Site icon

የእረፍት ጊዜ (ራእይ 10፡1-11፡14) እና የሰባተኛው መለከት ፍርድ (ዋይታ 3) ራእይ 11፡15-19

ከበደ ተወልዶ ያደገው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነው። ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት ጀርባውን ለክርስቶስ ሰጥቶ እንደ እግዚአብሔር ሕጎች ላለመመላለስ ወሰነ። የዐመፀኝነት መንፈሱን ካሳየባቸው መንገዶች መካካል አንዱ ወሲባዊ ኃጢአቶችን መፈጸም ነበር። በትምህርት ቤት ከተለያዩ ሴት ተማሪዎች ጋር ያመነዝር ነበር። ገንዘብ ሲኖረው ደግሞ ወደ ሴተኛ አዳሪዎች ጎራ ማለቱን ተያያዘው። ብዙውን ጊዜ ይህ ባህሪው የጨብጥ በሽታ ያስከትልበት ነበር። ይህም ከተግባሩ እንዲታቀብ እግዚአብሔር ያስተላለፈለት ማስጠንቀቂያ ነበር። እርሱ ግን የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ ለመስማት አልፈለገም። ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ከበደ የበሽታ ምልክቶች ይታዩበት ጀመር። መድኃኒት ሲወስድ ትንሽ ይቀልለዋል። ወዲያውኑ ደግሞ ይነሣበታል። ክብደትም መቀነስ ጀመረ። አንድ ጊዜ ሐኪም ቤት ሄዶ ሲመረመር የኤድስ ቫይረስ በደሙ ውስጥ እንዳለበትና በቅርብ ጊዜ እንደሚሞት ተነገረው። አሁንም እግዚአብሔር ለከበደ ስለፈጸማቸው ተግባራት ማስጠንቀቂያ በመስጠት ንስሐ የሚገባበትን ዕድል ሰጠው። እርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር እንደ መመለስ የቁጣ ስሜት አደረበት። በእግዚአብሔር ላይ ስለ ተቆጣ ንስሐ ለመግባት አልፈለገም። እንዲሁም አኗኗሩን ለመለወጥ አልፈለገም። ይባስ ብሎ ከሌሎች ሰዎች ጋር ወሲባዊ ግንኙነቶችን በመፈጸም ይህንኑ መድኃኒት የሌለው በሽታ ወደ ተለያዩ ሴቶች ማስተላለፉን ተያያዘው። ከእርሱ ጋር የተኙት ሴቶች ደግሞ የበሽታውን ቫይረስ ለሌሎች ወንዶች ማስተላለፍ ጀመሩ። ከበደ እግዚአብሔር የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለመስማት ቸል ብሎ ሕይወቱን አጥቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ሰዎችን አለማመናቸውና ዐመፀኝነታቸው ስለሚያስከትሉባቸው ውጤቶች የሚያስጠነቅቅባቸውን ሌሎች መንገዶች ግላጽ። ለ) ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ንስሐ የማይገቡት ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ሰዎችን ለማስጠንቀቅ አደጋን በመጠቀሙ ስለ ባሕሪው ምን እንማራለን? መ) አደጋ በሚመጣበት ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ካለመፈለጋቸው ስለ ሰዎች ልብ ምን እንማራለን?

ከዮሐንስ ራእይ አብዛኛው ክፍል እግዚአብሔር በተለይም በመጨረሻው ዘመን ወደ ምድር በሚልካቸው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ፍርዶች ላይ አጽንኦት ይሰጣል። እነዚህ አደጋዎች ሰዎችን ለመቅጣት የታሰቡ ናቸው። እንዲሁም አደጋዎቹ ሰዎች ንስሐ ባይገቡ ዘላለማዊ ሞት እንደሚጠብቃቸው ለማስጠንቀቅ የታሰቡ ናቸው። እግዚአብሔር በምሕረቱ ሁልጊዜም ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ እንጂ እንዲሞቱ አይፈልግም (ሕዝ. 18፡21-23 አንብብ)። ነገር ግን የሰዎች ልብ እጅግ ክፉ ከመሆኑ የተነሣ ብዙ ሰዎች አደጋ በሚመጣበት ወቅት ወደ እግዚአብሔር አይመለሱም (ኤር 17፡9)። ነገር ግን ያለ እግዚአብሔር እርዳታ አደጋውን ለማሸነፍና በዐመፀኛነታቸው መንገዳቸው ለመቀጠል ይፈልጋሉ። ሞት በሚመጣበት ጊዜ ንስሐ የምንገባበትን ዕድል እናጣለን። ከዚህ በኋላ የሚጠብቀን ዘላለማዊ ሞትና ሲዖል ይሆናል። ሰዎች ሥራቸው ስለሚያስከትሏቸው ውጤቶች ልናስጠነቅቃቸው አይገባምን? ከዚህ ታላቅ መከራ ለማምለጥ ብቸኛ መንገድ ስለሆነው ክርስቶስ ለሰዎች ልንነግራቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 10–11 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ለዮሐንስ የሰጠው የመጽሐፍ ጥቅልሉ ጠቀሜታ ምንድን ነው? ለ) ስለ ሁለቱ ምስክሮችና በእነርሱ ላይ ስለተፈጸመው ሁኔታ ግለጽ።

፩. የእረፍት ጊዜ (ራእይ 10፡1-11፡14)  

በብዙ መንገዶች የዮሐንስ ራእይ የሠርግ ፎቶ ይመስላል። በአንድ ሰው ሠርግ ላይ ካልተገኘህ፥ በዚያን ጊዜ የተነሣቸው ፎቶግራፎች ስለ ሠርጉ ብዙ መረጃዎችን ይሰጡሃል። ነገር ግን የክስተቶቹን ቅደም ተከተል አያሳዩህም። የዮሐንስ ራእይ በተለይም መካከለኛው ክፍል (ራእይ 10-18)፣ በመጨረሻው ዘመን ታላላቅ ሚናዎች የሚጫወቱትን ሰዎች የሚገልጽ ይመስላል። ነገር ግን ራእዮቹ የድርጊቶቹን ቅደም ተከተል አያሳዩንም።

ዮሐንስ አሁንም ገለጻውን አቋርጦ የተለያዩ ነገሮችን ይመለከታል። ይህንንም ያደረገው ስለ መጨረሻው ዘመን የተሻለ ግንዛቤ ሊሰጠን ስለፈለገ ነው።

ሀ) መልአኩና ትንሿ መጽሐፍ (ራእይ 10)። በመጀመሪያ የተገለጸው ለዮሐንስ ትንሿን መጽሐፍ እንዲበላት የሰጠው መልአክ ነው። ይህ ዮሐንስ በእስትንፋሰ እግዚአብሔር ከተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለውን ግንኙነት ያመለክታል። በተጨማሪም፥ ዛሬ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለንን ግንኙነት ያሳያል። ዮሐንስ ወደ ምድር የተመለሰ ሲሆን፥ ወዲያውኑ አንድ ታላቅ መላእክ ከሰማይ ሲወርድ ያየዋል። መልአኩ በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለው ለማሳየት በባህርና በመሬት ላይ ይቆማል። በእጁ ትንሽ መጽሐፍ ይዟል። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ከወሰዳት መጽሐፍ በተቃራኒ፥ ይህቺኛዋ መጽሐፍ በመጠን አነስ ያለች ስትሆን፥ በጽሑፍ መሞላቷም አልተገለጸም። ይህም እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ከሚፈጸመው ተግባር ጥቂቱን ብቻ እንደገለጸልን ያሳያል። የተገለጸልን ግን የእግዚአብሔርን እውነት፥ የድነት (ደኅንነትን) መንገድ፥ እንዲሁም በመጨረሻው ዘመን ምን እንደሚከሰት ለመገንዘብ በቂያችን ነው።

መልአኩ ለዮሐንስ ትንሿን መጽሐፍ ከመስጠቱ በፊት በታላቅ ድምጽ ይጮሃል። በዚህም ጊዜ ሰባት ነጎድጓዶች ምላሽ ይሰጣሉ። ዮሐንስ እነዚያ ሰባት ነጎድጓዶች በፍርድ የተናገሩትን ሊጽፍልን ፈልጎ ሳለ መልአኩ ግን እንዳይጽፍ ከልክሎታል። ይህ ራእይ እግዚአብሔር በታሪክና በመጨረሻው ዘመን ስለሚፈጸመው ነገር ጥቂቱን ብቻ እንደገለጸልን ያሳያል። የሚከሰተውና የሚከሰትበትም ምክንያት በአብዛኛው በእግዚአብሔር ምሥጢራት ውስጥ የተደበቀ ነው። ይህም ለሰው ልጆች ያልተገለጸ መሆኑን እንመለከታለን። በታሪክ የመጨረሻዎቹ ቀናት የሚከሰተው ነገር አልተገለጸም። ነገር ግን እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንደሚቆጣጠር ለማወቅ የሚያስችል በቂ መረጃ ተሰጥቶናል። መጪዎቹ ጊዜያት ክፉዎችና አስቸጋሪዎች ቢሆኑም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ (ሰዎችም ሆኑ ሰይጣን) ያሽንፋል።

ዮሐንስ የበላት ትንጂ መጽሐፍ እግዚአብሔር ለዮሐንስና በእርሱም በኩል ለእኛ የሰጠንን መለኮታዊ ቃል በተምሳሌትነት ታሳያለች። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የዮሐንስ ራእይ ተጠቃልሎ እንመለከታለን። መለኮታዊው ትንቢት ኃጢአተኛ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት ኅብረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስለሚናገር፥ ጣፋጭ ነው። እንዲሁም የኢየሱስን ዘላለማዊ መንግሥትን ክብር ይገልጻል። ይህም ብቻ አይደለም። ለማመን በማይፈልጉ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር የሚያመጣቸውን ፍርዶች ስለሚገልጽ መራራም ነው። ዛሬ ጣፋጩም ሆነ መራራው የእግዚአብሔር ቃል ለሰዎች ሁሉ መነገር አለበት። ዳቦ በምንበላበት ጊዜ በሰውነታችን ሁሉ ተሰራጭቶ ይገነባናል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ መልአኩ ዮሐንስ ትንሿን መጽሐፍ እንዲበላት ነግሮታል። ይህም የእግዚአብሔርን ቃል ለሌሎቹ ከማጋራታችን በፊት በማጥናት፥ በማሰላሰልና በመታዘዝ የሕይወታችን አካል ልናደርገው እንደሚገባ ያሳያል። ብዙ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከሕይወታቸው ጋር ሳያገናዝቡ ለምእመናን ያስተላልፋሉ። የቤተ ክርስቲያን አባላት ይህንን ግብዝነት በሚመለከቱበት ጊዜ ለአገልጋዮቻቸው አክብሮት ማጣት ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ሳይሆን የእነዚህኑ መሪዎች ምሳሌነት ይከተላሉ። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔር ቃል በተለይም የዮሐንስ ራእይ እንዴት ጣፋጭም መራራም ሊሆን እንደቻለ ግለጽ። ለ) ዮሐንስ መጽሐፉን በተቀበለ ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ እኛስ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ባለን ግንኙነት ምን ልናደርግ ይገባል? ሐ) ሰባኪዎችና አስተማሪዎች መጀመሪያ ከራሳቸው ሕይወት ጋር ሳይዋሃዱ የእግዚአብሔርን እውነት ለሰዎች ሲያስተላልፉ የተመለከትከው እንዴት ነው? ይህ በግላሰቡና በቤተ ከርስቲያን ላይ የሚያስከትለው አደጋ ምንድን ነው?

ለ) ሁለቱ ምስክሮች (ራእይ 11፡1-14)። ሁለተኛዎቹ ምድቦች ሁለት ምስክሮች ናቸው። ይህ በራእይ ውስጥ ለመተርጎም እጅግ ከሚያስቸግሩ ምንባቦች አንዱ ነው። በዚህ ምንባብ ላይ የምሁራኑ አስተሳሰብ በሁለት ዐበይት ቡድኖች የተከፈለ ነው። በመጀመሪያ፥ አንዳንዶች ይህ ትንቢት በታላቁ መከራ ጊዜ በእስራኤል ላይ የሚከሰተውን ሁኔታ ለመግለጽ በሚያስችል መልኩ በቀጥታ መተርጎም አለበት ይላሉ። እነዚህ ምሁራን በመጨረሻው ዘመን አይሁዶች ቤተ መቅደላቸውን እንደገና ገንብተው እዚያው ውስጥ እንደሚያመልኩ ይናገራሉ። ከዚያ በኋላ ግን ሐሳዊው መሢሕ ተነሥቶ ከአይሁዶች እግዚአብሔርን እንዳያመልኩ ይከለክላቸዋል። ብዙ አይሁዶችንም ይገድላል። ነገር ግን እግዚአብሔር ታማኝ አይሁዶች ሙሉ በሙሉ በሐሳዊ መሢሕ እንዳይደመሰሱ ይጠብቃቸዋል። እንዲሁም እግዚአብሔር ሁለት አይሁዶችን መርጦ ቃሉን እንዲናገሩና እንዲመሰክሩ ኃይልን ይሰጣቸዋል። ሁለተኛ፥ ራእዩ ቤተ ክርስቲያንን በተምሳሌትነት የሚያቀርብ ነው የሚሉ ምሁራን አሉ። እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የመመስከርና ሰዎችን የማስጠንቀቅ (ወንጌልን በመስበክ) ኃላፊነት እንደ ሰጣት ይገልጻሉ። እንዲሁም እግዚአብሔር እርሱን ለማምለክ እንዲያስችለንና በውስጣችን በኃይል እንዲሠራ መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶናል። እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ከአጠቃላይ ውድመት ቢጠብቃትም፥ አንዳንድ አማኞች በስደት መጎዳታቸው የማይቀር ነው። ነገር ግን በትንሣኤ አማካኝነት ድሉ የራሳችን ስለሆነ ልንጨነቅ አይገባም። የዚህ ራእይ ቁልፍ ተምሳሌቶች የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. የቤተ መቅደስ ውጫዊ ክፍል፥ የመሠዊያውና የማምለኪያዎቹ መለካት፡- በዚህ ራእይ ውስጥ ዮሐንስ አንድ መልአክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሲለካ ተመልክቷል። በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ መላእክት አንድን ነገር የሚለካበት ታላቅ በረከት (ኤር. 31፡38-40፤ ዘካ 1፡16) ወይም ጥፋት (አሞፅ 7፡7-9) እንደሚመጣ ለማሳየት ነው። የቤተ መቅደስ ውስጣዊ ክፍል መለካቱ እግዚአብሔር እውነት ተከታዮቹን ለማወቅና ሙሉ ለሙሉ እንዳይወድሙ ለመጠበቅ መፈለጉን የሚያሳይ ይመስላል። ለዚህ ራእይ የሚሰጡ ሁለት ዐበይት አተረጓጎሞች አሉ። ሀ) ይህ ራሳቸውን ለማቆሸሽ ባለመፈለግ ለእግዚአብሔር በታማኝነት ጸንተው የቆሙትን ሰዎች ያመለክታል። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች ከአካላዊ ሞት ሳይሆን የመንግሥተ ሰማይን ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ እንዳያጡ የጠበቀ ይመስላል። ለ) ወይም ደግሞ ይህ እግዚአብሔር ሐሳዊ መሢሕ አይሁዶችን ሙሉ ለሙሉ እንዳይጨርስ የሚጠብቃቸው መሆኑን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።
  2. የውጭው አደባባይ፡ መልአኩ አሕዛብ የሚያመልኩበትን ውጫዊ የቤተ መቅደስ አደባባይ አልለካም፡፡ ሀ) ይህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ላልሆኑት ሰዎች ጥበቃ እንደማይደረግላቸውና የኋላ ኋላም እንደሚደመሰሱ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። እሕዛብ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ለመስጠት ያልፈለጉትንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያሳድዱትን ዓለማውያንን ይወክላሉ። ለ) ወይም ደግሞ ይህ እግዚአብሔር የሐሳዊ መሢሕ ሠራዊት የኢየሩሳሌምን ከተማ እንዲደመስስና አምልኮዋን ጨምሮ ሁሉንም ነገር እንዲቆጣጠር የሚፈቅድ መሆኑን የሚያመላክት ሊሆን ይችላል።
  3. ሁለቱ ምስክሮች፡– ቤተ ክርስቲያን ወይም እስራኤል ከፍተኛ ስደት በደረሰባቸውና ታላቅ ቀውስ በተከሰተበት በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሁለት ልዩ ነቢያትን ያስነሣል። የእነዚህ ነቢያት አገልግሎት መመስከር ነው። እነዚህ ምስክሮች ሙሴንና ኤልያስን የሚመስሉ ሲሆን፥ የሚፈጽሟቸው ተአምራትም የእነዚህን አገልጋዮች ይመስላሉ። ለሦስት ዓመት ተኩል ጊዜያት ማንም እንዳይገድላቸው እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል። ከዚያ በኋላ ግን እግዚአብሔር የጥበቃ እጁን ያነሣና ሁለቱ ምስክሮች ከሰይጣን ኃይልን ባገኘው ሐሳዊ መሢሕ ይገደላሉ። ዓለም በእነዚህ ሰዎች መገደል ደስ ስትሰኝ፥ ከሦስት ተኩል ቀናት በኋላ ከሞት ተነሥተው ወደ ሰማይ ያርጋሉ። በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ሰባ ሺህ ሰዎችን የሚገድል የመሬት መንቀጥቀጥ በመላክ ኃይሉን ይገልጻል። አንዳንዶች እነዚህ ሁለት ምስክሮች እንደ ዮሐንስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ለወንጌሉ በድፍረት መቆማቸውን ያመለክታል ይላሉ። ሌሎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊመጣ ሲል እግዚአብሔር ሁለት ልዩ ነቢያትን በመላክ በቅርብ ጊዜ የሚከሰተውን የእግዚአብሔር ፍርድና የክርስቶስን ወንጌል እንዲያውጁ ያደርጋል ብለው ያስተምራሉ። 

ይህ የሁለቱ ምስክሮቹ ራእይ እውነትን በሁለት ደረጃ ዎች ይገልጻል። በመጀመሪያ፥ ሁለቱ ምስክሮች በስደት ጊዜም ሳይቀር ዛሬ ከአማኞች ምን እንደሚጠበቅ ያሳያሉ። እምነታችንን ከመደበቅ ይልቅ የተሰደድን አማኞች ስለ እምነታችን ማወጃችንን መቀጠል ይኖርብናል። የምናገለግለው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። ክርስቲያኖች ሕይወታችን በእግዚአብሔር የተጠበቀ መሆኑንና እርሱ የወሰነው ጊዜ ሳይደርስ ማንም እጁን በእኛ ላይ ሊጭን እንደማይችል መረዳት አለብን። ትንሣኤ ሞትን የሚከተል በመሆኑ፥ አማኞች አካላዊ ሞትን መፍራት የለብንም። ሁለተኛ፥ በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር ሁለት ልዩና ኃይለኛ ነቢያትን የሚያስነሣ ይመስላል። እነዚህ ነቢያት ስለሚመጣው ፍርድ ሰዎችን ለማስጠንቀቅ፥ ንስሐ እንዲገቡ በመጠየቅና በሚፈጽሟቸው ተአምራቶች የእግዚአብሔር ነቢያት መሆናቸውን በማሳየት የእግዚአብሔርን ቃል ያስፋፋሉ። በእነዚህ ሁለት ምስክሮች አማካኝነት የእግዚአብሔር ቃል በዓለም ሁሉ ይሰራጫል። ነገር ግን እግዚአብሔር እነዚህ ምስክሮች እንዲገደሉ ይፈቅዳል። ይሁንና እግዚአብሔር በሁኔታው ላይ ያለውን ተቆጣጣሪነት በማሳየት ሁለቱን ምስክሮች ከሞት ያስነሣቸዋል፤ ያሳደዷቸውን ዓለማውያን ደግሞ ይቀጣል። 

የውይይት ጥያቄ፡– ከዚህ ራእይ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን መሪዎችና በሚያሳድዷቸው ሰዎች መካከል ስላለው ግንኙነት ምን እንማራለን?

፪. የሰባተኛው መለከት ፍርድ (ዋይታ 3) (ራእይ 11፡15-19)

እንደ ሰባተኛው ማኅተም ሁሉ ሦስተኛው ዋይታ የተባለው ሰባተኛው የመለከት ፍርድም በቀጥታ ከአንድ ፍርድ ጋር የተያያዘ አይደለም። ይልቁንም በዚህ ጊዜ የዓለም መንግሥታት ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ኃይልና ሥልጣን ሥር መዋላቸው ታውጇል። ይህ ሰባተኛው የመለከት ፍርድ ሁለት አሳቦችን ያዋህዳል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ ጠላቶቹን ለማሸነፍ እንደሚመጣና በራእይ 19 እንደተገለጸው በአገሮች ሁሉ ላይ እንደሚነግሥ ያሳያል። በራእይ 11፡17 ና 19፡11-16 ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንገሥ መጀመሩን እንመለከታለን። ሁለተኛ፥ ይህ ምናልባትም ሰባት የጽዋ ፍርዶችን የሚያካትት ይሆናል። እነዚህም ፍርዶች ተከታታይነት ያላቸውና የጠነከሩ ሲሆኑ፥ ፍጻሜ የሚያገኙት የክርስቶስ መንግሥት ሲመጣ ነው (ራእይ 15-16)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version