የዮሐንስ ራእይ ልዩ ባሕርያት


  1. የዮሐንስ ራእይ አፖካሊፕቲክ በመባል የሚታወቅ ለየት ያለ የሥነ ጽሑፍ ይዘት ያለው ነው። ምንም እንኳን ዛሬ አፖካሊፕቲክ ሥነ ጽሑፎች በብዛት ባይታዩም፥ በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ውስጥ ለነበሩት አይሁዶችና ክርስቲያኖች ዘንድ ይህ በሚገባ የታወቀ የሥነ ጽሑፍ ዓይነት ነበር። በብሉይ ኪዳን ዳንኤልና ዘካርያስ ይህንኑ የሥነ ጽሑፍ ዓይነት ተጠቅመዋል። ሌሎች አይሁዶች በብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን መካከል በነበሩት የ400 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የጻፉአቸውና አይሁዶችና ክርስቲያኖች የሚያነቧቸው የአፖካሊፕቲክ ሥነ ጽሑፎችም ነበሩ።

የዮሐንስ ራእይ ከአይሁድ የኤጲካሊፕቲክ ሥነ ጽሑፎች ጋር የሚመሳሰልባቸው መንገዶች፡-

ሀ) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ መንፈሳዊ እውነቶች በተምሳሌታዊ ቋንቋ ቀርበዋል። ለምሳሌ ያህል፥ ክርስቶስ አንበሳና በግ ተብሎ ተጠርቷል። እነዚህም ተምሳሌቶች ክርስቶስ እንደ አንበሳ ድል ነሺ፥ ገዢ፥ እንዲሁም እንደ በግ መሥዋዕት ሆኖ ለሰዎች ኃጢአት የሞተ መሆኑን ያሳያሉ። ክፉ የዓለም መሪዎች በዘንዶ አምሳል ተገልጸዋል። መጽሐፉን ለመተርጎም ከባድ የሚሆነውም ከዚሁ ተምሳሌታዊ ቋንቋ የተነሣ ነው። ብዙውን ጊዜ የተገለጸው ነጥብ በቀጥተኛ መልኩ ወይም ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ የሚፈጸም መሆኑን ለመወሰን ያስቸግራል። ለዚህ መጽሐፍ ብዙ የተለያዩ አተረጓጎሞች የቀረቡት ከዚህ የተነሣ ነው። ምንም እንኳ የእነዚህ ራእዮች ቋንቋ ለእኛ እንግዳ ቢሆንም፥ ለቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ግን በሚገባ የሚታወቅ ነበር።

ለ) በሰማይና በምድር መካከል የነበረው መጋረጃ በመወገዱ ሰዎች በሰማይ ላይ የሚከናወነው ተግባር በምድር ላይ የሚከሰቱትን ነገሮች የሚወስንበትን ሁኔታ ለመመልከት ችለዋል።

ሐ) ይህ መጽሐፍ የሚደመደመው የእግዚአብሔርን የመጨረሻ መንግሥት ብሥራት በማመልከት ነው። ይህም መንግሥት በሚያስደንቅ ሁኔታ በምድር ላይ እንደሚገለጥ ይጠበቃል። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያሳድዱ ክፉ ሰዎችና መንግሥታት ይወገዳሉ። እግዚአብሔርም ለታማኝ ተከታዮቹ ሽልማትን ይሰጣል።

  1. ዮሐንስ በአንድ ወቅት ከተመለከተው አንድ ረጅም ራእይ ይልቅ፥ የዮሐንስ ራእይ ተከታታይ ራእዮችን ያካተተ ይመስላል። አንዳንዶች በመጽሐፉ ውስጥ ከ60 የሚበልጡ ራእዮች እንደነበሩ ይገምታሉ። እግዚአብሔር በእነዚህ አጫጭር ራእዮች አማካኝነት ታሪክን እንደሚቆጣጠርና በመጨረሻው ዘመን ምን እንደሚከሰት የሚያመለክቱትን መንፈሳዊ እውነቶች አስተምሯል። ከእነዚህ ራእዮች አብዛኞቹ ከብሉይ ኪዳን ተምሳሌቶች የተወሰዱ ናቸው። እንዲያውም፥ የዮሐንስ ራእይ ብሉይ ኪዳንን 360 ያህል ጊዜያት እንደሚጠቅስ ይገመታል። ይህም ከማንኛውም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በላይ ብዙ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች የተጠቀሱበት መጽሐፍ መሆኑን ያመለክታል።
  2. ዮሐንስ ተምሳሌታዊ ቁጥሮችን ይጠቀማል። በተለይም ፍጹምነትን ወይም ምሉእነቱን የሚያመለክተውን 7 በተደጋጋሚ ሲጠቅስ እንመለከታለን። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ 7 ቁጥር 52 ጊዜያት ያህል ተጠቅሷል። ይህ ቁጥር ከተገለጸባቸው ሁኔታዎች መካከል 7 አብያተ ክርስቲያናት፥ 7 መናፍስት (ራእይ 1፡4)፥ 7 የወርቅ መቅረዞች (ራእይ 1፡12) 7 ከዋክብት (ራእይ 1፡16)፥ 7 ቀንዶችና 7 ዓይኖች (ራእይ 5፡6)፥ 7 መለከቶች (ራእይ 8፡2)፥ 7 ነጎድጓዶች (ራእይ 10፡3)፥ 7 ኮረብታዎች (ራእይ 17፡9) 7 ነገሥታት (ራእይ 17፡10)፥ ወዘተ…። ሌላው ዮሐንስ አዘውትሮ የሚጠቀመው 10 ቁጥርን ነው። ይህም ፍጹምነትን ወይም ምሉእነትን ያመለክታል (ራእይ 2፡10፣ 12፡3፤ 13፡1)። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያመለክተው ቁጥር 12 ተገልጾአል (ራእይ 7፡4-8፤ 21፡12፤ 21፡14)። አንዳንድ ጊዜ ዮሐንስ እነዚህን ቁጥሮች በማቀላቀል ይጠቀማል። አንዳንድ ምሁራን እነዚህ ተቀላቅለው የቀረቡት ቁጥሮች ተምሳሌታዊ ፍቺ እንደሚሰጡ ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፥ ዮሐንስ 144ሺህ አይሁዶችን ይጠቅሳል። ይሄም የ12 እና የ10 ቁጥር ውህደት ነው (12×12፥ 10x10x10)። እንዲሁም ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥት ይናገራል (10x10x10)። ምሁራን እነዚህ ቁጥሮች ተምሳሌታዊ ወይም ቀጥተኛ ትርጉም አላቸው በሚለው ላይ ይከራከራሉ።
  3. ዮሐንስ ለክርስቶስ ብዙ ስሞችን ይጠቀማል። እነዚህም ስሞች በዚሁ በዮሐንስ ራእይ ብቻ የሚገኙ ናቸው። ለአይሁዶች የአንድ ሰው ስም ስለ ባህሪው ወይም ደረጃው አንድ መልእክት ያስተላልፍ ነበር። ዮሐንስ የክርስቶስን ታላቅነት ከተለያዩ የእይታ አቅጣጫዎች ለማሳየት ሲል እነዚህን ስሞች ይዘረዝራል። ዮሐንስ ከተጠቀማቸው የዮሐንስ ልዩ ስሞች መካከል፡ሀ) የታመነና እውነተኛ ምስክር፥ ለ) ከሙታን በኩር፥ ሐ) አልፋና ኦሜጋ፥ መ) ሁሉን ቻይ፥ ሠ) የመጀመሪያውና የመጨረሻው፥ ረ) የይሁዳ ነገድ አንበሳ፥ ሰ) በጉ፥ ሽ) የእግዚአብሔር ቃል፥ ቀ) ፊተኛውና ኋለኛው፥ በ) የዳዊት ሥርና ዘር፥ እንዲሁም ተ) የሚያበራ የንጋት ኮከብ የሚሉ ይገኙባቸዋል። ዮሐንስ ክርስቶስን «በጉ» በሚል ስያሜ መጥራት ያስደስተዋል። በመሆኑም ይህን ቃል 28 ጊዜያት ጠቅሶት እናገኘዋለን። 

የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 20፡1-6 አንብብ። ዮሐንስ በሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምን ይከሰታል ይላል?

  1. ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሁሉንም በመቆጣጠር ላይ እንዳለ የሚያስረዳው የዮሐንስ ራእይ አጠቃላይ መልእክት ለሁሉም ሰው ግልጽ ቢሆንም፥ ምሁራን በዝርዝር አተረጓጎሞች ላይ የተለያየ አቋም ይይዛሉ። አንዳንዶቹ የዮሐንስ ራእይ የሚናገረው ወደፊት ስለሚከሰተው ሁኔታ ሳይሆን፥ ነገር ግን በዮሐንስ ዘመን እንደ ነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በዘመናቸው ለነበሩት ሁኔታዎች ነው ይላሉ። በእነዚህ ምሁራን አስተሳሰብ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ተምሳሌታዊ አገላለጾች በሮም መንግሥት ውስጥ ተፈጻሚነትን አግኝተዋል። ሌሎች ምሁራን በበኩላቸው ይህ መጽሐፍ ከዮሐንስ ዘመን አንሥቶ ክርስቶስ እስከሚመለስበት ጊዜ ያለውን ሁኔታ በቅኝት መልክ የሚዳስስ ነው ይላሉ። ከእነዚህ የተለዩት ደግሞ ራእይ 6–22 ወደፊት የሚመጣውን ዘመን በተለይም ክርስቶስ ሊመለስ ሲል የሚታየውን የዓለም ሁኔታ ያሳየናል ይላሉ። ዮሐንስ ሁልጊዜም የሚታየውን በክፋትና ደግነት መካከል የሚካሄድ ጦርነት ለማሳየት ፈልጎ ነው የሚሉም አሉ። በእነዚህ ምሁራን አስተሳሰብ ዮሐንስ በመጽሐፉ ውስጥ የጠቀሰው በራሱ ዘመን ወደፊት የሚታየውን ታሪካዊ ክስተት አይደለም። ከእነዚህ አራቱ አመለካከቶች አንዱን በምንይዝበት ጊዜ መጽሐፉን የምንተረጉመው በዚያው መንገድ ነው።

ከእነዚህ አመለካከቶች አብዛኞቹ ከፊል እውነትነት ያላቸው ይመስላል። እግዚአብሔር በዮሐንስ ዘመን ለነበሩት አማኞች ስለ ሮም መንግሥት ክፋትና ስለሚደርስበት ውድቀት ለማስተማር የፈለገ ይመስላል። ስለሆነም መጽሐፉ ታሪካዊ መሠረት እንዳለው እንመለከታለን። በተጨማሪም እግዚአብሔር በሰማይ ውስጥ ባለማቋረጥ በእርሱ እና በሰይጣን (ሰይጣን ሰብአዊ መሪዎችን በመጠቀም ሕዝቡን እየተዋጋ) መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ሲካሄድ ለማሳየት ይፈልጋል። ይህም ሆኖ የዮሐንስ ራእይ በአመዛኙ የሰው ልጅ ታሪክ ወደሚያበቃበት እና ክርስቶስ ወደሚመለስበት የወደፊቱ ዘመን የሚያመለክት ይመስላል።

የዮሐንስ ራእይ በዓለም መጨረሻ ስለሚሆኑት ነገሮች የሚናገር ነው ብለው የሚያስቡ አማኞችም ሳይቀር በዮሐንስ ራእይ አተረጓጎም ላይ የተለያዩ አቋሞች አሏቸው። ምናልባትም ከማንኛውም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በላይ ስለ የመጨረሻው ዘመን የምንይዘውን አቋም የዮሐንስ ራእይ አተረጓጎም ይለውጠዋል። ምሁራን በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ስለወደፊቱ ዘመን የተገለጹትን ትምህርቶች የሚረዱባቸው አራት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡፡

ሀ. ክርስቶስ ለአንድ ሺህ ዓመታት በምድር ላይ ይገዛል። ይህ አብዛኞቹ የጥንቷ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የያዙትና ዛሬም ሰፊ ተቀባይነት ያለው አመለካከት ነው። ይህን አመለካከት የሚይዙት ሰዎች የዮሐንስ ራእይ፥ አማኞች እየጨመረ የሚሄድ ስደትና የተፈጥሮ አደጋ በምድር ላይ የሚከሰት መሆኑን እንዲገነዘቡ ይፈልጋል ሲሉ ያስተምራሉ። መጨረሻው ሊደርስ ሲል ሐሳዊ መሢሕ የተባለ ታላቅ ክፉ መሪ ይነሣል። ነገር ግን ክርስቶስ ይህን ክፉ አስተማሪ በምድር ላይ ለ1000 ዓመታት ይገዛል። ከአጭር የዐመፅ ጊዜ በኋላ እግዚአብሔር አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን ይመሠርታል። እነዚህ ምሁራን እንደሚሉት ራእይ 6–22 ክርስቶስ ሊመለስ ሲል በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር ያስረዳል።

ለ. ሺህ ዓመት ክርስቶስ እስከሚመለስ ድረስ ያለውን የቤተ ክርስቲያን ዘመን የሚያሳይ ተምሳሌታዊ አገላለጽ ነው። ይህ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት እንደሚያስተምረው፥ አሁን ክርስቶስ በብዙ በምድር ላይ በአማኞች ልብ ውስጥ በሰማይ ደግሞ በሞቱ መናፍስት ላይ በመግዛት ላይ ነው። ክርስቶስ በቀጥታ በምድር ላይ ለ1000 ዓመት አይገዛም። ነገር ግን ዛሬ በአማኞች ልብ የሚገዛው ክርስቶስ ከዳግም ምጽአት በኋላ በሰማይ በፍጹማዊ ሉዓላዊነት ይገዛል ሲሉ ያስተምራሉ። እነዚህ አማኞች የዮሐንስ ራእይ ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ ክርስቶስ እስከሚመለስበት ጊዜ ድረስ ያለውን በምድር ላይ የተከሰተውን ሁኔታ ያመለክታል ይላሉ። በምድር ላይ ስደቶችና የእግዚአብሔር ፍርዶች ይገለጣሉ። እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ክርስቶስ ወደሚመለስበት ጊዜ እየተቃረብን ስንሄድ ይበልጥ እየከፉ ይሄዳሉ። ክርስቶስ ሊመለስ ክፋትን በማጥፋት፥ የሞቱትን በማስነሣትና ፍርድን በመስጠት አገዛዙን ተግባራዊ ያደርጋል። ከዚያም እግዚአብሔር ይህችን ምድር አጥፍቶ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን ይፈጥራል። 

ሐ. ሺህ ዓመት ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ እንደምትስፋፋ የሚያሳይ ተምሳሌታዊ አገላለጽ ነው። ይህ አመለካከት በ18ኛው ክፍለ ዘመን ብዙ ተከታዮች የነበሩት ሲሆን፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ተቀባይነት እያጣ መጥቷል። እነዚህ አማኞች የዮሐንስ ራእይና ሌሎችም ትንቢቶች በወንጌል ምስክርነት አማካኝነት ክርስትና ዓለምን እንደሚወርስ ያስተምራል ይላሉ። በዚህም ጊዜ ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያንና ቤተ ክርስቲያን በማኅበረሰቡ ላይ በምታሳድረው አዎንታዊ ተጽዕኖ በኩል በምድር ላይ ስለሚገዛ፥ በዓለም ላይ ፍትሕ ይሰፍናል ሲሉ ያስረዳሉ። በዚህ የወርቃማ ዘመን መጨረሻ ላይ ክርስቶስ ወደ ምድር ተመልሶ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን በማምጣት የዘላለምን መንግሥት ይጀምራል ሲሉ ያስረዳሉ።

መ. ሐሳዊ መሢሕ ከመምጣቱ በፊት ቤተ ክርስቲያን ትነጠቃለች። ከዚያም ክርስቶስ የዘላለምን መንግሥት ከመመሥረቱ በፊት በምድር ላይ ለሺህ ዓመታት ይነግሣል። ይህ አመለካከት ከራእይ 6 በፊት እውነተኛ አማኞች ሁሉ ወደ ሰማይ እንደሚወሰዱ ያስረዳል። ከራእይ 6-19 በምድር ላይ ከባድ ፈተና የሚመጣባቸውን 7 ዓመታት ያሳያል ይላሉ። በእነዚህ 7 ዓመታት ውስጥ የእግዚአብሔር ዓላማ ታሪካዊ ሕዝቡ የሆኑትን እስራኤላውያን ወደ ክርስቶስ ማምጣት ይሆናል። ይህ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሲል፥ ስደት እያየለ ይሄድና በዓለም ላይ ከፍተኛ ችግር ይከሰታል። ሐሳዊው መሢሕ የዓለም ገዢ ሆኖ ይነግሣል። ከ7ቱ ዓመታት በኋላ ግን ክርስቶስ ተመልሶ ክፋትን ሁሉ ከምድር ላይ ያጠፋል። ክርስቶስ ኢየሩሳሌም ላይ ሆኖ አይሁዶችንና አማኝ አሕዛብን ይገዛል። በዚህ የ1000 ዓመት ክፍለ ጊዜ ፍጻሜ ላይ (የዐመጽ ጊዜው ሲያልቅ) የዘላለም መንግሥት ይጀመራል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ መጨረሻው ዘመን በሚናገሩ በእነዚህ አራት አመለካከቶች ውስጥ የምትመለከታቸው ዐበይት ልዩነቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ከእነዚህ አመለካከቶች አንደኛው በዮሐንስ ራእይ ላይ ያለንን ግንዛቤ የሚወስነው እንዴት ነው? ሐ) የትኛው አመለካከት ትክክለኛ እንደሚመስልህ ግለጽ። ትክክለኛ ነው ብለህ የምታምንባቸውን ምክንያቶች አቅርብ።

የዚህ የጥናት መምሪያ ጸሐፊ እንደሚያምነው የዮሐንስ ራእይን በሚገባ ለመረዳት የሚከተሉትን ነገሮች ማስታወሱ ጠቃሚ ነው፡

ሀ) አብዛኛው የዮሐንስ ራእይ በተምሳሌታዊ ቋንቋ የተሞላ ነው። ተምሳሌቶቹን ሁሉ ለማብራራት ከመሞከር ይልቅ በዐበይት ሁነቶች ላይ ማተኮሩ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል፥ 666 ማንን እንደሚያመለክት ለመገመት ከመሞከር ይልቅ እግዚአብሔር ለታማኝ ተከታዮቹ የሐሳዊ መሢሕን ማንነት እንደሚገልጽ በሚያሳየው እውነት ላይ ማተኮሩ ጠቃሚ ነው። እንዲሁም ተምሳሌቶቹ ምን እንደሚያሳዩ (ለምሳሌ፥ የብርጭቆ ባህር ምን ያሳያል) ከመገመት ይልቅ ዮሐንስ የተመለከተውን ነገር በምናባችን ለመሳልና እርሱ የተሰማውን ስሜት ወደ ልባችን ለማስረጽ መሞከሩ የተሻለ ነው።

ለ) ራእይን፥ ዮሐንስና በመጀመሪያው ምእተ ዓለም የነበሩት አንባቢዎቹ በተረዱበት መንገድ ለመረዳት መሞከሩ አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር ይህንን ጠቃሚ መጽሐፍ የሰጠው ወደፊት ስለሚፈጸሙት ነገሮች ለመግለጽ ሳይሆን፥ በዚያን ዘመን የነበሩትን ምስኪንና የተሰደዱ ክርስቲያኖች ለማበረታታት ጭምር ነው። የዮሐንስ ራእይ እነዚያን አማኞች በዚያ የጨለማ ዘመን ውስጥ የሚያበረታታቸው እንዴት ነበር? ዘሬም እኛን የሚያበረታታን በተመሳሳይ መንገድ ነው። ስለሆነም፥ የዮሐንስ ራእይን ማጥናት ያለብን በመጨረሻው ዘመን ምን ይከሰት ይሆን በሚል ሥጋት ሳይሆን፥ ዛሬ እግዚአብሔርንና እርሱ የፈጠረውን ዓለም ለመረዳት የሚያግዙንን ትምህርቶች ለመሻት ሊሆን ይገባል። እግዚአብሔር በአገራችን፥ በመሪዎቿ፥ በረሃብና በድርቅ፥ እንዲሁም በስደት ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ተቆጣጣሪ መሆኑን በመገንዘብ ልንበረታታ ይገባል።  

ሐ) የዮሐንስ ራእይ ሁለት የተዛምዶ ደረጃዎች እንዳሉት መገንዘቡ ወሳኝ ነው። በመጀመሪያ፥ ከአሁኑ ዘመን ጋር የሚዛመዱትን ትምህርቶች መመልከት ይኖርብናል። እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ትንቢትን ለሕዝቡ የሚሰጠው በነበሩበት ዘመን ጠቃሚ መንፈሳዊ ትምህርት እንዲያገኙ በማሰብ ነው። እግዚአብሔር ወደፊት ስለሚከሰቱት ነገሮች የአእምሮ እውቀት የምናደርግበትን መረጃ መስጠት ብቻ እየፈለገ አይደለም። ስለሆነም እግዚአብሔር በዮሐንስ ዘመንና በታሪክ ሁሉ ለነበሩት ክርስቲያኖች እግዚአብሔር አሁን በዓለም ውስጥ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ጠቃሚ እውነቶችን ለማስተላለፍ ይፈልጋል። ከሁሉም ትውልዶች ውስጥ በነበሩት ክፉ መሪዎች ላይ እርሱ የተቆጣጣሪነት ሚናውን ይጫወታል። ሰይጣን የፈለገውን እንዳያደርግ አቅሙን የሚገድቡ መላእክትን ይልካል። ሰዎች ንስሐ ይገቡ ዘንድ የተፈጥሮ አደጋዎችን ይልክባቸዋል። የዮሐንስ ራእይ በዘመናችን የእግዚአብሔርን እጅ በሥራ ላይ እንድንመለከት ያግዘናል። ሁለተኛ፥ የወደፊቱን ዘመን የሚመለከቱ ትምህርቶች አሉ። የዮሐንስ ራእይ ምንም እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ነገሮች አሁን በታሪክ ውስጥ ቀስ በቀስ የሚፈጸሙ ቢሆኑም፥ ክርስቶስ ዳግም ከመመለሱና የዘላለም መንግሥት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ እነዚህ ነገሮች በተሟላ መልኩ ከፍጻሜ እንደሚደርሱ ያስረዳል።

  1. የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ከመጀመሪያው የዘፍጥረት መጽሐፍ ጋር የተዛመደ ነው። የዘፍጥረት መጽሐፍ የእግዚአብሔርን ፍጥረት የመጀመሪያ የደመቀ ክብር በማሳየት ይጀምርና ኃጢአትና ፍርድ ወደ ዓለም ገብቶ እግዚአብሔር የሠራውን ሁሉ እንዴት እንዳበላሸ ይተርካል። የዮሐንስ ራእይ ግን እግዚአብሔር በኃጢአትና በፍርድ የተበላሸችውን ዓለም ለመለወጥ እንዴት አዲስ ሰማይና ምድር እንደሚፈጥር ያሳያል። በዚህ ጊዜ የዘፍጥረት 3 እርግማን ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የዮሐንስ ራእይ ልዩ ባሕርያት”

  1. mulatu eticha

    thanks for sharing to me such type of amazing word of God.

    On Fri, Jun 28, 2019, 7:45 PM ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት wrote:

    > tsegaewnet posted: ” የዮሐንስ ራእይ አፖካሊፕቲክ በመባል የሚታወቅ ለየት ያለ የሥነ ጽሑፍ ይዘት ያለው
    > ነው። ምንም እንኳን ዛሬ አፖካሊፕቲክ ሥነ ጽሑፎች በብዛት ባይታዩም፥ በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ውስጥ ለነበሩት
    > አይሁዶችና ክርስቲያኖች ዘንድ ይህ በሚገባ የታወቀ የሥነ ጽሑፍ ዓይነት ነበር። በብሉይ ኪዳን ዳንኤልና ዘካርያስ ይህንኑ
    > የሥነ ጽሑፍ ዓይነት ተጠቅመዋል። ሌሎች አይሁዶች በብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን”
    >

Leave a Reply to mulatu etichaCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading