ክርስቶስ ከሙሴ ይበልጣል (ዕብ. 3፡1-19)

ጸሐፊው ክርስቶስ ከመላእክት እንደሚበልጥና ሰብአዊ ባህሪን በመልበሱ ምክንያት ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳን ከገለጸ በኋላ፥ አማኞች (ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋይ የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች) ወደ ክርስቶስ እንዲመለከቱ ይጋብዛል። (ማስታወሻ፡- ዕብ. 3፡1 እንደ «ስለዚህ» ዓይነቶቹን ቃላት በትኩረት መመልከቱ ክፍሉን መረዳታችንን ለማረጋገጥ ጥሩ ምሳሌያችን ነው። ስለዚህ የሚለው ቃል ቀደም ሲል ከተገለጸው እውነት የተነሣ አንድ ልንሰጥ የሚገባን ምላሽ እንዳለ ያመለክታል።) አይሁዶች እርዳታ ፍለጋ ወደ መላእክት መሄድ አያስፈልጋቸውም ነበር። ክርስቲያንና የፖለቲካ መሪዎች የሆኑትን ሰዎችን መፈለግ አያስፈልጋቸውም። ስመ ጥር ወደሆኑ ሰዎች መልስ ፍለጋ መሄድ አያስፈልጋቸውም ነበር። ማየት የሚያስፈልጋቸው ክርስቶስን ብቻ ነበር።

ሀ) ሐዋርያ፡- ከእርሱ በበለጠ አካል በውክልና እንዲሠራለት የሚላክ አገልጋይ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ሙሉ ሥልጣን ይዞ ነበር የተላከው። ወደ ምድር የመጣው፥ የተናገረውና ያደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፋንታ የተከናወነ ነበር። ስለሆነም ክርስቶስ የተናገረው ወይም ያስተማረውን አለመቀበል ማለት እግዚአብሔር አብን እንዳለመቀበል ማለት ነው። አይሁዶች፥ «እግዚአብሔር አብን እንደ አያት ቅድማያቶቻችን እናመልከዋለን እያሉ ክርስቶስ ግን አንፈልገውም» ሊሉ አይችሉም ነበር። ምክንያቱም ክርስቶስን ባለመቀበል እግዚአብሔር አብንም እየተቃወሙ ነበርና።

ለ) ሊቀ ካህናት፡- የአይሁዶች የአምልኮ ሥርዓት የሚመራው በሊቀ ካህናት ነበር። ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ ያገኙ ዘንድ የኃጢአት መሥዋዕቶችን የሚያቀርበው እርሱ ነበር። ነገር ግን ጸሐፊው የተሻለ መሥዋዕት ያቀረበ (ራሱን) ሌላ የሚበልጥ ሊቀ ካህናት እንዳለ ያመለክታል። የክርስቶስን መሥዋዕት ትቶ ሰብአዊ ሊቀ ካህናት ወደሚያቀርበው የእንስሳት መሥዋዕት መመለሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከእንግዲህ ይቅርታ አያስገኝም ነበር።

አይሁዶች፥ «ክርስቶስ ከመላእክት ሊበልጥ ይችላል ነገር ግን በሲና ተራራ ሕግን ከሰጠን ከሙሴ ሊበልጥ አይችልም» ማለታቸው አይቀርም ነበር። ስለሆነም የዕብራውያን ጸሐፊ ክርስቶስ ከሙሴ እንደሚበልጥ ወደሚናገርበት ሦስተኛ ነጥቡ ይሸጋገራል። በአይሁዶች አስተሳሰብ ከሙሴ የሚበልጥ ሰው አልነበረም። ሙሴ ከግብጽ ባርነት ነፃ አውጥቷቸው ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉና ሕግም እንዲቀበሉ አድርጓል። ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ተነጋግሯል። ምንም እንኳን አብርሃምና ዳዊት ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች ቢሆኑም፥ ሙሴን የሚያህል አልነበረም። (አይሁዶች እንደ ብዙዎቻችን በሰው ላይ ትኩረት በማድረጋቸው አንድን ነገር ለማድረግ የሚያስፈልግ እውነተኛው ኃይል ከየት እንደሚመጣ ዘንግተው ነበር። እስራኤላውያንን ከግብጽ ያወጣው እግዚአብሔር እንጂ ሙሴ አልነበረም።) ሕግንና ቃል ኪዳንን የሰጠው እግዚአብሔር እንጂ ሙሴ አልነበረም። በተመሳሳይ መንገድ ለሰዎችም ድነት (ደኅንነት) የሚሰጠው እግዚአብሔር እንጂ እኛ አይደለንም። በአምልኮ፥ በዝማሬና በቃል፥ በስብከት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው እግዚአብሔር እንጂ ኳየሩ ወይም ሰባኪው አይደለም።

የዕብራውያን ጸሐፊ ሙሴ ከክርስቶስ ይበልጣል ለሚለው የአይሁዶች አስተሳሰብ መልስ ለመስጠት፥ ሙሴንና ክርስቶስን ያነጻጽራል።

ተመሳሳይነታቸው፡ ሀ) ሙሴና ኢየሱስ 1) ሁለቱም ለእግዚአብሔርና ለተሰጣቸው ሥራ ታማኞች ነበሩ። (ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከግብጽ ባርነት ማውጣት ኃላፊነት ሲሰጠው፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከመንፈሳዊ ባርነት ነፃ የማውጣት ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር።) ለ) ሁለቱንም ለአገልግሎት የሾማቸው እግዚአብሔር ነበር። ራሳቸው አገልግሎቱን አልመረጡም።

ልዩነቶቻቸው፡ ክርስቶስ በሚከተሉት ምክንያቶች ከሙሴ ይበልጣል ምክንያቱም፡-

ሀ) ሙሴ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ነበር (የእግዚአብሔር ቤተሰብ)። ሙሴ አይሁዳዊ በመሆኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት የብሉይ ኪዳን አይሁዳውያን ቤተሰብ ነበር። ክርስቶስ ግን አምላክ እንደ መሆኑ፥ የቤቱ ማለትም የእግዚአብሔር ሕዝብ አናጺ ነበር። የብሉይ ኪዳንንም ሆነ የአዲስ ኪዳንን ሕዝብ የመሠረተው ክርስቶስ ነበር።

ለ) ሙሴ በቤቱ ውስጥ (የአይሁድ ሕዝብ) የእግዚአብሔር አገልጋይ ነበር። እርሱም ወደፊት የሚመጣውን ታላቅ ቤት አመልክቷል። ክርስቶስ ለዘላለማዊ ቤት (በእግዚአብሔር ሕዝብ) ላይ ሥልጣን ያለው የእግዚአብሔር ልጅ ነው።

ምንም እንኳን ሙሴ ታላቅ፥ የእግዚአብሔር ሰው ቢሆንም፥ አይሁዳውያን አማኞች ሙሴ ሰው መሆኑን መገንዘብ ነበረባቸው። ሰው ደግሞ መመለክ የለበትም፡፡ ክርስቶስ ግን የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚገነባ አምላክ ነው፡፡ ድነትን (ደኅንነትን) ፍለጋ ወደ ሕግና ሙሴ መመለሱ ከአምላክ ወደ ሰው የመመለስ ያህል ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- እኛም ክርስቶስን ከማመን ሰውን ወደ ማመን እንዴት ልንመለስ እንደምንችል ግለጽ። ይህ የተሳሳተ የሚሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: