በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ የሚሳተፉ ቁልፍ ግለሰቦች (ራእይ 12:1-14:20) 

የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 12-14 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል በቀረቡት ራእዮች ውስጥ የተገለጹትን እያንዳንዳቸውን ገጸ ባሕርያት ዘርዝር። እያንዳንዳቸው እንዴት የተለዩና ከሌሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ግለጽ። ለ) ይህ ክፍል ስለ እግዚአብሔር አብና ወልድ ምን ያስተምረናል? ሐ) ስለ አማኞች ምን እንማራለን?

ዛሬ በምድር ላይ የሚፈጸሙትን ነገሮች ማለትም እንደ ስደት፥ ረሃብና ጦርነት የመሳሰሉትን እንዴት ልንረዳቸው ይገባል? ክርስቶስ ሊመለስ ሲል በዓለም ላይ የሚሆነው ሁኔታ ምን ይመስላል? ዮሐንስ እግዚአብሔር ወደ ምድር ስለሚልካቸው የመጨረሻዎቹ ተከታታይ ፍርዶች ከመግለጹ በፊት፥ ወደ ፊት ቁልፍ ሚና በሚጫወቱ ግለሰቦች ላይ ያተኩራል። ነገር ግን የእነዚህ ግለሰቦች ባሕርያት ሙሉ በሙሉ በመጨረሻው ዘመን የሚታይ ቢሆንም፥ አሁንም በመጠኑ እየታየ መሆኑ ግልጽ ነው።

፩. በሴቲቱና በዘንዶው መካከል የተደረገ ጦርነት (ራእይ 12)

ዮሐንስ ይህንን ራእይ «ታላቅ ምልክት» ሲል ይጠራዋል። ምልክት ከክስተት ወይም ከራእይ በስቲያ ያሉትን አስደናቂ ክስተት ወይም ራእይ ነው። ለምሳሌ ያህል፥ ብዙዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራት ምልክቶች ተብለው ይጠራሉ። ለዚህም ምክንያቱ እነዚህ ነገሮች ምን እንደ ተከሰተ የሚያሳዩ ታሪኮች ብቻ ሳይሆኑ፥ ክርስቶስ እንደ ሞት ባሉት ነገሮች ላይ መለኮታዊ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩና መሢሕነቱን የሚገልጹ መሆናቸው ነው (ዮሐ 6፡30)። በዚህ የራእይ ምልክት ዮሐንስ ሴቲቱና ልጁ ከዘንዶው ጋር ያደረጉትን ትግል ያመለክታል።

ዮሐንስ በዚህ ራእይ ላይ ባለ 12 ከዋክበት አክሊል የደፋች እርጉዝ ሴት ይመለከታል። ይህች ዙፋን የሚወርስ ወንድ ልጅ ልትወልድ ያለች ሴት ማን ነበረች? ሦስት አመለካከቶች አሉ። መጀመሪያ፥ አንዳንዶች ይህቺ ሴት የክርስቶስ እናት የሆነችው ማርያም ናት ይላሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ የአማኞች ማኅበረሰብና መንፈሳዊት እስራኤል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ናት ይላሉ። ሦስተኛ፥ አሁንም ሴቲቱ መሢሑ የመጣባት እስራኤል ናት የሚሉ አሉ። ትክክለኛው አመለካከት ሁለተኛው ወይም ሦስተኛው ይመስላል።

ሴቲቱ ልትወልድ ስትል አንድ ታላቅ ቀይ ዘንዶ መጣባት። ይህ ዘንዶ የእግዚአብሔርና የልጆቹ ጠላት የሆነው ሰይጣን ነው። ዘንዶው ከከዋክብት ሲሶዎቹን ወደ ምድር ጣለ። ይህ ምናልባትም ሰይጣን በኃጢአት የወደቀበትን ሁኔታ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሰይጣን ከመላእክቱ ሲሶዎቹን (አንድ ሦስተኛ) ይዞ ወድቋል። ሌሎች ደግሞ ይህ ሰይጣን ብዙ አማኞችን ለመግደል መሞከሩን ያሳያል ይላሉ። ዘንዶው ሰባት አክሊሎች ያሉባቸው ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ነበሩት። ይህ ምናልባትም የዘንዶውን ታላቅ ኃይልና ሥልጣን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ዘንዶው ከሴቲቱ የሚወለደውን የመንግሥት ወራሽ የሆነ ልጅ ለመዋጥ ፈልጎ ከአጠገቧ ቆመ።

ወንዱ ልጅ ኢየሱስ ክርስርቶስን ያመለክታል። ሰይጣን ኢየሱስ ክርስቶስን በኃጢአት ፈተናና በመስቀል ላይ ሞት ሊያጠፋው ሞክሯል። ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ድል ነሺነቱን ያመለክታል። ከዚያም እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰይጣን ጥቃት አርቆ ወደ መንግሥተ ሰማይ ወስዶታል። ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ እንዲገዛ የተሰጠውን መብት ማንም አይወስድበትም።

ዘንዶው ሴቲቱን ሊያጠፋት ሲፈልግ (ሴቲቱ እስራኤል ወይም ቤተ ክርስቲያን ትሆናለች) እግዚአብሔር ለአንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀናት (ዘመን፥ ዘመናትና የዘመን እኩሌታ) በምድረ በዳ ውስጥ ይሸሽጋታል። (ማስታወሻ፡ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀናት፥ ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜን ያመለክታሉ። ይህ ደግሞ ሁለቱ ምስክሮችና ይኼኛው ክስተት በእኩል የጊዜ ርዝመት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያመለክታል።) ዘንዶው ሴቲቱን ሊያጠፋ በሚፈልግበት ጊዜ የተፈጠረች ምድር እንኳን ከእግዚአብሔር ጋር ተባብራ ትረዳታለች። ይህ በሰይጣንና በእስራኤላውያን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት የሚያመለክት ከሆነ፥ እግዚአብሔር በመጨረሻው የታላቁ መከራ ዘመን ሰይጣን የእስራኤልን ሕዝብ እንዳይጨርስ የሚከላከል መሆኑን ያሳያል። ሴቲቱ ቤተ ክርስቲያን ከሆነች፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምድር ላይ ሙሉ ለሙሉ ከመውደም የሚጠብቃቸው መሆኑን ያሳያል። ከሌሎች የዮሐንስ ራእይ ክፍሎች ለመረዳት እንደሚቻለው፥ አማኞች ለእምነታቸው የሚገደሉ መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን በአጠቃላይ ሊያጠፋት አይችልም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ዛሬም ሆነ በታሪክ ሁሉ፥ እንዲሁም ሐሳዊ መሢሕ አማኞችን ለማጥፋት በሚፈልግበት በመጨረሻው ዘመን ሕዝቡን ይጠብቃል። ዘንዶው ሴቲቱን ለማጥፋት ባለመቻሉ ልጇን ለማጥፋት ይሞክራል። ይህ እስራኤላውያን ወይም የቤተ ክርስቲያን አማኞችን ሊያመለክት ይችላል፥ በአመዛኙ ሁሉንም አማኞች ይወክላል። ዮሐንስ እንዴት እንደሚገልጻቸው ልብ ብለህ ተመልከት። አማኞች የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚከተሉ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች ሁልጊዜም እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እንደሚተጉ ያስባል። እነዚህ አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስን ምስክርነት ይጠብቃሉ። አማኞች በወንጌሉ ላይ ያላችውን ንጹሕ እምነት በመጠበቅ ከስደት ሁሉ ባሻገር ስለ ክርስቶስ ይመሰክራሉ። ሰይጣን የሴቲቱን ልጅ ለማጥፋት የሞከረው እንዴት ነበር? በራእይ 13 ሰይጣን ሌሎች ሁለት ዓይነት ሰዎችን እንደሚጠቀም ተገልጾአል። ከባህር እንደሚወጣ አውሬ የተገለጸው የመንግሥት መሪ አለ። ይህም ሐሳዊ መሢሕ ነው። ከምድር እንደሚወጣ የተገለጸው ደግሞ ሃይማኖታዊ መሪ መሆኑን እንመለከታለን።

በምድር ላይ በሰይጣንና በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ከሚካሄደው ጦርነት በስተጀርባ ሌላ ታላቅ ጦርነት አለ። (በራእይ ምዕራፍ 13 እንደምንመለከተው፥ ሰይጣን የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎችን በመጠቀም ጦርነትን ያካሂዳል።) ይህ በሰይጣንና በኃይሎቹ፥ እንዲሁም በእግዚአብሔርና በኃይሎቹ መካከል የሚካሄድ ታላቅ ጦርነት ነው። የእግዚአብሔር ሠራዊት መሪ የሆነው ሊቀ መልአኩ ሚካኤል ሰይጣንና መላእክቱን ከሰማይ ወደ ምድር ይወረውራቸዋል። ይህ ራእይ መቼ እንደ ተፈጸመ አናውቅም። ነገር ግን ይህ በክርስቶስ መስቀል ላይ የተካሄደውን ጦርነት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሀ) ክርስቶስ በሞት ጊዜ የተካሄደ ጦርነት። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሚሞትበት ጊዜ ሰይጣን ድል ያገኘ መስሎት ነበር። ክርስቶስ ከሞት ሲነሣ ግን ሰይጣን በሰው ነፍሶች ላይ ያለውን ኃይል በማጥፋት ድል ነሥቶታል (ቆላ. 2፡15 አንብብ)። ለ) በአመዛኙ ይህ የመጨረሻው ዘመን እጅግ ክፉ የሚሆንበትንና የእግዚአብሔር ሕዝብ ለእምነታቸው የሚሞቱበትን ምክንያት የሚያስረዳ ይመስላል። ፍጻሜው እየተቃረበ በሚመጣበት ጊዜ እግዚአብሔር ሰይጣን ከመንግሥተ ሰማይ እንዲርቅ ያደርገዋል። (ሰይጣን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት እንደሚቀርብ ለመመልከት ኢዮብ 1-2 አንብብ።) ስለዚህ በምድር ላይ ብቻ እንዲሠራ ይገደባል። ሰይጣን አጭር ጊዜ ብቻ እንደቀረው ስለሚገነዘብና እንቅስቃሴዎቹም በምድር ላይ ብቻ በመወሰናቸው፥ የእግዚአብሔርን ዕቅዶችና ሕዝብ ለማጥፋት የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።

ነገር ግን የሰይጣን ወደ ምድር መምጣት የፍጻሜው መጀመሪያ ሊሆን፥ ክርስቶስ በሁሉም ላይ የሚነግሥስት ጊዜ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ዮሐንስ በራእይ 12፡10-12 ባቀረበው ታላቅ መዝሙር የሁሉም ዘመን አማኞች በሰይጣን ላይ ድል መቀዳጀት እንዳለባቸው ይናገራል። ይህ በተለይም ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት ተግቶ በሚሠራበት በመጨረሻው ዘመን አስፈላጊ ነው። ለመሆኑ አማኞች ሰይጣንን የሚያሸንፉት እንዴት ነው? ድምጻቸውን ጮክ አድርገው በመጸለይ ይሆን? ወይስ ከአካባቢያቸው እንዲርቅ በመገሠጽ ነው? ወይስ ወደ ጥልቁ እንዲወርድ በማዘዝ? ዮሐንስ ድል የሚያስገኙትን ሦስት ነገሮች ይጠቅሳል።

ሀ) የበጉ ደም፡ ሰይጣንን የምናሸንፈው የእግዚአብሔር ልጆች፥ የመንግሥቱ አካሎች በመሆንና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም (በክርስቶስ ሞት) በመታመን ነው። በመልካም ሥራችን ድነትን (ደኅንነት) ልናገኝ አንችልም። ነገር ግን የድነትን ነፃ ስጦታ በእምነት እንቀበላለን። ይህም ከሰይጣን መንግሥት አውጥቶ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ያኖረናል። አማኞች ሆነን ኃጢአት ስንፈጽምና ሰይጣን ሲከስሰን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ለኃጢአታችን እንደ ተከፈለና እግዚአብሔርም በነፃ እንዳሰናበተን ልንነግረው እንችላለን። ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለማደስ ኃጢአታችንን እንናዘዛለን።

ለ) የምስክርነታችን ቃል፡ ስደት ክርስቲያኖች እምነታችንን እንድንደብቅ፥ አፋችንን እንድንዘጋና ምስክርነታችንን እንድናቆም ያደርገናል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሰይጣን አሸናፊ ይሆናል። ዮሐንስ ሰይጣንን የምናሸንፍበት መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል በማወቅና እምነታችንን ለዓለማውያን በማካፈል መሆኑን ይናገራል።

ሐ) ለእምነታችን ለመሞት በመፍቀድ፡ ሕይወታችንን በምንወድበት ጊዜ ሰይጣን በብዙ መንገዶች ሊያሸንፈን ይችላል። ገንዘብን በመጠቀም የዓለምን ነገሮች እንድንፈልግ ይማርከናል። የአመራር አገልግሎታችንን በተዛባ መልኩ እንድንጠቀም ያደርገናል። ፈርተን እምነታችንን እንድንደብቅ ስደትን ይጠቀማል። እነዚህ ሁሉ ራስን የመውደድ ምሳሌዎች ናቸው። ነገር ግን ድል የሚገኘው ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ በመኖር ነው (ማቴ. 6፡33)። ለራሳችን የራስ ወዳድነትና የትዕቢት ፍላጎቶች በምንሞትበት ጊዜ ሰይጣን ሊያሸንፈን አይችልም። በስደት ጊዜ ጸንተን ስንቆምና ለእምነታችን ስንሞት ሰይጣን ሊያሸንፈን አይችልም። ነገር ግን ሊያገኘን ወደማይችልበት ሰማይ ይልከናል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞትና በመነሣት ሰይጣንን እንዳሸነፈ ሁሉ፥ እኛም ሰይጣንን የምናሸንፈው ለክርስቶስ በታማኝነት እየኖርን በመሞትና ለዘላለም ከሞት በመነሣት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ እኛ ሰይጣንን እናሸንፋለን ብለን የምናስብባቸውን መንገዶች ዮሐንስ ከገለጻቸው ሰይጣንን የማሸነፊያ መንገዶች ጋር አነጻጽር። ለ) እነዚህ ሦስት ነገሮች ሰይጣንን ለማሸነፍ የምትጠቀምባቸው የመሣሪያዎች ክፍሎች የሆኑበትን ሁኔታ ግለጽ።   

፪. ከባህር የወጣው አውሬ (ራእይ 13፡1-10) ዘንዶው ሴቲቱን ለማሸነፍ ባለመቻሉ መንፈሳዊ ልጆቿን ለማጥፋት ይሻል። እነዚህም መንፈሳዊ ልጆቿ አማኞች ናቸው። ስለሆነም ዘንዶው ከባህር አጠገብ ቆሞ አንድ አውሬ ከእርሱ ሥልጣን ተቀብሎ በምድር ላይ እንዲገዛ ይጠራዋል። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ልጆች ለማሸነፍ ከሚጠቀምባቸው ሁለት አውሬዎች በስተጀርባ የሚሠራ ኃይል መሆኑ ግልጽ ነው። የመጀመሪያው አውሬ ከባህር ይወጣል። ይህ አውሬ እንደ ዘንዶው ሰባት ራሶች፥ አሥር ቀንዶችና አሥር አክሊሎች ነበሩት። ይህ ምናልባትም ዘንዶው ኃይሉና ሥልጣኑ ለፖለቲካ መሪው እንዴት እንደሚሰጥና በእርሱ አማካኝነት እንዴት እንደሚገዛ የሚያመለክት ይሆናል። አንዳንዶች ራሶች፥ ቀንዶችና አክሊሎች ታላቅ ጥበቡንና ሥልጣኑን እንዲሁም በአገሮች ላይ ያለውን አገዛዝ የሚያሳዩ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ ፖለቲካዊ አውሬ በአሥር መንግሥታት ላይ የሚገዛ መሆኑን ይናገራሉ። ዮሐንስ የዳንኤል 7፡2-7ን ራእይ በመጥቀስ ይህ አውሬ በብሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የገዙትን የዓለም መንግሥታት ክፉ ባሕርያት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ያስረዳል።

አውሬው ማን ነው? ምንም እንኳን አንዳንዶች ዮሐንስ በሮም ስለነበረው ግዛት እየተናገረ ነው ብለው ቢያስቡም፥ ዮሐንስ በዚህ ስፍራ ለማመልከት የፈለገው ሐሳዊ መሢሕ ተብሎ በሚጠራ መሪ ሥር የሚተዳደረውን የመጨረሻ የዓለም መንግሥት ይመስላል። ዮሐንስ በዚሁ ታላቅ ገዢ ላይ በማተኮር አያሌ ነገሮችን ይነግረናል።

ሀ) የገዢው ኃይልና ሥልጣን የሚመጣው በቀጥታ ከሰይጣን ነው። ልብ ላንል ብንችልም ሰይጣን ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ሰዎችን (በተለይም የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎችን) በመሣሪያነት በመጠቀም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥቃት ይሞክራል። ነገር ግን ይህ የመጨረሻው ገዢ በታሪክ ሁሉ ከታዩት መሪዎች በላይ በሰይጣን ኃይልና ክፋት የተሞላ ይሆናል።

ለ) ከራሶቹ አንደኛው ክፉኛ ይቆስላል። ምሁራን ይህን በሁለት መንገዶች ይተረጉማሉ። በመጀመሪያ፥ ይህ ሐሳዊ መሢሕ ሊገደልና በኋላ ግን ተአምርን በሚመስል መንገድ ከሞት እንደሚነሣ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ይህም ሰዎች እንዲያመልኩትና ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳዋል። ሰውዬው ሐሰተኛው ክርስቶስ መሆኑን አትዘንጉ። በመሆኑም የክርስቶስ የመስቀል ላይ ቁስል ድነትን (ደኅንነት) እንደሚያስገኝልን ሁሉ፥ ሐሰተኛው ክርስቶስ ለችግሮች ሁሉ መልስ እንደሆነና ቁስሎቹ እንደሚያሳዩት መለኮታዊ እንደሆነ በመግለጽ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመኮረጅ ይሞክራል። ሁለተኛ፥ ሌሎች ምሁራን ይህ ለሰይጣን የተለያዩ መንግሥታት (ሐሳዊ መሢሕንና መንግሥቱን ጨምሮ) ምን ያህል በቀላሉ የማይሞቱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ይላሉ። የሰይጣን መንግሥት የወደቀና የጠፋ ቢመስልም፥ የበለጠ ኃይልን ተላብሶ ይመለሳል።

ሐ) ሐሳዊው መሢሕ ፖለቲካዊ መሪ ብቻ ሳይሆን፥ ከሰዎች አምልኮ የሚፈልግም ጭምር ነው። ሐሰተኛው ክርስቶስ እንደ መሆኑ መጠን፥ የሰዎችን አምልኮ ከእውነተኛው ክርስቶስ ሰርቆ ለመውሰድ ይፈልጋል። በዮሐንስ ዘመን ዶሚቲያን ሰዎች እንዲያመልኩት እንደ ጠየቀ ሁሉ፥ በመጨረሻ ዘመንም ይኸው ሐሳዊ መሢሕ በዓለም ሁሉ የሚኖሩት ሰዎች ሁሉ እንዲያመልኩት ያዝዛቸዋል። ለበጉ በሆነው የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ያልተገኘ ማንኛውም ሰው ይህንን ታላቅ መሪ ያመልከዋል።

መ) ሐሳዊው መሢሕ አምላክ ነኝ በማለቱ የትዕቢትና የስድብ ባሕርያትን ያሳያል። እንደ እግዚአብሔር ለመሆን በመፈለጉ ምክንያት የወደቀውን የሰይጣን ባሕሪ ይላበሳል (ራእይ 14፡12-14) አንብብ)። በእግዚአብሔር ላይ በመመካትና በመሳለቅ እርሱን የሚያመልኩትን ያሳድዳቸዋል።

ሠ) ሐሳዊ መሢሕ በምድር ላይ ለአርባ ሁለት ወራት፥ ማለትም ለሦስት ዓመት ተኩል፥ ለአንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀናት ወይም ለዘመን፥ ዘመናትና ለዘመን እኩሌታ ይገዛል። (ይህ ሁለቱ ምስክሮች የሚሠሩበትና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወይም ሕዝብ የሚረገጥበት ጊዜ አውሬው ከሚገዛበት ዘመን ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የሚያሳይ ይመስላል።) የሐሳዊው መሢሕ ሥልጣን በምድር ላይ ባሉት ሁሉ ላይ ይሰፋል። ሐሳዊው መሢሕ የመጀመሪያው ዓለም አቀፋዊ መሪ ይሆናል። ምንም እንኳን ሰይጣን ወኪሉ በሆነው ሐሳዊ መሢሕ አማካኝነት ለዘላለም ለመግዛት ቢፈልግም፥ እግዚአብሔር ሁሉንም የሚቆጣጠር አምላክ በመሆኑ የሰይጣንን ኃይል፥ ሥልጣንና የአገዛዝ ዘመን ይወስናል። እግዚአብሔር ለዚህ መሪ የሚገዛበትን ሥልጣን እንደ ሰጠው እናነባለን። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ሰይጣንን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር መሆኑን ይገልጻል።

ረ) ሐሳዊ መሢሕ አማኞችን በመዋጋት ያሸንፋቸዋል። ቀደም ሲል አማኞች በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት፥ ታማኞች ሆነው በመጽናትና ለእምነታቸው በመሞት ሰይጣንን እንዳሸነፉ ተመልክተናል (ራእይ 12፡11)። አሁን ደግሞ እግዚአብሔር አውሬው (እና ሌሎች የፖለቲካ መሪዎች አማኞችን እንዲያሸንፉና) እንዲገድሉ ይፈቅድላቸዋል። ምንም እንኳን እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ አማኞችን በስደት ጊዜ ከሞት ቢታደጋቸውም፥ ብዙውን ጊዜ ለእምነታቸው እንዲሞቱ ይፈቅዳል። ዮሐንስ አንዳንድ ክርስቲያኖች ወደ ምርኮ ወይም ወኅኒ እንደሚወርዱ ይናገራል። ሌሎች ደግሞ ይገደላሉ። አማኞች ለሽንፈት በሚጋለጡባት በዚህ ጊዜ ሁለት ባሕርያትን መላበስ ይኖርባቸዋል። በመጀመሪያ፥ በትዕግሥት መጽናት ያስፈልጋቸዋል። ክርስቶስ ክፉ መሪዎችን አጥፍቶ ዘላለማዊ መንግሥቱን እንደሚመሠርት የገባላቸውን የተስፋ ቃል ተመልሶ እስከሚፈጽምበት ጊዜ ድረስ አማኞች በትዕግሥት ሊጠባበቁትና እስከ ሞት ድረስ ሊጸኑ ይገባል። ሁለተኛ፥ ታማኞች መሆን ያስፈልጋቸዋል። ሌላው ሰው በዓለም ውስጥ ምንም ቢያደርግ ወይም ምንም ዓይነት ስደት ቢመጣባቸው አማኞች በኢየሱስ ክርስቶስና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ከዚህ ክፍል አማኝ ከስደት ጋር ስላለው ግንኙነት ምን እንማራለን? 

፫. ከመሬት የወጣው አውሬ (ራእይ 13፡11-14) 

ብዙውን ጊዜ ሃይማኖትና መንግሥት አብረው ይሠራሉ። ይህ በዮሐንስ ዘመንም እውነት ነበረ። የሮም ንጉሠ ነገሥት ሕዝቡ እንዲያመልኩት ሲጠይቅ፥ የቤተ መቅደስ ካህናትና የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ይህንኑ ንጉሣዊ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግና ያልታዘዙትን ሰዎች ለማሳደድ በጋራ ይሠሩ ነበር። ይህ በመጨረሻው ዘመንም የሚከናወን ተግባር ነው።

ሰዎችን ሁሉ ለመቆጣጠርና እንዲያመልኩት ለማድረግ በሚሻው ሐሳዊ መሢሕ የሚመራ ዓለም አቀፍ መንግሥት ከመኖሩ በተጨማሪ፥ በሌላ አውሬ የሚመራ ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ይመሠረታል። አንዳንድ ምሁራን ይህ ከመሬት የሚወጣው አውሬ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር የሚሠራውን ፀረእግዚአብሔር ሃይማኖታዊ ሥርዓት በተምሳሌትነት ያሳያል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ የእግዚአብሔርን እውነት የሚዋጋ ሐሰተኛ ነቢይ ወይም ሃይማኖታዊ መሪ ነው ይላሉ። በመጨረሻው ዘመን ስለሚገለጠው ሁለተኛው ቁልፍ ግለሰብ የተጠቀሰውን ከዚህ በታች ተመልከት፡

ሀ) ከመሬት የሚወጣው አውሬ እንደ በግ ንጹሕና መንፈሳዊ መስሎ ይቀርባል። እንዲያውም በግ እንደሆነው እንደ ክርስቶስ ተመስሎ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን እንደ ዘንዶ ይናገራል። ሰይጣን ለቃላቱ ኃይል ስለሚሰጥ ሰዎች እርሱ የተናገረውን ያምናሉ።

ለ) ይህ አውሬ ከባህር በወጣው አውሬ ወይም በሐሳዊ መሢሕ ሥልጣን ይሠራል።

ሐ) የሃይማኖታዊ መሪው ዐቢይ አገልግሎት በምድር ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ ከባህር የወጣውን አውሬና በእርሱም በኩል ሰይጣንን እንዲያመልኩ ማድረግ ነው። ከመሬት የወጣው አውሬ ሰዎች ያመልኩት ዘንድ የሐሳዊ መሢሕን ምስል ያኖራል። ኃይሉ እጅግ ታላቅ በመሆኑ ይህ ምስል ነፍስ ይዘራና ይናገራል።

መ) ሁለተኛው አውሬ እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢይ ኃይልን ያገኝና በሰይጣን ኃይል ተአምራትን ይሠራል። ይህም ሰዎች ሐሳዊው መሢሕ አምላክ ነው ብለው እንዲቀበሉት ያደርጋል።

ሠ) ለምስሉ ወይም ለአውሬው የማይሰግዱትን ለመግደል ተግቶ ይሠራል።

ረ) ሃይማኖታዊ መሪው አውሬውን የሚያመልኩ ሰዎች ብቻ በግንባሮቻቸው ወይም በእጆቻቸው ላይ ምልክት የሚቀበሉበትን ሥርዓት ያዘጋጃል። በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች የጥበቃ ምልክት እንደሚደረግላቸው ሁሉ፥ ሰይጣንም የመንግሥቱ ተካፋዮች ለሆኑትና ሐሳዊ መሢሕን ለሚከተሉት ሰዎች ምልክትን ያዘጋጃል። ይህ ለሐሳዊ መሢሕ ታማኝነታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው። ያለዚህ ምልክት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ አይችልም። ስለሆነም ለእግዚአብሔር ለሚታመኑና የሐሳዊ መሢሕን ምልክት ለመቀበል ለማይፈልጉ ሰዎች ሕይወት መራራ ትሆንባቸዋለች።

ሰ) ክርስቲያኖች ሐሳዊ መሢሕን ለይተው ያውቁታል። ይህም ሊሆን የሚችለው ስሙ ተሠልቶ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ስለሚመጣ ነው። በታሪክ ሁሉ ይህ ቁጥር አማኞች የተለያየ መላ እንዲመቱ አድርጓቸዋል። የተለያዩ ሥርዓቶችን በመከተል፥ እንደ ኔሮ፡ ሂትለር፥ እስታሊን፥ ኪሲንጀር፥ እንዲሁም የሮም ካቶሊክ ጳጳስ የመሳሰሉ ሰዎች ይህንን ቁጥር እንደሚያሟሉ በማሰብ፥ ብዙዎች ሐሳዊ መሢሕ ናቸው ሲሉ ደምድመዋል። ይህ የተለያዩ የቁጥር ቀመሮችን በመጠቀም እገሌ ሐሳዊ መሢሕ ነው እንዳንል ሊያስጠነቅቀን ይገባል። ምክንያቱም ዮሐንስ ቁጥሮችን በተምሳሌታዊ መንገድ ስለሚጠቀም ነው። (ለምሳሌ ያህል፥ ሰባት፥ አሥርንና አሥራ ሁለት ቁጥርን ለፍጹምነት! ይጠቀማል።) ብዙ ምሁራን ዮሐንስ የክርስቶስን ቅዱስነት ከሐሳዊ መሢሕ ኃጢአተኝነት ጋር እያነጻጸረ ነው ብለው ያስባሉ። ክርስቶስ ፍጹም ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ (ስለሆነም ቁጥሩ ሰባት ሰባት ሰባት ይሆናል)፤ ሐሳዊው መሢሕ ቅዱስ መስሎ ሊቃረብ ቢችልም በሰይጣን ኃይል የሚሠራ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በክፋት የተሞላ ነው። ስለሆኑም ቁጥሩ ስድስት ስድስት ስድስት ይሆናል። የሰባት ቁጥር ፍጹምነት ይጎድለዋል። ዮሐንስ አማኞች ሐሳዊው መሢሕ አምላክና ለሰዎች ሁሉ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ነው የሚለውን ውሸት እንዳይቀበሉ ያስጠነቅቃቸዋል። ዮሐንስ ሐሳዊው መሢሕ ሰው ብቻ ሳይሆን፥ የሰይጣን መገለጫ መሆኑን ያስረዳል። ሰይጣን ሕይወቱን ተቆጣጥሮ ተግባሩን እያከናወነበት መሆኑን ያስረዳል። 

የውይይት ጥያቄ፡- በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከተገለጹት ሦስት አውሬዎች በሰይጣን፥ በመንግሥታት፥ በሃይማኖቶችና በአማኞች መካከል ስላለው ግንኙነት ምን እንማራለን? 

፬. በጉና አንድ መቶ አርባ አራ ሺህዎቹ (ራእይ 14፡1-5)

ዮሐንስ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ የሚታዩትን ሦስት ዐበይት ኃይላት ገልጾአል። እነዚህም ዘንዶው (ሰይጣን)፥ ፖለቲካዊ መሪ (ሐሳዊ መሢሕ)፥ እና ሃይማኖታዊ መሪ (ነቢይ) ናቸው። እነዚህ እንደ ውሸተኛ ሥላሴ ናቸው። አሁን ዮሐንስ፥ «በዚህ ጊዜ በአማኞች ላይ ምን ይከሰታል?» የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል። ይህንንም የሚያደርገው ቀደም ሲል በጠቀሳቸው አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ ላይ ምን እንደሚደርስ በመግለጽ ነው (ራእይ 7፡4)። እነዚህ ሰዎች እስራኤላውያን አማኞችን ወይም ቤተ ክርስቲያንን ሊያመለክቱ እንደሚችሉ አስተውል። ምሁራን ይህ በራእይ 14፡1-5 የተገለጸው ራእይ የሚፈጸመው በምድራዊቷ የጽዮን ተራራ (ኢየሩሳሌም) ወይም በሰማያዊቷ የጽዮን ተራራ ስለመሆኑ ይከራከራሉ። ነገር ግን ይህ ሰማያዊቷን ጽዮን የሚያመለክት ይመስላል።

ዮሐንስ በዚህ ራእይ ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው በመጽናታቸው የዓለም ሥርዓት ለመከተል የማይፈልጉ፥ የዓለምን የተለያዩ አማልእክት እንዲያመልኩ የሚቀርብባቸውን ጫና የማይቀበሉና ካስፈለገም በእምነታቸው ለመሞት የሚፈቅዱ አማኞች፥ አንድ ቀን የላቀ ሽልማት እንደሚያገኙ ነው። ዮሐንስ ስለተባረኩት ሕዝቦች ምን እንደሚል ተመልከት፡-

ሀ) አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ እነርሱ ብቻ የሚያውቁትን መዝሙር ይዘምራሉ። በእግዚአብሔር አብ ፊት ከዓለም መከራዎችና ስደት ሁሉ ነፃ ሆነው ቆመዋል። ወደ እግዚአብሔር ቀርበው የክብርን ስፍራ አግኝተዋል። ይህን መዝሙር ሊዘምሩ የሚችሉት እነርሱ ብቻ ናቸው። ምክንያቱም መዝሙሩ የወጣው ከስደት ባሻገር ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው በመቆየታቸው ነው።

ለ) አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ ሰውነታቸውን በሴቶች ሳያቆሽሹ ንጹሐን ሆነው ኖረዋል። ይህ እነዚህ አማኞች በወሲባዊ ኃጢአት አለመርከሳቸውን ብቻ ሳይሆን፥ በዓለም ውስጥ ካለው ክፋትና ርኩሰት ሁሉ ራሳቸውን እንደ ጠበቁ የሚያሳይ ተምሳሌታዊ አገላለጽ ይመስላል። በሌላ አነጋገር የተቀደሰ ሕይወት ኖረዋል።

ሐ) ባለማቋረጥ በጉን ይከተሉታል። በምድር ላይ በእምነት ዓይኖቻቸው ክርስቶስን በመከተል፥ ትምህርቱን በማድመጥና ለእምነታቸው መሞት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሳይቀር ቃሉን በመታዘዝ ደቀ መዛሙርቶቹ ሆነው ተመላልሰዋል። አሁን በትንሣኤ አካላቸው ተከብረው በጉ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የቅርብ ግንኙነት (ኅብረት) እያደረጉ ይኖራሉ።

መ) እነዚህ አማኞች ውሸት ያልተገኘባቸውና እንከን የሌላቸው ነበሩ። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ብዙውን ጊዜ መዋሸት የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚያስከትል ኃጢአት መሆኑ ተገልጾአል (ራእይ 21፡8)። ምናልባትም ይህ የሆነው ሰዎች፥ «ቄሳርን ወይም ሐሳዊውን መሢሕ አመልካለሁ» ብለው ከዋሹ በኋላ በልባቸው ክርስቶስን ለማምለክ ሊፈተኑ ስለሚችሉ ይሆናል። ወይም ደግሞ ክርስቲያኖች ነን እያሉ እንደ ዓለማውያን የሚኖሩ ሰዎች በመኖራቸው ምክንያት ይሆናል። እግዚአብሔር ያከበራቸው ሰዎች በክርስቶስ ስላላቸው እምነት እውነቱን ይናገራሉ። በክርስቶስ እናምናለን እያሉ እንደ ዓለማውያን በመመላለስ ሊዋሹም አይፈልጉም። 

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ዮሐንስ በዚህ ራእይ ውስጥ በምድር ላይ ስለምናሳልፈው ሕይወት ለአማኞች ምን ለማስተማር የሚፈልግ ይመስልሃል? ለ) እነዚህ እውነቶች በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ስለመሆናቸው ግለጽ። 

፭. መላእክት ምድርን በፍርድ ያጭዳሉ (ራእይ 14፡6-20)

ዮሐንስ በዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት የተለያዩ የመላእክት ቡድኖችን ይገልጻል። እነዚህም የእግዚአብሔርን ልብና የመጨረሻውን ዘመን ባሕሪ የሚያንጸባርቁትን ተግባራት የሚያከናውኑ ናቸው።

ሀ. ሦስቱ መላእክት (ራእይ 14፡6-13)። ሦስቱ መላእክት እግዚአብሔር፥ የሰው ልጆች ሁሉ ሊያስታውሷቸው የሚገቧቸውን መልእክቶች ያውጃሉ።

  1. የመጀመሪያው መልአክ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ የሚኖሩ ሰዎች ወንጌልን እንዲሰሙ፥ ከሐሰተኛ አምልኮ እንዲመለሱና እውነተኛውን ፈጣሪ አምላክ እንዲያመልኩ የሚፈልግ መሆኑን ያስተምረናል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት እግዚአብሔር አስከፊ ፍርዱንና ዘላለማዊ ቅጣቱን ከማውረዱ በፊት ሰዎች አምነው የሚድኑበትን የመጨረሻ ዕድል ይሰጣቸዋል።
  2. ሁለተኛው መልአክ የባቢሎንን ውድመት ያውጃል። በራእይ 17-18 እንደምንመለከተው፥ ባቢሎን ክፉ የዓለም ሥርዓቶችን በተምሳሌትነት ታመለክታለች። እነዚህ ሥርዓቶች መንግሥታዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ናቸው። ሥርዓቶቹ ክፋትን ለማስፋፋትና የእግዚአብሔር ፍላጎቶችን ለመዋጋት የሚታገሉ ናቸው። እግዚአብሔር ሰዎች እርሱን የሚቃወም እርምጃ በመውሰድ የባቢሎን ተባባሪዎች እንዳይሆኑ፥ ይህን ካደረጉ ግን የሚፈረድባቸው መሆኑን ያስጠነቅቃል።
  3. ሦስተኛው መልአክ ሰዎች የአውሬውን ምልክት እንዳይቀበሉ ያስጠነቅቃል። ለእኛ ይህ የአውሬው ምልክት የእግዚአብሔርን ቃል የሚጻረር ማንኛውም የዓለም ሥርዓት፥ የሰዎች አስተሳሰብና ተግባር ይሆናል (1ኛ ዮሐ.)። በመጨረሻው ዘመን ግን ይህ ምልክት ሐሳዊው መሢሕን የመከተል መግለጫ ነው። ከእግዚአብሔር ይልቅ ሐሳዊ መሢሕን ለመከተል የሚመርጡ ሰዎች ዘላለማዊ ፍርድ ይጠብቃቸዋል። ይህ መመለሻ የሌለው ገደል ነው። ስለሆነም ሰዎች እግዚአብሔርንና የእርሱን ምልክት መምረጥ ይኖርባቸዋል። ከሰይጣን፥ ከሐሳዊ መሢሕና ከነቢዩ ጋር ከወገኑ፥ ከሰይጣንና ከአውሬዎቹ ጋር ወደ ሲዖል ይጣላሉ። አማኞች የዓለምን ምልክት ተቀብለው ከቅጣት ለማምለጥ እንዳይሞክሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን በትዕግሥት ልንጸና፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ተግባራዊ ልናደርግና ታማኞች ሆነን ለክርስቶስ ልንቆም ይገባል። ከአስፈሪው የፍርድ ቀን የምንድነው ያኔ ብቻ ነው።

ለ) ዓለምን በፍርድ የሚያጭዱ ሁለት መላእክት (ራእይ 14፡14-20)። ዮሐንስ በመጨረሻው ዘመን የሚከሰቱትን የተለያዩ ግለሰቦች መመልከቱን አብቅቶ፥ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚያመጣውን የተሟላና የመጨረሻ ፍርድ ያሳየናል። ይህ ፍርድ እግዚአብሔር መንገዱን በማይቀበሉት ላይ የጽድቅ ቅጣቱን እንደሚያወርድ በሚያሳይ መልኩ ጠቅለል ብሎ ቀርቧል። በራእይ 15-18 ግን ከሰባቱ የጽዋ ፍርዶችና ከባቢሎን ጥፋት ጋር ዘርዘር ብሎ ተገልጾአል። ዮሐንስ በሚያምኑ ሰዎች ላይ ስለሚመጣው ፍርድ ለማብራራት ሁለት የመብል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። በመጀመሪያ፥ በራእይ 14፡14-16 ዮሐንስ የአጨዳ ምሳሌ ያቀርባል። በዚህ ስፍራ የተጠቀሰው መልአክ ክርስቶስ ሳይሆን፥ ሌላ ታላቅ መልአክ ይመስላል። ይህ መልአክ በእግዚአብሔር ላይ በሚያምጹ ክፉ ኃይላት ሁሉ ላይ ፍርዱን ያመጣል። (ነገር ግን አንዳንዶች ይህ ራእይ አማኞች ከምድር ላይ ተነጥቀው እንደሚሄዱ ያሳያል ብለው ያምናሉ።) ሁለተኛ፥ በራእይ 14፡17-20 ዮሐንስ የወይን ዘለላዎችን ስለመቁረጥ የሚያወሳውን ምሳሌ ይጠቀማል። ይህ ፍርድ የሚመነጨው በሰማይ ካለ መሠዊያ ውስጥ ነው። ይህ ምናልባትም በራእይ 6፡9-11 እግዚአብሔር እስከ መቼ ፍርዱን እንደሚያዘገይ ስለጠየቁት ሰማዕታት ጸሎት ለማስታወስ የቀረበ ሊሆን ይችላል። አሁን እነዚህ ሰዎች የጸሎታቸውን መልስ ያገኛሉ። የፍርድና የበቀል ቀን ደርሷል።

አይሁዶች የወይን ዘለላዎችን በማጨድ ከቆረጡ በኋላ እነዚህኑ ዘለላዎች ከድንጋይ ተቆፍሮ በተዘጋጁት ጉድጓዶች ውስጥ ያኖሩ ነበር። ከዚያም በእግራቸው ይረግጡታል። በዚህ ጊዜ ጭማቂው ወደ አነስተኛ ጉድጓድ ይከማችና ሰዎች ይጠጡታል። አሁን የእግዚአብሔር መላእክት በዓለም ያሉት ክፉ ሰዎች እንዲታጨዱ አዝዟል። ይህ ፍርድ ምን ያህል ታላቅ እንደሚሆን ለመግለጽ ዮሐንስ ደማቸው ከ300 ኪሎ ሜትሮች የበለጠ ጥልቀት እንደሚኖረው (እስከ ፈረሶች ልጓም እንደሚደርስ) ይገልጻል። አንዳንዶች ይህ በዓለም ላይ የሚካሄደውን የመጨረሻ ጦርነት የሚያመለክት ነው ይላሉ (ራእይ 19)። ነገር ግን ዮሐንስ ይህንን ክፍል ያቀረበው የእግዚአብሔር የመጨረሻው ፍርድ ምን ያህል አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ለማሳየት ይመስላል። 

ዮሐንስ እግዚአብሔር አፍቃሪ አምላክ ብቻ ላይሆን፥ ፈራጅም እንደሆነ ሊያስገነዝበን ይፈልጋል። እግዚአብሔር ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ፥ ወደ እርሱ እንዲመለሱና ልጆቹ እንዲሆኑ በትዕግሥትና በምሕረት ይጠባበቃል። ነገር ግን በትዕቢት እያመጹ ያሻቸውን ሲያደርጉና በእግዚአብሔርና በመንገዶቹ ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የፍርድ ቀን ይመጣባቸዋል። ሰይጣንና ክፉ መላእክት፥ የዓለም መንግሥትና የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተቃውሟቸውን ይገልጻሉ። የእነዚህ ሰዎች ተቃውሞ እርምጃ ለጊዜው የተሳካላቸው ይመስለናል። በመጨረሻው ግን አስከፊውን ፍርድ ከእግዚአብሔር ይቀበላሉ። እግዚአብሔር ጦርነትን፥ መላእክትን፥ ወይም በራእይ 15-16 እንደተጠቀሰው ሌሎች መቅሰፍቶችን ሊጠቀም ይችላል። መጨረሻው ግን ያው አንድ ነው። ይኸውም ኃጢአተኞች የሚቀጡ መሆናቸው ነው። 

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ጥቅሶች ከዓለም ጋር ለመወዳጀትና በተመሳሳይ ጊዜ ክርስቶስን ለመከተል ለሚፈልጉ አማኞች ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: