“ለእኔ … ሞትም ጥቅም ነውና።” (ፊልጵስዩስ 1:21)

ፊልጵስዩስ 1:21 እንዲህ ይላል፣ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።” ይህን የጳውሎስን ሃሳብ ለመረዳት በመጀመሪያ ዐውደ-ጽሑፉን መመርመር ይኖርብናል፡፡

የፊልጵስዩስ መጽሐፍ ከሐዋሪያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን የተላከ ደብዳቤ ነው፡፡ በመልእክቱ ውስጥ፣ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን ያበረታታል፣ ምክር ይሰጣል፣ ክርስቲያኖች ሊመሩበት የሚገባውን ሕይወት ያሳያል፣ ወዘተ፡፡ በምዕራፍ 1 መጀመሪያ ላይ፣ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ በመስጠት ምን ያህል እንደሚናፍቃቸው ያሳውቃቸዋል (ፊልጵስዩስ 1:1-8)፡፡ ቀጥሎም፣ በሮም ስለታሰረበት ሁኔታ በመናገር የአማኞችን አእምሮ ለማረጋጋት ጥረት ያደርጋል (ቁጥር 12 እስከ 14)፡፡ ጳውሎስ እየተቀበለ ያለው መከራ ለአንድ ዓላማ መሳካት መሆኑን ያውቃል፤ ያም ዓላማ የወንጌል ስርጭት ነበር፣ “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።” (ቁጥር 12)፡፡

በዚህ ዐውደ-ጽሑፋዊ አወቃቀር ውስጥ ነው እንግዲህ የጳውሎስን፣ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።” የሚለውን ንግግር የምናየው (ፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 19 እስከ 20)። እስከዚህ ጊዜ ድረስ፣ ጳውሎስ በሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ብዙ መከራን ተቀብሏል፡፡ ተደብድቧል፣ በድንጋይ ተወግሯል፣ ተጠልቷል፣ ተፌዞበታል፣ የመርከብ አደጋ ደርሶበታል፣ እና አሁን ደግሞ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን፣ ጳውሎስ እየተቀበለ ያለው መከራ እምነቱን እጅግ ስላጠነከረውና ስለ ክርስቶስ እንደ ታማኝ ምስክር ሆኖ እንዲቆም ምክንያት ስለሆነው፣ በመከራው ከማጉረምረም ይልቅ ደስ ተሰኝቶ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መስበክ እና የሰበከውን ቃል በተግባር መኖር የጳውሎስ ዋነኛ የሕይወት ግብ ነበር፤ እናም እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለዚህ ዓላማው መሳካት ምቹ እድሎችን ፈጠሩለት፡፡ ሰውነቱን (አካሉን) ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋት “እንደ ሕያው መሥዋዕት” (ሮሜ 12:1) አድርጎ አቀረበ፡፡ በፊቱ ያለውን ሩጫ  በታማኝነት ስለሮጠ (ዕብ 12፡1)፣ በሕይወቱ እና በሞቱ እግዚአብሔር እንደሚከብር ያውቅ ነበር (ፊልጵስዩስ 1፡19-20)፡፡

እንደ ክርስቲያኖች፣ መላው ሕይወታችን ለእግዚአብሔር ክብር ማምጣት ላይ የነጣጠረ ሊሆን ይገባል፤ ጳውሎስ በመከራው ወቅት እንኳን ሳይቀር ያንን ግብ እየፈፀመ ነበር (“ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ…ነውና”)፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕይወቱ ብቻ ሳይሆን ሞቱ ጭምር ለእግዚአብሔር ክብርን እንደሚያመጣ ያውቅ ነበር፤ እናም፣ በሞት መሣፈሪያ ከኢየሱስ ጋር ፊት ለፊት የሚተያይበትን ቀን ተመኘ (ቁጥር 23)፡፡

ሁሉም ክርስቲያኖች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለዘላለም ለመኖር  ይናፍቃሉ፡፡ ኃጢአት፣ ህመም እና ሞት በማይኖርበት ስፍራ ከአባታችን ጋር ስለምንሆን መንግስተ ሰማያት ከምድራዊ ሕይወት ይልቅ እጅግ የተሻለች ሥፍራ እንደሆነች እናውቃለን (2ኛ ቆሮንቶስ 5፡8)፡፡ በዚህ ሕይወት ያጣነውን በሰማይ እናገኛለንና፡፡ ያ ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ግን፣ በምድር ላይ ያለን ዓላማና ግብ በኃጢያት እና በሞት ጨለማ ውስጥ እንደ ተስፋ ብርሃን መኖር ሊሆን ይገባል (ማቴዎስ 5፡16)። እንደ ጳውሎስ ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን ሞታችን እንኳን ሳይቀር ለክርስቶስ ኢየሱስ ክብር በሚያመጣበት አግባብ ሊቃኝ ይገባዋል፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: