ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ሌሎች አማኞችን መውደድን እና የዓለምን የአኗኗር ዘይቤ አለመውደድን ይጠይቃል (1ኛ ዮሐ 2፡7-17)

፩. ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ሌሎች አማኞችን መውደድን ይጠይቃል (1ኛ ዮሐ 2፡7-14)

የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ከሌሎች አማኞች ጋር ያለን ግንኙነት ነው። በቤተሰብ ውስጥ የሁለት ልጆች መጣላት የተቀሩትን የቤተሰብ አባላት እንደሚነካ ሁሉ፥ በአማኞች መካከል የሚካሄድ ጸብ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይጎዳዋል። ዮሐንስ በአማኞች መካከል ያለውን ግንኙነት «ፍቅር» በሚል ቃል ይገልጸዋል። ዮሐንስ ይህን ሲል ስለ ስሜታዊ ፍቅር መናገሩ ብቻ አይደለም፥ ወይም በአማኞች መካከል ሊኖር ስለሚገባ መልካም ስሜት ብቻ መናገሩ አይደለም። ይልቁንም ከፍቅር የሚመነጩትን ተግባራት ለማመልከት ይፈልጋል። እነዚህም ተግባራት በአሳብ ወይም በተግባር የተከናወኑትን በደሎች ይቅር ማለት ሊያካትቱ ይችላሉ፥ ወይም ደግሞ በችግር ውስጥ ያሉትን መርዳትን ሊያመለክቱ ይችላሉ። ዮሐንስ በዚህ መልእክት ውስጥ ወደዚሁ ማዕከላዊ ትምህርት ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ይመለሳል።

እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የሚለው ትእዛዝ በአንድ በኩል በጣም ያረጀ ነው። ይህ ትእዛዝ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ይገኛል (ዘሌዋ. 19፡18 አንብብ)። በተጨማሪም ይህ ትእዛዝ አዲስ የሆነው በብዙ መንገዶች ነው። በመጀመሪያ፥ የብሉይ ኪዳን የፍቅር ትእዛዝ የተመሠረተው በጎሰኝነት ላይ መሆኑ፥ ይህ እርስ በርስ ተዋደዱ የሚለው ትእዛዝ አዲስ ነው። አይሁዳውያን ወገኖቻቸውን እንዲወዱ ነበር የተጠየቁት። ነገር ግን አይሁዳውያን ያልሆኑትን እንዲወዱ የታዘዙበት ስፍራ አልተጠቀሰም። አሁን ግን እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ እንድንወድ አዞናል (ማቴ. 22፡39-40)፡፡ ሁለተኛ፥ በስፋቱም አዲስ ነው። ብሉይ ኪዳን አይሁዶች ድሆችን እንዲረዱ ሲያዛቸው፥ ወዘተ… ፥ ከሰዎች የሚጠበቀውን ነገር ይወስነዋል። በመጀመሪያ: የብሉይ ኪዳን ፍቅር በተለይም ለአይሁዶች መልካም ከሆኑት ሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረግን ያበረታታል። አዲስ ኪዳን ግን በመሥዋዕትነት ፍቅር ላይ ያተኩራል። ይህም ለእኛ ጥሩዎች ያልሆኑትን (ጠላቶቻችንን ጨምሮ) መውደድን ያካትታል (ማቴ. 5፡43-47)። የአዲስ ኪዳን ፍቅር ሕይወታችንን ሳይቀር ለሌላ ሰው ፍቅር በመሥዋዕትነት እንድናቀርብ ይጠይቀናል (1ኛ ዮሐ. 3፡16)።

ዮሐንስ አንድ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ነኝ እያለና ከእግዚአብሔር አብ ጋር መልካም ኅብረት እንዳለው እየተናገረ ዳሩ ግን ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን የሚያሳይ ከሆነ፥ ድነትን (ደኅንነትን) ያላገኘ የጨለማ ውስጥ ተጓዥ መሆኑን ይናገራል። አሁንም ዮሐንስ «ጥላቻ» የሚለውን ቃል የሚጠቀመው እንደ ስሜታዊ አለመውደድ ሳይሆን፥ ሌሎችን ለመርዳት አለመፈለግን ለማሳየት ነው። አንድ አማኝ በችግር ውስጥ እያለ ልንረዳው ካልፈለግን ጠልተነዋል ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ግንኙነቶች ተለይተው የሚታወቁት በፍቅር ነው ወይስ በጥላቻ? ለ) የኮሚኒስት መንግሥት ከወደቀ በኋላ በአማኞች መካከል መከፋፈል የበረከተው ለምን ይመስልሃል ? ሐ) ይህ በክርስቶስ ላይ ስላለን እምነት ምን ያሳያል?

በ1ኛ ዮሐንስ 2፡12-14፤ ጸሐፊው በአማኞች ሕይወት ውስጥ የተመለከተውን ነገር ያስታውሳል። ይህም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነበር። ምሁራን ልጆች፥ ጎበዞችና አባቶች የሚለው ማንን እንደሚያመለክት ይጠራጠራሉ? ይህ ቅደም ተከተላዊ የዕድሜ መግለጫ ነው? ወይስ የመንፈሳዊ ብስለት መግለጫ ? በአመዛኙ ዮሐንስ መንፈሳዊ ብስለትን የሚያመለክት ይመስላል። ዮሐንስ እነዚህን የተለያዩ ነገሮች ከተለያዩ የዕድሜ ቡድኖች ጋር የሚያዛምደው ለምንድን ነው? አናውቅም። ዮሐንስ አማኞች ሁሉ ሊያስታውሷቸውና ሊያድጉባቸው የሚገባቸውን ሦስት ባሕርያት ለማሳየት የሚፈልግ ይመስላል።

ሀ) ኃጢአታችን እንደ ተሰረየ እናውቃለን። አዳዲስ እማኞች፣ ሊያውቋቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ ከክርስቶስ ደም የተነሣ ለቀድሞዎቹ፣ ለአሁኖቹና ወደፊት ለሚያደርጓቸው ኃጢአቶች ሁሉ ዋጋ እንደ ተከፈለ ነው። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ይቅር ብሏቸዋል። ሰይጣን በቀድሞው ኃጢአታቸው ሳቢያ ልባቸውን እንዳያዝልባቸው፥ ይህን ማወቁ ጠቃሚ ነው። በክርስቶስ ከማመናችን በፊትና ካመንን በኋላ ለበደለኛነት ስሜት የሚያጋልጡንን ኃጢአቶች ልንፈጽም እንችላለን። ዮሐንስ ግን እነዚህን ኃጢአቶች ለእግዚአብሔር ከተናዘዝን ይቅርታ እንደሚደረግልን ይናገራል፡፡ ለፈጸምናቸው ኃጢአቶች ዋጋ መክፈላችንን ልንቀጥል እንችላለን (ለምሳሌ: አንዲት ሴት ከጋብቻ ውጭ ዝሙት ፈጽማ ብታረግዝ፣ እግዚአብሔር እርግዝናውን አያስወግድላትም)። ነገር ግን እግዚአብሔር ይቅር ስላለን ለዚያ ኃጢአት አይቀጣንም። ኃጢአት እንዳልፈጸምን ያህል ከእርሱ ጋር ግንኙነት ልናደርግ እንችላለን።

ለ) አማኞች «ከመጀመሪያው ከነበረው» ወይም ከእግዚአብሔር አብ ጋር ሕያው ግንኙነት አላቸው። ዮሐንስ «ማወቅ» የሚለውን ቃል የተጠቀመው ምሁራዊ እውቀትን ሳይሆን ዝምድናዊ እውቀትን ለማሳየት ነው። በብስለት የሚያድጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት በማወቅ ይበልጥ ወደ እርሱ እየቀረቡ ይሄዳሉ። ግንኙነቶች ሁሉ በእውቀት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። አንድን ሰው የበለጠ ስናውቅና ብዙ ጊዜ አብረነው ስናሳልፍ፥ ግንኙነታችን እየጠለቀ ይመጣል። እንደ አባት ከሚወደንና ዳሩ ግን ዘላለማዊ ከሆነ አምላክ ጋር ግንኙነት ማድረጉ ምንኛ ታላቅ ዕድል ነው።

ሐ) በሕይወታችን ውስጥ ባለ ኃጢአት ላይ ድልን እንቀዳጃለን። ዮሐንስ ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ልንሆን እንደማንችል ይናገረናል። ይህ ማለት ግን በቅድስና ልናድግ፥ ኃጢአትን ልናሸንፍና ለእግዚአብሔር ክብር ልንኖር አንችልም ማለት አይደለም። ነገር ግን ዮሐንስ የሚናገረው በሕይወታችን ውስጥ ስላለ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ከክፉ ስለሚመጣው የፈተና ምንጭ ጭምር ነው። (በግሪክ ቋንቋ፥ ትኩረት የተሰጠው ኃጢአትን በማሸነፍ ላይ ሳይሆን፥ «ክፉ» የተባለውን ሰይጣንን በማሸነፍ ላይ ነው፥ የሚፈትነን እርሱ ነውና።) ዮሐንስ የሚናገረው ሰይጣን መቼ በኃጢአት እንደሚፈትነን ነው? በብስለት እያደግን ስንሄድ በመንፈሳዊ ጥንካሬም እናድጋለን። በመንፈሳዊ ብስለት ማደግ ከሚያስገኛቸው ውጤቶች አንዱ ሰይጣን እንዳያሸንፈንና ወደ ኃጢአት እንዳይመራን መከላከል መቻል ነው። እግዚአብሔር በእምነታችን ጠንካሮች እንድንሆን ለማገዝ የሰጠን ዋናው መሣሪያ ምንድን ነው? ይህ በውስጣችን ሊኖር የሚገባው የእግዚአብሔር ቃል ነው።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) እነዚህ ሦስት እውነቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሳይ ጠቃሚ አመልካቾች የሚሆኑት ለምንድን ነው? ለ) መዝ 119፡9 አንብብ። ይህ ምንባብ ሰይጣንንና ኃጢአትን ስለምናሸንፍበት መንገድ ምን ይላል? ይህ ሰይጣንን ከሕይወታችን ለማራቅ መጸለይና መገሠጽ ብቻ በቂ እንዳልሆነ የሚያሳየን እንዴት ነው?

፪. ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ማለት የዓለምን የአኗኗር ዘይቤ አለመውደድ ነው (1ኛ ዮሐ 2፡15-17)

አንድን ሰው ስትወድ ሰውየው የሚወደውን እንጂ የሚጠላውን አታደርግም። እንወደዋለን የምንለው ሰው የማይፈልገውን ነገር የምናደርግ ከሆነ፥ ይህ ግንኙነታችንን፥ ከማደፍረሱም በላይ ለግለሰቡ ፍቅር እንደሌለን ያሳያል። እግዚአብሔርን ከወደድን እንዲሁም ከእርሱ ጋር ኅብረት ካለን፥ እርሱ የሚወደውን ልንወድና ደስ የማያሰኘውን ከማድረግ ልንቆጠብ ይገባል። ዮሐንስ እግዚአብሔር ከማይወዳቸው ነገሮች አንዱን ይጠቅሳል። ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ ሲል ይመክረናል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ዮሐንስ የሚናገረው ስለተፈጠረው ዓለም አይደለም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩም በላይ መልካም መሆኑን ተናግሯልና (ዘፍጥ. 1፡31)። ዮሐንስ ሰዎችን ማለቱም አይደለም፥ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰዎችን ከመውደዱ የተነሣ ልጁ እንዲሞትላቸው ልኮታልና (ዮሐ 3፡16)። ዮሐንስ «ዓለም» ሲል ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ የሆነ ፍልስፍና ወይም ትምህርት ማለቱ ነው። ይህ የዓለም ዘይቤ በኩራትና በራስ ወዳድነት የተሞላ ነው። እነዚህ ባሕርያት በዐመፅ ወደ ተሞሉ ተግባራትና የግንኙነቶች መፈራረስ ይመራሉ። የገንዘብ፥ የሥልጣን፥ በወሲባዊ ግንኙነቶች ሌሎችን የማሸነፍና ለተሳሳቱ ዓላማዎች የመማር ፍቅር የሚመጣው የማያምኑ ሰዎች ከሚያስተምሩት የአኗኗር ዘይቤ ነው። እግዚአብሔር ልጆቹ እነዚህን ነገሮች ባለመውደድ ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲገልጹለት ይፈልጋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ከዓለም ዘይቤ ክርስቲያኖች እንዳንድ ጊዜ የሚወዷቸውንና በሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን ነገሮች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: