብራውያንን መጽሐፍ ከጳውሎስ መልእክቶች መጨረሻና ከቀጣይ ጽሑፎች መጀመሪያ ላይ አስቀምጠውታል። ምሁራን ከዕብራውያን እስከ ይሁዳ ያለውን ክፍል «አጠቃላይ መልእክቶች» ሲሉ ይጠራሉ። አጠቃላይ መልእክቶች የተባሉበትም ምክንያት መልእክቶቹ የተጻፉት ለግለሰብ (እንደ ቲቶ) ወይም ለአንድ ቤተ ክርስቲያን (እንደ 1ኛ ቆሮንቶስ) ሳይሆን፥ ለአጠቃላይ ክርስቲያኖች ወይም በዛ ላሉ ተአንባቢያን በመሆኑ ነው። (ለግለሰቦች የተላኩት 2ኛ ና 3ኛ ዮሐንስ መልእክቶች ከ1ኛ ዮሐንስ ጋር አብሮ ስለሚካተቱ፥ የአጠቃላይ መልእክቶች አካላት ተደርገው ተወስደዋል።) እነዚህ ስምንት መጻሕፍት የተጻፉት በአምስት የተለያዩ ጸሐፊያን ነው። (ማስታወሻ፥ አጠቃላይ መልእክቶች ከዕብራውያን ሳይሆን ከ1ኛ ጴጥሮስ እንደሚጀምሩ የሚያስቡ ምሁራን አሉ።)

(ማስታወሻ፡ እነዚህ ስምንት መጻሕፍት በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቀረቡበት የአቀማመጥ ቅደም ተከተል ከአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ይለያል። ይህም የሆነው የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስን ቅደም ተከተል ስለሚከተልና እንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ የላቲንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅደም ተከተል ስለሚከተል ነው።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስምንቱን የአጠቃላይ መልእክቶች መጽሐፍ በቅደም ተከተል ዘርዝር። ለ) ስለ ዕብራውያን መልእክት ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ ስለ መልእክቱ ተቀባዮችና የመጽሐፉ ዓላማ፥ ወዘተ. የቀረበውን ትምህርት ጠቅለል አድርገህ አቅርብ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “የዕብራውያን መግቢያ”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading