የ2ኛ ዮሐንስ መግቢያ

ገብሬ የአንድ ቤተ ክርስቲያን የመሪዎች ኃላፊ ነበር። አንድ ቀን አንድ ወንጌላዊ ነኝ ባይ ገብሬ ወዳለበት ከተማ መጣ። ወንጌላዊው የሚያርፍበት ቤት ስላልነበረው፥ በገብሬ ቤት ለማረፍ ይችል እንደሆነ ጠየቀው። ገብሬም ፈቃደኛነቱን ገለጸ። ብዙም ሳይቆይ ገብሬ ይህ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ የወንጌል እውነት ጋር የሚጻረር ትምህርት እያስተማረ መሆኑን ተገነዘበ። ይሁንና ገብሬ እንግዳን ለማስቀየምና የሚከፋፈል አሳብ ለመሰንዘር አልፈለገም። ስለሆነም ገብሬ እንግዳው እቤት ውስጥ እንዲቆይ ፈቀደለት። በዚህም ጊዜ እንግዳው በገብሬ ቤት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሚያካሂዱት ሰዎች ጋር እንዲገናኝና እሑድ እሑድ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሄድ አደረገው። ግለሰቡ ከገብሬ ጋር በመኖሩና ከእርሱ ጋር አብሮ ወደ ቤተ ክርስቲያንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስለሚመጣ ከቤት ወደ ቤት እየዞረ ሐሰተኛ ትምህርቶቹን ባስተማረበት ወቅት፥ ሰዎቹ በቀላሉ ሊያምኑትና ወደ ሐሰተኛ ትምህርት ሊወሰዱ ቻሉ። ብዙም ሳይቆይ ከቤተ ክርስቲያናቱ አባላት ብዙዎቹ ይህን ግለሰብ ተከትለው ሐሰተኛ ትምህርት በማስፋፋታቸው፥ በቤተ ክርስቲያናቱ ውስጥ ክፍፍል ተከሰተ።

የ2ኛ ዮሐንስን መልእክት ጸሐፊ ያሳሰበው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ነበር። የቤተ ክርስቲያን አባላት አንድ ሰው ከቤተ ክርስቲያን መሪ ጋር ሲተባበር በሚመለከቱበት ጊዜ፥ ሰዎች ግለሰቡ አማኝ ብቻ ሳይሆን ከክርስቶስ ወንጌል ጋር የሚዛመድ ትምህርት እንደሚከተል ያስባሉ። ከዚህም የተነሣ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሐሰተኛ ትምህርቶችን የሚከተሉ ሰዎች ይኖራሉ። መሪው ሐሰተኛ አስተምህሮዎች የሚያስተምሩትን ወንጌላውያን ምን ማድረግ ይኖርበታል? የክርስቲያኖች ፍቅር ከዚህ ሁኔታ ጋር የሚጣጣመው እንዴት ነው? የ2ኛ ዮሐንስ ጸሐፊ፥ «ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፥ ሰላምም አትበሉት፥ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላል» ይላል። መሪዎች መንጋቸውን ከሐሰተኛ ትምህርት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ይህም ማለት ሐሰተኛ ትምህርት በሚያስተምር ሰው ሁሉ ላይ ግልጽና ጠንካራ አቋም መውሰድ አለባቸው ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱን ሰው በእንግድነት መቀበልና ወይም ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ማድረግ ምእመናንን በማሳሳት ወደ ሐሰተኛ ትምህርት ይነዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው እውነትን በመታዘዝ ወይም በቅድስና ባለመመላለስ በእግዚአብሔር ላይ ግልጽ የዐመፀኛነት እርምጃ ሲወስድ፥ አማኞች ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዳያደርጉ በግልጽ ያስጠነቅቃል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች እውነትን እንከተላለን ከማይሉት ዓለማውያን በላይ ከክርስቲያኖች እንዲርቁ መደረግ ይኖርበታል (1ኛ ቆሮ. 5፡9-13)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የአንድ መሪ ከሐሰተኛ አስተማሪ ጋር መተባበር ወይም የአንድ አማኝ በግልጽ ኃጢአት እየፈጸመ መኖር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሐሰተኛ ትምህርት ወይም ኃጢአት እንዲስፋፋ ያደረገበት ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? ሁኔታውን ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር ከእንዲህ ዓይነቱ ሰዎች ጋር እንዴት ያለ ግንኙነት እንድናደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል? ሐ) የገብሬን ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ፥ እግዚአብሔር ከሰውየው ጋር ምን ግንኙነት እንድታደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል? ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ምን ታደርጋለህ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ 2ኛ ዮሐንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ስለ ጸሐፊው፥ ስለ አንባቢዎቹ፥ እና ስለ መጽሐፉ ዓላማ የተገለጸውን ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) 2ኛ ዮሐ. 1ን አንብብ። ጸሐፊው ማን ነኝ ይላል? መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነው?

፩. የ2ኛ ዮሐንስ ጸሐፊ

የጸሐፊውንና መልእክት የተጻፈላቸውን ሰዎች ማንነት ከማይጠቅሰው ከ1ኛ ዮሐንስ በተቃራኒ፥ 2ኛ ዮሐንስ የጥንታዊ ደብዳቤ አጻጻፍ ስልትን በመከተል የጸሐፊውንና የተቀባዮቹን ማንነት ይገልጻል። ነገር ግን ጸሐፊው የራሱን ስም ከመጥቀስ ይልቅ፥ የአመራር ደረጃውን ይገልጻል። በመሆኑም ራሱን «ሽማግሌ» ሲል ይጠራዋል።

ምሁራን የ2ኛ ዮሐንስ ጸሐፊ ማን ይሆን? በሚለው ጉዳይ ላይ ይከራከራሉ። በዚህ ረገድ ሁለት ዓይነት አሳቦች ይሰነዘራሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንዶች ጸሐፊው ሽማግሌው ዮሐንስ የሚባል ሰው ነው ይላሉ። ከጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንዱ ሐዋርያው ዮሐንስንና ሽማግሌው ዮሐንስ የሚባለውን የተከበረ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነጣጥሎ ያያቸዋል። ይህ ሰው ሽማግሌው ዮሐንስ 2ኛና 3ኛ ዮሐንስን እንደ ጻፈ ይናገራል። ሁለተኛ፥ በአብዛኛው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመን ይህን መልእክት የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሆነ ሲታመን ቆይቷል። ይህ አመለካከት በስፋት ተቀባይነት ካገኘባቸው ምክንያቶች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

ሀ) የ1ኛና የ2ኛ ዮሐንስ የአጻጻፍ ስልቶችና የቃላት አጠቃቀም ተመሳሳይ መሆኑ፥ ሁለቱም መልእክቶች በአንድ ጸሐፊ የተጻፉ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስላል። እንዲያውም፥ በ2ኛ ዮሐንስ ውስጥ ከሚገኙ 13 ጥቅሶች ስምንቱ በ1ኛ ዮሐንስ ከሚገኙ ጥቅሶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። (2ኛ ዮሐ 7፤ ከ1ኛ ዮሐ 4፡2-3 ጋር፤ 2ኛ ዮሐ 7ትን ከ1ኛ ዮሐ. 2፡22-23 ጋር አነጻጽር።)

ለ) አብዛኞቹ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች የዚህ መልእክት ጸሐፊ ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን ይናገራሉ።

ለመሆኑ ዮሐንስ ራሱን ሐዋርያ ሳይል ሽማግሌው ብሎ የጠራው ለምን ነበር? ለዚህ ሁለት አማራጭ ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ ዮሐንስ በትንሹ እስያ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መሪ ሽማግሌ ነበር። በዚህ ክፍል «ሽማግሌ» የሚለው ቃል የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪን የሚያመለክት አይደለም። ይልቁንም ዮሐንስ በክልሉ ውስጥ የነበሩት የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሽማግሌዎች መሪ ሽማግሌ (ወይም ጳጳስ) ነበር። (1ኛ ጴጥ. 5፡1 ላይ ጴጥሮስ ራሱን ሽማግሌ ብሎ ይጠራል።) ሁለተኛ፥ ዮሐንስን አንባቢዎቹ ስለሚያውቁት፥ ሐዋርያነቱን መናገር አላስፈለገውም። ይልቁንም ዮሐንስ የሚጽፈው ከተከበረ መንፈሳዊ የአባትነት ስፍራ ሆኖ በእምነት ልጆቹ ለሆኑት ክርስቲያኖች ነበር።

፪. መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነበር?

መልእክቱ የተላከው፥ «እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ለሚወዷቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆቿ፥» ነበር። ይህ ማንን እንደሚያመለከት የሚናገሩ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች፡- በመጀመሪያ፥ በትንሹ እስያ ውስጥ ለምትገኝ የታወቀች ክርስቲያንና ለልጆቿ ነው የሚሉ ምሁራን አሉ። ዮሐንስ ይህችን ሴት ያውቃት የነበረ ሲሆን፥ ስሟ ግን ለዛሬይቷ ቤተ ክርስቲያን አይታወቅም። ቤቷ የቤተ ክርስቲያን መሰብሰቢያ ሆኖ ያገለግል የነበረ ይመስላል። ሁለተኛ፥ ብዙ ምሁራን ዮሐንስ ተምሳሌታዊ ቋንቋ እየተጠቀመ ነው ይላሉ። ሴቲቱ ቤተ ክርስቲያን ነች። ልጆቿ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አባላት ናቸው። ይህን አቋም የሚይዙ እንዳንድ ምሁራን ይህ መልእክት የተጻፈው ዮሐንስ በኃላፊነት ለሚቆጣጠራቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደነበረ ያስረዳሉ።

፫. 2ኛ ዮሐንስ የተጻፈበት ዘመንና ቦታ

ጸሐፊው መልእክቱን በጻፈበት ወቅት የት እንደ ነበረና ጊዜውም መቼ እንደሆነ የሚያመለክት በቂ መረጃ በመልእክቱ ውስጥ አልተጠቀሰም። በ1ኛና 2ኛ ዮሐንስ መልእክቶች መካከል ከሚታዩት በርካታ ተመሳሳይነቶች የተነሣ፥ ሁለቱ መልእክቶች በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ እንደ ተጻፉ ይገመታል። ስለሆነም፥ ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን መልእክት በኤፌሶን አካባቢ ሆኖ ከ85-95 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የጻፈ ይመስላል።

፬. የ2ኛ ዮሐንስ መልእክት ዓላማ

የ2ኛ ዮሐንስ ዓላማ በብዙ መንገዶች ከ1ኛ ዮሐንስ ጋር ይመሳሰላል። የመጀመሪያው ዓላማ፡ ዮሐንስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ አማኞች ሳይከፋፈሉ በአንድነትና በፍቅር እንዲኖሩ ያበረታታቸዋል።

ሁለተኛ ዓላማ፡- አማኞችን ከስፍራ ስፍራ ከሚጓጓዙ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ለማስጠንቀቅ ነው። እንደ 1ኛ ዮሐንስ ሁሉ፥ እነዚህ ሐሰተኞች የክርስቶስን ሰብአዊነት ወይም አምላክነት ይክዱ ነበር። አማኞች ከእነዚህ ሐሰተኞች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ አይገባቸውም ነበር። ከ50 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበረው፥ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ወንጌልን የሚሰብኩ ወንጌላውያን ወይም ሚሲዮናውያን ነበሩ። እነዚህ ወንጌላውያን የሚያርፉባቸው ሆቴሎች በዚያን ጊዜ ስላልነበሩ፥ የመጠለያ፥ የምግብና ለጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት ከአማኞች ነበር። የሚያሳዝነው የኖስቲሲዝም አስተማሪዎች ይህንኑ መንገድ መጠቀም ጀመሩ። ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚዘዋወሩበት ጊዜ በአማኞች ቤት ውስጥ ያርፉ ነበር። ይህም ሐሰተኛ ትምህርታቸውን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ለማሰራጨት በር ከፈተላቸው። በተዘዋዋሪ መንገድ እነዚህ የዋህ ክርስቲያኖች የሐሰተኛ ትምህርት ማከፋፈያ መሣሪያዎች ሆነው ነበር። ስለሆነም ዮሐንስ አማኞች ወደ ቤታቸው የሚጋብዟቸውን ሰዎች ጠንቅቀው እንዲያውቁ ያሳስባቸዋል። አማኞች እውነተኛ አማኞችን ብቻ በእንግድነት መቀበል ያስፈልጋቸው ነበር። ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ግን ወደ ቤታቸው አለመጋበዝ ብቻ ሳይሆን፥ ከእነርሱ ጋር ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቲያኖችም ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር የሚያደርጉት ማንኛውም ዓይነት ወዳጅነት እና ግንኙነት ሰይጣን ሐሰተኛ ትምህርቱን ለማስፋፋት እንዲጠቀምባቸው ያደርጋቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡ ዛሬ የማይታወቁ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚሰብኩት እና ከአማኞች ጋር ስለሚኖሩበት ሁኔታ ዮሐንስ ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ይመስላል?

፭. የ2ኛ ዮሐንስ ልዩ ባሕርያት

  1. እንደ ፊልሞና፥ 3ኛ ዮሐንስ እና ይሁዳ ሁሉ፥ ይህ መልእክት በጣም አጭር በመሆኑ አንድ ምዕራፍ ብቻ ይዟል።
  2. ዮሐንስ በእውነት ላይ ያተኩራል። በዚህ አጭር መልእክት ውስጥ ዮሐንስ እውነት የሚለውን ቃል አምስት ጊዜያት ጠቅሷል። አማኞች የወንጌሉን እውነት መውደድ ያስፈልጋቸው ነበር። እውነትን የሚያውቁ ሰዎች ደግሞ እምነታቸው እውነት መሆኑን በማሳወቅ በእውነት መመላለስ ያስፈልጋቸው ነበር።

፮. የ2ኛ ዮሐንስ አስተዋጽኦ

  1. ሰላምታ (2ኛ ዮሐ 1-3)
  2. እውነትን የሚያውቁ ሰዎች በፍቅርና በታዛዥነት ይመላለሳሉ (2ኛ ዮሐ. 4-7)
  3. ክርስቲያናዊ ኅብረት የሚያቅፈው እውነትን የሚያምኑትን ብቻ ነው (2ኛ ዮሐ 8-13)

የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ዮሐንስ አንብብ። ሀ) ይህ መልእክት ለእውነትና ትክክለኛ እምነት አስፈላጊነት ምን ያስተምራል? ለ) ከዚህ መልእክት ስለ ክርስቲያናዊ ኅብረት ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d