እምነታችን እየደከመ ከሚሄድባቸው ምክንያቶች አንዱ ስለ ክርስቶስ ያለን ግንዛቤ እየደበዘዘ በመምጣቱ ነው። ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ምን ያህል ታላቅ ዋጋ እንደከፋፈለ እንዘነጋለን። የክርስቶስ መስቀል ብዙም የማያስደንቀን ልባችንን የማይሰብር ታሪክ ይሆንብናል። የክርስቶስን ታላቅነት፥ እውነታዎችን ሁሉ መቆጣጠር መቻሉንና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገኝቶ ሁሉንም ነገር ለማየት መቻሉን እንዘነጋለን። እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገኝቶ ደካማና ጠንካራ ጎኖቻችን ሁሉ እንደሚያይ እንረሳለን። ክርስቶስ ሁለት ወይም ሦስት አማኞች በስሙ በተሰበሰቡት ስፍራ በመካከላቸው እንደሚገኝ ቃል ገብቷል (ማቴ. 18፡20)። በራእይ 1፡3፥ ክርስቶስ ለአማኞች ይህንኑ እውነት ያስገነዝበናል። እርሱ በአብያተ ክርስቲያናት (መቅረዞች) መካከል እየተመላለሰ ባህሪያቸውንና ተግባራቸውን በቅርብ ይከታተላል። በመካከላቸው ያለውን ታላቅ ጌታ እንዳይዘነጉ ለማሳሰብ ክርስቶስ ታላቅነቱን ለዮሐንስና ለ7ቱ አብያተ ክርስቲያናት ያሳያል። ይኸው ክርስቶስ ዛሬም በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ እየተመላለሰ ነው። እርሱ ከእኛ ርቆ በሰማይ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን፥ አብሮን የሚኖር አምላክ ነው። ክርስቶስ በእኛ ውስጥ የሚያየው ምን ይሆን?
የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ስለ ክርስቶስ ማንነትና በመካከላችን እየተመላለሰ ስለመሆኑ የጠራ ግንዛቤ ቢኖረን፥ አምልኮአችንና ተግባራችን እንዴት እንደሚለወጥ ግለጽ። ለ) ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚመለከተው መልካም ነገር ምን ይመስልሃል? ሐ) ኢየሱስ ባንተ ሕይወት ውስጥ የሚያየው መጥፎና መልካም ነገር ምን ይመስልሃል? እንዲያሳይህ ለመጠየቅ አሁኑኑ ጊዜ ውሰድ።
፩. ለአብያተ ክርስቲያናት መልእክቱን ያስተላለፈው የክርስቶስ ራእይ (ራእይ 1፡9-20)
ይህ የክርስቶስ ራእይ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ለሚተላለፈው መልእክቱ መሠረት ነው። ዮሐንስ የዚህን ራእይ ክፍል ለሰባቱም አብያተ ክርስቲያናት ባስተላለፋቸው መልእክቶች ውስጥ ያካትታል (ራእይ 2-3)። በዚህ የክርስቶስ ራእይ ውስጥ ዮሐንስ በሰባቱ መቅረዞች መካከል የሚጓዘው ክርስቶስ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ያሳየናል። እነዚህም ሰባት መቅረዞች ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናት የሚያመለክቱ ናቸው። ክርስቶስ አማኞች መልእክቱን ቀለል አድርገው እንዲመለከቱ አልፈለገም። ምሁራን እያንዳንዱ የራእዩ ክፍል ምን እንደሚያሳይ በሚሰጡት ትንታኔ ይለያያሉ። ነገር ግን የተላላፈው መልእክት ግልጽ ነው። የምናመልከው ክርስቶስ አፍቃሪ እና የሚመች ብቻ አይደለም። እርሱ በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል የሚመላለስ፥ የሚመለከትና የሚገመግም፥ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናቱን ለማንጻት ፍርድን የሚሰጥ ታላቅና ፈራጅ አምላክ ነው። ከዚህ ራእይ ውስጥ አንዳንድ ቁልፍ ነገሮችን ልንመለከት እንችላለን:-
ሀ. ክርስቶስ የሰውን ልጅ እንደሚመስል ተገልጾአል። ዮሐንስ ክርስቶስ የዳንኤል 7፡13ን ራእይ እንደሚፈጽም ለአብያተ ክርስቲያናቱ ለማስገንዘብ ይፈልጋል። በዚህ ራእይ ውስጥ ታላቁ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ሥልጣን ከእግዚአብሔር አብ ሲቀበል እንመለከታለን (ዳን. 7፡13-14 አንብብ)።
ለ) ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትና ዳኛ ነው። የክርስቶስ ልብሶች በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናቱ ከሚለብሳቸው ጋር የሚመሳሰሉ ይመስላል። ስለዚህ አማኞች ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። በተጨማሪም ልብሱ የሮማውያን ዳኞች የሚለብሱትን ይመስላል። ይህም አማኞች ክርስቶስ ዳኛ መሆኑንና በፊቱ ቆመው መልስ እንደሚሰጡ ያስገነዝባቸዋል።
ሐ) ክርስቶስ ታላቅ አምላክ ነው። ዮሐንስ ከዳንኤልና ከሕዝቅኤል መጽሐፎች የወሰዳቸውን ተምሳሌቶች በመጠቀም ክርስቶስ ታላቅ፥ ኃያልና ቅዱስ አምላክ መሆኑን ያስረዳል። እንደ ፈራጅ፥ ቅዱስ ብርሃን የሚተፉ ዓይኖች አሉት፥ ጠላቶቹን የሚደመስስ ሰይፍም በእጁ ይዟል።
መ) ክርስቶስ ታሪክን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። እርሱ የሁሉም ነገር መጀመሪያ በመሆኑ፥ ታሪክ ሁሉ ሲጠናቀቅና ፍጥረት ሁሉ ሲጠፋ የመጨረሻው ሆኖ ይኖራል። በተጨማሪም እርሱ በሞትና በዘላለማዊ ፍርድ ላይ ሙሉ የበላይነት አለው። ስለሆነም አማኞች ሰውነታቸውን ሊገድሉ የሚችሉትን ሰዎች መፍራት አይኖርባቸውም። ነገር ግን እኛን ለመግደል የሚፈልጉትን ሰዎች መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን፥ ሰዎችን ወደ ሲዖል የመላክ ሥልጣን ያለውን ክርስቶስን መፍራት ይኖርብናል። ያለ እርሱ ፈቃድ ማንም የእግዚአብሔርን ልጆች ሊገድል አይችልም።
ሠ. ክርስቶስ በመቅረዞች (በአብያተ ክርስቲያናቱ) መካከል እየተመላለሰ ነው። እርሱ ከእኛ ርቆ በሰማይ የሚኖር ብቻ ሳይሆን፥ በመካከላችን ያለ አምላክ ነው። ሰባቱን ከዋክብት በእጁ የያዘው እርሱ ነው። እነዚህ ሰባት መላእክት ክርስቶስ በሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የሾማቸው መላእክት ይሁኑ ወይም በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኃላፊነት የሚያገለግሉ ሰባት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በትክክል የምናውቀው ነገር የለም። እነዚህ በክርስቶስ ቁጥጥር ሥር የሚሠሩ በመሆናቸው ለራሳቸው ጥቅም መኖር የለባቸውም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ ራእይ ውስጥ በመከራ ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ የሚያበረታቱ ምን ምን ቁልፍ እውነቶችን ትመለከታለህ? ለ) ከዚህ ራእይ ውስጥ ለአንተም ሆነ ለቤተ ክርስቲያንህ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ ቁልፍ እውነቶች ምን ምንድን ናቸው?
፪. ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩ መልእክቶች (ራእይ 2-3)
ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩት እያንዳንዳቸው መልእክቶች ተመሳሳይ ቅርጽ አላቸው።
ሀ) ደብዳቤው ለቤተ ክርስቲያን መላእክት በሚተላለፈው መልእክት ይጀምራል፡፡ ይህ ምናልባትም ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በኃላፊነት የሚያገለግለውን መሪ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ለ) ከራእይ 1፡13-18 ካለው ራእይ የተወሰደ የክርስቶስ ገለጻ ይከተላል። ይህም ገለጻ ክርስቶስ ለዚያች ቤተ ክርስቲያን ከሚሰጠው መልእክት ጋር የሚዛመድ ነው።
ሐ) ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመልካም ተግባሯ ያመሰግናታል። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እጅግ በደከመ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው፥ ክርስቶስ ስለ ምንም መልካም ነገር ሊያመሰግናቸው አልቻለም።
መ) ከዚያም ክርስቶስ፥ በምን እንዳሳዘኑት ይገልጻል። በጣም ድሆችና የተሰደዱ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ክርስቶስን እጅግ ደስ በማሰኘታቸው ከማንኛውም ተግሣጽ ነፃ ለመሆን ችለዋል።
ሠ) ክርስቶስ እርሱን ደስ ያሰኙና ከቅጣቱ ያመልጡ ዘንድ ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ይነግራቸዋል።
ረ) መልእክቱ ድልን ለሚነሣና ክርስቶስን በሚያስከብር ሕይወት ለሚመላለስ ሰው ክርስቶስ በሚገባው የተስፋ ቃል ይደመደማል።
(ማስታወሻ፡ እነዚህ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ያሉትን ምዕራፎች በተምሳሌትነት እንደሚያመለክቱ የሚናገሩ ምሁራን አሉ። ለምሳሌ ያህል፥ ኤፌሶን በዮሐንስ ዘመን የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ታመለክታለች ይላሉ። ሰምርኔስ በሁለተኛ እና በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ጠንካራ ስደት የተጋፈጠችውን ቤተ ክርስቲያን የምታመለከት መሆኗን ይናገራሉ። ጴርጋሞን ሐሰተኛ ትምህርትና ኃጢአት በነገሠበት የመካከለኛው ዘመን የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን የምታሳይ መሆኗን ያስረዳሉ። ሎዶቅያ ደግሞ ዛሬ በሃብትና በለብታ የምትታወቀውን ቤተ ክርስቲያን ታሳያለች ሲሉ ያስተምራሉ። ነገር ግን፥ እግዚአብሔር ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ባስተላለፈው መልእክት ሊነግራቸው የፈለገው ይህንን አይመስልም። በሁሉም የቤተ ክርስቲያን ታሪኮች የፍቅር ቅዝቃዜ፥ ስደት፥ ሐሰተኛ ትምህርት፥ ኃጢአትና ለብ ማለት የሚፈታተናቸው የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ስለሆነም በየትኞቹም አገሮች እና ዘመናት የሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩትን መልእክቶች ሊያነቡና ለራሳቸው የሚጠቅሙ ግላዊ መልእክቶች ሊያገኙ ይችላሉ።)
ሀ. ኤፌሶን፡ የመጀመሪያ ፍቅሯን ያጣች ትጉሕ ቤተ ክርስቲያን (ራእይ 2፡1-7)። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በእስያ ለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እናት ወይም ቁልፍ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ጳውሎስ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሁለት ዓመታት በላይ ያገለገለ ሲሆን፥ ዮሐንስም የጳጳስነት ወይም የሽምግልና አገልግሎቱን ለረጅም ጊዜ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አበርክቷል። ዮሐንስ በሮም ግዛት ውስጥ ባለችው የእስያ እውራጃ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ያስተባባሪነት ሥራውን የሚያከናውነው በኤፌሶን ውስጥ ተቀምጦ ነበር። በመሆኑም የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ለዮሐንስ እንደ ዋና ጽሕፈት ቤት ያገለግል ነበር። እንዲሁም ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መልእክት የሚያስተላልፈው ግለሰብ በፍጥሞ ደሴት ከነበረው ከዮሐንስ የተቀበላቸውን መልእክቶች መጀመሪያ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ያደርስ ነበር። ክርስቶስ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ብዙም አልነቀፋትም። ኤፌሶን ወንጌሉን ለማዳረስ የምትተጋ ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። አማኞቹ ከደረሰባቸው ስደት ባሻገር በእምነታቸው ጸንተው ቆመዋል። እንዲሁም ኤፌሶን የሐሰተኞችን ትምህርት ለመከተል ያልፈለገች ንጹሕ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። እነዚህ ሐሰተኞች ሐዋርያት ነን ይሉ ነበር። ኒቆላውያን እነማን እንደ ነበሩ በትክክል ለማወቅ አንችልም። እነዚህ ሰዎች አማኞች ነን እያሉ የእግዚአብሔርን ጸጋና ይቅርታ በማመሃኘት የተቀደሰ ሕይወት ላለመኖር የሚመርጡ ይመስላል። እነዚህ ሰዎች አማኞች በአካባቢያቸው እንዳሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስተምሩ ነበር። እነዚህም ማኅበረሰቦች ከቤተ መቅደስ ካህናት ጋር ወሲብ መፈጸም የሚታከልበትን ባህላዊ የጣዖት አምልኮ ይፈጽሙ ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ከዚህ ጠለቅ ብሎ የሚያሳስበውን ነገር ይመለከታል። ይኸውም ለእርሱ፥ ለእርስ በርሳቸውና ድነትን (ደኅንነትን) ላላገኙት ሰዎች የነበራቸው ፍቅር መቀዝቀዙ ነበር። ክርስቶስ ፍቅራቸው እየቀዘቀዘ በሚሄድበት ጊዜ መልካም ነገሮቻቸው ሁሉ እንደሚከስሙ ያውቅ ነበር። ይህም በጽኑ ስላሳሰበው ክርስቶስ ንስሐ እንዲገቡ፥ ካልሆነ ግን መጥቶ መቅረዛቸውን እንደሚወስድባቸው ያስጠነቅቃል። በሌላ አገላለጽ፥ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ይቀራል ማለት ነው። ሕንጻው ላይፈርስ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች እየመጡ ሊሰበሰቡ ይችላሉ። ነገር ግን መንፈሳዊ ሕይወት በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለማይኖር፥ በክርስቶስ ዓይን ቤተ ክርስቲያን ሊሆኑ አይችሉም። እርሱም በመካከላቸው አይመላለስም። ክርስቶስ ከዓለማዊ ልምምድ ለተመለሱ እና ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር ላደሱ ሰዎች በእግዚአብሔር ገነት ካለው የሕይወት ዛፍ ይበሉ ዘንድ እንደሚሰጣቸው ቃል ይገባላቸዋል። ዮሐንስ ወደ በኋላ ላይ መጀመሪያ በኤድን ገነት የነበረው ዛፍ በመንግሥተ ሰማይ እንደሚገኝ ያሳያል (ዘፍጥ. 2፡9፤ ራእይ 22፡2፥ 14)። ይህ ምናልባትም ለክርስቶስ ታማኞች ሆነው የተመላለሱት ሰዎች በመንግሥተ ሰማይ ለዘላላም የሚያገኙትን ኅብረት እና ዘላለማዊ ሕይወት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያንህን ከኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ጋር አነጻጽር። የሚመሳሰሉትና የሚለያዩት እንዴት ነው? ይህ ደብዳቤ ለቤተ ክርስቲያንህ ምን ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣታል? ለ) ክርስቶስ በፍቅራችን ባንጸና፥ መቅረዛችንን ከስፍራው በመውሰድ እንደሚፈርድብን ስለ ሰጠው ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ምን እንማራለን?
ለ. ሰምርኔስ፡ ደሀና የተሰደደች ቤተ ክርስቲያን (ራእይ 2፡8-11)። የሰምርኔስ ከተማ ከሮም ጋር ቅርበት የነበራት ውብ ከተማ ነበረች። የዚህች ከተማ ኗሪዎች ለሮም ንጉሥ ያላቸውን ታማኝነት ለመግለጽ ሲሉ ነገሥታትን በሚገባ ያመልኩ ነበር። ይህም በቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት አስነሣ አንዳንድ ምሁራን አብያተ ክርስቲያናት የሮም ሕግ በሚፈቅደው የምኩራብ አምልኮ ውስጥ በመሳተፍ ከስደት ለማምለጥ መሞከራቸውን ይናገራሉ። አይሁዶች ግን አማኞችን ከምኩራብ በማስወጣት መንግሥት እንዲያሳድዳቸው አደረጉ። እነዚህ አማኞች ቤታቸውን ስላጡ፥ ከሌሎች የመግዛትና የመሸጥ መብት ስላልነበራቸውና ምናልባትም ወደ ወኅኒ ቤት ስለወረዱ ሊሆን ይችላል ድሆች የሆኑት። ቤተ ክርስቲያኒቱ ለድህነት ተጋለጠች። ክርስቶስ ለዚች ቤተ ክርስቲያን የማበረታቻ ቃል ይልክላታል። እነዚህን ክርስቲያኖች ስለምንም ነገር አልገሠጻቸውም። እርሱ ፊተኛና ኋለኛ እንደ መሆኑ መጠን፥ የሮም መንግሥት ካለፈ በኋላም እንደሚኖር ገልጾላቸዋል። እንዲሁም ከሞት ውስጥ ሕይወትን የሚያፈልቅ እርሱ እንደሆነ በመግለጽ ሞትን እንዳይፈሩ አሳስቧቸዋል። ክርስቶስ ለእነዚህ አማኞች ያሉበትን ሁኔታ፥ ማለትም ድህነታቸውንና የእግዚአብሔር ሕዝብ ነን እያሉ የሰይጣን መሣሪያ ለመሆን በቻሉ አይሁዶች መሰደዳቸውን እንደሚያውቅ ገልጾላቸዋል። ክርስቶስ አማኞች ስደትን እንዳይፈሩ እና ለእምነታቸው መሞት ሲያስፈልጋቸው እንኳን በታማኝነት እንዲጸኑ ያሳስባቸዋል። ክርስቶስ ስደቱ የ10 ቀናት እድሜ ብቻ እንደሚኖረው ቃል ይገባላቸዋል። ምሁራን እነዚህ 10 ቀናት ምን እንደሚያመለክቱ ይከራከራሉ። የሚደርስባቸውን ስደት የሚቆጣጠረው ክርስቶስ የስደቱ ጊዜ እንደሚያጥር መናገሩን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። በስደት ጊዜ ታማኞች ሆነው ለሚጸኑ ሰዎች ክርስቶስ የሕይወትን አክሊል እንደሚሰጣቸው ቃል ይገባላቸዋል። ክርስቶስ ሰውነታቸውን የሚገድሉ ሰዎች ሊወስዱባቸው የማይችል ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚሰጣቸው ይናገራል። ከሚያሳድዷቸው እይሁዶች እና ሌሎች በተቃራኒ፥ አማኞች ወደ ሲዖል (ወደ ሁለተኛው ሞት) አይላኩም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስደትን ስለ መቀበል ከሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን የምንማራቸውን ጠቃሚ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) ደሀ እና የተሰደደች ቤተ ክርስቲያን እንዴት እግዚአብሔርን በሚያስከብር ሁኔታ ልትኖር እንደ ቻለች ግለጽ። ስደት ቤተ ክርስቲያንን ሊያነጻ የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ።
ሐ. ጴርጋሞን፡ ሐሰተኛ ትምህርትን እና ዓለማዊነትን የታገሰች ቤተ ክርስቲያን (ራእይ 2፡12-17)። የጴርጋሞን ከተማ ከሰምርኔስ በስተሰሜን 100 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ የምትገኝ ሲሆን፥ ምናልባትም ከዮሐንስ የተላከው መልእክተኛ የሚጎበኛት ሦስተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ሳትሆን አትቀርም። ጴርጋሞን የእስያ አውራጃ ርእሰ ከተማ ስትሆን፥ የዙስ ጣዖት የሚመለክበት ትልቅ ቤተ መቅደስ እና መሠዊያ ይገኝባት ነበር። በተጨማሪም፥ የንጉሥ አምልኮ ይፋዊ የነበረበት ማዕከል ነበረች። ከዚህ ጠንካራ ሐሰተኛ አምልኮ የተነሣ ክርስቶስ ከተማይቱ የሰይጣን ዙፋን የሚገኝባት እንደሆነች ገልጾአል። ክርስቶስ ራሱን ስለታምና በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ እንደያዘ አድርጎ ገልጾአል። ይህም ክርስቶስ ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን የሰላምን ቃል ሳይሆን ፍርድን ይዞ እንደሚመጣ ያሳያል። ክርስቶስ መልእክቱን የጀመረው የምሥጋና ቃል በማስተላለፍ ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ በስደት ጊዜ ክርስቶስን አልካደችም ነበር። ምንም እንኳን ከአባሎቻቸው አንዱ የሆነው አንቲጳስ ቢገደልም፥ በእምነቷ ለመጽናት በቅታለች። ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው፥ አንቲጳስ ከመጀመሪያዎቹ የእስያ ሰማዕታት አንዱ ነበር። የቤተ ክርስቲያን አፈ-ታሪክ እንደሚያወሳው ይህ ሰው እስከነ ሕይወቱ በበርሜል ውስጥ ተቀቅሎ እንዲሞት ተደርጓል። እንደ ክርስቶስ (ራእይ 1:5)፥ ይህ አማኝ የታመነ ምስክር ነበር። ሕይወቱን እስከ መስጠት ድረስ በእምነቱ ጸንቶ ቆሟል። ይሁንና በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ብዙ የተሳሳቱ ነገሮች ነበሩ። ልክ በለዓም ምድያማውያን ሴቶቻቸውን ወደ አይሁዳውያን በመላክ በወሲብ ኃጢአትና የጣዖት አምልኮ እንዲወድቁ እንዳደረገ ሁሉ፥ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላትን ወደ ጣዖት አምልኮ፥ የወሲብ ኃጢአትና ለጣኦታት ከሚሠዉ ሰዎች ጋር ኅብረት ወደ ማድረጉ ተግባር (ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ እንዲበሉ) እየመሩ የቅጣት እርምጃ ያልተወሰደባቸው ሰዎች ነበሩ። ኒቆላውያን አማኞች እምነታቸውን እንዲያለሳልሱ ያስተምሯቸውና ይመክሯቸው ዘንድ ትተዋቸው ነበር። ክርስቶስ እነዚህ ሰዎች ንስሐ ገብተው ኃጢአታቸውን መናዘዝ ብቻ ሳይሆን፥ አኗኗራቸውንም እንዲለውጡ ይነግራቸዋል። ይህ ካልሆነ እንደ ጦረኛ መጥቶ ይወጋቸዋል። ክርስቶስ ዓለምን ላልመሰሉ እና እምነታቸውን በንጽሕና ለጠበቁ አማኞች መናና ነጭ ድንጋይ እንደሚሰጥ ይናገራሉ። ምሁራን – የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምን እንደሆነ ይከራከራሉ። የተሰወረው መና በሰማይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግን ኅብረት የሚያመለክት ይመስላል (አብረን በመመገብ ደስ እንደምንሰኝ ሁሉ ማለት ነው)። ይህም እምነታቸውንና ሕይወታቸውን በንጽሕና የጠበቁት አማኞች ብቻ የሚያገኙት ዕድል ነው። በዮሐንስ ዘመን ነጭ ድንጋይ ለተለያዩ ነገሮች ሊያገለግል ይችላል። አንዳንዶች ነጭ ድንጋይ አንድ ሰው የቤተ መቅደስ ጋለሞቶችን ለመጎብኘት ወይንም በቤተ መቅደስ ውስጥ ለመመገብ በሚሄድበት ጊዜ የሚጠቀምበት እንደሆነ ያስባሉ። ክርስቶስ ግን እርሱ የሚሰጠን ነጭ ድንጋይ ወደ መንሥተ ሰማይ ለመግባትና በዚያም ሲጠባበቁን የነበሩትን በረከቶች እንድንቀበል የሚያስችለን በመሆኑ ታላቅ ዋጋ እንዳለው ይናገራል። አዲስ ስም አዲስ ግንኙነት መኖሩን ያመለክታል። አሁን ንጹሐን ሆነን ብንቆይ፥ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ልዩ ግንኙነት እያደረግን ደስ እንሰኛለን።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለቤተ ክርስቲያን ንጹሕ ሆኖ መቆየትና ዓለማዊ ልምምዶች እንዳይበርዛት መከላከል የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) ዓለማዊ አስተሳሰቦች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰርጸው ሲገቡ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) ክርስቶስ ይህ እንዲሆን ከፈቀድን ምን ዓይነት ቅጣት እንደሚጠብቀን ያስጠነቅቀናል? ክርስቶስ ስለዚህ እውነት ይህን ያህል የጠነከረ ቃል የሚናገረው ለምንድን ነው?
መ. ትያጥሮን፡ ሐሰተኛ አስተማሪዎችና ምግባራዊ ብልሹነት ያለባቸው ሰዎች በመሰላቸው እንዲኖሩ የፈቀዱ አማኞች (ራእይ 2፡18-19)። የትያጥሮን ከተማ በኢንዱስትሪዎች በተለይም ልብስን በማቅለም ችሎታዋ የታወቀች ነበረች። የተለያዩ ሙያዎች ያሏቸው ሰዎች በማኅበራት ይታቀፉ ነበር (ለምሳሌ፥ የአናጺዎች ማኅበር፥ የሸማኔዎች ማኅበር)። በእያንዳንዱ ማኅበር ላይ ደግሞ አንድ አምላክ ነበር። የማኅበሩ አባላት ይህንኑ አምላክ የማክበር ግዴታ ነበረባቸው። አንድ ሰው በከተማይቱ ውስጥ ለመግዛትና ለመሸጥ ቢፈልግ የዚህ ማኅበር አባል መሆን ያስፈልገው ነበር። ይህ ደግሞ ለጣዖቱ መሥዋዕት ማቅረብን ያጠቃልል ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አማኞች ይህን ለማድረግ እምነታቸው አይፈቅድላቸውም ነበር። ይህ የክርስቲያኖችን ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ ከተተው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ነብይቱ የተባለች ዝነኛ ሴት ነበረች። ዮሐንስ ግን ይህችን ሴት «ኤልዛቤል » ሲል ይጠራታል። ይህንንም ያደረገው ሴቲቱ የባዕድ አምልኮ ወደ እስራኤል እንዳመጣችው ንግሥት ኤልዛቤል ኃጢአተኛ መሆኗን ለማሳየት ነበር (1ኛ ነገ. 16፡31)። ይህቺ ሴት ለጣዖታት ባለመሠዋቷ ምክንያት ሥቃይን መቀበል ሲኖርባት፥ አማኞች እምነታቸውን በማመቻመች የዓለማውያንን አምልኮ እንዲካፈሉ፥ ለጣዖታት እንዲሠዉ፥ ለመሥዋዕትነት የመጣን ሥጋ አብረዋቸው እንዲበሉና እንዲሁም ወሲባዊ ኃጢአቶች እንዲፈጽሙ ታበረታታ ነበር። ይህቺ ሴት፥ «ክርስቶስን በልባችሁ እስካመለካችሁት ድረስ የሚጎዳችሁ ነገር አይኖርም» እያለች ትመክራቸው ነበር። ይህቺ ሴት የቅጣት እርምጃ እንዲወሰድባት ከማድረግ ይልቅ አማኞቹ ትምህርቷን ይታገሡ ነበር። በዚህ ምክንያት ይህ ትምህርት ወደ ሌሎች አማኞች ሊሰራጭ በቅቷል። እግዚአብሔር በሌላ የቤተ ክርስቲያን መሪ በኩል ያቺ ሴት ከኃጢአቷ ንስሐ እንድትገባ ያስጠነቀቃት ይመስላል። እርሷ ግን ፈቃደኛ አልሆነችም። አሁንም እግዚአብሔር በበሽታ እንደሚቀጣት ይናገራል። ከእርሷም ጋር የዝሙትን ኃጢአት የሚፈጽሙትን ሁሉ እንደሚቀጣ ያስታውቃል። ይህ ምናልባትም የወሲብ ኃጢአትን ሳይሆን ትምህርቱን የሚከተሉትን ወይንም ሊቀጧት ያልፈለጉትን አማኞች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። እነርሱም የእግዚአብሔር ቅጣት ይጠብቃቸው ይሆናል። ልጆቿ የተባሉት ምን አልባትም ተከታዮቿ ሊሆኑ ይችላሉ። ክርስቶስ እነዚህን ሰዎች እንደሚገድላቸው ይናገራል። ክርስቶስ አማኞች ትምህርቷን እንዳይከተሉ ያስጠነቅቃቸዋል። ይህንን ካደረጉ የቅጣቷ ተካፋዮች ይሆናሉ። እምነታቸውን ጠብቀው ለሚቆዩ ሰዎች ግን ከእርሱ ጋር በመንግሥቱ ውስጥ የመግዛት ዕድል እንደሚኖራቸው ቃል ይገባላቸዋል። እንዲሁም ክርስቶስ የንጋትን ኮከብ ይሰጣቸዋል። ይህ ምናልባትም የንጋት ኮከብ የሆነው ክርስቶስ ለመግዛት በሚመለስበት ጊዜ በክፉ ዓለምና ሞት ላይ ድልን እንደሚነሡ የሚያመለክት ይሆናል (ራእይ 22፡10)።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ዛሬ ለአማኞች ጠቃሚ ማስጠንቀቂያ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሐሰተኛ ትምህርቶች እየተሰራጩ መሪዎች እርምጃ የማይወስዱት እንዴት ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን፥ እንዲሁም ዓለማዊ አኗኗርን የሚከተሉትንና ክፉ ልምምዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገቡ የሚያደርጉትን ሰዎች እንዴት ልትቆጣጠር ትችላለች?
ሠ) ሰርዴስ፡ ሞተው ሳሉ በሕይወት አለን ብለው የሚያስቡ አማኞች (ራእይ 3፡1-6)። የሰርዴስ ከተማ በአንድ ወቅት ሀብታም የነበረች ስትሆን፥ የቀድሞው የሊዲያ መንግሥት ርእሰ ከተማ ነበርች። ከተማይቱ የተገነባችው በኮረብታ ላይ ሲሆን፥ በታላቅ ቅጥር የተከበበች ነበረች። ነዋሪዎቿ ማንም ይህችን ከተማ ሊወራት እንደማይችል ያስቡ ነበር። ነገር ግን ትዕቢታቸውና ልበ ሙሉነታቸው ለሽንፈት ዳረጋቸው። ከተማይቱ ቀስ በቀስ እየፈራረሰች የነበረች ቢሆንም እንኳ፥ እነርሱ ግን ስለ ቀድሞ ክብሯ እየተናገሩ ይታበዩ ነበር። የሚያሳዝነው ቤተ ክርስቲያኒቷም የእነርሱን ምሳሌነት መከተል ጀመረች። አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጤናማ እንደሆኑ በማሰብ በቀድሞ ታላቅነታቸው ይመኩ ጀመር። በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ግን ሙታን ነበሩ። ምክንያቱም ምግባረ ብልሹነት ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲገባ አድርገው ነበር። ክርስቶስ በአንድ ወቅት ታላቅ በነበረችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጥቂት ታማኞች እንደነበሩ ያውቅ ነበር። ስለሆነም እነዚህ አማኞች ሕይወታቸውን እንዲመረምሩና ንስሐ ገብተው ባሕርያቸውን እና ተግባራቸውን እንዲለውጡ ያስጠነቅቃቸዋል። ይህ ካልሆነ ግን ክርስቶስ እንደ ሌባ መጥቶ እንደሚፈርድባቸው ይናገራል። ይህም ከብዙ ዓመታት በፊት የፋርስ ሠራዊት ከተማቸውን ከደመሰሱበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰል ነበር። ክርስቶስ ታማኞችና ንጹሐን ሆነው የሚጸኑ አማኞች ግን ከእርሱ ጋር ነጭ ልብስ ለብሰው እንደሚሄዱ ይናገራል። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ነጭ ልብስ የዳኑትን፥ የተከበሩትን፥ እንዲሁም ከዓለም ቆሻሻና ክፋት ነፃ የወጡትን አማኞች ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች ከተማቸው ከሚታወቅበት አልባሳት የላቁ ሌሎች ልብሶችን ይጎናጸፋሉ። ስማቸውም ከሕይወት መጽሐፍ አይደመሰስም። በጥንት ዘመን የዜጎች ስሞች በትልቅ መጽሐፍ ውስጥ ይመዘገብ ነበር። ነገር ግን አንድ ሰው በራሱ ወይንም በሚኖርበት ከተማ ላይ አሳፋሪ ተግባር ከፈጸመ፥ የከተማይቱ መሪዎች የግለሰቡን ስም ይሰርዙ ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች ዓለምን በመምሰል የክርስቶስን ስም ካሰደቡ ስማቸውን ከመንግሥተ ሰማይ ዜጎች ስም ውስጥ እንደሚሰርዝ ያስጠነቅቃል። ንጹሐን ሆነው ካልኖሩ በሰማይ ክርስቶስ እውቅናን እንደማይሰጣቸው ይናገራል። እርሱ «ይህ ልጄ ነው የመንግሥተ ሰማይ አባል ነው» ሲል አይመሰክርም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ይህን መልእክት ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልጋት ለምንድን ነው? ለ) አንዳንድ አብያተ ክርስቲያን አሁን ካሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ ይልቅ በቀድሞ ክብራቸው ላይ ትኩረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
ረ. ፊልድልፍያ፡ በስደት የጸናች ቤተ ክርስቲያን (ራእይ 3፡7-13)። የፊልድልፍያ ከተማ በጠንካራ ግንብ የታጠረችና መልካም ኢንዱስትሪ የነበራት ሲሆን፥ ከተማይቱን አቋርጦ የሚያልፍ ጠቃሚ ጎዳና ነበር። ብዙውን ጊዜ ግን የመሬት መንቀጥቀጥ ይነሣባት ነበር። ከዚህም የተነሣ ብዙ ሰዎች ከከተማይቱ ውጭ ይኖሩ ነበር። ይህም የነዋሪዎቿን ቁጥር አመነመነው። ዮሐንስ ይህን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ የፊልድልፍያ ቤተ ክርስቲያን አሁንም ጥቂት ምእመናን ብቻ ነበሯት። ነገር ግን እግዚአብሔር የሕዝብን ብዛት እንደ ዋነኛ በረከት አይቆጥረውም። እርሱን በበለጠ የሚያሳስበው ታማኝነታችን ነው። የፊልድልፍያን ቤተ ክርስቲያን ከደረሰባት ስደት ባሻገር ለክርስቶስ ጸንታ የቆመች ነበረች። በመሆኑም ክርስቶስ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ተግሣጽ ሊሰነዝር አንመለከትም። ይልቁንም ክርስቶስ ማንም ሊዘጋው የማይችል የአገልግሎት በር እንደሚሰጣቸው ቃል ይገባል። በባለሥልጣናት ፊት የሚከራከሯቸው የማያምኑ አይሁዶች እንኳን ሊዘጉባቸው አይችሉም ነበር። ክርስቶስ አይሁዶችን “የሰይጣን ምኩራብ” ሲል ጠርቷቸዋል። ምክንያቱም የሰይጣን መሣሪያዎች ሆነው በአማኞች ላይ ስደትን ያመጡ ነበር። እንዲያውም፥ ክርስቶስ አንድ ቀን አይሁዶች ክርስቲያኖችን ለማክበር እንደሚገደዱ ይናገራል። ከብዙ አሥርተ ዓመት በኋላ፥ በአንድ ዝነኛ ሰባኪ ወይንም ነቢይ አገልግሎት ይህቺ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ደረጃ አደገች። እስልምና የአገሪቱን አካባቢ ከወረረ በኋላ ሳይቀር ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ለቀጣይ 500 ዓመታት በክርስቶስ ላይ ያላትን እምነት ለመያዝ በቅታለች።
ክርስቶስ በተጨማሪም ለዚህች ቤተ ክርስቲያን “ምድር ላይ የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከመከራው ሰዓት እጠብቅሃለሁ” የሚል የተስፋ ቃል ሰጥቷል። ክርስቶስ ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ምሁራን የተለያየ ሐሳብ ያቀርባሉ። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች የፈተናውን ሰዓት እንዳይጋፈጡ የሚጠብቃቸው መሆኑን ያሳያል። ሁለተኛ፥ በፈተናው ውስጥ ጉዳት ሳይደርስባቸው እንደሚያልፉ ቃል መግባቱ ነው። ክርስቲያኖች ይህን የተስፋ ቃል በሚተረጉሙበት መንገድ የተለያየ አቋም አላቸው። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ አማኞች ክርስቶስ ዮሐንስ ይህን መልእክት ከጻፈ በኋላ በሮም ግዛት ውስጥ በሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ ላይ ሊመጣ ስላለው የስደት ማዕበል መናገሩ ነው ይላሉ። ክርስቶስ የዚህች ቤተ ክርስቲያን አማኞች በእምነታቸው ምክንያት ከስደቱ እንደሚጠበቁ ቃል መግባቱ ነው ይላሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ክርስቲያኖች ይህ አማኞች በራእይ 6-19 ውስጥ ለተገለጠው ታላቁ መከራ መፈተን ሳይኖርባቸው ወደ ላይ የሚነጠቁ መሆናቸውን ያመለክታል ይላሉ። ይህ ጥቅስ ብቻ ክርስቲያኖች ከታላቁ መከራ በፊት የሚነጠቁ መሆናቸውን አያረጋግጥም። ክርስቶስ በታማኝነት ጸንቶ ለሚቆም ሰው አያሌ የተስፋ ቃሎችን ሰጥቷቸዋል።
ሀ) በአምላኬ መቅደስ አምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ። በፊልድልፍያ ብዙውን ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተነሥቶ ካለፈ በኋላ የሚቀሩት የቤተ መቅደስ አምዶች ብቻ ነበሩ። ስለሆነም ክርስቶስ በዘላለማዊ መንግሥቱ ውስጥ ታማኝ ክርስቲያኖች ማንም የማይወስድባቸውና ከቶውንም የማይነቃነቅ የክብር ስፍራ እንዳላቸው ቃል መግባቱ ይሆናል። ወይም ደግሞ አንዳንድ ሀብታም ሰዎች በቤተ መቅደስ አምድ ጨምረው ስማቸውን በዚያው አምድ ላይ ያሰፍሩና ታላቅነታቸውን ያሳዩ ነበሩ። ክርስቶስ ከስደት ሁሉ ባሻገር ለእርሱ ጸንተው የሚኖሩትን በሰማይ የተለየ ክብር እንደሚያገኙ መግለጹ ይሆናል።
ለ) ክርስቶስ የአብን፥ የአዲሲቱን ኢየሩሳሌምንና አዲስ ስሙን በግለሰቡ ላይ ይጽፋል። በመንግሥተ ሰማይ ታማኝ ሆኖ የሚጸና በእግዚአብሔር ፊት ይከበራል። የእግዚአብሔርና የኢየሩሳሌም ስም የሚጻፍበት መሆኑ ምናልባትም አማኙ የእግዚአብሔር ልዩ ንብረት ሆኖ የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ዜግነት እንደሚያገኝ የሚያመለክት ይሆናል። አዲሱ ስም አማኙ በመንግሥተ ሰማይ በእግዚአብሔር ፊት የሚኖረውን አዲስ ግንኙነት ሊያመለክት ይችላል። አማኞች በምድር ላይ ሊናቁ ቢችሉም፥ በሰማይ ላይ ግን ታማኞች ሆነው ከተገኙ በእግዚአብሔር ዘንድ ይከብራሉ።
የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ዛሬ ከእኛ ስለሚፈልገው ነገር ከፊልድልፍያ ቤተ ክርስቲያን ምን እንማራለን?
ሰ. በሎዶቅያ፡ ለመንፈሳዊ ነገሮች ግድ ያልነበራት (ለብ ያለች) ሀብታም ቤተ ክርስቲያን (ራእይ 3፡14-22)። የሎዶቅያ ከተማ በሀብቷ የታወቀች ነበረች። ባንኮች የተስፋፉባት፥ ልዩ ጥቁር የሱፍ ልብሶች የሚመረቱባት፥ እንዲሁም የታወቀ የሕክምና ትምህርት ቤት የሚገኝባት ከተማ ነበረች። ይህ የሕክምና ትምህርት ቤት በተለይ በዓይን ሕክምና ምርጥ መሆኑ ይነገራል። ችግሩ በከተማይቱ ውስጥ ጥሩ የውኃ አቅርቦት አልነበረም። ወደዚህች ከተማ ውኃ የሚመጣው ከስምንት ኪሎ ሜትሮች በላይ ተጉዞ ነበር። ውኃው ወደ ከተማይቱ በሚገባበት ጊዜ ለብ ስለሚል፥ ለመጠጥ አይመችም ነበር። የሎዶቅያ ነዋሪዎች ለነገሮች ብዙም ስሜት ያልነበራቸውና ሁልጊዜም የሌሎችን ፍላጎቶች ፍላጎታቸው ለማድረግ የሚጥሩ ነበሩ። በሀብታቸው ምክንያት የራስ ብቃት የነበራቸው ስለሆነም፥ ብዙውን ጊዜ ከተማይቱ በመሬት መንቀጥቀጥ በምትደመሰስበት ጊዜ የሌሎችን እርዳታ ሳይሹ ራሳቸው ይገነቧት ነበር። የሚያሳዝነው ይኸው የትዕቢት፥ በራስ የመመካትና የግዴለሽነት አመለካከት በቤተ ክርስቲያኗም ውስጥ ይታይ ነበር። አማኞቹ ክርስቶስን በሙሉ ልባቸው አይከተሉትም ነበር። እነዚህ አማኞች በቂ ገንዘብ ያላቸው በመሆናቸው የተሳካልን ነን ብለው ያስቡ ነበር። እግዚአብሔር በእኛ ደስ ባይሰኝ ኖሮ እንዴት ሀብታም ልንሆን እንችል ነበር? ብለው ያስቡ ነበር። ነገር ግን አማኛቹ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ምን እንደሚመስሉ አልተገነዘቡም ነበር። እግዚአብሔር ሲያያቸው ድሆች፥ የተራቆቱና ለመንፈሳዊ ዓይናቸው መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው ነበሩ። እግዚአብሔር እንዲረዳቸው፥ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያበለጽጋቸው፥ ጽድቁን እንዲያለብሳቸውና መንፈሳዊ እውነቶችን የሚመለከቱበትን ዓይን እንዲሰጣቸው ከፈለጉ፥ መለወጥ ያስፈልጋቸው ነበር። ራሳቸውን አዋርደውና የነበሩባቸውን ችግሮች ተረድተው እግዚአብሔር ጽድቅን፥ መንፈሳዊ ዓይኖችንና መንፈሳዊ ጤንነትን እንዲሰጣቸው መጠየቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቶስ በልባቸው እና በቤተ ክርስቲያናቸው ደጅ ላይ ቆሞ ነበር። ወደ ውስጥ ገብቶ ከእነርሱ ጋር ኅብረት ለማድረግ ይፈልጋል። ነገር ግን ችግራቸውን ተረድተው በራቸውን መክፈትና እርሱን ወደ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋቸው ነበር። ይህን ካላደረጉ፥ ክርስቶስ በፍርድ ከአፉ እንደሚተፋቸው ያስጠነቅቃቸዋል። ይህም በከተማቸው ውስጥ የሚገኘውን ውኃ ከቀመሱ በኋላ ከሚተፉበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነበር። ንስሐ ገብተው ከክርስቶስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና ኅብረት፥ ካደሱ፥ ክርስቶስ በዘላለማዊ መንግሥቱ ውስጥ የመግዛትን መብት እንደሚሰጣቸው ቃል ይገባላቸዋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሀብታሞች ለሰው ወይም ለቤተ ክርስቲያን የትዕቢትንና በራስ የመመካትን ባሕሪ ሲያሳዩ የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) ለትዕቢተኞች ክርስቶስና ከእርሱ ጋር የሚደረግ ኅብረት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን መረዳት ከባድ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን የተላለፈው መልእክት ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያናችን የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)