Site icon

ሰባት የመለከት ፍርዶች (ራእይ 8፡2-11፡19)

ሰባቱ የማኅተም ፍርዶች የመጨረሻውን ዘመን ባሕርያት የሚገልጹ ሲሆን፥ ሰባቱ የመለከት ፍርዶች እና ሰባቱ የጽዋ ፍርዶች ክርስቶስ ሊመለስ ሲል ስለሚሆኑት ሁኔታዎች ዝርዝር ማብራሪያ ያቀርባሉ። በራእይ 6፡9-11፥ ሰማዕት አማኞች፥ እግዚአብሔር በገደሏቸው ሰዎች ላይ ፍትሕንና በቀልን መቼ እንደሚያመጣ ሲጠይቁ እንመለከታለን። አሁን በቅዱሳን ጸሎት ምክንያት በሚገለጹት ሰባት የመለከት ፍርዶች አማካኝነት እግዚአብሔር በኃጢአተኞች ላይ ፍትሕንና በቀልን ሲገልጽ እንመለከታለን። እግዚአብሔር በፍርድ ለሰው ልጅ የሰጣቸውን የተፈጥሮ ስጦታዎች መልሶ መውሰድ ይጀምራል። ሰዎች ለእነዚህ ስጦታዎች እግዚአብሔርን አላመሰገኑም ነበር። እንዲሁም እግዚአብሔር ቀደም ሲል ገድቦ የያዘውን የሰይጣን ኃይል በመልቀቅ ሰይጣን በምድር ላይ ባሉት ኃጢአተኞች ላይ ሥቃይን እንዲያበዛ ያደርጋል። ከእነዚህ ፍርዶች አብዛኞቹ እግዚአብሔር በሙሴ ዘመን በግብጽ ላይ ያወረዳቸውን መቅሰፍቶች የሚመስሉና ነገር ግን ከዚያ የከበዱ ናቸው። ዮሐንስ ስለ ሰባት የመላከት ፍርዶች በሚያቀርበው ገለጻ በተለይ በስድስተኛውና አምስተኛው መለከቶች ላይ ትኩረት ያደርጋል። 

ሀ) የመጀመሪያው መለከት፡ እግዚአብሔር የምድርን አንድ ሦስተኛ (ሲሶ) በእሳት ያጠፋል። ይህም ዛፎችንና ሣርን የሚያጠቃልል ሲሆን፥ ሰዎች እህል ዘርተው የሚበሉበትን ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ምሁራን ይህ ሲሶ የተባለው አሃዝ ቀጥተኛ ወይም ተምሳሌታዊ በመሆኑ ላይ ይከራከራሉ። በይበልጥ ግን ዮሐንስ አብዛኛው የመሬት ክፍል ሰብል የማምረትና አትክልቶችን የማብቀል አቅም እንደሚያጥረው የገለጸ ይመስላል። ብዙዎች ይህ ራእይ ምንን እንደሚያመለክት የተለያዩ አሳቦችን ያቀርባሉ። ይህ የምድርን አብዛኛውን ክፍል የሚያጠፋ መለኮታዊ ፍርድ ይሆን? ወይስ እንደ አካባቢያዊ ብክለት ወይም የኒኩለር ጦርነት ያለ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር የሚከናወን የሰው ልጅ የተግባር ውጤት ይሆን? ይህ ምንን እንደሚያመለክት በትክክል ባናውቅም፥ መልእክቱ ግልጽ ነው። እህልን የሚያበቅል ሰፊ መሬት በማይኖርበት ወቅት እግዚአብሔር ለብዙ ሰዎች ሕይወትን አስቸጋሪ እንደሚያደርግ እንመለከታለን።

ለ) ሁለተኛው መለከት፡ እግዚአብሔር የባህርን ሲሶ በባህር ውስጥ የተለያዩ ነገሮች የሚሸከሙትን መርከቦች ሲሶ፥ እንዲሁም በባህር ውስጥ የሚገኙትን ነገሮች ሲሶ ያጠፋል። በአብዛኞቹ ደሴቶችና በባህር ዳርቻዎች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምግባቸውን የሚያገኙት ከባህር ነው። በተጨማሪም የብዙ አገሮች ኢኮኖሚ ከአንድ አገር ወደ ሌላው አገር ምርቶችንና ቁሳቁሶችን በሚያጓጉዙ መርከቦች ላይ የተመሠረተ ነው። ስለሆነም፥ ይህ ፍርድ የብዙ አገሮችን የምግብ ፍጆታና ኢኮኖሚ ይጎዳል።

ሐ) ሦስተኛው መለከት፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ ለመጠጥነት ከሚያገለግለው ውኃ ሲሶውን ያጠፋዋል። ሬቶ የተባለው ኮከብ እንደ ስሙ መራራ ነው። ይህ ኮከብ መርዛማ ባይሆንም፥ የአንድን ነገር ጣእም በከፍተኛ ደረጃ ይለውጣል። እግዚአብሔር የሰውና የእንስሳት ሕይወት የተመሠረተበትን ውኃ ያስወግዳል። ወይም አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት፥ ይህ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚያመጣው ፍርድ የተነሣ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚደርሰውን ምሬት የሚያሳይ ነው።

መ) አራተኛው መለከት፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ ብርሃን የሚያመጡትን ነገሮች ያጠፋል። የፀሐይ፥ የጨረቃና የከዋክብት ሲሶ ብርሃኑን ያጣል። ይህ በምድር ላይ ብርሃን የሚታይበት ጊዜ እንደሚቀንስና የጨለማው ሰዓት እንደሚጨምር የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ሠ) አምስተኛው መለከት (ዋይታ )። ይኼኛውና ቀጣዩ ፍርድ በጣም የጠነከሩ በመሆናቸው፥ ሁለቱም የዋይታ ፍርዶች በመባል ይታወቃሉ። ይህ ራእይ ሰይጣንና አጋንንቱ ምድርን ለማጥፋት ተጨማሪ ኃይል ማግኘታቸውን ያሳያል። ከሰማይ የወደቀው መላእክት አብዶን ወይም አጶሊዎን የሚባለው (ትርጉሙ አጥፊ) ሰይጣን ሳይሆን አይቀርም። እግዚአብሔር አሁን ጥልቁን ጉድጓድ እንዲከፍት ሥልጣን ይሰጠዋል። ይህም እስከዚህ ጊዜ ድረስ እግዚአብሔር ብዙ አጋንንትን አስሮ ያቆየበት ስፍራ ነው። እነዚህ አጋንንት በምድር ዙሪያ በመዟዟር የእግዚአብሔር ማኅተም የሌለበትን ሰው ሁሉ እንዲያሠቃዩ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። በመሆኑም አማኞችን የመግደል ሳይሆን የማሠቃየት ሥልጣን አላቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ራእይ እግዚአብሔር፥ በሰይጣንና በአማኞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት የሚያግዘው እንዴት ነው? ለ) ይህ ብዙ ሰዎች ስለ ሰይጣን አሠራር ከሚያውቁት የሚለየው እንዴት ነው?

በዚህ ፍርድ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ እውነት እንመለከታለን። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ሰይጣንን በመቆጣጠር ላይ ነው። እርሱ ሰይጣን የትና እንዴት ሊሠራ እንደሚገባ ዳርቻውን ይወስንለታል። ከእግዚአብሔር ፈቃድ እስካላገኘ ድረስ ሰይጣን በሕይወታቸው ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ያለባቸውን አማኞች ሊነካ አይችልም። ሊፈትነን ቢችልም፥ የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን እግዚአብሔር ካላጸደቃቸው ከማናቸውም ጥቃቶች የተጠበቅን ነን።

ረ) ስድስተኛው መለከት (ዋይታ 2)፡ በእግዚአብሔር ትእዛዝ አራት መላእክት ከኤፍራጥስ ወንዝ ይለቀቃሉ። በእነዚህ መላእክትና ሁለት መቶ ሚሊዮን ፈረሶችና ጋላቢዎች ባሉበት ሠራዊታቸው አማካኝነት የሰዎች ሲሶ ይገደላል። እነዚህ ታላቅ ሠራዊት ማንን እንደሚያመለክቱ ምሁራን በሚሰጡት ትንታኔ ይለያያሉ። አንዳንዶች ሰዎችን ማሠቃየት ብቻ ሳይሆን የመግደልም ሥልጣን የተሰጣቸው የአጋንንት ሠራዊት ናቸው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ ታላቅ የዓለም ጦርነት የተገለጸበት ክፍል ነው ሲሉ ያስተምራሉ። ይህን አመለካከት የሚከተሉ ሰዎች የእስያ በተለይም የቻይና ሠራዊት የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚመጣ ይናገራሉ። እሳት፥ ጭስና ድኝ፥ የቦንቦችና የታንኮች ወይም የኑክሌር ጦርነት ውጤቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም ታላቅ ጦርነት የሰዎችን ሲሶ (ወይም አብዛኛውን ሕዝብ) ይጨርሳል። እነዚህ ፈረሶችና በፈረሶቹ ላይ የተቀመጡት እነማን እንደሆኑ ላናውቅ ብንችልም፥ ውጤቱ ግን በግልጽ የሚታይ ነው። እግዚአብሔር ሰይጣንን ስላላስቆመው፥ ሞት ዓለምን ይሸፍናል። ከአምስተኛው የመለከት ፍርድ በተቃራኒ፥ እግዚአብሔር አማኞችን ከሞት እንደሚታደግ የሚያመለክት ነገር አይገለጽም።

በዚህ ክፍል ዮሐንስ ስለ መናፍስት ዓለም አንዳንድ አስገራሚ ነገሮችን ያስተምራል። ከእግዚአብሔር ታላላቅ ምሕረቶች አንዱ ሰይጣንና አጋንንት የሚፈልጉትን ክፋት ሁሉ እንዳይፈጽሙ መገደቡ ነው። ሰይጣንና አጋንንቱ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው (ዮሐ. 8፡44)፡፡ ለመጉዳት፥ ለመግደልና ለማጥፋት ይፈልጋሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚፈልጉትን ሁሉ እንዲያደርጉ አይፈቅድላቸውም። ኃይላቸውን ይገድበዋል። ነገር ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር ከሰይጣን ላይ የቁጥጥር እጁን በማንሣት ሰዎች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲሠቃዩና በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ለሞት እንዲጋለጡ ያደርጋል።

በአንድ በኩል እነዚህ የመለከት ፍርዶች እግዚአብሔር በሰዎች አለማመንና ኃጢአት ላይ ያመጣቸው ፍርዶች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ የእግዚአብሔር የምሕረቱ ምልክቶች ናቸው። ሰዎች በዐመፀኛነታቸው ሳይቀጥሉ ወደ እርሱ ተመልሰው ምሕረቱንና ይቅርታውን እንዲቀበሉ ለማበረታታት ፍርዱን በመሣሪያነት ይጠቀማል። የሚያሳዝነው ግን ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ከመመለስ ይልቅ በዐመፃቸውና በክፉ ሥራቸው ይቀጥላሉ። የተሳሳተው አምልኳቸው በአጋንንት ቁጥጥር ሥር የሚካሄድ ነው። እንዲሁም ስርቆት፥ ግድያና ወሲባዊ ኃጢአቶች ይፈጽማሉ። በአንድ አገር ላይ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ይህንኑ አደጋ የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር በዚሁ አደገኛ ሁኔታ (ለምሳሌ፥ ጦርነት፥ ረሀብ፥ ኤድስ) አማካኝነት ለመፈጸም ከሚፈልጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ ሕዝቡ ወደ ምሕረቱ እንዲመለስ፥ ይህ ካልሆነ ግን ወደፊት ከዚህ የከፋ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ለማስገንዘብ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተከሰተ አንድ አደጋ ግለጽ። እግዚአብሔር በዚህ አደጋ አማካኝነት ለሕዝቡ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምን ይመስልሃል? ለ) ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው በዐመፀኝነታቸው የሚገፉት ለምን ይመስልሃል? ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ኃይል፥ ተቆጣጣሪነትና ምሕረት ምን ያስተምሩናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version