የብሉይ ኪዳን ቅጂዎቻችን እንዴት ሊደርሱን እንደቻሉ

እኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን የምናምነው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነው። የእግዚአብሔርን ሙሉ ሥልጣን የያዘ ከመሆኑም ሌላ ክርስቲያን እውነትን የሚረዳበት መሠረት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ማንነቱን፥ ሰው ማን እንደሆነ፥ ከዘላለማዊ አምላክም ጋር ግንኙነት ለማድረግና እርሱን ደስ ለማሰኘት ምን ማድረግ እንዳለበት አስፈላጊውን እውነት ሁሉ እንደገለጠ እናምናለን። ዳሩ ግን ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ሌላም እውነት ገልጾልናል። ይህም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የምናምነው እውነት አንዳችም ስሕተት የሌለበት የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚል ነው። ዛሬ በእጃችን የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው ዋና ዋና ትምህርቶች ምንም ስሕተት የሌለባችው ቢሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በመገልበጥ ረገድ የታዩ አንዳንድ ስሕተቶች እንዳሉ እንገነዘባለን። ዛሬ በእጃችን ስላለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ጥቂት ነገሮችን እናጠናለን።

ብሉይ ኪዳን ረጅም ዕድሜ ያለው መጽሐፍ ነው። በ1400 ዓ.ዓ. አካባቢ ሙሴ የመጀመሪያዎቹን አምስት መጻሕፍት መጻፍ ጀመረ። ይህም ከ3500 ዓመታት ያህል በፊት ማለት ነው። የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ የተጻፈው በ400 ዓ.ዓ. ገደማ ነበር፤ ስለዚህ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ ተጽፈው ለማለቅ 1000 ዓመታት ያህል ወስደዋል። በሌላ በኩል አዲስ ኪዳን ተጽፎ ያለቀው በ100 ዓ.ም. ነው። የአዲስ ኪዳን ዕድሜ በ2000 ዓመታት ያነሠ ነው፤ ስለዚህ አዲስ ኪዳንን በመገልበጥ ረገድ የተሠራው ስሕተት በብሉይ ኪዳን ከተሠራው ስሕተት ያነሰ ነው፤ ደግሞም ምሁራን የመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከተጻፉ በኋላ በ150 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተሠርተው የነበሩ ቅጂዎችን በከርሰ ምድር ጥናት አማካኝነት አግኝተዋል፤ ስለዚህ ምሁራን ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይበልጥ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ችለዋል። ምሁራን ያገኙአቸው አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች የመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት ከተጻፉ ከብዙ መቶዎች ወይም ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ የተገለበጡ ናቸው፤ ስለዚህ ከአዲስ ኪዳን ይልቅ በርካታ ስሕተት የመፈጸም ዕድል ያለው በብሉይ ኪዳን ውስጥ ነው።

በጥንቱ ዓለም የጽሕፈት መኪናዎች፡ የጽሑፍ ማባዣዎችም ሆነ ወረቀት አልነበሩም። መጻሕፍት ሁሉ በእጅ መጻፍ ነበረባቸው። በጥንት ዘመን ሰዎች ለመጻፍ ይጠቀሙ የነበረው በተለያዩ ነገሮች ነበር። አንዳንዶች እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ትእዛዝን በሚሰጥበት ጊዜ እንደተጠቀመው በድንጋይ ይጠቀማሉ (ዘጸ. 24፡12፤ 31፡18፤ ኢያ. 8፡32-35 ተመልከት)። ሌሉች በእርጥብ ሸክላ ላይ ይጽፉ ነበር። እርጥቡ ሸክላ ሲደርቅ በላዩ ላይ የተጻፈው ነገር ቋሚ ሆኖ ይቀራል። ሌሉች በእንስሳት ቆዳ ላይ ይጽፉ ነበር። በኋላ ደግሞ ሰዎች ፓፒረስ ተብሎ በሚጠራ ከሸምበቆ በተሠራ ነገር ላይ ይጽፉ ነበር። በድንጋይና በሸክላ የተጻፉት ነገሮች ለብዙ መቶ ዓመታት የቆዩ ቢሆኑም በእንስሳት ቆዳና በፓፒረስ የተጻፉት ግን ጊዜያዊና የሚበሰብሱ ነበሩ፤ ስለዚህ በሚያረጁበት ጊዜ ተገልብጠው ሌላ ቅጂ ሊዘጋጅላቸው ያስፈልግ ነበር። ሰዎች ለራሳቸው የግል ቅጂ እንዲኖራቸው ሲፈልጉም በእጃቸው በመጻፍ ሊገለብጡት ያስፈልግ ነበር። አይሁድ ብዙ ጊዜ የሚጽፉት በእንስሳት ቆዳ ላይ ሲሆን፥ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በብራና ጥቅል ላይ ይጻፍ ነበር። (ለምሳሌ ሉቃ. 4፡16-21)። 

በጥንት ዘመን ብዙ ሰዎች ማንበብ አይችሉም ነበር። ጸሐፍት የተባሉ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ማንበብና መጻፍ ይችሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ደብተራዎችን የሚመስሉ ነበሩ። እነዚህ ጸሐፍት ለጥንታዊቷ እስራኤል በጣም አስፈላጊ ሰዎች ነበሩ። ለነገሥታቱ ልዩ አማካሪዎች በመሆናቸው፥ እንደ ዲፕሉማትና አምባሳደር ሆነው ወደ ሌሉች አገሮች ይላኩ ነበር። ለአይሁድ ግን ከሁሉ የሚበልጠው የእነዚህ ሰዎች ሥራ ቅዱሳት መጻሕፍትን መገልበጣቸው ነበር። ቅዱሳት መጻሕፍቱ ይቀመጡ የነበሩት ሰዎች በሚያመልኩበት በቤተ መቅደስ ስለነበር፥ በጥንቷ እስራኤል ጸሐፍቱ የአምልኮ መሪዎች የሆኑት ካህናትና ሌዋውያን ነበሩ። እነዚህ የጥንት ጸሐፍት የእግዚአብሔር ቃል ቅዱስ መሆኑን ያውቁ ስለነበር፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥንቃቄ ይገለብጡ ነበር። በ586 ዓ.ዓ. የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከተደመሰሰና እስራኤላውያን በአሕዛብ መካከል ከተበተኑ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይገለብጡ የነበሩ ጸሐፍት ለአይሁድ ሕዝብ በጣም አስፈላጊ ሰዎች ሆኑ። እንደ ዕዝራ ያሉ ካህናት ጸሐፍት የሃይማኖት ሰዎች ሆኑ። እነዚህ ጸሐፍት (አንዳንድ ጊዜ «የሕግ መምህራን» ይባሉ የነበሩ) ኢየሱስ በኖረበት ዘመን በሕዝቡ ላይ ታላቅ ሥልጣን ያላቸው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኑ። የኢየሱስ ጠላቶችም ነበሩ (ማቴ. 12፡38-39 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ለመጠበቅ አይሁድ ያደረጉት ነገር ወይም ሁኔታ ከጥቂት ትውልድ በፊት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያ ያደርጉት ከነበረው ሁኔታ ጋር እንዴት ይመሳሰላል?

በ586 ዓ.ዓ. የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እስከተደመሰሰበት ጊዜ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን በመገልበጥ ረገድ ስሕተት ለመሥራት የሚያደርስ በቂ ምክንያት አልነበረም። ዋናው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ያለው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበር። እንደ እስራኤል ነገሥታት ያሉ አንዳንድ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ቢገለብጡም (ዘዳግ. 17፡18፤ 2ኛ ነገሥት 11፡12 ተመልከት)፤ ዛሬ በእጃችን እንዳለው የእግዚአብሔር ቃል በበርካታ ቁጥር አልነበረም። የእስራኤል ሕዝብ በዓለም ሁሉ በተበተኑበት ጊዜ ግን የተለያዩ ቅጅዎችና ትርጉሞች መኖር አስፈላጊ ሆነ። ለምሳሌ፡- እንደ ዳንኤልና ሕዝቅኤል ያሉ ሰዎች በባቢሎን ነበሩ። በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ አይሁድ የራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ማግኘት አስፈለጋቸው። ብዙዎቹ አይሁድ በኋላ ወደ እስራኤል ቢመለሱም፥ ሌሎች በርካታ አይሁድ በባቢሎን ቀሩ። በባቢሎንም ሆነው ቅዱሳት መጻሕፍትን መገልበጥ ቀጠሉ። በባቢሎንና በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ጸሐፍት ቅጂዎቻቸውን ለማወዳደር ዕድሉ አልነበራቸውም፤ ስለዚህ በየስፍራው ባሉት ቅጂዎች መካከል ልዩነቶች መታየት ጀመሩ። ደግሞም በ200 ዓ.ዓ. አንዳንድ አይሁድ በግሪክ ቋንቋ የእግዚአብሔር ቃል አስፈለጋቸው። በግብፅና በሌሎች አካባቢዎች ስለኖሩና መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ስለረሱ በሚናገሩት በግሪክ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ አስፈለጋቸው፤ ስለዚህ ምሁራን ብሉይ ኪዳንን ወደ ግሪክ ቋንቋ ተረጎሙት። ይህም ትርጉም ሴፕቱዋጀንት በመባል ይታወቅ ጀመር። ክርስቶስ በኖረበት ዘመን ሴፕቱዋጀንት እጅግ ተወዳጅ ቅዱስ መጽሐፍ ሲሆን፥ ብዙ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችም ከዚህ ትርጉም ይጠቅሱ ነበር፤ ስለዚህ ሦስት ዋና ዋና የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች አሉን። እነርሱም በኢየሩሳሌም የነበረው፥ በባቢሎን የነበረውና በግሪክ ቋንቋ የተጻፈው ናቸው፡፡ በሌሉች ስፍራዎች የነበሩ ሰዎችም የየራሳቸውን ቅጅ መገልበጥ ጀመሩ። ለምሳሌ:- ሳምራውያን አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት (ፔንታቱክ) ለራሳቸው አምልኮ ገለበጡ፤ ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን በርካታ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች ሲኖሩ፥ ማንም ሰው በቅጂው ውስጥ ስሕተት እንደነበረና እንዳልነበረ ለማወቅ አላወዳደረም፤ ስለዚህ በትርጉሞች ውስጥ ስሕተቶች እየጨመሩ መጡ። የትርጉሞች ወይም የቅጂዎች ስሕተቶችም እየጨመሩ የመጡት ጸሐፊዎቹ በሚገለብጡበት ጊዜ በሠሩት ስሕተት ምክንያት ነው።

የመጻሕፍቱን ቅጂዎች በመገልበጥ እንዴት ስሕተቱ ሊፈጸም እንደሚችል የሚከተለውን መግለጫ እንመልከት፡- የማዕከላዊው ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት በየአውራጃው ለሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤቶች አንድ ደብዳቤ እንደላከ አስብ። በደብዳቤውም ውስጥ የተወሰኑ መመሪያዎችና ደንቦች ነበሩ። እነዚህ የአውራጃ አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ደብዳቤ በእጃቸው ገልብጠው ለወረዳ አብያተ ክርስቲያናት ቢሮዎች ይልካሉ፤ የወረዳ አብያተ ክርስቲያናት ቢሮዎች ደግሞ ይህን ደብዳቤ በእጃቸው ገልብጠው ለየአብያተ ክርስቲያናት ቢሮዎች ይልካሉ። እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ደብዳቤዎችን በእጁ ገልብጦ ለየአባላቱ ማደል ነበረበት እንበል። ይህን ነገር ማድረግ ቢኖርብን በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሆኑ ሁለት ዋና ነገሮች ሲፈጸሙ እናይ ነበር። የመጀመሪያው፥ በእጅ በመገልበጥ ረገድ ስሕተት መታየት መጀመሩ ነው። ሰዎች በእጃቸው በመጻፍ በሚገለብጡበት ጊዜ አንዳንድ ፊደላትን ወይም ቃላትን ይተዋሉ። ደብዳቤው ከማዕከላዊው ቢሮ ማለትም መጀመሪያ ከተጻፈበት ቦታ እየራቀ በሄደ ቁጥር የስሕተቱ መጠን እየጨመረ ይሄዳል። ሁለተኛው፥ ስሕተቶቹ አንድ የተወሰነ መንገድ የሚከተሉ መሆናቸው ነው። አንድ የአውራጃ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት ከማዕከላዊ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት የመጣውን ደብዳቤ በሚገለብጥበት ጊዜ አንድ ቃል ቢተው ከዚያ አውራጃ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ የሚደርሳቸው የወረዳ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤቶች ሁሉ ተመሳሳይ ስሕተት የያዙ ይሆናሉ። ይህም ስሕተት ያንን ቃል ያለመያዝ ይሆናል። 

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተለያዩ ስፍራዎች በእጅ ጽሑፍ በሚገለበጡበት ጊዜም የተሠራው ስሕተት ይህንኑ የመሰለ ነበር፤ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ያደረጉት አንድ ዋና ነገር ስሕተቱ ከየት እንደመጣ ለማወቅ የተገኙትን የተለያዩ ቅጂዎች ማወዳደር ነበር። በኢየሩሳሌም የተገለበጡትን መዛግብት ከባቢሎን፥ ከግሪክ እንዲሁም በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሚገኘው የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሁሉ ያመሳክራሉ። በዚህ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ከመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር የበለጠ የሚቀራረበው የትኛው እንደሆነ ለመወሰን የማያቋርጥ ጥረት እያደረጉ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይህን በማድረግ ረገድ እርስ በእርስ ያልተስማሙበት ነገር ስለሚኖር ዛሬ በእጃችን ባሉ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል የትርጉም ልዩነት ሊኖር ቻለ።

በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ አብዛኞቹ ቅዱሳት መጻሕፍት የተመሠረቱት ማሶሬቲክ በአይሁዶች በመባል በሚታወቁ አንዳንድ አይሁዳዊያን በተዘጋጀው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው። እነዚህ አይሁድ የኖሩትና የሠሩት ከ500-900 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜ ያገኙትን ሁሉንም መጽሐፍ ቅዱስ ወስደው የበለጠ ትክክል ነው ብለው ያሰቡትን ቅጂ ጻፉ። የላቲኑ (የሮማ ካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስና) በአሁኑ ጊዜ ብዙ የምንጠቀምባቸው ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች የተተረጎሙት በእነዚህ አይሁድ ሥራ ላይ በመመሥረት ነው። እንደ ሶርያ፥ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስና የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ምንጫቸው ሴፕቱዋጀንት የተባለው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ሴፕቱዋጀንት ማለት ሰባ ማለት ነው። ይህ ስም የተሰጠው ብሉይ ኪዳንን ሰባ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በሰባ ቀናት ውስጥ ተርጉመውታል ተብሎ ስለሚታመን ነው)። ይህም ዛሬ በምንጠቀምበት በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዴት መጠነኛ ልዩነት እንዳመጣ በኋላ እንመለከታለን።

በ1948 ዓ.ም. የከርሰ ምድር አጥኚዎች በእስራኤል ውስጥ ሙት ባሕር በሚባለው አካባቢ ባለ ዋሻ ውስጥ በ200 ዓ.ዓ. የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍትን አገኙ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እነዚህን ቅዱሳት መጻሕፍት (የሙት ባሕር ብራናዎች በመባል የታወቁትን) አሁን በእጃችን ከሚገኙ ቅጂዎች ጋር ሲያወዳድሩአቸው አንዳንድ ልዩነት ቢያገኙም በተመሳሳይነታቸውና የእግዚአብሔር ቃል በዘመናት ሁሉ በሚገለበጥበት ጊዜ በአንፃራዊነት ሲታይ በተገኘው ጥቂት ስሕተት ተደንቀዋል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እኛ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ለመለወጥ ይቃጣ የነበረውን የተለመደ አዝማሚያ እንደተቋቋመው እናምናለን። ትላንትና እንዳየነው እግዚአብሔር ቃሉን በሚያስደንቅ መንገድ ስለጠበቀው ዛሬ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ስለማወቅና ከእርሱ ጋር እንዴት ግንኙነት እንደምናደርግ የሚያስፈልገንን እንደሚነግረን እርግጠኞች ነን። 

የውይይት ጥያቄ፥ አንድ ሙስሊም መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት የሞላበት ነው፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም ቢልህ እንዴት ትመልስለታለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: