Site icon

የብሉይ ኪዳን ጥናት መግቢያ 

ለመሆኑ ከመንግሥት ወይም ከቤተ ክርስቲያንህ መሪ አንድ ደብዳቤ ቢደርስህ ደብዳቤውን ምን ታደርገዋለህ? ደብዳቤውን ሳታነበው ማስታወሻ ይሆንህ ዘንድ በግድግዳ ላይ ትለጥፈዋለህን? ደግሞም መሪው አንድ ነገር እንድታደርግ ቢጠይቅህ ታደርገዋለህን? ደብዳቤው የተጻፈው ግልጽ በሆነ ቋንቋ ቢሆንም እንኳ፥ ድብቅ የሆነ ትርጉም በመፈለግና የቃላትን ትርጉም በማዛባት የተሳሳተ መልእክት እንዲያስተላልፍ ታደርጋለህ? አታደርግም። ከአገራችን መንግሥት መሪ የተጻፈልን ደብዳቤ ቢደርሰን የምናደርገው የመጀመሪያ ነገር፡- ደብዳቤውን በመክፈት መሪያችን የሚለውን ነገር በጥንቃቄ ማንበብና በደብዳቤው ውስጥ የሚገኙትን ትእዛዛት በሙሉ ለመፈጸም መጣር ነው። መሪው ወዳጃችን ከሆነ ደግሞ ደብዳቤው የበለጠ ደስ የሚያሰኘን ይሆናል።

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከመሪዎች ሁሉ የላቀ ኃይል ካለው መሪ ደብዳቤ የማግኘት ልዩ ዕድል አለን። እርሱ እያንዳንዳችንን እጅግ ይወደናል። ያም መሪ እግዚአብሔር አባታችን ነው። የተጻፈልን ደብዳቤ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የሚያሳዝነው ነገር ብዙዎቻችን ይህንን ደብዳቤ ወይም መጽሐፍ ለማንበብ የምንሰጠው ጊዜ በጣም ጥቂት መሆኑ ነው። ከዚህ የተነሣ ብዙውን ጊዜ መሪያችን እንድናደርግ የሚፈልገውን ነገር አናደርግም። ወይም ስናነብ ብዙ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱሳችን የተደበቀ ትርጉም እንሻለን፤ እግዚአብሔር ሊነግረን የፈለገውን ነገር ትርጉም እንለውጣለን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ያለውን መልእክት እንስታለን።

በዚህ የጥናት መመሪያ አማካይነት እግዚአብሔር በተለይ ለእያንዳንዳችን ከሰጠን መጽሐፍ ውስጥ የተወሰነውን ክፍል እንመለከታለን። ብሉይ ኪዳንን ሰፋ ባለ ሁኔታ ለማወቅ በሚያስችለን መልክ እንመለከተዋለን። በእያንዳንዱ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ዋና ዋና መልእክቶች ለመማር እንፈልጋለን። ደግሞም የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ መንገድ እንዳንረዳውና ከሕይወታችንም ጋር ያለ አግባብ እንዳናዛምደው፥ በትክክል እንዴት እንደምንተረጉመው አንዳንድ መመሪያዎችን እንመለከታለን። በአገራችን የሐሰት ትምህርታቸውን የማረጋገጥ ሙከራ ለማድረግ ሲሉ የእግዚአብሔርን ቃል ትርጉም የሚያጣምሙ በርካታ የሐሰት አስተማሪዎች አሉ፤ ስለዚህ ለእነርሱ መልስ ለመስጠት የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት በትክክል መረዳት እንደምንችልና ሐሰተኛ አሳባቸውን ለመዋጋት እንዴት እንደምንጠቀምበት ማወቅ አለብን፤ (1ኛ ጢሞ. 4፡1-7 ተመልከት)። በተጨማሪም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች ስለ አንዳንዶቹ መጻሕፍትና አተረጓጎም ያላቸውን የተለያየ አመለካከት እናያለን። በእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጻፉ አንዳንድ ትርጓሜዎች ስለእነዚህ የምታነብብ በመሆኑ፥ ተግባራዊ መስሎ ባይታይም ስለ እነርሱ በቅድሚያ ማወቅ መልካም ነው።

የብሉይ ኪዳን ጥናታችን ቢያንስ 40 ሳምንታት ይፈጃል። የዚህ ጥናት ዓላማ አንተን ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋር ለማስተዋወቅ እንዲሁም እውነትን ከሕይወታችን ጋር ለማዛመድ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ያለውን መልእክት በጋራ ለመፈለግ ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንድናውቀው ብቻ ሳይሆን፥ ከሕይወታችን ጋር እንድናዛምደው ጭምር የተጻፈ መሆኑን አስታውስ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ከሕይወታችን ጋር ባናዛምደው፥ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን መንፈሳዊ ጉዞ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል፤ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም እንዝላለን። ይህ ኮርስ ከእያንዳንዱ ተማሪ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከራስህ ጋር ካዛመድከውና ጥያቄዎቹን በሙሉ በመመለስ የቤት ሥራዎቹን ከሠራህ፥ ብሉይ ኪዳንን በተሻለ አኳኋን ትረዳዋለህ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ጉዞም በጥልቀት ያድጋል። በምታውቃቸው ክፍሎች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ለእግዚአብሔር ቃል በአጠቃላይ ፍቅር ይኖርሃል። እንዴት እንደምትጠቀምበትም ታውቃለህ። ሮሜ 15፡4 «በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና» ይላል።

የውይይት ጥያቄ:-  ኤፌ 3:14-19 አንብብ፡፡ ሀ) ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን የጸለየው ጸሎት ምን ነበር? ለ) ይህ ጸሎት በዘመናችን ላሉትም አብያተ ክርስቲያናት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

የጥያቄዎቹን መልስ በደብተር ላይ ጻፍ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ከሌለህ፣ ለዚህ ጥናት እንዲረዳህ ለመግዛት ሞክር፡፡ አዲሱ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምና የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ካሉህ ከእነርሱም ውስጥ አንብብ።

ተማሪውን በጥናቱ ይረዳው ዘንድ እያንዳንዱ ትምህርት በአምስት የየዕለቱ ትምህርቶች ተከፍሏል። የየዕለቱን ትምህርት (ክፍል) በአንድ አፍታ አጥንተህ ለመጨረስ ሞክር። አንዳንዶቹ ትምህርቶች ከሌሎቹ ረዘም ያሉ ስለሆኑ፥ ጠቅላላ ትምህርቱን ከሳምንታዊው ስብሰባ በፊት ለማጠቃለል የሚያስችል በቂ ጊዜ መስጠትህን አረጋግጥ። በትምህርቶቹ ውስጥ በርካታ አጣቃሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ። ስለዚህ «ተመልከት» የሚለውን ጥቅስ ሁሉ ለመመልከት እርግጠኛ ሁን። «ተመልከት» የሚል ቃል የሌለባቸውን ጥቅሶች ጊዜ ካለህ ትመለከታቸዋለህ፤ ወይም በሌላ ጊዜ ታጠናቸዋለህ።

የመጀመሪያዎቹ ሦስት ትምህርቶች ስለ ብሉይ ኪዳን አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶችን ያስተዋውቃሉ። እነዚህ አሳቦች አዲስና አስቸጋሪ ቢሆኑም እንኳ እነርሱን ለመረዳት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። አንዳንዶቹ ትምህርቶች አግባብነት ያላቸው ባይመስሉም እንኳ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በእንግሊዝኛ የተጻፉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ስለሚገኙ፥ እነዚህ ትምህርቶች በነርሱ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ጉዳዮች ለመረዳት ይጠቅሙሃል።

የዚሁ የጥናት መጽሐፍ አንደኛው ግብ መጽሐፉን የሚያጠኑ ሰዎች ሁሉ ብሉይ ኪዳንን ሙሉ በሙሉ እንዲያነቡ ለማበረታታት ነው። ስለዚህ የሚሰጡትን የንባብ ክፍሎች በሙሉ አጠናቅቆ ማንበብ በጣም አስፈላጊ ነው። መጨረሻ በሚሰጠው አጠቃላይ ፈተና ላይ እያንዳንዱ ተማሪ የተጠኑትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ ማንበብ ያለግንበቡን እንዲያሳውቅ ይጠየቃል።

ማሳሰቢያ በዚህ መጽሐፍ ያሉት የዘመን አቆጣጠሮች እንደ ኤውሮጳ አቆጣጠር ናቸው። ዓ.ዓ. የሚለው ምሕጻረ ቃል ዓመተ ዓለም ማለቱ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውን ዘመን የሚያመለክት ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version