የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሰዎች ላይ ተስፋ መቁረጥና ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉትን የዓለም ክስተቶች ዘርዝር። ለ) ክርስቲያኖች ክርስቶስን በመከተላችን ምክንያት የምንሠቃይባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) መከራን በምንቀበልበት ጊዜ የመከራውን ዓላማ ማወቃችን እንዴት እንደሚረዳን ግለጽ።
በዓለም ላይ እጅግ ታላላቅ የሆኑት ሰዎች ስለ ዕቅዶቻቸው ሲነጋገሩ የመስማት ዕድል ገጥሞናል እንበል። አዲስ አበባ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ገብተው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በአንተ እና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩ ነገሮች የሚወስዷቸውን እርምጃ ዎች ብትሰማ ምን ታደርጋለህ? ወደ ኋይት ሐውስ ገብተህ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለዓለምና ለአገራቸው ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት የወጠኗቸውን ዕቅዶች ብታውቅስ? ወይም የሩሲያ፥ የኬንያ፥ የእንግሊዝ፥ የጀርመን፥ የፈረንሳይ መሪዎች የወጠኗቸውን ዕቅዶች ብታውቅስ? ይህ ተጨማሪ ግንዛቤ በሕይወትህ ውስጥ የሚያመጣው ለውጥ ምንድን ነው? በዚህ ጊዜ በዓለም ላይ የሚከሰቱ ነገሮች ለአንተ የተለየ ትርጉም የሚሰጡት እንዴት ነው? መሪዎች ውሳኔያቸውን የሚሰጡባቸውን ምክንያቶች ማወቁ ብዙ ተስፋ መቁረጥን ሊያስከትል ይችላል። እንደዚህ ከሆነ፥ ለምን ቀረጥ እንከፍላለን? ለምን ወደ ጦርነት እንሄዳለን? የተወሰኑ አገሮች ለአገራችን ገንዘብ የሚያበድሩት ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች የሚተላለፉባቸውን ምክንያቶች ብናውቅ፥ በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ የሚያስከትሉትን ውሳኔዎች ለመቀበል ይቀልለናል።
ነገር ግን በበለጠ የሚያሳስቡን ሌሎች ጉዳዮች አሉ። ረሀብ የሚነሣው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር ኤድስ ብዙ ወጣቶችን እንዲፈጅ የፈቀደው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር ልጆቹ ስደትን እንዲጋፈጡ እና ለእምነታቸው እንዲሞቱ የሚፈቅደው ለምንድን ነው? ታላላቅ አገሮች በሚያካሂዷቸው ጦርነት ሳቢያ ዓለም በኒውክሌር ቦንብ ትጠፋ ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሶችን የምናገኘው ወይም ቢያንስ እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች እንደሚቆጣጠር የምናውቀው እንዴት ነው?
ራእይ 4-19 እጅግ ወደላቀው የአመራር ስፍራ እንድንገባ በር ይከፍትልናል። እግዚአብሔር በሰማይ ወደአለው ዙፋኑ እንድንቀርብና ውሳኔዎቹን እንድንሰማ ፈቅዶልናል። እነዚህ ውሳኔዎች በምንኖርባት ዓለም ላይ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ እንድንገነዘብ እስችሎናል። እግዚአብሔር ከኢትዮጵያ፥ ከአሜሪካ፥ ወይም ከሩሲያ መሪዎች የበለጠ ታላቅ አምላክ ነው። እርሱ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ እንዲሁም በምድር ላይ የሚወሰኑትን ውሳኔዎች ሁሉ የሚቆጣጠር አምላክ ነው። በዮሐንስ ዘመን፥ እግዚአብሔር በምድር ላይ ባሉት ሕዝቡ ላይ በቅርቡ ታላቅ ስደት እንደሚነሣ ያውቅ ነበር። እንዲሁም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ስደት በአብዛኞቹ ዘመናት ውስጥ የሚቀጥል ነበር። የእግዚአብሔር ልጆች ታሪክን እንዲረዱ እና ወደፊት ሊሆን ስላለው ጨረፍታውን እንዲመለከቱ በማገዝ፥ የዮሐንስ ራእይ እግዚአብሔር አጽናፈ ዓለሙን የሚገዛበትን ሁኔታ ወደ መንግሥተ ሰማይ ቀርበን እንድንመለከት ይጋብዘናል። እግዚአብሔር ነገሮችን እንደሚቆጣጠር መመልከቱ በምድር ላይ መከራ በምንቀበልበት ጊዜ እጅግ ያበረታታናል። የየትኛውም ንጉሥ አገዛዝ፥ ውሳኔ፥ የትኛውም የተፈጥሮ አደጋ ሁሉ በዙፋኑ ላይ ባለው አምላክና የታሪክን ጥቅልል በያዘው አንበሳና በግ በሆነው ልጁ ቁጥጥር ሥር የሚከናወን ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ይነግሣል! የተፈጥሮ አደጋ በሚመታን ጊዜም እርሱ ንጉሥ ነው። ጦርነት ቢነሣም፥ ስለ እምነታችን ስንሰደድም፥ እርሱ በዙፋኑ ላይ ነው። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ በተገለጡት እውነቶች አማካኝነት ዓይኖቻችን (የእምነት) ወደ ታላቁ የመንግሥተ ሰማይ ዙፋን እንዲመለከቱ ልንፈቅድ ይገባል። እንዲሁም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ምሥጋና ልናቀርብለት ይገባል። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ እንደሚሠራ በማወቅ በልበ ሙሉነት ልንመላለስ እንችላለን።
የውይይት ጥያቄ፡- ራእይ 4-5 እንብብ። ሀ) ስለ እግዚአብሔር አብ የተሰጡትን ስምና ገለጻዎች ዘርዝር። ከእነዚህ ራእዮች ስለ እግዚአብሔር አብ ኃይልና አገዛዝ ምን እንማራለን? ለ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጡትን ስሞችና ገለጻዎች ዘርዝር። ከእነዚህ ራእዮች ስለ ኃይሉ እና ስለ አገዛዙ ምን እንማራለን? ሐ) እነዚህን ሁለት ራእዮች በምንመለከትበት ጊዜ ምን ዓይነት ስሜት ሊሰርጽብን ይገባል?
በራእይ 4-5፥ የዮሐንስ መገለጦች ከዮሐንስ ዘመን ወደፊት ይገሰግሳሉ። እግዚአብሔር ለዮሐንስ ከራሱ ዘላለማዊ ዙፋን ላይ ተቀምጦ የሚሰጠውን አገዛዝና ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተላለፈውን የታሪክ ቁጥጥር ሥልጣን ያሳየዋል። ይህም የሰው ልጅ ታሪክ እግዚአብሔር በወሰነው መልኩ የሚፈጸም ነው። ከራእይ 6–22 ድረስ እግዚአብሔር ለልጆቹ ወደ ፊት የሚፈጸሙትን ነገሮች ያሳያል። እግዚአብሔር በዚህ ክፍል ውስጥ የገለጻቸው አብዛኞቹ ነገሮች ክርስቶስ ጠላቶቹን ለማሸነፍና ለመንገሥ ሊመለስ ሲል የሚከሰቱ ይሆናሉ። ነገር ግን እነዚህ ራእዮች ዛሬም እንኳን በሰማይ ላይ የሚከናወኑትን አንዳንድ ነገሮች እንድንገነዘብ ያግዙናል። የወደፊትን ዘመን የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር እርሱ የዛሬንም ዘመን ይቆጣጠራል።
ክርስቲያኖች ሁሉ በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች በክፉ መሪዎች ቁጥጥር ሥር አለመሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የእነዚህ ነገሮች ተቆጣጣሪ ሰይጣንም አይደለም። ነገር ግን በምድር ላይ የሚሆነውን ሁሉ የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር አብና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አብና ወልድ በሰማይ ሆነው ሁሉንም ይቆጣጠራሉ።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ሁኔታዎችን እንደሚቆጣጠር ሳንረዳ ወይም ሳናምን ስንቀር በሕይወታችን ውስጥ ምን ይከሰታል? ለ) ለአማኝ እግዚአብሔር በሕይወቱ ውስጥ ያሉትን ነገሮች፥ እንዲሁም በአገሩ እና በዓለም ሁሉ የሚካሄዱትን ነገሮች እንደሚቆጣጠር ማወቁ ለምን ያስፈልጋል?
በራእይ 4፡2፥ ዮሐንስ «ወደዚህ ቦታ ውጣ» ተብሎ ሲጠራ እንመለከታለን። በዚህም ጊዜ በተምሳሌታዊ በር በኩል ወደ ሰማይ ተወስዶ እግዚአብሔር የሚቀመጥበትንና ታሪክን ሁሉ የሚቆጣጠርበትን ዙፋን ተመልክቷል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህን ጥቅስ በመጠቀም ክርስቲያኖች በዚህ ጊዜ እንደሚነጠቁ ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ ለዮሐንስ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሁሉ የቀረበ ጥሪ አለመሆኑን መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። ዮሐንስ በሰማይ የተመለከተው ምን ነበር?
፩. የእግዚአብሔር አብ ራእይ (ራእይ 4)
ዮሐንስ ወደ ሰማይ ሲደርስ መጀመሪያ የተመለከተው የእግዚአብሔር አብን ዙፋን ነው። ይህ የአጽናፈ ዓለሙ እምብርት ነው። እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር የሚቆጣጠረው ከዚህ ሆኖ ነው። በተቀረው የዮሐንስ ራእይ ክፍል በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች ሁሉ ከዚህ ዙፋን እንደሚመነጩ እንመለከታለን። ዮሐንስ እግዚአብሔር አብን በግልጽ ሊያብራራልን አልቻለም። ይህም የሆነው ምናልባትም እግዚአብሔር አብ ከምናውቀው ነገር ሁሉ በላይ የላቀ እና የተለየ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ መረዳት አስቸጋሪ በመሆኑ ይሆናል። እንዲሁም እግዚአብሔር አብ እጅግ ቅዱስና ታላቅ በመሆኑ፥ ለፍጥረቶቹ ሙሉ በሙሉ ተገልጾ አያውቅም። (1ኛ ጢሞ. 6፡16 አንብብ።) ዮሐንስ ሊያደርግ የቻለው ነገር ቢኖር በእግዚአብሔር አብ ዙሪያ የነበሩትን አስገራሚ ቀለሞችና ኃይል መግለጽ ነበር። ዮሐንስ የጠቀሳቸው የከበሩ ድንጋዮች እና ቀስተ ደመና አረንጓዴ፥ ቀይ፥ ነጭ እና ሌሎችንም ልዩ ቀለሞች ያመለክታሉ። መብረቅ እና ነጎድጓድ በዘፋኑ ላይ የተቀመጠውን አምላክ ታላቅነትና ኃይል ያሳያሉ። ዮሐንስ በእግዚአብሔር እና በፍጥረቶቹ መካከል የብርጭቆ ባህር ተመልክቷል። ይህም እግዚአብሔር አብ ምን ያህል ቅዱስና የተለየ እንደነበር ያሳያል።
ዮሐንስ በዚህ ራእይ ነገሮችን ሁሉ በሚቆጣጠረው በእግዚአብሔር አብ ብቻ ሳይሆን፥ በዙፋኑ ዙሪያ ባሉትና እነዚህም በዙፋኑ ዙሪያ ያሉት ፍጥረታት ከእግዚአብሔር አብ ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። ዮሐንስ የሚጠቅሳቸውን የሚከተሉትን ፍጥረታት ተመልከት።
ሀ) በ24 ዙፋናት ላይ የተቀመጡ 24 ሽማግሌዎች፡ አንዳንድ ምሁራን እነዚህ የሰማይ መማክርት የሆኑ ገዢ መላእክት እንደሆኑ ያስባሉ። ነገር ግን እነዚህ ፍጥረታት ጠቅላላውን የእግዚአብሔር ሕዝብ በተምሳሌትነት የሚያመለክቱ ይመስላል። የብሉይ ኪዳን አይሁዶች በ12 ነገዶች፥ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በ12 ሐዋርያት በተምሳሌትነት ተወክለዋል።
ለ) ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት የሆኑ ሰባቱ መቅረዞች፡ «ሰባት መናፍስት» የሚሉ ቃላት «ሰባት እጥፍ መንፈስ» ተብለው ሊተረጎሙ ይችላሉ። ይህም ፍጹም ንጹሕ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ በተምሳሌትነት ያሳያል። በእግዚአብሔር አብ ተልዕኮ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ እየተጠባበቅ ከዙፋኑ ፊት ይቆማል። የዮሐንስ ወንጌል እንደሚለው እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ መንፈስ ቅዱስ ዕቅዳቸውን ተግባራዊ ያደርግ ዘንድ ወደ አማኞች ይልኩታል (ዮሐ 14፡26፤ 15፡26 አንብብ)።
ሐ) አራቱ እንስሶች፡ በሕዝቅኤል 1፡6–14 እንደተጠቀሱት ኪሩቤል፥ እነዚህ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የመፈጸም ኃላፊነት ያለባቸው ኃያላን መላእክትና የእግዚአብሔር አብ የቅድስና ጠባቂዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ፍጥረታት ዓይኖች የሞሉዋቸው መሆናቸው ተገልጾአል። ይህም እየሆነ ያለውን ሁሉ ለማየት የሚችሉ መሆናቸውን ያሳያል። ስድስት ክንፎቻቸው የእግዚአብሔርን ዕቅዶች በፍጥነት እንዲያከናውኑ ያስችሏቸዋል። እነዚህ እንስሳት እንደ አንበሳ፥ በሬ፥ ንሥርና ሰው ያሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የፍጥረትን ሥርዓት የሚገዙ ናቸው። አንበሳ የዱር አራዊት ንጉሥ ነው፥ በሬ የቤት እንስሳት ንጉሥ ነው፥ ንሥር የአእዋፍ ንጉሥ ነው፥ እንዲሁም ሰው የፍጥረት ሁሉ ንጉሥ ነው።
የዮሐንስ ራእይ ባለማቋረጥ ለእግዚአብሔር በሚቀርበው አምልኮ ላይ አጽንኦት ይሰጣል። ሕያዋን ፍጥረታት «ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ» እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። ምንም እንኳ እነዚህ ፍጥረታት ኃያላን ቢሆኑም፥ በታላቁ አምላክ ፊት ምንም እንዳልሆኑ ያውቃሉ። እርሱ ፍጹም ልዩና ቅዱስ በመሆኑ፥ በምድርም ሆነ በሰማይ ካሉት ማንኛውም ነገር ሊስተካከለው አይችልም። እነዚህም ፍጥረታት የእግዚአብሔርን ባሕርይ ያወድሳሉ። ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም አብረዋቸው ያመልካሉ። ሁሉም ራሱን ዝቅ አድርጎ በእግዚአብሔር አብ ፊት ይወድቃል። አክሊላቸውንም በዙፋኑ ፊት ያኖራሉ። እነዚህም አክሊሎች የተቀበሉት ምናልባትም ከእግዚአብሔር አብ በሽልማት መልክ ይሆናል። በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አክሊሎቹን መልሰው ማኖራቸው እርሱ ሁሉም የሚገባው አምላክ መሆኑን በመገንዘብ ነው። በመሆኑም የነገሮች ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን አምላክ ያመሰግናሉ።
የውይይት ጥያቄ፡- ከአራቱ እንሳሳትና ከሃያ አራቱ ሽማግሌዎች እግዚአብሔርን ስለ ማምለክ ምን እንማራለን?
፪. አንበሳና በግ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ (ራእይ 5)
የዮሐንስ ዓይኖች ወደ እግዚአብሔር አብ የኋሊት ተስበው በእጁ ላይ የመጽሐፍ ጥቅልል ተመለከተ። ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ጥቅልሎች የሚጻፉት በአንድ ወገን ብቻ ነበር። ይሄኛው ጥቅልል ግን ብዙ መልእክቶችን ስለያዘ ፊትና ጀርባው በጽሑፎች ተሞልተዋል። ይህ ጥቅልል ታሪክን በተምሳሌትነት የሚያሳይ ይመስላል። ጥቅልሉ እየተጻፈ አለመሆኑን ልብ በል። ቀደም ብሎ የተጻፈ ሲሆን፥ አሁን እየተገለጠ ነበር። እግዚአብሔር ቀድሞውኑ ታሪክን ወስኗል። ቀድሞውኑ ተጽፎአል።
የእግዚአብሔር ዕቅድ በኢየሱስ ክርስቶስ በመከፈቱ በውስጡ የተጻፈው ሁሉ ተፈጽሞአል። ጥቅልሉን ለመውሰድና ለመክፈት፥ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ዕቅዶች ከፍጻሜ ለማድረስ ሥልጣን ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። መላእክት መንፈስ ቅዱስ፥ ሰዎች፥ እንዲሁም ታላላቅ የዓለም መሪዎች ይህ ሥልጣን የላቸውም። ሥልጣኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
ክርስቶስ ለመግዛትና ለማሸነፍ ሥልጣን ባለው በኃይለኛ አንበሳ ተመስሎ እንመለከተዋለን። ዮሐንስ ግን ክርስቶስን የተመለከተው እንደ ታረደ በግ ሆኖ ነበር። ክርስቶስ ታሪክን እንዲቆጣጠር መብት የሰጠው ምንድን ነው? ይህን ሥልጣን ያገኘው የታላቅ አምላክ ልጅ ወይም የዳዊት ልጅ በመሆኑ ብቻ አይደለም። ይህን ሥልጣን ያገኘው ራሱን ዝቅ አድርጎ ለሰው ልጆች የሞተ በግ በመሆኑ ነው። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2፡5-11 የገለጸው፥ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ ስላደረገ፥ እንደ ባሪያ ሆኖ በመስቀል ላይ ስለ ሞተ፥ ከስሞች ሁሉ የበለጠ ስም ተሰጥቶታል። ፍጥረት ሁሉ በፊቱ እየሰገደ ክብርን ይሰጠዋል። ዮሐንስ ክርስቶስ በአራቱ እንስሳት መካከል መሆኑን ይናገራል። በሌላ አገላለጽ ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ሊሄድ የሚችለው እርሱ ብቻ ነበር። ምክንያቱም እርሱ አምላክ ነውና። ክርስቶስ ሰባት ቀንዶች እንዳሉት በተምሳሌታዊ መልኩ ተገልጾአል። ይህም ፍጹም ኃይልና ሥልጣን እንዳለው ያሳያል። ሰባት ዓይኖቹ ደግሞ ሁሉንም ነገር የማየትና የማወቅ ችሎታ እንዳለው ያሳያሉ።
የ«ኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች እግዚአብሔር አብና ወልድ አንድ ናቸው ብለው ያስተምራሉ። ነገር ግን የተለያዩ መሆናቸውን ከዚህ ራእይ ውስጥ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ክርስቶስ የመጽሐፉን ጥቅልል የ ተቀበለው ከእግዚአብሔር አብ እንጂ ከራሱ አይደለም። ነገር ግን ክርስቶስ ሌላ ፍጡር እንዳልሆነ ደግሞ ግልጽ ነው። እርሱ አምላክ ነው። ክርስቶስ ጥቅልሉን በተቀበለ ጊዜ በሰማይ አምልኮ ሲደረግለት እንመለከታለን። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን እንጂ ፍጥረታቱን ማምለክ እንደሌለብን በግልጽ ያስተምራል። ወልድን ማምለክ የጀመሩትን የተለያዩ የሕዝብ ቡድኖች ልብ ብለህ ተመልከት። ዮሐንስ እግዚአብሔር አብን ያመልኩ የነበሩ ቡድኖች ወልድንም ማምለካቸውን ይገልጻል።
ሀ) አራቱ እንስሶች።
ለ) የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጸሎት በተምሳሌትነት የሚወክለውን የዕጣን ጥና የያዙ ሃያ አራት ሽማግሌዎች። እነዚህ ሽማግሌዎች ክርስቶስ ለሰዎች ሁሉ በመሞት መንግሥት ስላደረጋቸውና እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ፥ እንዲሁም በምድር ላይ ለዘላለም የሚነግሡ ካህናት ስላደረጋቸው ያመሰግኑታል። ዮሐንስ በራእይ 19-20 ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽአትና መንገሥ የሚያቀርበው ገለጻ ይህንን የእግዚአብሔር ዕቅድ ፍጻሜ ያሳያል። የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች ከእርሱ ጋር አብረው ይነግሣሉ።
ሐ) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት፡ እነዚህ መላእክት ከአራቱ እንስሳት ውስጣዊ ክበብና ከሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ክበብ ቀጥሎ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ይቆማሉ። እነዚህ መላእክት ቀደም ሲል ለእግዚአብሔር አብ ባቀረቡት የምስጋና ቃላት ኢየሱስ ክርስቶስን ያመልኩታል። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆኑን ያሳያል።
መ) በሰማይም ሆነ በምድር፥ ከምድርም በታች ያሉ ፍጥረታት ሁሉ፡- የዮሐንስ ራእይ በሰማይ ተወስኖ ሳይቀር፥ ሰማይንና ምድርን በተመሳሳይ ጊዜ ይመለከታል። ይህም መላእክትን፥ ሰዎችንና ፍጥረታትን በሙሉ ያካትታል። እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር አብንና ወልድን ያመልካሉ።
ዮሐንስ በዚህ አስደናቂ ራእይ አማካኝነት ካስተላለፋቸው ትምህርቶች አንዱ ሁለት ወይም ሦስት አማኞች ወይም አነስተኛ ቤተ ክርስቲያን ወይም ትልቅ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ በምታካሂድበት ጊዜ ምን እንደሚከሰት ነው። በዓይናችን ባናይም በምድር ላይ በምናመልክበት ጊዜ በሰማይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የተዋቀረውን ታላቅ የአምልኮ ኳየር መቀላቀላችን ነው። ዮሐንስ በሚያሳየን መልኩ አምልኮአችንን መቅረጽ ይኖርብናል። አምልኮ እግዚአብሔር ለእኛ ባደረገልን ነገር ብቻ ማተኮር የለበትም። ነገር ግን ከሁሉም ንጹሕ የሆነው አምልኮ እግዚአብሔርን ለባሕርያቱ (ለማንነቱ) ማመስገን ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር አብን፥ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ልታመሰግን የምትችልባቸውን ቢያንስ ሃያ ባሕርያት ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር ያደረገልህን ቢያንስ ሃያ ነገሮች ዘርዝርና ስለ እነዚሁ ነገሮች አመስግነው። ሐ) እግዚአብሔርን ለእነዚህ ነገሮች በማመስገን አሥር ደቂቃዎችን አሳልፍ። ከሰማያዊ ኳየር፥ ማለትም ከአራቱ እንስሳት፥ ከሃያ አራቱ ሽማግሌዎች፥ ከመላእክትና ከተቀረው ፍጥረት ሁሉ ጋር በመሆን እግዚአብሔርን ስለ ታላቅነቱና ስለ ኃያልነቱ አመስግነው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)