“ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፣ … ነውና።” ፊል 1:21 

ፊልጵስዩስ 1:21 እንዲህ ይላል፣ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።” ብዙ ሰዎች፣ “…ሞትም ጥቅም ነውና።” በሚለው በጥቅሱ ሁለተኛ ክፍል ላይ በማተኮር አማኝ ከሞት በኋላ ስለሚገጥመው የሰማይ ደስታ ብቻ ሲያወሩ ይሰማል። ሆኖም የጥቅሱን ቀዳሚ ክፍል ማለትም፣ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ…ነው” የሚለውን ችላ ማለት የለብንም፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ…ነው” የሚለው ሐረግ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ማዕከላዊ ሃሳብ መሆን ያለበት ነው፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የምንመለከተው፣ ሐዋሪያው ጳውሎስ ጌታ ኢየሱስን መከተል ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሆነው እና ለመሆነ ያሰበው ነገር ሁሉ ክርስቶስ ኢየሱስን ማእከል ያደረግ መሆኑን ነው፡፡ ከተለወጠበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሰማዕትነቱ ድረስ የወሰደው እያንዳንዱ እርምጃ ወንጌልን ላልሰሙ ሁሉ በማዳረስና ቤተክርስቲያንን በማሳደግ ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ የጳውሎስ የሕይወት ዘመን ነጠላ ዓላማ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ማምጣት ብቻ ነበር፡፡

“ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ…ነው” ማለት የክርስቶስን ወንጌል በጊዜውም ያለጊዜውም ማወጅ ማለት ነው፡፡ ጳውሎስ በምኩራቦች ሰብኳል፤ በወንዝ ዳርቻዎች ሰብኳል፤ እንደ እስረኛ ሰብኳል፤ እንደ ሐዋርያ ሰብኳል፤ እንደ ድንኳን ሰፊ ሰብኳል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን መልእክቱ ወጥ እና አንድ ነበር፣ “…ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር” እንዳያውቅ መቁረጡ (1ኛ ቆሮንቶስ 2:2)። የክርስቶስን ቤዛዊ መስዋዕትነት ለነገሥታቶች፣ ለወታደሮች፣ ለገዥዎች፣ ለካህናትና ፈላስፋዎች፣ ለአይሁድና ለአህዛብ፣ ለወንዶችና ለሴቶች፣ በአጭሩ ሊሰሙት ለሚወዱ ሁሉ ሰብኳል፡፡

“ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ…ነው” ማለት የክርስቶስን ምሳሌነት መከተል ማለት ነው። ኢየሱስ ያደረገውን እና ​​የተናገረውን ነገር ሁሉ ነበር ጳውሎስ ማድረግ እና መናገር የፈለገው። ቤተ ክርስቲያን ከጳውሎስ የምሳሌነት ሕይወት ተጠቅማለች፣ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” (1 ኛ ቆሮንቶስ 11:1)። “ዛሬ ኢየሱስ በምድር ላይ ቢኖር ኖሮ ምን ያደርግ ነበር?” የሚለውን ጥያቄ ራሳችንን መጠየቅና ተግባራዊ ምላሹን በእርሱ ፈንታ እኛ ማድረጋችንን መገምገም የእርሱን ምሳሌያዊ ሕይወት እየተከተልን መሆን አለመሆናችንን ለመለካት ጥሩ መሣሪያ ነው።

“ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ…ነው” ማለት ክርስቶስን ማወቅ ማለት ነው፡፡ በየቀኑ ክርስቶስን ከትላንትናው በተሻለ ለማወቅ እንፈልጋለን ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን፣ ስለ ክርስቶስ አንዳንድ እውነታዎችን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ ራሱን ማወቅን ይጨምራል፡፡ “እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ”  (ፊልጵስዩስ 3:10-11)፡፡

“ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ…ነው” ማለት ከክርስቶስ ጋር የጠበቀ ሕብረት እንዳይኖረን የሚከለክለንን ማንኛውንም ነገር ለመተው ፈቃደኛ ነን ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የጳውሎስ ምስክርነት አስገራሚ ነው:- “ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤”(ፊልጵስዩስ 3:7-9)። ከዚህ የመስዋዕትነት ሕይወት ጎን ለጎን በማርቆስ 10፥29-30 ውስጥ የተሰጥውን የተስፋ ቃል ማስታወስ እጅግ አበረታች ነው:- “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”

“ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ…ነው” ማለት ክርስቶስ የእኛ ዋና ትኩረት፣ ዋና ግብ እና ዋና ፍላጎታችን ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቶስ የአዕምሯችን፣ የልባችን፣ የአካላችን እና የነፍሳችን ማዕከል ይሆናል፡፡ የምናደርገውን ነገር ሁሉ ለክርስቶስ ክብር እናደርጋለን፡፡ “ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት” በማስወገድ “የእምነታችን.. ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት” እንሮጣለን (ዕብ. 12:1-2)። 

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ

4 thoughts on ““ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፣ … ነውና።” ፊል 1:21 ”

  1. በናዝሬቱ: በኢየሱስ: ስም: ትምህርታችሁ /ጥናቱ /በጣም: ሕይወትን: ለዋጭ:
    ነው።ጌታ:ይባርካችሁ።የእግዚአብሔርን:ቃል:ለማጥናት: የሚጠቅም:ቀላል:መንገድ: እና: መሰረት:የሚያሲዝ: ነው።በእዚህ:
    ዘመን:እንደዚህ: አይነት: ትምህርት: ማግኘት: ትልቅ: እድል: ነው።

Leave a Reply

%d