መግቢያ (ራእይ 1፡1-8)

የተስፋ ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ውስጥ እጅግ ከታወቁት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ነበረች። ይህች ቤተ ክርስቲያን አስደናቂ ታሪክ አላት። መጀመሪያ ጽኑ ስደት ቢነሣባቸውም ጥቂቶቹ አማኞች ለእምነታቸው በመቆም በአገሪቱ ሁሉ እምነታቸውን አወጁ። መልካሙን የምሥራች የመስማት ዕድል እንዲያገኙ በመገንዘብ፥ ከመጀመሪያው ጀምሮ ገንዘባቸውን በመሥዋዕትነት በማዋጣት ወንጌላውያንን ወደ ተለያዩ ጎሳዎች ይልኩ ጀመር። እግዚአብሔር እነዚህን ያልተማሩ ወንጌላውያን በመጠቀሙ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት እያደገች ሄደች። ብዙም ሳይቆይ ይህች ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ታላላቅ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ለመሆን በቃች። ይህ ከሆነ በኋላ አንድ ትውልድ፥ ከዚያም ሁለት ትውልዶች አለፉ። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በጉልህ የማይታዩ ለውጦች ይከሰቱ ጀመር። አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባላት የቀድሞዎቹ እማኞች ልጆች ነበሩ። እነዚህ እማኞች ድነትን (ደኅንነትን) ያገኙት ከክርስቲያን ወላጆች በመወለዳቸው ምክንያት እንደሆነ ያስቡ ጀመር። ባሏቸው ብዙ አባላት ይኩራሩና ቤተ እምነታቸውን በበለጠ ታላቅ ስለሚያደርጉበት መንገድ ያስቡ ጀመር። አባላቱ ሌሎች ሰዎችን በሚያስደንቁ ተግባራት ላይ ማተኮር ያዙ። ታላላቅና አስደናቂ ሕንጻዎች መገንባት ጀመሩ። ለመዘምራን ቡድኖቻቸው ውብ አልባሳትንና ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ገዙ። አባላቱ በቤተ እምነቱ ውስጥ የሚካሄዱትን እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሚመራ ጠንካራ ማዕከላዊ አስተዳደራዊ መዋቅር ለማዘጋጀት ተግተው ይሠሩ ጀመር። በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትም ለውጦች ይካሄዱ ነበር። እማኞቹ ወንጌል ላልደረሰባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ወንጌል ለማድረስ ማሰባቸውን ትተው እንደ ልሳንና የፈውስ አገልግሎቶች ባሉት ነገሮች ላይ አጽንኦት መስጠት ጀመሩ። ሦስተኛ ትውልድ አማኞቻቸው በልግስና ለመስጠት ፈቃደኞች አልነበሩም። ለዚህም ምክንያቱ መሪዎቻቸው በገንዘብ አያያዝ በኩል እምነት የሚጣልባቸው መስለው አለመታየታቸው ነበር። የአገሪቱን ፖለቲካዊ ድባብ ተከትለው አማኞች በቋንቋ እና በጎሳ በመከፋፈላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ይናጋ ጀመር። በቤተ ክርስቲያን መሪዎችና በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል የራስ ወዳድነት ጸቦች ተጧጡፈው ቀጠሉ። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በተስፋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተው መሠረታዊ ችግር ምን ነበር? ለ) እምነታቸው ወደ ሁለተኛና ሦስተኛ ትውልድ አማኛች በሚተላለፍበት ጊዜ እንዴት እየከሰመ ሊሄድ እንደቻለ ግለጽ። ይህ የተለመደ ሁኔታ ይመስልሃል? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ይህን ዝንባሌ እንዴት እንደተመለከትህ ግለጽ። መ) ቤተ ክርስቲያን ቀናኢ ፍቅሯና እምነቷ ከትውልድ ትውልድ ላይቀንስ እንዲተላለፍ ምን ልታደርግ ትችላለች?

ዮሐንስ መጽሐፉን የጻፈው እንደ ዛሬዎቹ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያኖቻችን ሁለተኛ እና ሦስተኛ ትውልድ አማኞች ለሚገኙባቸው አብያተ ክርስቲያናት ነበር። በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ችግሮች በመከሰት ላይ ነበሩ። ክርስቲያኖች ለራሳቸው ምቾትና ታላቅነት በማሰብ ራስ ወዳድ እየሆኑ መጥተው ነበር። ለእግዚአብሔር የነበራቸው የቀናኢነት ፍቅር ቀዝቅዞ በእምነታቸው ለብ ብለው ነበር። ሌሎች ደግሞ ኃጢአተኞችን ከመቅጣት ይቆጠቡ ነበር። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እውነተኛውን እምነት ሳይጠብቁ ሐሰተኛ አስተማሪዎች በክርስቲያኖች መካከል ውሸትን እንዲዘሩ ይፈቅዱ ነበር። ክርስቶስ ይህንን የአብያተ ክርስቲያናት ውድቀት በመመልከቱ ዮሐንስ በእርሱ ፈንታ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ጠየቀው። በእነዚህ 7 ደብዳቤዎች ውስጥ ዛሬ አብያተ ክርስቲያኖቻችን የሚጋፈጧቸውን ብዙ ችግሮች ልንመለከት እንችላለን። ከምእመኖቻችን ብዛት ባሻገር በእምነታችን ለብ እያልን በመሄዳችን ራሳችንን ለእግዚአብሔር ፍርድ እያዘጋጀን ይሆን? 

የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 1-3 አንብብ። ሀ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወይም እግዚአብሔር አብ የተሰጡትን የተለያዩ ገለጻዎች ዘርዝር። እያንዳንዱ ገለጻ ስለ አብና ወልድ ምን ያስተምረናል? ለ) እንድ ሠንጠረዥ ሥራ። በመጀመሪያው አምድ (ረድፍ) ውስጥ 7ቱን አብያተ ክርስቲያናት ዘርዝር። በሁለተኛው አምድ ውስጥ ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናቱን ያመሰገነባቸውን ጉዳዮች ጻፍ። በሦስተኛው ረድፍ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የነቀፈበትን ጉዳዮች ጻፍ። በአራተኛው አምድ ውስጥ ክርስቶስ ለአብያተ ክርስቲያናቱ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያዎች ጻፍ። በአምስተኛው አምድ ውስጥ ክርስቶስ ለሚታዘዙት የሰጣቸውን የተስፋ ቃል ዘርዝር። ሐ) በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን ዐቢይ ጉዳይና ይኸው ጉዳይ ዛሬ ለእኛ ምን ዓይነት መልእክት እንደሚያስተላለፍ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። 

ዮሐንስ በዚህ መግቢያ ውስጥ በአያሌ ቁልፍ እውነቶች ላይ ያተኩራል።

  1. የዮሐንስ ራእይ የኢየሱስ ክርስቶስ «መገለጥ» ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ክርስቶስ የራእዩ ዋና ርእሰ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ ለዮሐንስ ራእዩን የሰጠው ራሱ ክርስቶስ ነው። የአማኛቹ ትኩረት በዮሐንስና በትንቢታዊ ሚናው ላይ ማረፍ የለበትም። ነገር ግን ክርስቲያኖች ሁልጊዜም በሰዎች ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
  2. ዮሐንስ የገለጻቸው ራእዮች ምናባዊ አይደሉም። እነዚህ ራእዮች ከኢየሱስ ክርስቶስ በመልአኩ በኩል ለዮሐንስ የተላለፉ፥ ከዚያም ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፥ ከዚያም ዛሬ ለእኛ የደረሱ ናቸው።
  3. እግዚአብሔር ራእዩን የሰጠው ወደፊት የሚሆነውን እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን፥ እንድንታዘዘው ጭምር ነው፡፡ በተለይም በእምነታችን ጸንተን እንድንቆምና ከፍተኛ ስደት በሚታይባቸው ጊዜያት ሳይቀር የእግዚአብሔርን ቃል እንድናውጅና የተሰጠንን ትእዛዝ ተግባራዊ እንድናደርግ ይፈልጋል።
  4. እግዚአብሔር አሀዱ ሥሉስ አምላክ ነው። ምንም እንኳን የዮሐንስ ራእይ በእግዚአብሔር አብና ወልድ ላይ ቢያተኩርም፥ ሦስቱም የሥላሴ አካላት ተጠቅሰዋል። እግዚአብሔር አብ «የነበረው፥ ያለውና የሚመጣው» ተብሎ ተገልጾአል። ኢየሱስ ክርስቶስ በብዙ መንገዶች ተገልጾአል። ዮሐንስ በመግቢያው ውስጥ በስደት ጊዜ በሚያበረታቱን ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። እነዚህም ከክርስቶስ ሕይወት የተገኙ ናቸው። ዮሐንስ ክርስቶስን «የታመነ ምስክር» ይለዋል። ዮሐንስ ይህን ሲል ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ የቆመ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ያወጀ እና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ለእምነቱ የሞተ መሆኑን ለማሳየት ነው። እኛም እንደ ክርስቶስ ታማኝ ምስክሮች ልንሆን ይገባል። ክርስቶስ «ከሙታን በኩር» መሆኑ ተገልጾአል። እኛም ከሙታን እንነሣለን። ክርስቶስ «የምድር ነገሥታት ገዥ» መሆኑን እንመለከታለን። በመሆኑም የምድር ገዢዎች ከእርሱ ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው ስለሚያደርሱብን አደጋ ስጋት የለብንም። መንፈስ ቅዱስ «ከዙፋኑ ፊት ያሉ ሰባቱ መናፍስት» ተብሎ ተገልጾአል። ዮሐንስ መንፈስ ቅዱስን በዚህ ባልተለመደ ስያሜ የሚጠራው ተምሳሌታዊ አገላለጽ በመጠቀም ነው። ዮሐንስ ሰባት ቁጥርን በመጠቀም መንፈስ ቅዱስ በሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያከናውን ፍጹም አካል መሆኑን ያሳያል።
  5. የዮሐንስ ራእይ በከፊል ኢየሱስ ክርስቶስ በምዕራባዊ በትንሹ እስያ ክፍል ለሚገኙ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት የጻፈውን ደብዳቤ ይመስላል። ምንም እንኳን እነዚህ ሰባት ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት ቢሆኑም፥ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ የነበሩትን የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ትግል በምሳሌነት ያሳያል። እንደ እነዚህ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ፥ እኛም የፍቅር ጉድለት፥ ክፋትንና ሐሰተኛ ትምህርትን መታገሥ፥ ዓለማዊነትና ራስ ወዳድነት እንዲሁም ስደት የሚፈታተነን መሆኑ ግልጽ ነው።
  6. ዮሐንስ እግዚአብሔር ለአማኞች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ያስረዳል። የክርስቶስ ደም በሕይወታችን ውስጥ ካለው የኃጢአት ኃይል ነፃ አውጥቶናል። አማኞች አሁን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የምንኖር በመሆናችን፥ እንደ ካህናት ልናመልከው ይገባል። እግዚአብሔርን በማምለክ ለሰዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወጅ ይኖርብናል።
  7. ዮሐንስ ክርስቶስ በቶሎ እንደሚመጣ ያስገነዝበናል። ለኃጢአት ውጥረት እጅ ላንሰጥ ወይም በስደት ጊዜ እምነታችንን ሳንደብቅ ለምጽአቱ ተዘጋጅተን መጠበቅ ይኖርብናል። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “መግቢያ (ራእይ 1፡1-8)”

Leave a Reply

%d bloggers like this: