የዘፍጥረት መጽሐፍ ትልቅ ውበትን በመግለጽ ይጀምራል። እግዚአብሔር በብርሃን፥ በእንስሳትና በሰዎች፥ እንዲሁም በአትክልት ስፍራ የተዋበች ዓለም ፈጥሯል። ከዚህም በላይ እግዚአብሔር በተደጋጋሚ የኤድን ገነት ነዋሪዎች ከሆኑት ወንድና ሴት ጋር እየተገናኘ ይወያያል። በመካከላቸውም ምንም ዓይነት መጋረጃም ሆነ ኃፍረት አልነበረም። ያ ሁሉ ውበት አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር በሕይወታቸው ላይ የነበረውን ቁጥጥር በመቃወማቸው ከመቅጽበት ተናደ። በዚህም ጊዜ ያ ሁሉ ውበት በኃጢአት ቆሸሸ። ይህም እሾሆች፥ ላብ ጠብ የሚያደርግ ብርቱ ሥራ፥ የወሊድ ምጥና ሞት፥ ግድያ፥ ወሲባዊ ኃጢአት፥ ጦርነቶች፥ ወዘተ… እንዲስፋፉ አደረገ። በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮች ሁሉ የመነጩት በዘፍጥረት ውስጥ ከተከሰተው ዐመፅ ነው።
የዮሐንስ ራእይ የዘፍጥረት መጽሐፍ ከተጀመረበት ሁኔታ ጋር በሚቃረን መልኩ ይጠናቀቃል። ራእይ የሚጀምረው በኃጢአት፥ ዐመፅ፥ ጦርነቶች፥ የተፈጥሮ አደጋና በታሪክ በማንኛውም ስፍራ ከታየው ሁሉ በላቀ ክፋት ነው። ነገር ግን ያ ሁሉ ይወገዳል። እንዲሁም በድጋሚ አንድ ጊዜ፥ ውበትና ግልጽ የሆነ ግንኙነት ከአምላካችን ጋር እናደርጋለን። ማንኛውም የሥቃይ ስሜት የሚያመጣብን ምድራዊ ነገር ሁሉ ይወገዳል። ይህ አዲስ ሰማይና ምድር ምን እንደሚመስል ወይም የመጀመሪያዋን ምድር የምትመስል ትሁን ወይ ሌላ ሙሉ ለሙሉ አናውቅም። ነገር ግን እኛ ከምንገምተው ከማናቸውም ነገሮች በላይ ውብ እንደምትሆን እናውቃለን። አሁን የምንኖርባት ምድር እንኳን በኃጢአት ከተበከለችበት ሺህ ዓመታት በኋላ እንኳን ውብ ናት፥ ፈጽሞ የምትታደሰው አዲሲቱ ምድር ምን ልትመስል እንደምትችል እስኪ አስብ! ምንም ሥቃይ የሌለበት ዓለም ምን ይመስል ይሆን? ከሁሉ በላይ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ምንም የኃጢአት ጋሬጣና ግድግዳ እንዲሁም ያለ አንዳች እፍረት ፊት ለፊት የምንገናኝበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል ገምት።
ወንድሞችና እኅቶች፥ ዮሐንስ ስለ አዲሲቱ ሰማይና ስለ አዲሲቱ ምድር እንድናስታውስ ይፈልጋል። ምክንያቱም ያ ቋሚ መኖሪያችን ነው። በዚህን ሰዓት በእምነት ጉዞ ላይ እንገኛለን። እውነት ነው በአሁኑ ዓለም ውስጥ በኃጢአትና በበሽታ ምክንያት እንቸገራለን። በተጨማሪም የክፉ መሪዎችና የአስጨናቂ ሃይማኖቶች ጊዜ ይሆናል። ነገር ግን በታማኝነት ክርስቶስን ብንከተልና ብንጸና፥ አንድ ቀን ይህ ሁሉ ችግር ልንገልጸው እስከማንችል ድረስ ወደ ክብር ይለወጣል።
የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 15-16 አንብብ። እግዚአብሔር በምድር ላይ በመጨረሻው ጊዜ ላይ የሚያመጣውን የመጨረሻ ፍርድ ግለጽ።
የመጨረሻው የፍርድ ጊዜ ፍጻሜ በደጅ ነው። ታላቁ መከራም በመጠናቀቅ ላይ ነው። ከዚህ በኋላ በምድር ላይ የሚመጣው አንድ ቀጣይነት ያለው ታላቅና መጥፎ የፍርድ ጊዜ ብቻ ነው። የዮሐንስ ራእይ የእግዚአብሔር ዙፋን ወዳለበት ሰማያዊ ክፍል ይመለሳል። በዚያም ሕዝብ በዙፋኑ ፊት ቆሞ ያያል። አማኞች አሸናፊዎች ናቸው። ሰይጣን ሐሰተኛው ነቢይና ሐሳዊው መሢሕ እምነታቸውን ለማስጣል ካመጡባቸው ፈተናዎች በተቃራኒ ታማኝ ሆነው በመቆማቸው ምክንያት አሸንፈዋል። ክርስቲያኖች ለማመቻመችና እንደ ምስል ላሉ ለማናቸውም ነገሮች ላለመስገድ ወስነዋል። የአውሬውን ምልክት በመቀበል የዓለም ሥርዓትን አስተናግደው ለዓለም ታማኝነታቸውን ለማሳየት አልፈለጉም። እነዚህ ቅዱሳን ስደትና የኑሮ ጉድለት አጎሣቁሏቸው ነበር። አሁን ግን በእረፍት ላይ ናቸው። ይህም እግዚአብሔር የሚበቀልበት፥ የክርስቶስን ጠላቶች የሚያጠፋበትና መንግሥቱን የሚመሠርትበት ጊዜ ነው። የእግዚአብሔር መንገዶች ትክክል በመሆናቸው ምክንያት አማኞች በታላቅ የውዳሴ ዝማሬ እግዚአብሔርን ያመልኩታል። ከዐመፅና ከመከራ ውስጥ ውበትን ማውጣት የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች አሁን እግዚአብሔር በሁሉም ዘንድ ክብርን እንደሚያገኝ ያውቃሉ። ዐመፅ ይቆማል። «የምስክሩ ማደሪያ» ከሚባለው ዙፋንም የመጨረሻዎቹ የእግዚአብሔር የቁጣ ጽዋዎች ፍርዶች ለሰባት መላእክት ተሰጡ። ከእነዚህ ፍርዶች መካከል አንዳንዶቹ ከመለከት ፍርዶችና በሙሴ ዘመን በግብጽ ምድር ላይ ከወረዱት መቅሠፍቶች ጋር ይመሳሰላሉ። እነዚህ ፍርዶች በቅደም ተከተል ደረጃ ከመምጣት ይልቅ ከመቅጽበት አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ ይመጣል።
- የመጀመሪያ ጽዋ፡- የአውሬው ምልክት ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚመጣ ቁስል። እንደ ግብጹ መቅሠፍት ሁሉ (ዘጸ 7-11)፥ አንዳንዶቹ ፍርዶች ማኅተም ያለባቸውን የእግዚአብሔር ልጆችና የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ያላመኑ ሰዎች ለመለየት እንደሚያገለግሉ ዮሐንስ ያሳየናል። በዚህ ቁስል የሚመቱት የእግዚአብሔር ተቃዋሚዎችና የአውሬውን ምልክት የተቀበሉት የሰይጣን ግብረ አበሮች ብቻ ናቸው።
- ሁለተኛዋ ጽዋ፡- የባሕር ውኃ ሁሉ ወደ ደም መለወጥ። አስቀድመን የባሕር ሲሶ በፍርድ ውስጥ መመረዙን አይተናል። ይህም 2/3ኛው ለሰው ልጆች ተስማሚ እንደነበር ያሳየናል። አሁን ግን እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ ያሉትን ፍጥረታት በሙሉ ያጠፋል። ከዚያ በኋላ በባሕር ላይ የመርከብ ላይ ጉዞ አይኖርም። በባሕር ዳርቻ ላይ ለሚኖሩም ከባሕር ውስጥ የሚገኝ ምግብ አይኖርም።
- ሦስተኛው ጽዋ፡- የማንኛውም ንጹሕ ውኃ ወደ ደም መቀየር። ይህም መቅሠፍት ልክ እንደ ሁለተኛው ጽዋ ሁሉ ከመለከት ፍርዶች የከፋ ነበር። ምክንያቱም መለከት ፍርድ ላይ 1/3ኛው ንጹሕ ውኃ ብቻ ሲበከል፥ አሁን ግን በጽዋው ፍርድ የውኃ ዘር የተባለ ሁሉ ይበከላል። መልአኩም ይህንን ፍርድ ተስማሚ ፍርድ ይለዋል። እርኩሳን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ደም አፍስሰዋል። አሁን ግን በእግዚአብሔር ፍርድ አማካኝነት ደሙን እንደ ውኃ ይጠጣሉ።
- አራተኛው ጽዋ፡- የፀሐይ ሰዎችን ማቃጠል። በአንድ በሆነ ምክንያት የፀሐይ ኃይል በብዛት ይጨምርና ሰዎችን ማቃጠል ይጀምራል። (ማስታወሻ፡- እነዚህ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሚሰጣቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያዎች ሲሆኑ ከመጨረሻው ጊዜ በፊት የሚሆን የንስሐ ዕድል ነው። ነገር ግን ሰዎች ምላሽ የሚሰጡት በምን መንገድ ይሆን? ከእርኩሰታቸው ተመልሰው እግዚአብሔርን ያመልኩት ይሆን? በጭራሽ፥ የተነገረን እነዚህ ፍርዶች የመጡት ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑን እያወቁ እግዚአብሔርን እንደሚራገሙ ነው።)
- አምስተኛው ጽዋ፡- ጨለማና ሥቃይ። የክርስቶስ ተቃዋሚ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ ይኩራራል። ሰዎችም ያመልኩት ዘንድ ያስነግራል። የሁሉም ነገሮች ተቆጣጣሪ እንደሆነም ያውጃል። ሆኖም ግን የእግዚአብሔር ሰዓት ሲደርስ የእግዚአብሔር ፍርድ በክርስቶስ ተቃዋሚ፥ በቤተ መንግሥቱና በግዛቱ ሁሉ ላይ ይወድቃል። በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ጨለማ ሲከብድ፥ በዚያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የመጀመሪያው የጽዋ ፍርድ ቁስል ይሰማቸዋል። እንደገናም ሕዝቡ ንስሐ ገብቶ ወደ እግዚአብሔር እንደማይመለስ ተነግሮናል። የሰው ልብ ምንኛ ጠንካራ ነው!
- ስድስተኛ ጽዋ፡- ለአርማጌዶኑ ጦርነት የተደረገ የሕዝብ ስብሰባ። በእግዚአብሔር ትእዛዝ ክፉ መናፍስት ከዘንዶው፥ ከአውሬውና ከሐሰተኛው ነቢይ አፎች ውስጥ ይወጣሉ። እነርሱም ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋጉበት ሰዓት እንደ ደረሰ ያውቃሉ። እነዚህም እንቁራሪት መሣይ ክፉ መናፍስት የምድር ነገሥታትና እርኩሳት መናፍስትን ሁሉ አርማጌዶን ለተባለው ጦርነት እንዲሰበሰቡ ያሳምናሉ። አንዳንድ ተመራማሪዎች አርማጌዶን፥ የእግዚአብሔርን ቀንና እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ጋር የሚያደርገውን የመጨረሻ ጦርነት በተምሳሌትነት ብቻ እንደሚያሳይ ያምናሉ። ሌሎች ተመራማሪዎች ግን አርማጌዶን በሰሜን እስራኤል የሚገኝና የመጨረሻውም ጦርነት በትክክል የሚካሄድበት ስፍራ እንደሆነ ያስባሉ።
- ሰባተኛው ጽዋ፡- እግዚአብሔር በሰው ዘር ሁሉ ላይ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥንና በረዶን ያመጣል። (ማስታወሻ፡- ይህ ሰባተኛው ፍርድ እንደ ፍርድ የተገለጠበት የመጀመሪያ ጊዜ ነው።) እግዚአብሔር «ተፈጸመ» ብሎ ሲናገር፥ ይህንን የታላቅ ፍርድ ጊዜ ወደ ፍጻሜው አመጣለሁ ማለቱ ነው። በዓለም ታሪክ የምናውቀው የሰዎች የበላይነት አሁን ፍጻሜውን አገኘ። አሁን ጊዜው፥ ኢየሱስ የሚመለስበትና መንግሥቱንም የሚመሠርትሰት ነው። አሕዛብ፥ ቅኝ ግዛቶችና «የታላቂቱ ባቢሎን» ተምሣሌቶች የሆኑት የዓለም ከተማዎች ሁሉ ጠፍተዋል። እስከ መጨረሻው ድረስ የሰው ዘር ለንስሐ ማመፅና በተስፋ ቢስ ቁጣ እግዚአብሔርን መራገምን ተያይዞታል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች ለመጨረሻው የእግዚአብሔር ፍርድ ከሚሰጡት ምላሽ በመነሣት ስለ ሰዎች የልብ ድንዳኔ ምን ልንማር እንችላለን? ለ) እግዚአብሔር ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመለሱ በፍርዶች አማካኝነት ሲያስጠነቅቃቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ለምን ንስሐ እንደማይገቡ ግለጽ?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)