እስካሁን ድረስ በኦሪት ዘፍጥረት ጥናታችን ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉ ተመልክተናል። በመጀመሪያ፥ ከአይሁድ ሕዝብ አጀማመር በፊት ያሉትን ጊዜያት በአጭሩ የሚያካትተውን – ከዘፍጥ. 1-11 ያለውን ክፍል፥ በሁለተኛ፥ ደረጃ ደግሞ የአይሁድ ሕዝብ ራስ የሆነውን የአብርሃምን ታሪክ የሚያሳየውን – ከዘፍጥ. 12-24 ተመልክተናል። በተጨማሪ ለአብርሃም በተአምራት የተወለደለትን ይስሐቅ የተባለውን ልጁን ታሪክ መመልከት ጀምረናል።
ዛሬ ደግሞ የአብርሃም ልጅና የልጅ ልጅ ስለሆኑት ስላ ይስሐቅና ስለ ያዕቆብ መመልከት እንጀምራለን።
የውይይት ጥያቄ፥ ከዘፍጥረት 25-36 ያለውን ክፍል አንብብ። ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ይስሐቅ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ለ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ያዕቆብ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ሐ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ቃል ኪዳኑን አደጋ ላይ ጥለውት የነበሩት ነገሮች ምንድን ናቸው? መ) በእነዚህ ምዕራፎች እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ያስተላለፈውና የጠበቃቸው እንዴት ነው? ሠ) የዚህ ክፍል ዋና ዋና ትምህርቶችን ዘርዝር። ረ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ እግዚአብሔር የምንማራቸውን አንዳንድ ነገሮች ጥቀስ። ሰ) ከእነዚህ ምዕራፎች በእምነት ስለ መራመድ የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
ኦሪት ዘፍጥረት የአብርሃም ልጅ ስለሆነው ስለ ይስሐቅ ብዙ ነገሮችን አይነግረንም። እጅግ በጣም ታዛዥ ልጅ እንደነበረ የምናውቀው አብርሃም ሊሠዋው በነበረ ጊዜ በፈቃደኝነት በአባቱ ላይ በመታመን ሲታዘዝ በማየታችን ነው። የይስሐቅ ታሪክ ለያዕቆብ ታሪክ እንደመግቢያ ሆኖ የሚያገለግለን ነው። ያዕቆብ የ12ቱ የእስራኤል ነገዶች አባት በመሆኑ፥ ለአይሁድ ሕዝብ በጣም አስፈላጊ ሰው ነበር። ሙሴ፥ የአብርሃምን ታሪክ በመንገር የእስራኤልን ሕዝብ እንዴት እንደነበር ካሳየን በኋላ አሁን ደግሞ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች እንዴት እንደተመሠረቱ ሊጠቁመን ይጀምራል። የፔንታቱክ ታሪክ እምብርት እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በራሱ አነሣሽነት የመሠረተው ቃል ኪዳን መሆኑን አስታውስ።
ይስሐቅ
ከዘፍጥረት 25-36 ድረስ ቃል ኪዳኑ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረባቸውን የሚከተሉትን ሁኔታዎች ተመልከት፡
- ሌሎቹ የአብርሃም ልጆች ለይስሐቅ መተላለፍ የነበረበትን ቃል ኪዳን አደጋ ላይ ጥለውት ነበር። ቃል ኪዳኑ መተላለፍ ያለበት በተአምራት ለተወለደው በተስፋው ልጅ፥ ለይስሐቅ እንጂ ለሌሎቹ አልነበረም (ዘፍጥ. 25፡1-18)። አብርሃም ሌሎች ልጆችም ነበሩት። የአብርሃምና የአጋር የመጀመሪያ ልጅ እስማኤል ነበር። ለይስሐቅ የተሰጡት የቃል ኪዳን ተስፋዎች ችግር እንዳይገጥማቸው አብርሃም እስማኤልን አስቀድሞ ከቤቱ አስወጥቶት ነበር (ዘፍጥ. 21፡8-21)። ሁለተኛ፥ ከሣራ ሞት በኋላ አብርሃም ካገባት ኬጡራ ከምትባል ሴት የወለዳቸው 6 ወንዶች ልጆች ነበሩት። አብርሃም፥ ከመሞቱ በፊት ስጦታ በመስጠት እነዚህን ስድስት ልጆቹን አሰናበታቸው። ይህም በርስት ጉዳይ ከይስሐቅ ጋር እንዳይጣሉ ታስቦ የተደረገ ነው።
- የይስሐቅ ልጅን ያለ መውለድ አደጋ፡- ይስሐቅ ቃል ኪዳኑን የሚያስተላልፍለትና ርስቱን የሚወርሰው ልጅ እንደማይኖረው ያስመሰሉ ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። በመጀመሪያ፥ እንደ ሣራ ሁሉ ርብቃም መካን ነበረች፤ ነገር ግን በኋላ እግዚአብሔር ዔሳውና ያዕቆብ የተባሉ ሁለት ልጆችን ሰጣት። ሆኖም እነዚህ ልጆች በሚወለዱበት ጊዜ እንኳ ሲጣሉ የነበሩና በሕይወታቸው ዘመንም ሁሉ እየተጣሉ የሚኖሩ ሆኑ። ከመወለዳቸው አስቀድሞ እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን መስመር የሚቀጥለው ሰው ታናሹ (ያዕቆብ) እንጂ ታላቁ (ዔሳው) አይሆንም በማለት ተንብዮ ነበር። እግዚአብሔር አሁንም ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ ከሕዝቡ ባሕልና ከወላጆቻቸው ፍላጎት ተቃራኒ በሆነ መንገድ ተጓዘ (ዘፍጥ. 25፡ 19-23)።
ሁለተኛው አደጋ ደግሞ ርብቃ የሌላ ሰው ሚስት ልትሆን ነበር (ዘፍጥ. 26)። የዘፍጥረት 26 ታሪክ ከዘፍጥ. 25፡19-21 በፊት የተፈጸመ ሳይሆን አይቀርም። አብርሃምና ይስሐቅ ተመሳሳይ ድክመት ነበራቸው። ይስሐቅም በባዕድ አገር በተገኘ ጊዜ እግዚአብሔር ሕይወቱን ሊጠብቅለት እንደሚችል ማመንና በእግዚአብሔር መደገፍ አቃተው። ይስሐቅ በፍልስጥኤማውያን ምድር ለመኖር ሄደ። ልክ እንደ አብርሃም የሚስቱን ማንነት ላለመናገር ዋሸ። ሣራ፥ ታራ ከሌላ ሴት የወለዳት የአብርሃም ግማሽ እኅቱ ስለነበረች፥ እኅቴ ናት ብሎ በከፊል ዋሽቶ ነበር። ይስሐቅ ግን ርብቃ የአጎቱ የልጅ ልጅ ስለነበረች እኅቴ ናት ብሎ ሲናገር ሙሉ በሙሉ ዋሸ። ርብቃ የሌላ ሰው ሚስት ትሆን ዘንድ ተወስዳ ቢሆን ኖሮ ይስሐቅ ቃል ኪዳኑን ሊያስተላልፍለት የሚችል አንዳችም ልጅ አይኖረውም ነበር። እግዚአብሔር ግን በዚህ ድርጊት መካከል ጣልቃ ገባና ርብቃን የሌላ ሰው ሚስት ከመሆን አዳናት።
የውይይት ጥያቄ፥ ስሕተት ብንሠራም እንኳ እግዚአብሔር እንደሚረዳንና የተስፋ ቃሉንም እንደሚጠብቅልን መገንዘባችን በዚህ ዘመን ላለን ለእኛ ምን ያህል ማበረታቻ ይሆነናል?
ዘፍጥ. 26 እጅግ ጠቃሚ ክፍል የሆነበት ሌላ ምክንያት አለ። በዘፍጥ. 26 ሁለት ስፍራዎች ላይ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን የተስፋ ቃል በማረጋገጥ፥ እነዚያው ተመሳሳይ ተስፋዎች ለይስሐቅ እንደተላለፉለት ያሳየዋል (ዘፍጥ. 26፡3-5፥ 23-24)።
- የተስፋው ወራሽ የሆነው ያዕቆብ በዔሳው የመገደል አደጋ (ዘፍጥ.25፡19-34፥27፡1-4)፡- ያዕቆብና ዔሳው በሚወለዱበት ጊዜ ባሕርያቸው ተወስኖ ነበር። ያዕቆብና ዔሳው ሲወለዱ እንኳ እየተጋፉ ነበር የተወለዱት። ያዕቆብ የኖረው ልክ እንደስሙ ትርጉም ነው። ያዕቆብ ማለት «አታላይ» ወይም «አደናቃፊ» ማለት ነው። ያዕቆብ በሚወለድበት ጊዜ እንኳ የወንድሙን ተረከዝ ይዞ በመውጣት ሊያደናቅፈው ሞክሮ ነበር። በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለወጣለት ስም በመኖር ዔሳውን ኋላም ላባን ሲያታልልና ሲያደናቅፍ ኖሯል።
በጊዜው በነበረው ባሕል መሠረት ታላቁ ልጅ ዔሳው የይስሐቅ ወራሽ መሆን ነበረበት። በእግዚአብሔር ዓላማ መሠረት ግን ያዕቆብ ወራሽ ሆኗል። ያዕቆብ ወራሽ መሆኑን ያውቅ እንደ ነበር አንዳችም ጥርጥር የለም፤ ነገር ግን ያዕቆብ እግዚአብሔር ይህንን በረከት እስኪሰጠው ድረስ እንደመታገሥ የዔሳውን ብኩርናን ለመስረቅ ዓቀደ። በመጀመሪያ፥ ያዕቆብ የዔሳውን ራብ ተጠቅሞ በጥቂት ምግብ ብኩርናውን ማለትም የይስሐቅ ወራሽ የመሆን መብት ገዛ። ሁለተኛ፥ ዔሳውን መስሉ አባቱን በመቅረብ ለወንድሙ የሚገባውን በረከት በመረከብ የማታለል ተግባር ፈጸመ፤ (ዘፍጥ. 27)። በረከቱ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባለትን ቃል ኪዳን ሁሉ የመውረስ መብትን ይጨምራል። በረከቱን ለያዕቆብ መስጠት የእግዚአብሔር ዕቅድ መሆኑን ይስሐቅና ርብቃ ቢያውቁም፥ እርሱን ከመታዘዝና ከመደገፍ ይልቅ ይስሐቅ የብኩርና መብትን ለሚወደው ልጁ ለዔሳው ለመስጠት ሞከረ። ርብቃ ደግሞ ባሏ የሚታለልበትን መንገድ በማዘጋጀት የብኩርናውን መብት እርሷ ለምትወደው ልጇ- ለያዕቆብ ለማድረግ ፈለገች። እግዚአብሔር ግን ሁኔታዎቹን ሁሉ በመቆጣጠር የራሱ ዕቅድ እንደተፈጸመ አየ። በረከቱና የቃል ኪዳኑ በረከቶች በሙሉ ለያዕቆብ ተላለፉ።
የውይይት ጥያቄ፥ የወላጆች አንድ ልጃቸውን ከሌላው አስበልጠው መውደድ በቤተሰብ ውስጥ ሊፈጥር ስለሚችለው አደጋ ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል?
ዔሳው መታለሉን በተገነዘበ ጊዜ፥ ያዕቆብን ለመግደል ወሰነ። ይህም ነገር ያዕቆብ ከከነዓን ወደ ካራን እንዲሸሽ አደረገው። ከ20 ዓመት በኋላ ያዕቆብ ወደ ከነዓን ሲመለስ፥ ዔሳው እርሱን የመግደል አሳቡን ለመፈጸም ጥሩ አጋጣሚ ሆነለት። እግዚአብሔር ግን የዔሳውን ልብ ለወጠና ያዕቆብን እንደ ወንድም ተቀበለው፤ (ዘፍጥ. 33)።
- ያዕቆብ በካራን ምድር በነበረበት ጊዜ የገጠመው አደጋ፡- የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንዳይፈጸም ዕንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት ዋና ዋና አደጋዎች ያዕቆብን በካራን ምድር ገጥመውት ነበር። የመጀመሪያው፥ ያዕቆብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ- ከነዓን እንዳይመለስ የከለከለው አደጋ ነበር፤ (ዘፍጥ. 28-30)። በካራን ምድር ባለጸጋ ሆነ። ያዕቆብ ከከነዓን ወደ ካራን በሚጓዝበት ጊዜ እግዚአብሔር በቤቴል ተገናኘው። በሕልሙም እግዚአብሔር ሁለት ነገሮችን አሳውቆት ነበር፡-
- i) እግዚአብሔር በረከቱን የሚፈጽምለት በተስፋይቱ ምድር እንደሚሆን አስታወሰው። 2) የቃል ኪዳኑን በረከት አስቀድሞ ለአብርሃምና ለይስሐቅ እንደሰጠ አሁን ለያዕቆብ አስተላለፈለት፤ (ዘፍጥ. 28፡12-15)። በባዕድ አገር በሚኖርበት ጊዜም ከእርሱ ጋር እንደሚሆን በመንገር አበረታታው።
ያዕቆብ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይመለስ ሊያደርገው የሚችለው አደጋ ካራን በደረሰ ጊዜ እየጨመረ መጣ። በመጀመሪያ ለሁለቱ ሚስቶቹ – ለልያና ለራሔል ሲል 14 ዓመታት ተገዛ። ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለአማቹ ለላባ ቁሳቁሳዊ የሆነ ሀብትና ንብረት ለማስገኘት ብሎ ተጨማሪ 6 ዓመታት ተገዛ።
እግዚአብሔር ግን አታላዩን ያዕቆብን መለወጥ የጀመረው በካራን ምድር ነበር። ያዕቆብ ከእርሱ የባሰ አታላይ የሆነ አጎት አጋጠመው፥ እርሱም ላባ ነበር። እግዚአብሔር ሌላውን ሰው ለማጭበርበርና ቁሳቁሳዊ በረከት ለማግኘት የራስን ጥበብና የማታለል ዘዴ መጠቀም ከንቱ ጥረት መሆኑን ለያዕቆብ ለማሳየት ሲል ላባን ተጠቀመበት።
ከ12ቱ የያዕቆብ ልጆች 11ዱ የተወለዱት በካራን ነበር። ብንያም ግን የተወለደው ቆይቶ በከነዓን ምድር ነበር።
ሀ. የልያ ልጆች፡- ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሉን
ለ. የራሔል አገልጋይ የሆነችው የባላ ልጆች፡- ዳን፥ ንፍታሌም
ሐ. የልያ አገልጋይ የሆነችው የዘለፋ ልጆች፡- ጋድ፥ አሴር
መ. የራሔል ልጆች፡- ዮሴፍ፥ ብንያም ናቸው።
** ማስታወሻ ) ራሔልና ልያ ከአገልጋዮቻቸው ልጅ ለማግኘት በጊዜያቸው የነበረውን ባሕል ተጠቅመዋል። የአገልጋዮቻቸው ልጆች በሕግም አንፃር እንደ ራሳቸው ልጆች ይቆጠሩ ነበር።
- ii) የራሔል የመጨረሻ ልጅ ብንያም ወደ ከነዓን በገቡ ጊዜ ተወለደ። ዳሩ ግን ለራሔል ሞት ምክንያት ሆነ። ራሔል ብንያምን በምትወልድበት ጊዜ ሞተች።
iii) ብሉይ ኪዳን አንድ ሰው ሊኖረው የሚገባው አንድ ሚስት ብቻ እንደሆነ በቀጥታ አያስተምርም ነበር። ነገር ግን አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ብቻ የሚፈጽመው ጋብቻ በሁለት ምክንያት ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያስተምረናል። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር አዳምን ሲፈጥር የሰጠው አንዲት ሴትን እንጂ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ አይደለም። ሁለተኛ፥ ከአንድ በላይ ሚስቶች በሚኖሩበት ቤተሰብ ውስጥ ብዙ ጊዜ በሚስቶቹና በልጆቻቸው መካከል በሚፈጠር ቅንአት ምክንያት የማያቋርጥ ችግር ይከሰታል። በአዲስ ኪዳን ግን እግዚአብሔር በግልጥ ሕዝቡ አንድ ሚስት ብቻ እንዲኖራቸው አስተምሯል (1ኛ ጢሞ. 3፡2፥12)።
እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ከአንድ ሚስት በላይ ማግባትን በቀጥታ በመቃወም ለምን አልተናገረም? ለዚህ ምክንያቱ «በየጊዜው የሚሆን መገለጥ» ወይም «የገለጣ እድገት» ተብሎ የሚጠራው ነገር ነው። እግዚአብሔር ስለ ማንነቱ ከሰዎችም ምን እንደሚፈልግ ሁሉንም ነገር – በአንድ ጊዜ አልሰጠም። ነገር ግን በዘመናት ሁሉ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ቀስ በቀስ እየጨመረና እያደገ በሚሄድ እውቀት በትዕግሥት ገልጧል። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ትኩረት ሰጥቶ ይገልጠው የነበረው፡- ሊመለክ የሚገባው ብቸኛውና እውነተኛው አምላክ እርሱ ብቻ እንደሆነና ሕዝቡ ሌሎች አማልክትን እንዳያመልኩ ነበር። ቆይቶ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር አስቀድሞ አንድ ወንድ ከአንዲት ሚስት ጋር ብቻ እንዲኖር ያወጣውን ዕቅድ ይበልጥ ግልጥ አደረገው (1ኛ ጢሞ. 3፡2፥12)።
የውይይት ጥያቄ፥ የአሥራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች ስም በቃልህ አጥና። ከያዕቆብ ታሪክ ልጆችን ስለማሳደግ የምንማረው ነገር ምንድን ነው?
ያዕቆብ በካራን እያለ የገጠመው ሁለተኛ አደጋ ከላባና ከቤተሰቡ ጋር የገጠመው ጠላትነት ነበር። እግዚአብሔር ያዕቆብን በቁሳቁሳዊ ነገር – ስለባረከው ሀብታም ሆነ። ያዕቆብ እጅግ የተሳካለት ሰው ስለሆነ የሚስቶቹ ቤተሰቦች ቀኑበት። ላባም በያዕቆብ ድካም በመጠቀም ሊያጭበረብረው ሞከረ። በውጤቱም ያዕቆብ ላባን አጭበረበረው፤ የበለጡ ከብቶችንም አገኘ። በመጨረሻም ያዕቆብ ሕይወቱን ለማዳን መሸሽ ነበረበት። ላባም ያዕቆብን ሊይዘውና ሊገድለው ፈለገ። ዳሩ ግን ሁለቱ ሰዎች ከመገናኘታቸው በፊት ያዕቆብን እንዳይነካው እግዚአብሔር ላባን አስጠነቀቀው፤ (ዘፍጥ. 30፡25-31፡55)።
- ያዕቆብና ቤተሰቡን ከሴኬማውያን በኩል አጋጥሞአቸው የነበረው አደጋ (ዘፍጥ. 34)፡- ያዕቆብ ወደ ከነዓን በተመለሰ ጊዜ ከከነዓን ወጣ ብላ በምትገኝ ሴኬም በምትባል ከተማ ይኖር ጀመር። የዚያች ከተማ መሪ የነበረው ሰው ልጅ የያዕቆብን ሴት ልጅ ደፈራት። በምላሹ የያዕቆብ ልጆች ሴኬማውያንን አታለሉአቸውና በከተማው ውስጥ ያሉትን ወንዶች በሙሉ ገደሏቸው። ይህም የቀሩትን ከነዓናውያንን ቁጣ ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ያዕቆብን አደጋ ላይ ጣለው። በዚህ ጊዜ የእስራኤላውያን ቤተሰብ ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር።
በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አስፈላጊ እውነቶች፡-
- ያዕቆብ ከእግዚአብሔር መልአክ ጋር ታገለ፤ (ዘፍጥ. 32፡22-3)። ያዕቆብ ከካራን ተመልሶ ከዔሳው ጋር ሊገናኝ ሲል በድንገት ከእግዚአብሔር መልአክ ጋር ተገናኘና ታገለ። ይህ መልአክ ባለፈው ሳምንት ያጠናነው ልዩ የእግዚአብሔር መልአክ ይመስላል። ለመጀመሪያ ጊዜ ያዕቆብ ከሥጋዊ በረከት ይልቅ መንፈሳዊ በረከትን ፈለገ። ለመጀመሪያ ጊዜ የበረከቱ ምንጭ የእርሱ ጥበብና ችሎታ ሳይሆን እግዚአብሔር መሆኑን አመነ። ከእግዚአብሔር ጋር የጀመረውን ይህን ግንኙነቱን ለማመልከት ስሙ «እስራኤል» ተብሎ ተለወጠ። እስራኤል ማለት «ከእግዚአብሔር ጋር የሚታገል» ማለት ነው። ይህ አዲስ ስም ቆይቶ የአይሁዳውያን ሁሉ መጠሪያ ሆነና ሕዝቡ እስራኤላውያን ተባሉ። ይህ ስም ለአይሁድ ሕዝብም የሚስማማ ነው። ምክንያቱም በአሉታዊ መልኩ በታሪካቸው ሁሉ አይሁድ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታገሉ፥ እግዚአብሔርን ለመከተልና ለመታዘዝ የማይፈልጉ በመሆናቸው ነው።።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የያዕቆብ ሕይወት ከአንተ የእምነት እርምጃ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) ከያዕቆብ ታሪክ ስለመንፈሳዊ ነገሮች የምንማረው ምንድን ነው?
- በኦሪት ዘፍጥረት የአጻጻፍ ባሕርይ መሠረት፥ ሙሴ የተመረጠውን የአይሁድን ሕዝብ ታሪክ ከመቀጠሉ በፊት ያልተመረጡትን የሌሉቹን ሕዝቦች የትውልድ ታሪክ ይተነትናል። ሙሴ የይስሐቅን ታሪክ ከመናገሩ በፊት የእስማኤልን የትውልድ ታሪክ እንደሰጠ ቀደም ሲል ተመልክተናል፤ (ዘፍጥ. 25፡12-18)። በዘፍጥ. 36 ደግሞ የይስሐቅ ሌላው ልጅ የሆነውን – የዔሳውን የትውልድ ታሪክ ይተነትናል። ከዚያም ቀጥሉ የዮሴፍን ታሪክ ይነግረናል።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)