የመካከለኛው ምሥራቅ መልክዓ ምድር

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የአንድን ስፍራ መልክዓ ምድር መረዳት በዚያ ስፍራ የሚኖሩ ሰዎችን አኗኗር ለመረዳት እንዴት ይጠቅማል? ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳትና ለመተርጎምስ እንዴት ይጠቅማል?

የብሉይ ኪዳን ታሪክ እምብርት የከነዓን ምድር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ስፍራ አራት ስሞች ተሰጥቶታል። በመጀመሪያ፥ ብዙ ጊዜ የሚጠራበት «ከነዓን» የሚለው ስም ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 9፡18-27 ተመልከት። ከነዓን ማን ነው?

የኖኅ የልጅ ልጆች ከነበሩት መካከል ከነዓን የሚባለው አንዱ እንደ ነበረ በብሉይ ኪዳን እናነባለን። አባቱ በሠራው ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር ከነዓንን ለሴምና ለያፌት ዘሮች ባሪያ እንዲሆን ረግሞት ነበር። በዘፍጥረት 10 እንደምናነበው የከነዓን ዝርያዎች በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ በዮርዳኖስ ወንዝና በሜዲትራኒያን ባሕር መካከል ሰፍረው ነበር። ይህ አካባቢ የኖኅ የልጅ ልጅ በሆነው በከነዓን ዝርያዎች ስም ከነዓን ተብሎ ተጠራ። ደግሞም ይህ አካባቢ ከነዓን ይባል የነበረው «የሐምራዊ ምድር» ለማለትም ነው። ምክንያቱም በከነዓን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በዘመኑ ሀብታሞች ሊለብሱ የሚችሉትን ሐምራዊ ቀለም ያላቸው ልብሶችን ይሠሩ ስለነበር ነው። ጳለስጢና የሚለው ቃል ከኤፍራጥስ ጀምሮ እስከ ግብፅ ያለውን ምድር በሙሉ የሚያጠቃልል ሲሆን፥ ከነዓን የሚለው ቃል ግን በጳለስጢና ውስጥ ያለ አነስተኛ ምድርን የሚጠቅስ ነው።

ሁለተኛ፥ ምድሪቱ አንዳንድ ጊዜ «የተስፋይቱ ምድር» በመባል ትጠራለች። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ (በዘፍ. 15፡7) የከነዓንን ምድር ለአብርሃም ርስት አድርጎ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል። አብርሃምና ዝርያዎቹ ከ400 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ምድሪቱን ባይወርሱም እንኳ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል መሠረት የእነርሱ ነበረች። ለእስራኤል በርስትነት ተስፋ የተሰጠች ምድር ስለሆነች «የተስፋይቱ ምድር» ሆና ቆይታለች (ሕዝ. 48 ተመልከት)።

ሦስተኛ፥ ምድሪቱ አንዳንዴ «ጳለስጢና» ተብላ ተጠርታለች። ይህ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም፥ አሕዛብ ለከነዓን ምድር የሚሰጡት የተለመደ ስም ነው። (ስለ ፍልስጥኤማውያን፥ ስለ ለስጢናና ስለ ጳለስጢናውያን በትላንትና ትምህርታችን የተመለከትነውን ከልስ።)

አራተኛ፥ ምድሪቱ አንዳንዴ «እስራኤል» ተብላ ተጠርታለች። ይህ የሚያመለክትው ከ1400 ዓ.ዓ. . 70 ዓ.ም. እና ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ የአይሁድ ምድር መሆንዋን ነው። ከአይሁድ አባቶች አንዱ የሆነው ያዕቆብ በኋላ ስሙ እስራኤል ተብሎ እንደተለወጠ ይታወቃል (ዘፍ. 32፡28)። ስለዚህ እስራኤል የሚለው ስም የሚያመለክተው የያዕቆብን ዝርያዎችና በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ኪዳን መሠረት ስለወረሷት ምድር ነው።

እግዚአብሔር በጣም ትንሽ የሆነችውን የከነዓንን ምድር ይወርሱ ዘንድ ለአይሁድ የሰጠው ለምንድን ነው? እንደ አሜሪካ፥ ኢራቅ ወይም ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ትልልቅ አገሮች ለምን አልሰጣቸውም? ስለከነዓን ምድር በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

የከነዓን ምድር ትልቅ አይደለችም። የእስራኤል መንግሥት በጣም ትልቅ የነበረችው በዳዊትና በሰሎሞን ዘመን ሲሆን በዚያን ጊዜም 800 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 200 ኪሎ ሜትር ስፋት ነበራት፤ ይህም ከአሰብ እስከ አዲስ አበባ ያለው ርቀት ማለት ነው። ብዙ ጊዜ ግን የእስራኤል ምድር 225 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 100 ኪሎ ሜትር ስፋት ብቻ ነበራት፤ ይህ ከአዲስ አበባ እስከ ሻሸመኔ ድረስ ካለው ርቀት ጋር የሚወዳደር ነው።

ከነዓን የዓለም እምብርት ለመባል ትችላለች፤ ምክንያቱም ሁለት ዋና ዋና አህጉራት ማለትም አፍሪካና እስያ የሚገናኙባት ቦታ ናት። በጥንት ዘመን ደግሞ በጣም ጠቃሚ የነበረችው:- በአፍሪካ፥ በእስያና እንዲሁም በአውሮጳ ዋና የንግድ መሥመር ላይ ትገኝ ስለነበረ ነው። አሁንም ቢሆን በታሪክ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ሚና መጫወቷን ቀጥላለች፤ ምክንያቱም መካከለኛው ምሥራቅ በነዳጅ ዘይት ከፍተኛ ሀብት ያለው አካባቢ ስለሆነ ነው። የዚህ ዘመን ሥልጣኔ በነዳጅ ዘይት ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እነዚህን ስፍራዎች ለመያዝ አሕዛብ በሚያደርጉት ትግል በምድር ላይ የመጨረሻው ጦርነት የሚካሄደው በእስራኤል ነው ይላል። በተጨማሪ፥ የዓለም የሥነ- መለኮት ትምህርት ማዕከልም ናት። የዓለም ሦስቱ ዋና ዋና ሃይማኖቶች ይሁዲነት፥ ክርስትናና እስልምና መሠረታቸውን ያገኙት ከእስራኤል ነው።

በጥንቱ መካከለኛ ምሥራቅ የነበሩ ታላላቅ አገሮች

የተለያዩ የጥንት ሕዝቦች የት እንደ ነበሩና ከአሁኑ ዓለም ጋር እንዴት እንደሚወዳደሩ ለማወቅ የጥንቶቹን ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ሕዝቦችና በጊዜያችን ከየትኛው አገር እንደሆኑ እንመለከታለን። 

፩. ኢትዮጵያ ወይም ኩሽ፡- በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከግብፅ በስተደቡብ ቀጥሉ የሚገኘው አገር ኩሽ ተብሎ ይጠራ ነበር። ኋላም በሰፕቱዋጀንት የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግሪኮች ይህንን ምድር ኢትዮጵያ ብለው ጠርተዋል፤ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኩሽና ኢትዮጵያ የአንድ ስፍራ ሁለት ስሞች ናቸው። የእንግሊዝኛና የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶች ለዚህ ምድር «ኢትዮጵያ» የሚለውን የግሪክ ስም ይጠቀማሉ። የኩሽ ወይም የኢትዮጵያ ምድር ከአሁንዋ ኢትዮጵያ ጋር አንድ አይደለም፤ ነገር ግን በዓለም ታሪክ ውስጥ «ኑቢያ» ተብላ ትጠራ የነበረችው ዛሬ በሰሜን ሱዳን የምትገኝ አገር ነች። በመጽሐፍ ቅዱስ መልክዓ ምድር መሠረት ኑቢያ የመጨረሻዋ ደቡባዊ ክፍል ያለችው አገር ነች። የአሁንዋ ኢትዮጵያ መጀመሪያ ስምዋን ያገኘችው ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ወይም ኩሽ ብሉ መጽሐፍ ቅዱስ ከጠራው ስፍራ ጋር ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ አይደለችም። የአሁንዋ ኢትዮጵያ ከአክሱም መንግሥት ውስጥ በተለያዩ ነገሥታት አመራር ሥር የነበረችና አሁን ወዳለው የክልል ዳርቻ እያደገች የመጣች ነች።

የሳባ ሕዝብ ዛሬ የመን ተብሎ በሚጠራው በደቡብ ምዕራብ ዐረቢያ የነበረ ሳይሆን አይቀርም። ነገር ግን አንዳንዱ የግዛቱ ክፍል በቀይ ባሕር ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ ሊሆን ይችላል። 

፪. ግብፅ፡- ልክ እንደ ጥንትነቷ ያለች ብቸኛ አገር ግብፅ ናት። በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝና ከጥንቱ ዓለም ታላላቅ ሥልጣኔዎች የአንደኛው ማዕከል የነበረች አገር ናት። በብሉይ ኪዳንም በተደጋጋሚ አገሪቱ በዚህ ሁኔታ ተጠቅሳለች። የሕይወቷ ሁሉ ምንጭ የሆነው ከኢትዮጵያና ከሱዳን የሚፈሰው የዓባይ ወንዝ ነው። የዓባይ ወንዝ በበጋም ሆነ በክረምት ጊዜ ለሰብልና ለከብቶች ውኃን ስለሚሰጥ የግብፅ ምድር ሁልጊዜ ምግብ ያገኛል። አብርሃምና ያዕቆብ በድርቅ ጊዜ ወደ ግብፅ የሄዱት በዚህ ምክንያት ነው። 

፫. ከነዓን፡- የከነዓን ምድር የሚገኘው ከግብፅ በስተሰሜን ነው። በመጠን አነስተኛ ብትሆንም፥ የተለያዩ ሕዝቦችን ይዛለች። በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ የጥንት እስራኤል ጠላቶች የነበሩ ሦስት የአሕዛብ መንግሥታት ነበሩ። በደቡብ ኤዶም፥ ከኤዶም በስተሰሜን ሞዓብና ከሞዓብ በስተሰሜን ደግሞ አሞን ነበሩ። እነዚህ አገሮች ይገኙ የነበሩት በአሁኑ ጊዜ ዮርዳኖስ ተብሎ በሚታወቀው አገር ምዕራባዊ ጫፍ ነው።

ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ የእስራኤል ምድር ይገኛል። ታሪክ ሁሉ እስራኤላውያን የኖሩት በከነዓን ተራራማ አገር በአገሪቱ በስተ ደቡብ ከቤርሳቤህ በሰሜን እስከሚገኘው ዳን ድረስ ነው። በምዕራብ ሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ በዘመነ መሳፍንት የእስራኤላውያን ዋና ጠላቶች የነበሩት ጳለስጢናውያን ይገኛሉ። ልክ እንደ ጥንቱ ዘመን ይህ ምድር ዛሬ እስራኤል ተብሎ ይጠራል። ነገር ግን ከዚህ አካባቢ የተወሰነው ክፍል በዘመናችን ባሉ ፍልስጥኤማውያን፥ በሶርያና በዮርዳኖስ የይገባኛል ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

፬. ሶሪያ፡- ከእስራኤል በስተ ምሥራቅ የአራሚያን ወይም የሶርያ ሕዝቦች ይገኛሉ። ዋና ከተማቸው ደማስቆ የሆነው ሶርያውያን ብዙ ጊዜ የእስራኤል ጠላቶች ሆነው ሲቆዩ፥ በተለይ የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፍሎ በነበረ ጊዜ ዋና ጠላቶች ነበሩ። ዛሬ ይህ ሕዝብ ያለበት አገር ሶርያ ተብሎ ይጠራል። 

፭. ፎኒሺያ (ፊንቄ)፡- ከእስራኤል በስተሰሜን ምዕራብ በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ ፎኒሺያ (ፊንቄ) የምትባል አገር ነበረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ አካባቢ በተለይ የሚታወቀው በዋና ከተማዎቹ በጢሮስና በሲዶና ነው። ይህ ሕዝብ በጣም የሚታወቀው የሜዲትራኒያን ባሕር በሙሉ ይካሄድ በነበረው የባሕር ላይ ንግድ ነው። ዳዊትና ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና ቤተ መንግሥቱን ለመገንባት የሠለጠነ የሰው ኃይል ፍለጋ ወደ ጢሮስ ሄደው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ይህ አካባቢ ሊባኖስ በመባል ይታወቃል።

፮. አሦር፥ ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ፡- ከእስራኤል በስተሰሜን ምሥራቅ ራቅ ብሉ አሦር፥ ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ የሚባሉ አራት አገሮች ነበሩ። የእነዚህ አራት አገሮች ሕዝቦች በተለይ መስጴጦምያ በሚባለው አካባቢ ይኖሩ ነበር። መስጴጦምያ የሚባለው አካባቢ የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ይዞ በስተሰሜን ምዕራብ ከሁለት ታላላቅ ወንዞች ማለትም ከኤፍራጥስና ጤግሮስ አጠገብ የሚገኝ ነው። 

ሀ. አሦር፡- አሦር የሚገኘው ከመስጴጦምያ በስተሰሜን በጤግሮስ ወንዝ አጠገብ ነበር። ዋና ከተማው ነነዌ ነበረ። በ700 ዓ.ዓ. አሦር በመስጴጦምያ፥ ጳለስጢናና በግብፅ ሁሉ ላይ የበላይነት አግኝታ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆነች። እግዚአብሔር የሰሜኑን የእስራኤልን መንግሥት ለመቅጣትና ወደ ምርኮ ለመውሰድ አሦርን ተጠቀመ። አሦር ትገኝ የነበረው በአሁኒቱ ኢራቅ ድንበሮች ውስጥ ነው። 

ለ. ባቢሎን፡- ባቢሎን የምትገኘው ከመስጴጦምያ በስተደቡብ ራቅ ብላ ነበር። ዋና ከተማዋም ባቢሎን ተብላ ትጠራ ነበር። በ600 ዓ.ዓ. የባቢሎን መንግሥት የዓለም ኃያል መንግሥት በመሆን መስጴጦምያን፥ ጳለስጢናንና የግብፅን መንግሥታት ተቆጣጠረች። እንደምታስታውሰው፥ የደቡብ ይሁዳን መንግሥት ያሸነፈውና ወደ ግዞት የወሰደው የባቢሎን መንግሥት ነበር። ባቢሎንም ትገኝ የነበረው በአሁኑ የኢራቅ መንግሥት ውስጥ ነበር። 

ሐ. ሜዶን፡- ሜዶን ከመስጴጦምያ በስተሰሜን ምዕራብ የምትገኝ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱና በሩቅ ሰሜን ከሚገኙ አገሮች አንዷ ናት። በመጽሐፍ ቅዱስ ከፋርስ መንግሥት ጋር እንደተዋሐደችና የሜዶንና የፋርስ መንግሥትንም እንደመሠረተች ተጽፏል። ይህ መንግሥት በ539 ዓ.ዓ. ተጀምሮ በ331 ዓ.ዓ. ወድቋል። የሜዶን መንግሥት የሚገኘው በሰሜን ኢራን ነበር። 

መ. ፋርስ፡- የፋርስ መንግሥት የሚገኘው ከሜዶን በስተደቡብ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ አጠገብ ነበር። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ፋርስ ከሜዶን መንግሥት ጋር በመተባበር፥ አይሁድን ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ቤተ መቅደሳቸውን እንዲሠሩ እንደፈቀደ ተጽፏል። ፋርስም የምትገኘው በአሁኗ ኢራን ውስጥ ነበር።

፯. ትንሿ እስያ፡- ጥንታዊት የሆነችው ትንሿ እስያ ብዙ ጊዜ በብሉይ ኪዳን ያልተጠቀሰች ቢሆንም፥ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ግን ሐዋርያው ጳውሎስ በወንጌል አገልግሎት ጉዞው የሄደባት ስለነበረች በተደጋጋሚ ተጠቅሳለች። ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ዘመን ትንሿ እስያ የኬጢያውያን ምድር ነበረች። ኬጢያውያን ጳለስጢናን ከ1400 – 1190 ዓ.ዓ. የገዙ ነበሩ። ብዙ ምሁራን እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ ያደረገው ቃል ኪዳን የኬጢያውያን ነገሥታት በቁጥጥራቸው ሥር ካዋሏቸው ሕዝቦች ጋር ካደረጉት ቃል ኪዳን ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ይገምታሉ። ትንሿ እስያ በአሁኑ ጊዜ ቱርክ በመባል ትታወቃለች። 

የከነዓን መልክዓ ምድር 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ዓይነት የመሬት አቀማመጦችን ዘርዝር። ለ) ብዙ ሕዝቦች የሚኖሩት በየትኛው ዓይነት ምድር ላይ ነው?

የከነዓን ምድር በአካባቢው ከሚገኙት «ለም አገሮች» ውስጥ አንዱ ነው። ይህ የአዲስ ጨረቃ ቅርፅ ያለው ለም ምድር ከጤግሮስና ኤፍራጥስ ወንዞች አጠገብ ካለው ከመስጴጦምያ ጀምሮ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር በመዝለቅ፡ ከግብፅ ወንዝ ዳርቻ በስተደቡብና ከዓባይ ወንዝ በስተደቡብ ወዳለው አካባቢ ይደርሳል። በእነዚህ ለም አገሮች ብዙ ዝናብና ወንዞች ስላሉ ሰዎች በቂ እህል ያበቅሉ ነበር። አብዛኛው የጥንት ሥልጣኔ የተጀመረው በዚህ ክልል ነው። በዚህም ለም ክልል ነው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመው።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የከነዓንም ምድር ብዙ የተለያየ ዓይነት የመሬት አቀማመጥ ነበረው። በሰሜን የሐርሞን ተራራ ነበር። ይህ ተራራ 2800 ሜትር ከፍታ ያለው ረጅም ተራራ ነበር። ተራራው ብዙ ጊዜ በበረዶ የተሸፈነ ነበር። በደቡብ በኩል በዓለም ዝቅተኛ ስፍራ የሆነው ሙት ባሕር ይገኛል። እርሱም ከባሕር ጠለል በታት 400 ሜትር ነበር። ሙት ባሕር የተባለው፥ በውኃው ውስጥ ምንም ነገር በሕይወት እንዳይኖር የሚያደርጉ በርካታ ንጥረ ነገሮች ስላሉበት ነው።

በብሉይ ኪዳን ታላቁ ባሕር በመባል ይታወቅ በነበረው በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ አጠገብ ያለው የከነዓን ምድር ሜዳማና ለም ነበር። አንድ ሰው ከባሕሩ በስተምሥራቅ ሲጓዝ የምድሪቱ ከፍታ እየጨመረ ይመጣና የከነዓን መካከለኛ ምድር ተራራና ኮረብታ የሚበዛበት ክልል ሆኖ እናገኘዋለን። በጥንት ዘመን የባሕር ዳርቻዎች በአሕዛብ መንግሥታት ተይዘው ስለነበር ከእስራኤላውያን አብዛኛዎቹ የሚኖሩት በእነዚህ ተራሮች ላይ ነበር። ይህ መሬት በባሕር ዳር እንደሚገኘው ለም አልነበረም። ከከነዓን በስተምሥራቅ ሁለት ትላልቅ የውኃ ክፍሎች ነበሩ። በአዲስ ኪዳን ገሊላ በተባለው አካባቢ ማለት በስተሰሜን የገሊላ ባሕር ነበር። ይህ ንጹሕ የሆነ የሐይቅ ውኃ ብዙ የተለያዩ ስሞች ነበሩት። ብዙ ጊዜ በብሉይ ኪዳን የኪኔሬት ባሕር በመባል ይታወቅ ነበር (ዘኁ. 34፡11)። በተጨማሪ «የጌንሳሬጥ ባሕር» (ሉቃስ 5፡1) እና «የጥብርያዶስ ባሕርም» ይባል ነበር (ዮሐ. 6፡ 1)።

የገሊላ ባሕር ከእርሱ ተነሥቶ ወደ ታች ወደ ሙት ባሕር የሚፈሰው የዮርዳኖስ ወንዝ ምንጭ ነበር። ምድሪቱ በመካከለኛው ከነዓን ካሉት ተራራማ ስፍራዎች ወደ ታች በማሽቆልቆል ከባሕር ጠለል በታች ወደ ሆነው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ትወርዳለች። ምድሪቱ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ወደ አንድ ሰፊ ሜዳ ፈጥና ትዘረጋለች። በዚህ ደልዳላ ሜዳ ነበር የጋድ፥ የሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታዎች የሰፈሩት። በዚህ ደልዳላ ሜዳ በምዕራባዊና ደቡባዊ ክፍል ዘላን ነገዶች ብቻ የሚኖሩበት ድንጋያማ በረሃ ነበር።

የአንድን ሕዝብ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መረዳት ያንን ሕዝብ ለማወቅ በጣም ይረዳል። ለምሳሌ፡- አንድ ሰው የኦጋዴንን ወይም የሰሜን ኢትዮጵያን መልክዓ ምድር ሳያውቅ ለዘመናት በኢትዮጵያ ላይ የተካሄዱትን የተለያዩ ጦርነቶች ወይም የአውሮጳውያንን ለቅኝ ግዛት መቋመጥ እንዴት እንደተጀመረ መረዳት ያስቸግረዋል። በተመሳሳይ መንገድ የከነዓንን ምድር አቀማመጥ ማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ ለመረዳት ይጠቅማል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ ለምን ወደ ኢየሩሳሌም ስለ «መውጣት» ይናገራል? ምክንያቱም ኢየሩሳሌም ያለችው በአቅራቢያዋ ከሚገኙ ሌሎች ስፍራዎች ሁሉ ከፍ ብላ ስለሆነና ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ለመድረስ ሁልጊዜ ወደ ላይ መውጣት ስላለባቸው ነው።

የከነዓንን መልክዓ ምድር መረዳት ስለ እስራኤል የሚከተሉትን ነገሮች ለመረዳት ይጠቅመናል፡-

  1. እስራኤል በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ የነበረችበትን ምክንያት ለመረዳት ይጠቅመናል። ከነዓን የሦስቱ አህጉራት ማለት (የአውሮጳ፥ የእስያና የአፍሪካ) የንግድ ማዕከል ነበረች። ይህንን የንግድ ማዕከልነት የሚቆጣጠር ሁሉ ኃያልና ሀብታም ይሆን ነበር። 
  2. በነጋዴዎችና በገበሬዎች መካከል ትግል የተፈጠረው ለምን እንደነበር ያስረዳናል። ከነዓን የንግድ መናኸሪያ በመሆንዋ ምክንያት አንዳንድ እስራኤላውያን ከግብርና ይልቅ ንግድን ለመተዳደሪያነት መረጡ። በዚህም ምክንያት ሀብታም ለመሆን ችለው ነበር። ሀብታቸውን ግን ብዙ ጊዜ ድሀ የሆኑ ገበሬዎችን ለመጨቆን ይጠቀሙበት ነበር። በነቢያት መጻሕፍት ውስጥ ከተወገዙ ሥራዎች አንዱ ድሆችን መጨቆን ነው።
  3. የከነዓን ምድር በጣም ትንሽ ነበር። ብዙ ጊዜ ርዝመቱ ከ240 ኪሉ ሜትር ስፋቱ ደግሞ ከ160 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ነበር። ይህች ትንሽ ምድር የአይሁድን ሃይማኖት ላለመቀበል ጸንተው በተቃወሙ የአሕዛብ መንግሥታት ተከብባ ነበር። አይሁድ ከአሕዛብ ጋር በቅርብ ተወዳጅተው መኖራቸው ከእነርሱ ጋር በጋብቻ የመጣመራቸው አንዱ ችግር ሆኖ ቆይቷል። እንዲሁም አሕዛብ የአይሁድን ሃይማኖት ብዙ ጊዜ ለምን እንዳበላሹት ያስረዳናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን እነዚህ ተመሳሳይ ችግሮች እንዴት ይታያሉ?

በብሉይ ኪዳን የአይሁድ በእስራኤል ምድር የመኖር አሳብ ጥልቅ የሆነ የሥነ- መለኮት ትምህርት ነበረው። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳንን ባደረገ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑ አንድ ክፍል ምድራዊ የሆነው ከነዓን ነበር። እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው ተስፋ ነበር። ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ መሳፍንት ድረስ ያለው ታሪክ በአብዛኛው የሚናገረው እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን ለመጠበቅ የከነዓንን ምድር እንዴት ለአይሁድ እንደሰጠ ነው። እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን መሠረት የእርሱን ሕግ የመታዘዝ ሽልማት በምድሪቱ ያለማቋረጥ መኖር እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። ሰላምና ብልጽግና ይኖራቸዋል፤ ነገር ግን በቃል ኪዳኑ መሠረት የእርሱን ሕግ ያለመጠበቅ ከምድሪቱ የመውጣትን ችግር እንደሚያመጣም ሳያስጠነቅቃቸው አላለፈም። የቀረው አብዛኛው የብሉይ ኪዳን ታሪክ የሚያሳየው እስራኤላውያን ባለማቋረጥ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ከአሕዛብ ጋር ጦርነት ወደማድረግና ከዚያም ተሸንፈው በአሕዛብ መንግሥታት ወደ ምርኮ የመወሰዳቸው ታሪክ ነው። በነቢያት መጻሕፍት እግዚአብሔር ወደ ምድሪቱ እንደገና እንደሚመልሳቸውና በሰላም እንደሚኖሩ ለአይሁድ ቃል ገብቶላቸው ነበር። በእርግጥ አይሁድ ከተበተኑበት የዓለም ክፍል እንደሚመለሱና በከነዓን እንደሚኖሩ ቃል ተገብቶላቸዋል። በዚያን ጊዜ መሢሐቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በእነርሱ ላይ ይነግሣል። አይሁድ ለእስራኤል ምድር ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ለመረዳት በጣም አዳጋች ቢሆንም፥ የብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳኖችን በሙሉ ከተመለከትንና ከምድራዊቷ የእስራኤል ምድር ጋር ያለውን ግንኙነት ከተገነዘብን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ብቻ ሳይሆን የእስራኤል ሕዝብ የጥንት ግዛታቸውን በሙሉ ለመቆጣጠር ያላቸውን ጥብቅ ፍላጎትም እንረዳለን። ዛሬ የእስራኤል ሕዝብ በምድር መኖሩ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እያከበረ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ብሉይ ኪዳንን ማወቅ በዚህ ዘመን በአይሁድና በዐረብ መካከል ስላለው ትግል ለመገንዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?

ይህ የእስራኤል ጥንታዊ ታሪክ ክለሳና የመልክዓ ምድር መለስተኛ ጥናት ብሉይ ኪዳን የተጻፈበትን ጊዜ ለመረዳት እጅግ የሚጠቅም ነው። የጥንት ሰዎች የኖሩበትን ዘመንና ቦታ ስናውቅ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለእነርሱ ሲገልጥ ምን ማለቱ እንደ ነበር የበለጠ እንረዳለን። ይህ ለቃሉ የምንሰጠውን ትርጉም የበለጠ ትክክል ያደርገውና በምናስተምርበትና በምንሰብክበት ጊዜ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት እንደ ጥንት ሰዎች መናገር እንድንችል ያደርገናል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: