ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ቃል ነው

የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ጢሞ. 3፡16-17 ና 2ኛ ጴጥ. 1፡20-21 አንብብ። ሀ) እነዚህ ቁጥሮች መጽሐፍ ቅዱስን በማስገኘት ረገድ ስለ እግዚአብሔር ድርሻ ምን ይናገራሉ? ለ) እነዚህ ቁጥሮች መጽሐፍ ቅዱስን በማስገኘት ረገድ የሰው ድርሻ ምንድን ነው ብለው ያስተምራሉ? ሐ) እነዚህ ቁጥሮች እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን ለእኛ የሰጠበት ምክንያት ምንድነው ብለው ያስተምራሉ? መ) መጽሐፍ ቅዱስ በአንተ ሕይወት ውስጥ ለትምህርት፥ ለተግሣጽ፥ ልብን ለማቅናትና በጽድቅ ላለው ምክር እንዴት እንዳገለገለ ግለጥ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው? እንደ ቁርአንና ሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ሁሉ የሰው ሥራ ነውን? ወይስ ሰውን መሣሪያ አድርጎ ሳይጠቀም እግዚአብሔር በቀጥታ ለሰዎች የሰጠው ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ኃይል ያለው የምትሀት መጽሐፍ ነውን? እነዚህ ብሉይ ኪዳንን ማጥናት ከመጀመራችን በፊት ልንመልሳቸው የሚገቡ በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው። ክርስቲያኖችም ሆኑ አይሁዶች ብሉይ ኪዳን የተለየ የእግዚአብሔር ቃልና በውስጡም እግዚአብሔር ራሱንና ዓላማውን ለሰው ልጅ የገለጠበት መጽሐፍ እንደሆነ ይናገራሉ። ክርስቲያኖች ከአይሁዶች የሚለዩት አዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው።

ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ቃል ሁለት የተሳሳቱ ግንዛቤዎች አሉአቸው። የመጀመሪያው፥ ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንዲጻፍ የፈለገውን ቃል ለተለያዩ ሰዎች ቃል በቃል አጽፎአቸዋል ብለው ያስባሉ፤ ስለዚህ አንዳንዶች ብሉይ ኪዳን በሚጻፍበት ጊዜ ጸሐፊዎቹ ምንም ድርሻ አልነበራቸውም ብለው ያስተምራሉ። በዚህ መልክ የተጻፉ አንዳንድ ክፍሎች ቢኖሩም (ለምሳሌ ዘጸ. 24፡4-7)። እነዚህን የብሉይ ኪዳን ክፍሎች የጻፉት ጸሐፊዎች ግን የሚጽፉት ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገባ የቅዱሳት መጻሕፍት አካል መሆኑን እንኳ አያውቁም ነበር። አልፎ አልፎም ጸሐፊዎቹ ከሌሎች መጻሕፍት የቀዱበት አጋጣሚ ነበር (ለምሳሌ፡- ዘኁል. 22፡14-15፤ ኢያ. 10፡13)።

በሁለተኛ ደረጃ፥ እራሳቸውን ክርስቲያን አድርገው የሚቆጥሩ አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያለማሰባቸው ነው። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሥራ እንደሆነ ያስተምራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የአይሁድን ሃይማኖታዊ ልምምድ ለመረዳት የሚጠቅም እንጂ፥ እውነት አይደለም ብለው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቁርአን ወይም እንደ ሂንዱ እምነት መጻሕፍት ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም የሚናገሩት ሰው እግዚአብሔርን ለማወቅ ያደረገውን ጥረት ነው ይላሉ። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ገና ተጽፎ አላለቀም በማለት ዛሬም ቢሆን «የእግዚአብሔር ቃል» የሚሏቸውን ብዙ የሐሰት ትምህርቶች (ኑፋቄዎች) በመጨመር ላይ ይገኛሉ። የእነዚህ ትምህርቶች አመንጪ የሆኑት ሰዎች አሳባቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል በመቁጠር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያክላሉ፤ (ለምሳሌ፡- የይሖዋ ምስክሮች፥ የክርስቲያን ሳይንስ አማኞች፥ የሞርሞን ተከታዮች፥ ወዘተ)።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ የተሳሳቱ አሳቦች በመኖራቸው፥ እምነታችን የተመሠረተውም በእርሱ ላይ በመሆኑ፥ ክርስቲያን የሆንነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማመን ያለብን ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ አሳብ ሊኖረን ያስፈልጋል። ስለዚህ ጉዳይ አጭር አሳብ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

  1. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በ2ኛ ጢሞ. 3፡16 እና 2ኛ ጴጥ. 1፡19 መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ እንደሆነና ጸሐፊዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው እንደጻፉት እናነባለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ራሱ በግልጥ ይናገራል፤ ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ነገሮች እናምናለን፡-

ሀ. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሙሉ ሥልጣን አለው። የእግዚአብሔርን ቃልና ፍላጎቶች ይዟል፥ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ እግዚአብሔር በመካከላችን ያለና የሚናገረን ያህል ነው። እግዚአብሔር የተናገረውም የተጻፈውም ቃሉ እኩል ሥልጣን አላቸው። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔርን ቃል ስለ መስበክም ሆነ ስለ ማስተማር ይህ ምንን ያስተምረናል? ለ) ሥልጣኑ ያለው የት ላይ ነው? (ኢሳ. 55፡11 ተመልከት)። 

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ መሆናችን መጠን ሥልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ እንደሆነ ማስታወስ አለብን። የእኛ ቃላት ሥልጣን የሌላቸውና ስሕተት ሊገኝባቸው የሚችሉ ናቸው፤ ስለዚህ በምንሰብክበትና በምናስተምርበት ጊዜ የእኛ ኃላፊነት ሰዎች የእኛን አሳብ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ አንዳች ስሕተት በግልጥ ማወጅ ነው (2ኛ ቆሮ. 4፡1-5፤ 2ኛ ጢሞ. 2፡15 ተመልከት)። ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሚሰሙበት ጊዜ ሥልጣኑና ኃይሉ ሕይወታቸውን ይለውጠዋል።

ለ. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርም የሰውም ሥራ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማስገኘት እግዚአብሔር ሰዎችን በመሣሪያነት በመጠቀም በራሳቸው ቃላትና የአስተሳሰብ መንገድ እንዲጽፉት አደረገ፤ ነገር ግን የጻፉት ቃል ውጤት ብሉይ ኪዳንን ጨምሮ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ኢየሱስ እንዳለው በመጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የምታንሰው ፊደል ወይም ነጥብ እንኳ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ስለ ተጻፈ ሳይፈጸም አያልፍም (ማቴ. 5፡18 ተመልከት)። 

ሐ. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሥራ ስለሆነ አንዳችም ስሕተት የለበትም። እግዚአብሔር ሊዋሽና ስሕተት ሊሠራ ጨርሶ እንደማይችል ሁሉ (ዕብ. 6፡ 18) ቃሉም አይዋሽም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ ከሚያስተምረው ነገር ጋር የማይስማማ ማንኛውም ዓይነት አመለካከት ስሕተት ነው። እውነት ምን እንደሆነ የሚተረጉመው የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በማንኛውም ጊዜ እኛም ሆንን ሌሉች የአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እውነትነት በሚመለከት መጠየቅ ስንጀምር፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንፈርዳለን፥ በእግዚአብሔር ላይም ፈራጆች ሆንን ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሥልጣን አለው እያልን ትክክል መሆን አለመሆኑን መጠየቅ አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት ካለው በሕይወታችን ላይ ምንም ሥልጣን ሊኖረው አይችልም።

ይሁን እንጂ ይህንን ዐረፍተ ነገር በመጠኑ ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ በቅጅዎቹ ሳይሆን በመጀመሪያው አንዳችም ስሕተት የለበትም። ይህም ማለት ሙሴ፥ ዳዊት፥ ጳውሎስ ወይም ሉቃስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲጽፉ ሙሉ ለሙሉ የእግዚአብሔር ቃልና አንዳችም ስሕተት የሌለበት ነገር ጽፈዋል፤ ነገር ግን ሌሎች ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሚገለብጡበት (በሚቀዱበት) ጊዜ አንዳንድ ስሕተቶች ነበሩ ማለት ነው። በጥንት ዘመን በርካታ መጻሕፍትን ለማባዛት የሚያስችሉ ማተሚያ ቤቶች እንዳልነበሩ ማስታወስ ያስፈልጋል። ዛሬ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በሚታተምበት ጊዜ የሆሄያት ስሕተት ሊኖር ይችላል፤ ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት በእጅ ሲጻፉ በዘመናት ሁሉ የነበሩ ጸሐፊዎች አንዳንድ ስሕተቶችን ሠርተዋል፥ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ባሉት በርካታ ትርጉሞች ውስጥ ተርጓሚዎቹ አንዳንድ ጥቅሶችን በተለየ መንገድ ሊተረጉሙ እንደሚችሉ በመግለጥ የግርጌ ማስታወሻዎችን ጽፈዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ማር.16ን በአዲሱ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተመልከት። ከ9-20 ስላሉት ቁጥሮች በገጹ በስተግርጌ ላይ ምን ተጽፏል?

ይህንን ሐቅ ለመረዳት ያስቸግራል። በአሁኑ ዘመን፣ የመጀመሪያዎቹ ጹሑፎች የትኞቹ እንደነበሩ ለመወሰን ዐብይ ሥራቸው አድርገው የያዙት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አሉ። በሺህ የሚቆጠሩ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቅጂዎችን በመመልከት፣ የመጀመሪያው ቃል የቱ እንደነበር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመወሰን ይታገላሉ። የእነዚህ ምሁራን ሥራ ያላለቀ ስለሆነና እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላሉ ጥቅሶች መቶ በመቶ እርግጠኞች መሆን ባንችልም፥ ሆኖም ግን ምሁራኑ የሚከተሉትን ነገሮች ይነግሩናል። 

  1. መጽሐፍ ቅዱስ ከማንኛውም ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ በተሻለ ሁኔታ ተጠብቋል፤ ምክንያቱም አይሁዶችና ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያምኑ ስለነበር በትክክል ሊገለብጡት ይችሉ ዘንድ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል፤ ስለዚህ ከቁርአንም ሆነ ከማንኛውም ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ በተሻለ ሁኔታ ትክክለኛነቱ የተጠበቀ ነው። ደግሞም በሚጽፉበት ጊዜ ጸሐፊዎቹን የመራቸው መንፈስ ቅዱስ በመሆኑ፥ ቅጂዎቹ ለዘመናት በሚጻፉበት ጊዜ ሁሉ ጉልህ ስሕተት እንዳይፈጽሙ ረድቶአቸዋል። 
  2. በተለያዩ ቅጂዎች መካከል ያሉት ልዩነቶች በአንድነት ሲታዩ፥ የአጠቃላዩ መጽሐፍ ቅዱስ ትንሽ ክፍል ናቸው። በሁሉም ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ስምምነት ስላለ፥ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ዘጠና ከመቶ በላይ (90%) ከመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር አንድ ዓይነት እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። 
  3. በቅዱሳት መጻሕፍት ቅጂዎች መካከል ያለው ማንኛውም ልዩነት በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ትምህርት ላይ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም። ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ክርስቶስ ወይም ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት፥ ስለ ድነት (ደኅንነት) መንገድ፥ ወዘተ ባለን ግንዛቤ ላይ የሚያመጡት አንዳችም ለውጥ የለም፤ ልዩነቶቹ እምነታችንን የሚለውጡ አይደሉም (ለምሳሌ በዕዝ. 2፡3-70 እና በነህ. 7፡6-73 ያሉትን ዝርዝሮች አነጻጽር። በእነዚህ ሁለት ዝርዝሮች ውስጥ ያሉትን ልዩነቶች ጥቀስ)።

መ. መጽሐፍ ቅዱስ በነገሮች ሁሉ ላይ የመጨረሻው ባለሥልጣን ነው። እግዚአብሔር ማን እንደሆነ፥ ቀድሞ ምን እንዳደረገና ወደፊትም ምን እንደሚያደርግ፥ እንዲሁም ከፍጥረቱ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ በመናገር ረገድ የመጨረሻው ባለሥልጣን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሌሎች እምነቶችና ልምምዶች በሙሉ መመዘን ያለባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት የሚቃወም ማንኛውም ነገር ሊወገድ ይገባል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንደ እግዚአብሔር ቃል ስሕተት ቢሆንም፥ በሰዎች ዘንድ ግን እንደ መልካም የሚቆጠር አንድ ምሳሌ ከሕይወት ልምድህ ወይም ከምትኖርበት ባሕል ጥቀስ። ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ሐሰተኛ ትምህርትን ለማሸነፍ ወይም እግዚአብሔር ከሰዎች ሕይወት የሚጠብቀው ነገር ምን እንደሆነ ለማስረዳት መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ ሁኔታ በንቃት ልትጠቀምበት የምትችልባቸውን መንገዶች ጥቀስ።

ሠ. የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ፈቃዱ ልናውቀው የሚገባንን ሁሉ መንገር እንጂ እውነቶችን ሁሉ ማሳወቅ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አሳብ የማይሰጥባችውና ዳሩ ግን ልናውቃቸው የምንፈልጋቸው በርካታ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር ዓለምን እንዴት እንደ ፈጠረ በግልጥ ለማወቅ እንጠይቅ ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለዚህ በቂ ገለጣ አይሰጠንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት እንድንራመድ የሚያስችሉን ነገሮች በሙሉ ተጠቅሰዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ እምብርት እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ እግዚአብሔር ማን እንደሆነ፥ ምን እንደሠራና ከሰው ምን እንደሚፈልግ መግለጥ ነው፤ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ ተቀዳሚው ትኩረታችን በእግዚአብሔር ላይ መሆን አለበት። እርሱንና ፈቃዱን በበለጠ ለመረዳት መጣር አለብን። እግዚአብሔርን እያወቅንና በትእዛዙ ብቻ ስንሄድ እንባረካለን። 

የውይይት ጥያቄ፡- ዳን. 11፡31-32 አንብብ። እግዚአብሔርን ለሚያውቁት የተሰጣቸው ተስፋ ምንድነው?

ረ. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ሊመለክ ግን አይገባውም። እኛ የምናመልከው እራሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገለጠውን እግዚአብሔርን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን አይደለም። ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ምትሐት ወይም ኃይል የለውም ማለት ነው። እንደ መድኃኒት ልንጠቀምበት አይገባም። ለምሳሌ፡- አንዳንድ ሰዎች አንድ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያጽፉና በአንገታቸው ላይ ያደርጋሉ፤ ከአደጋ ግን አይጠብቃቸውም፥ ወይም ቁስል ላይ ቢደረግ ፈውስ አይሰጥም። የመፈወስና የመጠበቅ ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ በግዑዝ አካልነቱ የተለየ ኃይል እንዳለው የሚያምኑ ክርስቲያኖች አሉን? ለ) እንዴት አድርገው ይጠቀሙበታል? ሐ) ይህ ስሕተት የሆነው ለምንድን ነው? መ) የእግዚአብሔር ቃል ዓላማ ምንድን ነው?

ሰ. መጽሐፍ ቅዱስ አንዳች ስሕተት የሌለበትና የተሟላ የእግዚአብሔር ቃል ነው። የአዲስ ኪዳን መደምደሚያ የሆነው የዮሐንስ ራእይ፥ ለመጽሐፍ ቅዱስም የመጨረሻው መጽሐፍ ነው (ራእይ 22፡18-20 ተመልከት)። የምንጽፈው ወይም የምንናገረው ነገር እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት የሌለበት ነው ልንል አንችልም። ይህ ማለት፡-

  1. ማንም ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚጨመር ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ የሚያደርግ ሌላ መጽሐፍ ጽፌአለሁ ሊል አይችልም። ሌላ ወንጌል ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው መጽሐፍ አለኝ የሚል ሰው ተሳስቶአል።
  2. አንድ ሰባኪ በሚሰብክበት ጊዜ ወይም አንድ ጸሐፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ወይም ለጥናት የሚያገለግል መጽሐፍ በሚጽፍበት ጊዜ፥ በተቻለው መጠን ትክክል የመሆን ሐላፊነት ያለበት ቢሆንም የሚናገረውና የሚጽፈው ነገር ስሕተት ሊኖርበት ይችላል። መጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን የጻፉ ሰዎች የነበራቸው ሥልጣንና ብቃት ሊኖረው የሚችል ሌላ ተናጋሪ ወይም ጸሐፊ ጨርሶ ሊኖር አይችልም። 

የውይይት ጥያቄ፡- ይህ እውነት ለሰባኪዎችና ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጻሕፍት ጸሐፊዎች ምን ማስተማር አለበት?

በምንሰብክበትና በምንጽፍበት ጊዜ ሁሉ በአእምሮአችን ልናስታውሳቸው የሚገባን ሁለት ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው እየሰበክን ወይም እየጻፍን ያለነው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ሁልጊዜ የማስታወስ አስፈላጊነት ነው፤ ስለዚህ ዓቅማችን የፈቀደውን ያህል ትክክለኛ ሥራ ለመሥራት መጣር አለብን። ይህ ማለት ከመስበካችን ወይም ከመጻፋችን በፊት በሚገባ ልናጠናውና በምንሰጠው ትርጉም ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ማለት ነው። ሁለተኛው ሰባክያን፥ አስተማሪዎች እንዲሁም ጸሐፊዎች እንደመሆናችን መጠን ትሑታን መሆን አለብን። በምድር ላይ ሳለን እውቀታችን ከፊል መሆኑንና ሁልጊዜ ትክክለኛ ሊሆን እንደማይችል እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ማስታወስ አለብን (1ኛ ቆሮ. 13፡12 ተመልከት)። ስለዚህ ሰዎች አንድን ክፍል የተረዱበት ሁኔታና ለእርሱም የሰጡት ትርጉም ከእኛ የተለየ ሲሆን እውነትን ሁሉ በሚገባ አለማወቃችንን በትሕትና ልንቀበል፥ የሌሎችን ሰዎች አተረጓጎም ለማዳመጥና በእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ብርሃን ለመመርመር ፈቃደኞች መሆን አለብን። የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጥ ትምህርት የሚቃወም ማንኛውም ነገር ስሕተት መሆኑ እርግጥ ነው፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ግልጥ የሆነ ትምህርት የማይሰጥባቸውን ርእሶች በሚመለከት ትሕትና ልናሳይና ለሌሎችም ሰዎች የተለየ አመለካከት እንዲኖራችው ልንፈቅድ ይገባል።

ብሉይና አዲስ ኪዳንን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን ካመንን፥ አንድ ሌላ ነገር ግልጥ ሆነ ማለት ነው። አዲስ ኪዳን በመጻፉ ስለ እግዚአብሔርና በሕይወታችን ውስጥ ስላለው ፈቃዱ ልናውቀው የሚገባን ነገር ሙሉ ሆኖአል ማለት ነው። ክርስቲያኖች ስለዚህ «አዲስ እውቀት» መፈለግ የለባቸውም። ይልቁንም እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በገለጠው መሠረት ከእርሱ ጋር ያለንን ኅብረት ለማጽናት፥ በቃሉ ውስጥ ፈቃዱ እንደሆነ በግልጥ ያሳየንን ነገር ልንታዘዝ ይገባል። ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ኅብረት እያደግን ስንሄድ አስደናቂ እውነቱን እንድንረዳ ማስተዋልንና ጥበብን አብዝቶ ይሰጠናል።

እነዚህ እውነቶች ስለ ብሉይ ኪዳን ምን ያስተምሩናል? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን መገንዘብ አለብን፤ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ማጥናት የእኛ ኃላፊነት ነው። አምላካችን ማን እንደሆነና ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ አለብን። ስለዚህ የምንወደውንና የምናውቀውን ክፍል ብቻ ሳይሆን ብሉይ ኪዳንን በሙሉ ማጥናት አለብን። ኦሪት ዘሌዋውያን የመዝሙረ ዳዊትን ያህል ወይም ትንቢተ ሕዝቅኤል የ1ኛ ሳሙኤልን ያህል የእግዚአብሔር ቃል ነው። እያንዳንዱ መጽሐፍ ስለ እግዚአብሒርና ስለ ፈቃዱ የተወሰነ ነገር ያስተምረናል፤ ስለዚህ ከምንወደው ክፍል ብቻ ሳይሆን፥ ከሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ልናጠናና ልናስተምር ያስፈልጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ጊዜ የማናጠናቸውንና የማንሰብካቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዘርዝር። ለ) የእግዚአብሔር ሰዎች ብዙውን ጊዜ እነዚህን መጻሕፍት የሚያልፉአቸው ለምንድነው? ሐ) ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተሟላ አሳብና ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ቃሉን በሙሉ በቤተ ክርስቲያናችን ልናጠና የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? መ) የእግዚአብሔርን ፈቃድ በከፊል ሳይሆን በሙሉ መረዳት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading