የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዴት እንደተሰበሰቡ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ቅደም ተከተል ከአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ቅደም ተከተል ጋር አወዳድር። የተለያየ ቅደም ተከተል ያላቸው መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? ለ) የካቶሊክ እምነት ተከታይን መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲያሳይህ ጠይቀው። ከአንተ መጽሐፍ ቅዱስ ይለያልን? በእነርሱ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ስንት መጻሕፍት አሉ? ሐ) በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ስንት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዳሉ አንዱን የኦርቶዶክስ ቄስ ጠይቅ።

ለመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት የቀድሞ ክርስቲያኖች እንዴት «ብሉይ ኪዳን» የሚል ስያሜ እንደሰጡ ተመልክተናል። ነገር ግን የብሉይ ኪዳን ክፍል መሆን ያለባቸው መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ እንደሆኑ ሊቆጠሩ የሚገባቸው መጻሕፍትስ የትኞቹ እንደሆኑ ክርስቲያኖች ከስምምነት ላይ የደረሱት እንዴት ነው? 

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የተለያዩ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ የእግዚአብሔር ቃል ስለመሆናቸው ይከራከራሉ። እንደምታስታውሰው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፈው የተጠናቀቁት በ1000 ዓመታት ውስጥ ነው። ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዘዳግም ያሉት የመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት የተጻፉት በ1400 ዓ.ዓ. ነው። የመጨረሻ የሆነው መጽሐፍ ትንቢተ ሚልክያስ የተጻፈው በ400 ዓ.ዓ. ነው። በእነዚህ የ1000 ዓመታት ጊዜ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ እግዚአብሔር በተለያዩ ሰዎች ተጠቅሞአል። በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ከክርስቶስ ልደት ወዲህ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ያሉት 39 መጻሕፍት በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት የተጻፉ እንደሆነ እናውቃለን።

የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት በአንድ ላይ ለማቀናጀት ብዙ ደረጃዎችን ማለፍ እንዳስፈለገ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይገምታሉ።

የመጀመሪያ ደረጃ፡- በንግግር የማስተላለፍ ባሕል ነው። የመጀመሪያው ደረጃ የእግዚአብሔርን ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ በንግግር የማስተላለፍ ዘዴ ነው። የእግዚአብሔር ነቢያት በእግዚአብሔር ሕዝቦች ፊት ቆመው «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት የእግዚአብሔርን መልእክት ያስተላልፉ ነበር (ሕዝ.5፡5 ተመልከት)። በዚህ የንግግር ዘዴ ይተላለፉ የነበሩ አንዳንድ መልእክቶች ሳይጻፉ ብዙ ዘመን ሳያልፋቸው አይቀርም። ለምሳሌ፡- ከዘፍጥረት 1-50 ያሉት ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ደግሞ ቶሉ የመጻፍ ዕድል አግኝተዋል።

ሁለተኛ ደረጃ፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተጻፉ። የተለያዩ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አማካይነት የእግዚአብሔርን ቃል በተለያዩ መጻሕፍት ጽፈዋል።

ሦስተኛ ደረጃ፡- አይሁድ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን የተለያዩ መጻሕፍት መሰብሰብ ጀመሩ። ይህ ረጅም ጊዜ የወሰደ ሥራ ነው። ለምሳሌ፡- መዝሙረ ዳዊት በአንድ ላይ ተጠርዞ ለመቀመጥ ብዙ መቶ ዓመታት ወስዶአል። አንዳንዶቹ መዝሙሮች የተጻፉት በ1400 ዓ.ዓ. በሙሴ፥ ሌሎቹ ደግሞ በ500 ዓ.ዓ. በዕዝራ የተጻፉ ናቸው። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በማሰባሰብና በማደራጀት ረገድ ዕዝራ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ብዙ ምሁራን ይገምታሉ።

አራተኛ ደረጃ፡- አይሁድ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው የተቀበሏቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ሰብስበው ቅደም ተከተል በማስያዝ አስቀመጡአቸው። ይህ ማለት አንዳንዶቹን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል እንዳልሆኑ ቆጥረው አገለሉዋቸው ማለት ነው።

አይሁዳውያን እስከ መጀመሪያው መቶ ዓመት መጨረሻ ድረስ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአሁኑ መልካቸው ስለማስቀመጣቸው መረጃ የለንም። ዳሩ ግን ከክርስቶስ መምጣት በፊት 200 ዓ.ዓ. ማለትም የመጨረሻው መጻሕፍት ከተጻፈ ከ200 ዓመት በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው አይሁድ የገመቱአቸውን መጻሕፍት በሙሉ አይሁዳውያን አውቀውና መርጠው እንደነበር የሚገልጥ ማስረጃ አለ።

ይህ ሂደት በጣም የተወሳሰበ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ቃሉን በመጻፍ ሂደት ውስጥ ከሰዎች ጋር የሠራው እግዚአብሔር የተጻፉትን መጻሕፍት ያለአንዳች ስሕተት ሰዎች እንዲለዩ በማድረግ ረገድም እንደሠራ እናምናለን። እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ቃልና ሥልጣን ይዘዋል።

የቀድሞ አይሁዳውያን የእግዚአብሔር ቃል የሆኑትን ክፍሎች ከብዙ መጻሕፍት መካከል ለመለየት የተጠቀሙበት መመዘኛ ምንድነው? በአዲስ ኪዳን ዋናው መመዘኛ፡- «ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በአንድ ሐዋርያ ነው ወይስ አብሮት በሚሠራ ሰው?» የሚል ነበር። የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ለመለየት ግን አራት ዋና ዋና መመዘኛዎች የነበሩ ይመስላል። እነርሱም፡-

  1. መጽሐፉ በውስጣዊ ብቃቱና በመልእክቱ የእግዚአብሔር ሥልጣን እንዳለውና በእርሱ መንፈስ እንደተጻፈ የሚያሳይ ነገር አለን? የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች መጻሕፍቱን በሚመዝኑበት ጊዜ የእግዚአብሔር ጣት እንዳለበት እንዲያዩ መንፈስ ቅዱስ መርቶአቸዋል።
  2. የመጽሐፉ ጸሐፊ እግዚአብሔር በመለኮታዊነቱ መሪ እንዲሆን የመረጠው ሰው ነበርን? ለምሳሌ ንጉሥ፥ ካህን፡ ነቢይ፥ ወይም እግዚአብሔር በኃይል የተጠቀመበት በእስራኤል ላይ የሚፈርድ ሰው ነበርን? 
  3. በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ ትምህርቶች በሙሉ እርስ በእርስና እንዲሁም የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ በታወቀ በሌላ መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙ ትምህርቶች ጋር የሚስማማ ነውን? ለምሳሌ፡-በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ትምህርቶች በመጀመሪያዎቹ አምስት የሙሴ መጻሕፍት ውስጥ እግዚአብሔር ከተናገረው ነገር ጋር የሚስማሙ ናቸውን?
  4. መጻሕፍቱ በአይሁድ የአምልኮ ጊዜ በተግባር ላይ ሊውሉ የቻሉ ናቸውን ወይስ ለሌላ ለተለየ ዓላማ ምንም አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው? እያንዳንዱን መጽሐፍ በእጅ መገልበጥ ከባድ ድካም የሚጠይቅ ስለነበር፥ አይሁዳውያን ይገለብጡ የነበረው የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ያወቁዋቸውና ለእግዚአብሔር በሚሰጡት አምልኮ ውስጥ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉትን ዓይነት ብቻ ነበር።

እነዚህ አይሁዳውያን፥ እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እንዲካተት የፈለገውን ነገር ብቻ መምረጣቸውን እንዴት እናውቃለን? በአንድ በኩል ስናየው፥ ልናውቅ አንችልም። ሰዎች ቃሉን እንዲጽፉ በማድረግ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያደረገው እግዚአብሔር፥ በዓለም ላሉ ሰዎች ሁሉ እንዲደርስ የፈለገው ቃሉ ብቻ ተጠብቆ እንዲቆይ እንዳደረገ ማመን አለብን። በሌላ አንፃር ስናየው ግን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ሁሉ በምንመረምርበትና ዛሬ ካሉ ሌሎች መጻሕፍት ጋር በምናወዳድርበት ጊዜ ልዩነቱን ለማየት እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተካተቱት መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ጥራትና ብቃት ያለው መልእክት የላቸውም። በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እንደ ሌሎቹ መጻሕፍት ሳይሆኑ ምንም ዓይነት ያለመስማማት በማይታይበት ሁኔታ የመልእክት አንድነት ይታይባቸዋል። ሌሎች መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል አለመሆናቸውን የምናየው እርስ በርስ የሚቃረኑ ትምህርቶች ስላሉባቸው ነው። እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን እንዲጽፉ የተጠቀመባቸው የተለያዩ ሰዎች ቢሆኑም የብሉይ ኪዳን የመልእክት አንድነት ግን የሚያስደንቅ ነው። በተለያዩ መጻሕፍት መካከል ያሉ ትምህርቶች የተጻፉት በመቶ ዓመታት ልዩነት ቢሆንም፥ አንዳቸው ከሌላቸው ጋር በማይቃረን ሁኔታ ይስማማሉ። የእግዚአብሔር ልጆች መጻሕፍት እንደመሆናችን መጠን ዛሬ በእጃችን ያሉት ቅዱሳት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። የእግዚአብሔር ሥልጣን ይገኝባቸዋል፤ ስሕተት አያስተምሩም፤ ስለ እውነተኛው እግዚአብሔርና ከእርሱ ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነትም በትክክል ያስተምሩናል። የእግዚአብሔር ቃል የሆነውንና ያልሆነውን የወሰኑት አይሁድ እንዳልሆኑ ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ይልቁንም እግዚአብሔር በእስትንፋሱ የተጻፈውንና በእርሱ መሪነት የተሰጠውን ቃል ለመለየት ሰዎችን ተጠቀመባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የተሟላና አንዳችም ስሕተት የሌለበት የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ፥ ዛሬ እኛ በምንጽፋቸው መጻሕፍትና በምናዘጋጃቸው መልእክቶች ላይ እንዴት ተጽእኖ ያሳድርባቸዋል? ለ) እነዚህስ ጽሑፎቻችንና መልእክቶቻችን «የእግዚአብሔር ቃል» መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ሐ) «መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው» ከምንለው አሳብ ጋር ( የእኛ መልእክት በምን ይለያል?

ዛሬ ሰዎች በሚሰጡት ስብከትና በሚጽፏቸው መልእክቶች አማካይነት እግዚአብሔር የሚናገር ቢሆንም፥ ለእነዚህ ጽሑፎችና ትምህርቶች ስለምንሰጠው የሥልጣን መጠን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። የእግዚአብሔርን ሙሉ ሥልጣን የያዘው፥ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ምንም ስሕተት የሌለበት እርሱ ብቻ ነው። የትኛውም መጽሐፍ ወይም ስብከት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳችም ስሕተት የሌለበት ሊሆን አይችልም። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ያለው መልእክትም ሆነ መጽሐፍ የለም፤ የምንጽፈውም ሆነ የምንናገረው ነገር የሚመዘነው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሰባኪዎችና ጸሐፊዎች እንደመሆናችን መጠን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት የእኛ ሐላፊነት ነው። በመጨረሻ ግን ደካሞችና ኃጢአተኞች መሆናችንን በትሕትና መቀበል አለብን። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን መረዳት ውሱን ነው። ምንም ነቀፋና ስሕተት የለብንም ብለን ለመናገር አንችልም።

የውይይት ጥያቄ፥ ጸሐፊዎች፥ አስተማሪዎችና ሰባኪዎች ይህንን መገንዘብ የሚያስፈልጋቸው ለምንድነው? ክርስቲያኖች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተሟላ መሆኑን ያምናሉ፤ (ራእ. 22፡18-19)። የዮሐንስ ራእይ ከተጻፈ ወዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምንም ዓይነት መጽሐፍ መጨመር አይቻልም። ይህም ማለት ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጨመር ያለባቸው በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት አሉ የሚሉ ዛሬ የተነሡ የሐሰት ትምህርት አራማጅ ክፍሎች ተሳስተዋል ማለት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል አድርገው የሚያስተምሩትም ስሕተት ነው።

በ200 ዓ.ዓ. እይሁድ እንደ እግዚአብሔር ቃል መቆጠር አለባቸው ስለሚሉአቸው መጻሕፍት ግልጽ የሆነ አሳብ ነበራቸው፤ ነገር ግን በቅዱሳት መጻሕፍት የአቀማመጥ ቅደም ተከተል አልተስማሙም ነበር። ጸሐፊዎቹ ሲጽፉ ርእስ አልነበራቸውም። በኋላ ግን በመጽሐፉ የመጀመሪያ ዐረፍተ ነገር፥ ወይም መጽሐፉ የሚናገርለት ዋና ሰው ወይም መጽሐፉን ጽፎታል ብለው ይገምቱ በነበረው ሰው ስም በመሰየም ርእስ ይሰጡት ጀመር። በእንግሊዝኛውም ሆነ በአማርኛው (ግዕዝ) መጽሐፍ ቅዱስ ያሉት መጻሕፍት ርእሶች የተገኙት መጀመሪያ ሴፕቱዋጀንት ከሚባለው የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የላቲን ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት ውስጥ ምዕራፍና ቁጥሮች አልነበሩም። ለመጽሐፍ ቅዱስ የምዕራፍ ክፍፍል የተሰጠው በ1228 ዓ.ም. ሲሆን፥ የቁጥር ክፍፍሎች የተደረጉት ደግሞ በ1547 ዓ.ም. ነበር።

አይሁድ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው ያመኑባቸውን መጻሕፍት ሲያደራጁ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለዋቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሉቃ. 24፡44 አንብብ። ኢየሱስ በዚህ ስፍራ የሚጠቅሳቸው ሦስት የብሉይ ኪዳን ክፍሎች የትኞቹ ናቸው?

በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ አይሁድ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፋፈሉ ሃያ አራት መጻሕፍት ብቻ ነበራቸው። የመጀመሪያው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ክፍል ዛሬ አይሁድ ቶራኽ የሚሉት የሕግ ክፍል ነው። የሕግ መጻሕፍት የመጀመሪያዎቹን አምስት መጻሕፍት ማለትም ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉትን የያዙ ናቸው።

ሁለተኛው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ክፍል ነቢያት በመባል ሲታወቅ፥ በዚህ ክፍል ስምንት መጻሕፍት ይገኛሉ፡- ኢያሱ፥ መሳፍንት፥ ሳሙኤል፥ ነገሥት፥ ኢሳይያስ፥ ኤርምያስ፥ ሕዝቅኤል፡ እንዲሁም 12ቱ ነቢያት ናቸው። ከዚህ የምንመለከተው ሳሙኤል፥ ነገሥት እና 12ቱ ነቢያት (ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ) ራሳቸውን የቻሉ አንዳንድ መጻሕፍት ብቻ የሆኑ ናቸው። በአሁኑ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንዳለው የተለያዩ መጻሕፍት አልነበሩም።

ሦስተኛው ዋና ክፍል «ጽሑፎች» በመባል ይታወቃል። በዚህ ክፍል ውስጥ በሦስት ንዑሳን ክፍሎች የተከፈሉ 11 መጻሕፍት አሉ። በመጀመሪያው ክፍል ሦስት የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት (መዝሙረ ዳዊት፥ ምሳሌና ኢዮብ) ሲገኙ፥ በሁለተኛው ክፍል አምስት ጥቅል መጻሕፍት ነበሩ (መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን፥ ሩት፥ ሰቆቃወ ኤርምያስ፥ መክብብና አስቴር)። በሦስተኛው ክፍል ደግሞ «ታሪክ» ተብለው የሚጠሩ ዳንኤል፥ ከዕዝራ እስከ ነህምያ (አንድ መጽሐፍ)፥ ዜና መዋዕል (አንድ መጽሐፍ) ብቻ ነበሩ። 

ዛሬ በምንገለገልበት መጽሐፍ ቅዱስ 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አሉ። ይህ የሆነው አንዳንድ መጻሕፍት ለሁለት ስለተከፈሉ ነው። ለምሳሌ ዕዝራና ነህምያ አሁን ሁለት መጻሕፍት ናቸው። 1ኛና 2ኛ ሳሙኤል፥ 1ኛና 2ኛ ነገሥት እንዲሁም 1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል ተከፍለዋል። የመጻሕፍቱ ቁጥር በዚህ ዓይነት የተለያዩ ቢሆኑም፥ አይሁዶችና ክርስቲያኖች እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ያምናሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ የመጽሐፍ ቅዱስህን ማውጫ ተመልከት። በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቅደም ተከተል በመጠበቅ ሆሄያቸውን ጭምር በቃል አጥና። 

ነገር ግን የካቶሊክና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ከእኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለምን ተለየ? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ትንቢተ ሚልክያስ ከተጻፈ በኋላ እስከ ኢየሱስ መምጣት ድረስ ወደነበረው ዘመን መመለስ አለብን። ይህ ዘመን 400 «የጸጥታ ዘመናት» በመባል ይታወቃል፤ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ እስከ ሚልክያስ ዘመን እንደነበረው በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው የእግዚአብሔርን ቃል የጻፉ ምንም ነቢያት እንዳልነበሩ አይሁድ ስለሚያምኑ ነው። እነዚህ ዘመናት በብሉይና በአዲስ ኪዳን ዘመናት መካከል ያሉ ስለሆኑ «በኪዳናት መካከል ያሉ ዘመናት» በመባል ይታወቃሉ። በተጨማሪ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምን እንደተፈጸመ መመልከት አለብን።

በብሉይና በአዲስ ኪዳን ዘመናት መካከል የተጻፉ ሁለት ዓይነት ሥነ ጽሑፎች ነበሩ። የመጀመሪያው ዓይነት ጽሑፍ «አፖክሪፋ» በመባል ይታወቃል። እነዚህ ጽሑፎች ከ300 ዓ.ዓ. እስከ 100 ዓ.ም. የተጻፉ ናቸው። አፖክሪፋ ማለት ድብቅ ማለት ነው። በዚህ ስም የተሰየሙበት ሁለት ምክንያቶች አሉ፤ የመጀመሪያው፥ ብዙዎቹ መጻሕፍት የተደበቀ ወይም ምሥጢራዊ መልእክት ስለያዙ ሲሆን፥ ሁለተኛው ምክንያት፥ አይሁድ ከሌሉች ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እኩል ሥልጣን እንዳላቸው ስላላመኑበት ነበር። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት በዕብራይስጥና በአራማይክ ቋንቋ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ከብሉይ ኪዳን ጋር ተያይዘው ይቀርባሉ። 

አሥራ አራት ወይም አሥራ አምስት የሚሆኑት የአፖክሪፋ መጻሕፍት በመጀመሪያ የታዩት ሴፕቱዋጀንት ተብሎ በሚጠራው በግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። አንዳንዶቹ በባሕሪያቸው ታሪካዊ ናቸው። በአዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል የነበረውን ታሪክ ይናገራሉ። ሌሎቹ የፍቅር ታሪኮች እንዲሁም የነቢያት መጻሕፍት ናቸው። አይሁድ እነዚህ መጻሕፍት የብሉይ ኪዳን ክፍል መሆናቸውን የተቀበሉበት ጊዜ ጨርሶ የለም፤ ነገር ግን ደስ ስለ ተሰኙባቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲቀመጡ ፈቅደው ነበር። በኋላ ግን አይሁድ እነዚህን መጻሕፍት እንደ እግዚአብሔር ቃል እንደማያይዋቸው ያልተገነዘቡና ሴፕቱዋጀንት በተባለው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ይጠቀሙ የነበሩ ግሪክኛ ተናጋሪ ክርስቲያኖች እንደ እግዚአብሔር ቃል ይመለከቱአቸው ጀመር። ክርስትና አይሁድ ባልሆኑ ሕዝቦች መካከል እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር፥ እነዚህ መጻሕፍት እንደ እግዚአብሔር ቃል መታየታቸው እየጨመረ መጣ። ይህ ቢሆንም እንኳ የዕብራይስጥን ቋንቋ የሚያውቁ አብዛኛዎቹ ምሁራን የአፖክሪፋ መጻሕፍት በመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳልነበሩ ተገንዝበው ነበር። ከ382 እስከ 405 ዓ. ም. ጄሮም የተባለው ሰው መጽሐፉን የሮማ ንጉሠ ነገሥት ቋንቋ በነበረው በላቲን እንዲተረጉም በሮማ ቤተ ክርስቲያን ተጠይቆ ነበር። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በይፋ የምትጠቀምበት መጽሐፍ ሲሆን ቨልጌት በመባል ይታወቃል። ጄሮም አፖክሪፋ የተባሉት መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ አካል እንዳልሆኑ ቢያስብም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጨምራቸው ታዘዘ፤ ስለዚህ ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ እነዚህ መጻሕፍት የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነው ቀሩ። ከ1500 ዓ.ም በኋላ ግን የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት (ሉተራን፥ ባፕቲስት ወዘተ) በመሠረታዊ የክርስትና ትምህርት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተነጥለው ሲወጡና በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈውን የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲመረምሩ የአፖክሪፋ መጻሕፍት በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት ከተጻፉትና የእግዚአብሔር ቃል ከሆኑት መጻሕፍት መካከል እንዳልሆኑ ተገነዘቡ፤ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉሙ እነዚህን መጻሕፍት መተው ጀመሩ። አንዳንድ የትርጉም ዓይነቶች እነዚህን መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን መጨረሻ በተለየ ክፍል ያደርጉአቸዋል። 

የአፖክሪፋ መጻሕፍት ኢየሱስ በምድር ይኖር በነበረበት ዘመን የነበሩትን አይሁድ ታሪክና አስተሳሰብ ለመረዳት የሚያስችሉን የሚያጓጉ ነገሮች ያሉባቸው ቢሆንም እንኳ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሊቆጠሩ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ ለመረዳት ስንፈልግ ልናነባቸው እንችላለን፤ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ልናከብራችው ግን አይገባም። ከሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ጋር የማይስማሙ ግልጽ የሆነ ስሕተቶች ይታዩባቸዋል። ከካቶሊኮች ልዩ እምነቶች መካከል ፑርጋቶሪ ወይም ዓፀፋ-ንስሐ የሚባል፥ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በሕይወት ሳሉ ስለሠሩት ክፉ ሥራ የሚዳኙበት ቦታ መኖሩ፥ መልካም ተግባር ከፈጸምን በእግዚአብሔር ዘንድ የተሻለ ምሕረትን እናገኛለን የሚለውና የሞተ ሰው ሬሳ ከመቀበሩ በፊት ጸሎተ ፍትሐት ማድረግና የመሳሰለው ሁሉ ከእነዚህ መጽሐፍ የተገኘ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ በዛሬዪቱ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት እነዚህ አመለካከቶች እንዴት ይታያሉ? 

አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በመጽሐፍ ቅዱሳቸው የሚጨምሩት አንድ ሌላ ዓይነት ሥነ-ጽሑፍም አለ። በሁለተኛው ዓይነት የሥነ ጽሑፍ ሥራ «ሱደፒግራፋ» በመባል ይታወቃል። «በሌላ ሰው ስም የተጻፈ መጽሐፍ» ማለት ነው። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት ከ200 ዓ.ዓ. እስከ 200 ዓ.ም. ነው። የተጻፉትም በሰዎች ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኙ በሚጥሩ ሰዎች አማካይነት ነው፤ ስለዚህ በሚጽፉበት ጊዜ በራሳቸው ስም ፈንታ የታወቀ የብሉይ ኪዳን ሰው ስም ይጠቀማሉ። ለምሳሌ «የአዳምና የሔዋን መጽሐፍ» እና «መጽሐፈ ሄኖክ» በመባል የሚታወቁ አሉ። የካቶሊክም ሆኑ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት እነዚህ መጻሕፍት በእግዚአብሔር ምሪት የተጻፉ እንዳይደሉ ይስማማሉ። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን እነዚህ መጻሕፍት የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ናቸው ብላ ታምናለች፤ ስለዚህ ነው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስዋ ውስጥ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የሚበልጡ መጻሕፍት ያሏት። የካቶሊክም ሆነ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሠላሳ ዘጠኝ መጻሕፍት ያሉበትን የእኛን መጽሐፍ ቅዱስ ቢጠቀሙም እንኳ የታወቀው አቋማቸው እኛ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን ከምናስበው የበለጡ መጻሕፍት እንደ አሏቸው ነው። ይሁዳ በመልእክቱ ከቁጥር 14-15 ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል ከአንዱ ይጠቅሳል። ይህ ማለት ግን መጽሐፉ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው ማለት አይደለም።

** በአማርኛና በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ያሉት መጻሕፍት አንድ ዓይነት ቢሆኑም፥ በመጻሕፍቱ አቀማመጥ ቅደም ተከተል፥ ምዕራፍና ቁጥሮቹ በተጻፉበት ሁኔታ አልፎ አልፎ ልዩነት አለ። ይህንን በተለይ የምናየው በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ሲሆን በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቅንፍ ያለው ቁጥር ከእንግሊዝኛው ጋር አንድ ዓይነት ነው። ይህ የሆነው የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ለመጻሕፍቱ ቅደም ተከተል፥ ለምዕራፎቹና ለቁጥሮቹ የተጠቀመው የሴፕቱዋጀንቱን ትርጉም ስለሆነ ነው።

** የኦርቶዶክስ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው 58 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና 27 የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሲሆን በጠቅላላው 85 (ሰማንያ አምስት) ነው። የአሁኑ የፕሮቴስታንት መጽሐፍ ቅዱስ የአዋልድ መጻሕፍትን አስቀርቶ በካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን የቩልጌትን ቅደም ተከተል ይከተላል። ይሁን እንጂ የፕሮቴስታንት አማኞች በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚቆጠሩትን ብቻ ይቀበላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት የተጻፉ የትኞቹ መጻሕፍት እንደሆኑና እንደ እግዚአብሔር ቃል መቆጠር የሌለባቸው መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ ማወቅ ጠቃሚ የሚመስልህ ለምንድን ነው? 

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የጊዜ ቅደም ተከተል

የውይይት ጥይቄ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ያለውን ማውጫ ተመልከት። ቀደም ሲል ባነበብከውና ባጠናኸው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት፥ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት? ለመመደብ ከሚከተሉት የተሻለ ዘዴ ነው በምትለው ከፋፍላቸው። ሀ) በታሪክ መጻሕፍት፥ ለ) በግጥምና ቅኔ መጽሐፍ፥ ወይም ሐ) በነቢያት መጽሐፍ ውስጥ።

ብሉይ ኪዳንን በተለያዩ ክፍሎች መክፈል እንችላለን። በመጀመሪያ ፔንታቱክ የተባለ ክፍል አለ። ፔንታቱክ ወይም የሙሴ ሕግ የመጀመሪያዎቹን አምስት ቅዱሳት መጻሕፍት ይዞአል። በእነዚህ አምስት መጻሕፍት ውስጥ ብዙ የተለያዩ የሥነ -ጽሑፍ ዓይነቶች አሉ፡- ታሪክ፥ ግጥምና ቅኔ፥ ሕግና ትንቢት። ከአምስቱ ሦስቱ የሚናገሩት ከታሪክ ጋር የተያያዘ ነገር ነው። እነዚህም ዘፍጥረት፥ ዘጸአትና ዘኁልቁ ናቸው። የዘጸአትና የዘኁልቁ መጻሕፍት አንዳንድ ሕጎችን ይዘዋል። ደግሞም የተመረጠውን የአይሁድን ሕዝብ ታሪክ የሚናገር ክፍል ነው። ሁለት መጻሕፍት ማለት ዘሌዋውያንና ዘዳግም በአብዛኛው እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ስለ ሰጣቸው ሕግ ይናገራሉ። ዘሌዋውያን በተለይ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ላይ ሕግን ስለሰጠበት ሁኔታ ይናገራል። ዘዳግም ደግሞ ሙሴ ከ38 ዓመታት በኋላ እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሉ እንዴት ሕጉን እንደደገመው የሚነግረን ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ታሪክ የሚባል ክፍል አለ። በብሉይ ኪዳን ሁለተኛ ክፍል ውስጥ 12 መጻሕፍት አሉ። እነዚህ መጻሕፍት በኢያሱ መሪነት ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ (ኢያሱ)፥ ከ1000 ዓመታት በኋላ ከባቢሎን ምርኮ እስከተመለሱበት ጊዜ ድረስ (መጽሐፈ ነህምያ)፥ ያለውን የአይሁድ ሕዝብ ታሪክ ይናገራል። እነዚህ መጻሕፍት በአብዛኛው ጊዜ በቅደም ተከተል የተቀመጡ ናቸው። የቀሩት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተለያዩ ጊዜያት በዚህ የታሪክ ወቅት የተጻፉ ናቸው።

ሦስተኛው ክፍል፥ ግጥምና ቅኔ ይባላል። እነዚህ ከኢዮብ ጀምሮ እሰከ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ባሉት ጊዘያት ውስጥ የተጻፉ ናቸው። መጽሐፈ ኢዮብ በሙሴ ተጽፎ ይሆናል። አብዛኛዎቹ የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት የተጻፉት በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ነው። አንዳንዶቹ መዝሙሮች የተጻፉት ዘግየት ብለው በ400 ዓ.ዓ. በዕዝራ ነው ስለዚህ እነዚህ አምስት የጥምና የቅኔ መጻሕፍት የተጻፉት ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ ነው። ቅደም ተከተላቸው ግን ጊዜን የሚመለከት አይደለም፡፡

አራተኛው ክፍላችን፥ ትንቢት ይባላል። በብሉይ ኪዳን ትንቢት ውስጥ የተመደቡ 17 መጻሕፍት አሉ። እነዚህ መጻሕፍት በተጨማሪ በ2 ምድብ ተከፍለዋል። የመጀመሪያው የታላቅ ነቢያት መጻሕፍት ሲሆን፥ በዚህ ክፍል ውስጥ አምስት መጻሕፍት ይገኛሉ፥ እነርሱም ከኢሳይያስ እስከ ዳንኤል ያሉት ናቸው። ታላቅ የተባሉትም በመልእክታቸው ርዝመትና ጥልቀት ነው።

ሁለተኛ የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት ናቸው። ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉት እነዚህ 12 መጻሕፍት በመጀመሪያው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ መጽሐፍ ነበሩ።

በመጀመሪያ፥ የእስራኤልን ታሪክ የጊዜ ቅደም ተከተል መግለጫ የሚሰጡ 11 መጻሕፍት ብቻ አሉ። እነዚህ መጻሕፍት ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስራኤላውያን ከምርኮ እስከ ተመለሱ ድረስ ያለውን ታሪክ የሚያካትቱ ናቸው። በሌላ አነጋገር ከቀድሞው ዘመን ጀምሮ እስከ 400 ዓ.ዓ. ማለት ነው። የእነዚህ መጻሕፍት ታሪክ አብዛኛው ከ1450 እስከ 400 ዓ.ዓ. ያሉትን ዘመናት የሚያጠቃልል ነው። 

በርካታ የሆኑት ሌሎች መጻሕፍት ታሪካዊ ናቸው፤ ነገር ግን ታሪካቸው የተፈጸመው በሌላ ታሪካዊ መጽሐፍ ዘመን ነው። ለምሳሌ የሩት ታሪክ የተፈጸመው በመሳፍንት ዘመን ነው። 1ኛና 2ኛ ዜና መጻሕፍት ከ2ኛ ሳሙኤል እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉትን ታሪኮች ይደግማል። የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው ደግሞ በዕዝራ መጽሐፍ ታሪክ ዘመን ነው። 

ሁለተኛ፥ አብዛኞቹ መጻሕፍት የተጻፉት በእስራኤል ታሪክ ውስጥ በነበሩ ሦስት ጊዜያት ነው። በቅድሚያ፥ የመጀመሪያዎቹ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት (ፔንታቱክ) በሙሴ የተጻፉት እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ በተንከራተቱበት ጊዜ ነው። ሁለተኛ ጊዜ፥ አብዛኛዎቹ የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት የተጻፉት በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ነው። ሦስተኛ፥ ይሁዳ ከመማረኩ ጥቂት ቀደም ብሉ፥ ወዲያው ከምርኮ እንደተመለሱም በርካታ የነቢያት መጻሕፍት ተጽፈዋል። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት እግዚአብሔር ኃጢአተኛ የሆኑት እስራኤላውያን ወደ ንሥሐ እንዲደርሱ ፈልጎ በላካቸው ነቢያት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ክፍፍል በቃልህ አጥናና በእያንዳንዱ ክፍፍል ውስጥ ሊሆኑ የሚችሉትን መጻሕፍት ለይ። ለ) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ጊዜ ቅደም ተከተል በቃልህ አጥና።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: