የዮሐንስ ራእይ ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡ አብያተ ክርስቲያናት (ብዙ የሁለተኛ ትውልድ አማኞች የሚገኝባቸው) ራሳቸውን እግዚአብሔር በሚያያቸው መንገድ እንዲገመግሙ ለማበረታታት። እንደ ኤፌሶን የመጀመሪያ ፍቅራቸውን አጥተው ነበር? እንደ ሎዶቅያ ዓለማዊ ሆነው ነበር? እንደ ትያጥሮን ኃጢአት የፈጸሙትን ሰዎች ከመቅጣት ይቆጠቡ ነበር? እንደ ሰምርኔስና ፊልድልፍያ ጥቂቶች በመሆናቸውና ለስደት በመጋለጣቸው ተስፋ ቆርጠው ነበር? በእነዚህ በሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የሚጋፈጧቸው ዓይነት ችግሮች ነበሩ። በመሆኑም ስለ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ማጥናቱ ልንለውጥ የሚገቡንን ሁኔታዎች ለማወቅ የራሳችንን ሕይወትና አብያተ ክርስቲያናት ለመገምገም ያስችለናል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሁለተኛና ሦስተኛ ትውልድ አማኞች ልብ ውስጥ እምነትና ፍቅር እየከሰመ የሚሄደው ለምንድን ነው? ለ) እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለማስወገድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

ሁለተኛ ዓላማ፡- አማኞች በስደት ጊዜ በታማኝነት ጸንተው እንዲቆሙ ለማበረታታት። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጀመሪያና በሁለተኛው ምእተ ዓመት ውስጥ ክርስቲያኖች እየጨመረ የሚሄድ ቁጣ፥ ጥላቻና ስደት ከሮማውያን ይደርስባቸው ነበር። በኔሮ ዘመን በግዛቲቱ ውስጥ በጥቂት ስፍራዎች ብቻ መታየት የጀመረው ስደት በሮም ግዛት ሁሉ ተስፋፍቶ ቀጠለ። ሮማውያን ክርስትናን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ሞከሩ። በዚህ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በሚያሰቅቅ ሁኔታ ተገድለዋል። ዮሐንስ የራእይን መጽሐፍ በጻፈበት ወቅት ሮማውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ሁለተኛውን የስደት ማዕበል ማውረድ ጀምረው ነበር። ይህ ስደት እየጨመረ ከሄደባቸው ምክንያቶች አንዱ የሮም መንግሥት የአይሁዶች ሕጋዊ ሃይማኖት የነበረውን ይሁዲነት ከክርስትና (ሕጋዊ ኃይማኖታቸው ካልነበረው) ለመለየት መቻላቸው ነበር። በሮም ግዛት ሁሉ ሰዎች በዓመት አንድ ጊዜ ለንጉሡ መሥዋዕት በማቅረብ ለዶሚቲያን ያላቸውን ታማኝነት እንዲገልጹ ይደረግ ነበር። ይህ ነገሥታትን የማምለኩ ሁኔታ ክርስቲያኖች ከአጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው። ራሱን አምላክ አድርጎ ለሚመለከተው ዶሚቲያን መሥዋዕት አቅርበው ከስደት ያምልጡ ወይስ መሥዋዕት አናቀርብም ብለው ለእምነታቸው ይሠዉ? ክርስቲያኖች እንደ ሌሎች ሰዎች መሥዋዕት በማያቀርቡበት ጊዜ የሮምን መንግሥት እንደ ካዱ ይቆጠሩ ነበር። በዚህን ጊዜ ሰዎች ከእነርሱ ዕቃ ለመግዛትም ሆነ ለመሽጥ አይችሉም ነበር። ንብረቶቻቸውንም ይዘርፉባቸው ነበር። አንዳንዶችንም ደግሞ ይገድሏቸው ነበር። ምንም እንኳ በዶሚቲያን ጊዜ የነበረው ስደት በኋላ የተከሰተውን ያህል የከረረ ባይሆንም፥ ምናልባትም ዮሐንስ ታላቅ የስደት ጊዜ እንደሚመጣ በመረዳቱ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለዚያው የስደት ወቅት ለማዘጋጀት የፈለገ ይመስላል። ጸሐፊው እነዚህን ስደት የበረታባቸውን አማኞች ለማበረታታት የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሟል። 

ሀ) ዮሐንስ ስደት የደረሰባቸው አማኞች እስከ ሞት ድረስ ጸንተው በእግዚአብሔር ሊከበሩ እንደሚችሉ ያስረዳል። ክርስቶስ (ራእይ 1፡5)፥ ዮሐንስ (ራእይ 1፡9)፥ እንዲሁም አንቲጳስ (ራእይ 2፡13) ሁሉም እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ስደትን በትዕግሥት ተጋፍጠዋል።

ለ) ዮሐንስ ሁኔታዎችን ሁሉ ስለሚቆጣጠረውና ታሪክን እርሱ ወደ ዐቀደው ግብ ስለሚመራው መለኮታዊና ሉዓላዊ አምላክ ጥርት ያለ ገለጻ በማቅረብ አማኞችን ያበረታታል። በዙፋኑ ላይ ያለው እግዚአብሔር እንጂ የምድር መንግሥታት ሰብአዊ ገዢዎች አይደሉም። እግዚአብሔር ታሪክን ለመቆጣጠርና በምድር ላይ የሚከሰቱትን ነገሮች ለመለወጥ መላእክትን ይልካል። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በመቅጣት ጠላቶቹን አንድ በአንድ ያጠፋቸዋል።

ሐ) ዮሐንስ ከስደት በኋላ እግዚአብሔር ከእርሱና ከልጆቹ ጋር የሚዋጉትን ሰዎች እንደሚቀጣ ያመለክታል። ምንም እንኳን ሰይጣን ጦርነቱን እያሸነፈ እንዳለ ወይም የምድር ገዢዎች ያሻቸውን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ብናስብም፥ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ነው። የዮሐንስ ራእይ በክፉዎች ላይ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ እንደሚመጣ ያስተምራል። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በአጠቃላይ በአስከፊ መቅሰፍቶች ይቀጣቸዋል። ከእርሱ ጋር የሚዋጉትንና ልጆቹን የሚገድሉትን ገዢዎች ይቀጣል። በሰይጣን ኃይል በምድር ላይ ታላቅ ክፋት የሚፈጽመውን የመጨረሻውን የዓለም መሪ (ሐሳዊ መሢሕ) ይቀጣል። ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምጹ በሚያንቀሳቅሱት በሰይጣንና በተከታዮቹ ላይም ፍርዱን ይገልጣል።

መ) ዮሐንስ የአማኞችን ትኩረት እግዚአብሔር ለእርሱ ታምነው ለሚጸኑ አማኞች ወደሚያዘጋጃት አዲስ ሰማይና አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በመመለስ ስደትን ጸንተው እንዲጋፈጡ ያበረታታቸዋል። ከራእይ 6፡9-11 እንደምንመለከታቸው ቅዱሳን ብዙውን ጊዜ «እስከ መቼ» ብለን እንጮሃለን። እግዚአብሔር ክፋትን መቼ እንደሚያጠፋው በናፍቆት እንጠይቃለን። እግዚአብሔር ግን ጊዜው እስኪደርስ ድረስ በትዕግሥት እንድንጠባበቅ ይነግረናል። አንድ ቀን የዚህ ዓለም ኃጢአትና መከራ ፍጻሜውን ያገኛል። ለእግዚአብሔር በታማኝነት የሚጸኑ ወደ ሰማይ (አዲሲቱ ኢየሩሳሌም) ይገባሉ። 

የውይይት ጥያቄ፡– አማኞች እነዚህን እውነቶች ማወቃቸው ለምን እንደሚያስፈልግ ግለጽ።

ሦስተኛ ዓላማ፡ ለአማኞች ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለውን የዓለም ታሪክ ለማሳየት። በብሉይ ኪዳን ዘመን ኤልሳዕ አንድ ጊዜ እግዚአብሔር የማይታዩትን ሰማያዊ ሠራዊት ለመመልከት ይችል ዘንድ የባሪያውን ዓይኖች እንዲገልጥ ጸልዮ ነበር (2ኛ ነገ. 6፡8-17)። እግዚአብሔርም የኤልሳዕን ጸሎት በመስማት ታላቅ የመላእክት ሠራዊትን አሳየው። የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ በዓይናችን የማንመለከታቸውን እውነታዎች ያሳየናል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ከሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በበለጠ ጥርት ብለው የሚታዩት በዚሁ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ውስጥ ነው።

ሀ) እግዚአብሔር የአጽናፈ ዓለሙ ፍጹማዊ ገዢ ነው። በዓለም ውስጥ ያለው ክፋት አያግደውም። ነገር ግን እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ታሪክን ወደ ፍጻሜው ይመራዋል። በሰማይና በምድር መካከል ትልቅ ክፍተት እንዳለ አድርገን ልናስብ አይገባም። የሰማይ ውሳኔዎች ሁልጊዜም በምድር ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ይሁንና፥ ይህንን በሥጋዊ ዓይናችን ማየት አንችልም። የዮሐንስ ራእይ ግን የሰማይን ዙፋን በመክፈት የሰማይና የምድር ዓለማት እንዴት አብረው እንደሚሠሩ ያሳየናል። እግዚአብሔር ታላቅ በመሆኑ የሰማይና የምድር ፍጥረት በሙሉ አንድ ቀን በአምልኮና በስግደት በፊቱ ይወድቃል።

ለ) ክርስቶስ ታሪክን ወደ ፍጻሜው የማምጣት ሥልጣን አለው። የዮሐንስ ራእይን ያህል የክርስቶስን ታላቅ ኃይል የሚያሳይ ሌላ የመንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ የለም። ክርስቶስ አምላክና ዳሩ ግን ከእግዚአብሔር አብ የተለየ መሆኑን በግልጽ ያሳየናል። ክርስቶስ የይሁዳ አንበሳ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ መሆኑን ይገልጽልናል (ራእይ 19፡16)። በተጨማሪም ዮሐንስ ክርስቶስ በግ መሆኑንም እንድናስታውሰው ይፈልጋል። እርሱ ሕዝቡን በደሙ የዋጀ የእግዚአብሔር በግ ነው (ራእይ 5፡6፥ 9)። እግዚአብሔር ክርስቶስ ታሪክን እንዲቆጣጠር ሥልጣን ሰጥቶታል። ምክንያቱም ታሪኩ ሁሉ የተጻፈበትን የመጽሐፍ ጥቅልል ለክርስቶስ ሰጥቶታልና። ወደ ምድር ተመልሶ እግዚአብሔርን በሚቃወሙት ሁሉ ላይ ፍርድን የሚሰጠውም ክርስቶስ ነው። እንደ እግዚአብሔር አብ ሁሉ ክርስቶስ በሰማይም ሆነ በምድር ካሉት ሁሉ ስግደትን ሊቀበል ይገባዋል። 

ሐ) የእግዚአብሔር ሕዝብ እግዚአብሔር እራሱ የጠራቸውና ያዳናቸው ናቸው። በምድር ላይ ብዙውን ጊዜ ሰይጣንና ክፉ የዓለም መሪዎች የሚያሸንፉን ይመስላል (ራእይ 13፡7፥ 10)። ነገር ግን አማኞች እምነታችንን አጥብቀን በመያዝ እስከ ሞት ድረስ በምንጸናባት ጊዜ ሰይጣንና የዓለም መንግሥታትን ድል እንነሣለን (ራእይ 12፡11)። እግዚአብሔር ለእኛ ያቀደው አሁን ብዙ ድል እንድናገኝ ሳይሆን በኋላ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ከእርሱ ጋር አብረን እንድናሸንፍ ነው። አሁን የእግዚአብሔርን ቃል በመታዘዝ፥ በቅድስናና በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት አጥብቆ በመያዙ ላይ ልናተኩር ይገባል (ራእይ 6፡9)። 

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) እነዚህን ሦስት እውነቶች በግልጽ መረዳት በችግርና ስደት ጊዜያት የሚያበረታታን እንዴት ነው? ለ) ዛሬ አማኝ ስለሚቀበለው መከራ የሚናገሩት አብዛኞቹ እውነቶች በአብያተ ክርስቲያን ውስጥ የማይሰበኩት ለምንድን ነው? ከዘላለማዊ በረከቶች ይልቅ በምድራዊ በረከቶች ላይ ማተኮር ቀላል የሚሆነው ለምንድን ነው? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: