የዮሐንስ ራእይን ለመተርጎም የሚያግዝ አሳብ 

የዮሐንስ ራእይ ለመተርጎም እጅግ ከሚያዳግቱ የመንፈስ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱ ነው። ቀደም ሲል በአእምሮአችን ውስጥ ያሉት አስተሳሰቦች፥ ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦችና ለብሉይ ኪዳን ተአምራት ያለን አመለካከት በዮሐንስ ራእይ አተረጓጎማችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። የዮሐንስ ራእይ ለመተርጎም አስቸጋሪ የሚሆነው በሚከተሉት ምክንያቶች ሳቢያ ነው። በመጀመሪያ፥ በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኙት ራእዮች ምን ያህሎቹን በተምሳሌታዊ አገላለጽ፥ ምን ያህሎቹን ደግሞ በቀጥተኛ መንገድ መረዳት እንደሚያስፈልግ መወሰኑ አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ ያህል፥ የክርስቶስ የ1000 ዓመት ንግሥና ተምሳሌታዊ ነው ወይስ ቀጥተኛ? የተለያዩ ምሁራን ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት መልስ የተለያየ ነው። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ለእስራኤል አገር ስላለው ዓላማ ያለን ግንዛቤ በአተረጓጎማችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። እግዚአብሔር ከእንግዲህ ለእስራኤል የተለየ ዓላማ የለውም የምንል ከሆነ፥ በመጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ትምህርቶች አንዳንዶቹን በተምሳሌታዊ መንገዶች መተርጎማችን የግድ ይሆናል። ነገር ግን እግዚአብሔር ለእስራኤል ወደፊት የተለየ ዓላማ አለው የምንል ከሆነ፥ ስለ እስራኤል የተሰጡትን አንዳንድ ትንበያዎች በቀጥታ እንወስዳቸዋለን። ስለሆነም የዮሐንስ ራእይ ኢየሩሳሌምን ሲጠቅስ ይህ ቤተ ክርስቲያንን ወይም መንግሥተ ሰማይን ሳይሆን በእስራኤል አገር ያለችውን አካላዊት ኢየሩሳሌም የሚገልጽ መሆኑን እንረዳለን። ስለ ወደፊቱ ዘመን ያለንን አመለካከት ካስተካከልን በኋላ፥ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች ሁሉ ከአመለካከታችን ጋር ለማስማማት እንሞክራለን።

የዮሐንስ ራእይን ለመተርጎም በምንሞክርበት ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮች ማስታወስ ይኖርብናል፡-

ሀ. ለሰዎች ሁሉ ግልጽ በሆኑት ታላላቅ የመጽሐፉ ትምህርቶች ላይ ትኩረት ማድረግ። የዮሐንስ ራእይ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ሁሉ እንደሚቆጣጠርና በጠላቶቹም ላይ የኋላ ኋላ ድልን እንደሚቀዳጅ ያስረዳል። የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚሰደዱበት ጊዜ እንደሚመጣ በማሳየት፥ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እምነታችንን ከመካድ ወይም ከመደበቅ ይልቅ ለክርስቶስ ታማኞች ሆነን ልንጸና እንደሚገባ ያስተምራል። በዚህ ምድር ላይ የምንሰጠው ውሳኔ በዘላለማዊ መንግሥት በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይናገራል። ዛሬ ከእግዚአብሔር ጠላቶች (ሰይጣን፥ ዓለም፥ ክፉ መንግሥታት) ጋር መተባበሩ ለጊዜው ስደታችንን ሊያረግብ ቢችልም፥ ወደፊት ዘላለማዊ ፍርድ ያስከትልብናል። ነገር ግን ንጹሕ ሕይወት በመምራትና ዛሬ መከራ የሚያስከትልብንን ስደት ሁሉ በመቀበል ለክርስቶስ ታማኞች ሆነን ብንጸና፥ ወደፊት ዘላለማዊ ደስታ ይኖረናል።

ለ በእያንዳንዱ ራእይ ዝርዝር ጉዳዮች መዋጥ የለብህም። በእያንዳንዱ ራእይ ውስጥ ምሁራን የሚወዛገቡባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ትተህ ዐበይት ትምህርቶችን ተመልከት። ለምሳሌ ያህል፥ በእግዚአብሔር ፊት ስላለው የብርጭቆ ባህር እየተከራከርክ በዙፋኑ ላይ ያለውን የአምላካችንን ክብር መዘንጋት የለብህም (ራእይ 4)።

ሐ. ራእዩ ስሜትህን እንዲነካ ፍቀድ። ራስህን በዮሐንስ ቦታ አስቀምጥና ራእዩን እንደተመለከትህ ቁጠር። በዚህ ጊዜ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማሃል? አብዛኞቹ ራእዮች የታሰቡት ስሜታችንን እንዲነኩ፥ የእግዚአብሔርን ኃይል አይተን እንድናደንቀውና እንድንፈራው፥ ክርስቶስ የታሪክን የመጽሐፍ ጥቅልል በመውሰዱ የእፎይታ ስሜት እንዲሰማን፥ የዘንዶውን ኃይል እና ክፋት እንድንፈራ፥ ወዘተ.. ነው። ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሁሉ በላይ የዮሐንስ ራእይ በአእምሮአችን ብቻ ሳይሆን በስሜታችን ጭምር ልንረዳው የሚገባን መጽሐፍ ነው።

መ. የራእዩን ክፍል በዛሬው ዓለም ውስጥ ካለ ሰው ወይም መንግሥት ጋር ለማዛመድ ከሚጥር አጓጊ አተረጓጎም ተጠንቀቅ። በታሪክ ሁሉ ብዙ ሰዎች ሐሳዊው መሢሕ ክፉ የፖለቲካ መሪ (ኔሮ፥ ሂትለር፥ ሙሶሎኒ፥ ወዘተ..) እንደሆነ ቢገምቱም፥ ተሳስተዋል። ሌሎች ደግሞ ይህ አንድን መንግሥት (የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፥ ጀርመን፥ የአውሮፓ ኅብረት) ያመለክታል ቢሉም አልሆነም። እንዲህ ዓይነት ግምቶች ስሕተት መሆናቸው በሚረጋገጥበት ጊዜ የክርስቶስን ስም ያሰድባሉ።

ሠ. ተምሳሌታዊነታቸው ከዐውደ ንባቡ በግልጽ የሚታይ ካልሆነ በቀር ነገሮችን በቀጥታ ተረዳ። ለምሳሌ ያህል፥ የመጽሐፍ ጥቅልሉ ተምሳሌታዊ ነው እንልና በተምሳሌታዊ መንገድ ልንተረጉመው እንችላለን። ነገር ግን የክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥት ተምሳሌታዊ አይመስልም። ስለሆነም እንደ ቀጥተኛ ዘመን መረዳቱ የሚሻል ይመስላል።

ረ. ትሑት ሁን። ስለዚህ መጽሐፍ የተለያዩ ግንዛቤዎች ያሏቸው እግዚአብሔርን የሚወዱ አማኞች አሉ። ማናችንም ይህን መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ በትክክል አንረዳውም። በክርስቶስ ዘመን የነበሩት አይሁዶች ከሞቱና ትንሣኤው በፊት እንዴት ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን እንደፈጸመ ሊረዱ እንዳልቻሉ ሁሉ፥ እኛም በውስጡ የተገለጹት ክስተቶች ተፈጽመው እስኪያበቁ ድረስ የዮሐንስ ራእይን ሙሉ በሙሉ ልንረዳው አንችልም። ያለፉት ክስተቶች ለመፍታትም ሆነ ለመተርጎም ቀላሎች ናቸው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading