የውይይት ጥያቄ፥ ከዘፍ. 3 በሰው መጀመሪያ ኃጢአት በተሳተፉት ላይ የደረሰባቸውን እርግማን ዘርዝር።
ዘፍ. 3 ስለ ሰው የመጀመሪያ ኃጢአት ይናገራል። ይህም በእግዚአብሔር ላይ የፈጸመው የመጀመሪያው ዓመፅ ነበር። እግዚአብሔር በመጀመሪያ አዳምና ሔዋንን ሲፈጥር፥ በሥነ- ምግባር ፍጹም ነበሩ። የኃጢአት ተፈጥሮ ስለሌላባቸው ኃጢአት ሊያደርጉ የሚችሉበት ምክንያት አልነበረም። ምሁራን ይህንን «የንጽሕና ደረጃ» ብለው ይጠሩታል፤ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ምን እንደሆነ እንኳ አያውቁም ነበር። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን በዔደን ገነት ባኖረ ጊዜ ከፍሬው እንዳይበሉ የከለከላቸው አንድ ዛፍ ነበር። ይህ ፍሬ «መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቅ ዛፍ» የሚገኝ ነበር።
ሰይጣን በእግዚአብሔር ላይ ያመፀው አስቀድሞ ነበር። አዳምና ሔዋንም በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምፁ በማድረግ ፍጥረታትን ሁሉ ሊያበላሽ ቆረጠ፤ ስለዚህ ሰይጣን ወደ ሔዋን ቀረበ። ስለ እግዚአብሔር ትእዛዝ የተምታታ አሳብ እንዲኖራት አደረገ። ከዚህም በኋላ ሔዋንን ትእዛዙን በሰጣት በእግዚአብሔር ዓላማና ባህርይ ላይ እንድትጠራጠር አደረጋት። አዳምና ሔዋን ሁለቱም የተከለከለውን ፍሬ በሉ። በመጀመሪያ የተታለለችውና በኃጢአት በመውደቅ ለእግዚአብሔር ያልታዘዘችው ሔዋን ብትሆንም አዳምም በኃጢአት የወደቀው እያወቀ ነው። እግዚአብሔርን በመታዘዝ ፈንታ ሔዋንን መከተል መረጠ። አንዳንድ ምሁራን፡ – ሔዋን በተታለለች ጊዜ አዳም አብሮአት ነበር፤ ሆኖም ከስሕተት እንድትርቅ ሊያደርጋት አልፈለገም ይላሉ።
የውይይት ጥያቄ ፥ ኃጢአት በምናደርግበት ጊዜ አዳምና ሔዋን ከሠሩት ኃጢአት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
የመጀመሪያው የሰው ልጅ ኃጢአት ፈጣሪ በሆነው እግዚአብሔር ላይ ማመፅ ነበር። ፈጣሪያቸው የሆነው ጌታ ፍሬውን እንዳይበሉ የመከልከል ሙሉ መብት ነበረው፤ ነገር ግን የራሳቸውን ፍላጎት ለማድረግ ስለፈለጉ ዓመፁ። በእያንዳንዱ ኃጢአት ውስጥ ያለው ተመሳሳይ ዝንባሌ ይህ ነው። እያንዳንዱ ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ዓመፅ ነው። ለእግዚአብሔር ራስን ባለመስጠት ለትእዛዙ አልገዛም ማለት ነው። ፈጣሪያችን ለሆነው ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ራሳችንን ከማስገዛት ይልቅ በራሳችን ሕይወት ላይ ለመሠልጠን የምናደርገው ጥረት ነው።
የመጀመሪያው የአዳምና ሔዋን ኃጢአት ለብዙዎች የሚደርሱ አስጨናቂ ውጤቶችን አስከተለ።
- አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ወዲያውኑ አቋርጦ ከእግዚአብሔር እንዲደበቁ አደረገ።
- በአራት ነገሮች ላይ ቅጽበታዊ ፍርድ አመጣ፡-
ሀ. በእባቡ ላይ አካላዊና ተምሳሌታዊ ፍርድን አመጣ። እባብ ተፈጥሮው ተለውጦ በሆዱ የሚሳብ እንስሳ ሆነ። በእባብ ተመስሎ የቀረበው ሰይጣን ተፈርዶበት የመጨረሻ ሽንፈቱ ተነገረ።
ለ. ሔዋንና ሴቶች ሁሉ ተፈረደባቸው። ከዚህ የተነሣ ልጅ መውለድ አስጨናቂ ሂደት ሆነ። ሴቶች ከባሎቻቸው ጋር የነበራቸው የእኩልነት ግንኙነት ተለውጦ ለባሎቻቸው የሚገዙ ሆኑ።
ሐ. አዳምና ወንዶች ሁሉ ተፈረደባቸው። ሥራቸው ቀላልና የሚያስደስት መሆኑ ቀረና የቤተሰቦቻቸውን ሁሉ ፍላጎት ለማርካት በማያቋርጥ ፍልሚያ ውስጥ ገቡ።
መ. ፍጥረት ተረገመ። የሰው ልጅ ወዳጅ መሆኑ ቀረና ጠላት ሆነ። ለእሾህ፥ አሜከላ፥ ራብ፥ የመሬት መንቀጥቀጥና ሌሎች አጥፊ ነገሮች መከሰቻ ሆነ።
- የመጀመሪያውን እንስሳ መገደልና በመጨረሻም የሰዎች ሁሉ ሞትን አስከተለ። አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር «ደም ሳይፈስ ስርየት የለም» (ዕብ. 9፡22) የሚለው መንፈሳዊ መመሪያ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነው ይላሉ። እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን ራቁትነታቸውን ለመሸፈን ቁርበት ማልበስ ብቻ ሳይሆን፥ ለኃጢአታቸውም እንስሳን ሠዋ። በብሉይ ኪዳን ለጊዜውም ቢሆን ኃጢአቱን ይሸፍን የነበረው የእንስሳ ደም ነበር። በአዲስ ኪዳን ግን ኢየሱስ ለኃጢአት የሚሆን የመጨረሻ መሥዋዕት ሆነ (ዕብ. 9፡22፥ 26-27 ተመልከት)።
- ከእነርሱ በኋላ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አስከተለ። አዳምና ሔዋን ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱ ሰዎች በሙሉ ራስ በመሆናቸው በሰው ልጆች ላይ ፍርድን አመጡ። ይህ ፍርድ የሰዎችን ሕይወት በምድር ላይ አስቸጋሪ ከማድረጉ ሌላ ሥጋዊ ሞት የሰው ልጆች ሁሉ የመጨረሻ ዕጣ መሆኑን እርግጠኛ አደረገው። ይህም ማለት ልጆቻቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ያለማቋረጥ ወደማመፅ የሚወስዳቸውን የኃጢአት ባሕርይ ጭምር ወረሱ ማለት ነው።
- አዳምና ሔዋንን ከዔደን ገነት እንዲባረሩ አደረጋቸው። ይህ እርምጃ የጸጋም የፍርድም እርምጃ ነው። ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ወስደው በመብላት በኃጢአት ለዘላለም እንዳይኖሩ እግዚአብሔር በጸጋና በፍርድ ከዔደን ገነት አባረራቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ የእነዚህ ኃጢአቶች ውጤት ዛሬ በሕይወትህ እንዴት ይታያል?
በአዲስ ኪዳን፥ ክርስቶስ ኃጢአት ያመጣቸውን ነገሮች ማስወገድ ጀምሮ እናያለን። በባልና በሚስት መካከል የነበረው ግንኙነት መስተካከል ነበረበት። በመጨረሻም ዘላለማዊ መንግሥቱ ሲጀመር ይህንን እርግማን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚያስወግድ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ እንመለከታለን (ራእ. 21-22)።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)