በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳንን መፈጸም ማለት ምን ማለት ነው (ፊልጵስዩስ 2:12)?

በፊልጵስዩስ 2:12-13 ውስጥ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይጽፋል፣ “ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።”

ይህ ጥቅስ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ድነትን ካገኙ በኋላ ሊያጡት እንደሚችሉ ለማስረዳት በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል፡፡ ይህ ክፍል የሚያወራው አማኝ በእግዚአብሔር ፊት ስላለው አቋማዊ ቅድስ (positional sanctification) ማለትም በክርስቶስ አማካኝነት በእግዚአብሔር ፊት ስላለው ጽድቅ (justification) ሳይሆን  ቀጣይነት ስላለው መቀደስ (progressive sanctification) ወይም ስለ መንፈሳዊ ብስለት (spiritual maturity) ነው።

ለመሆኑ፣ መዳንን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መፈጸም ማለት ምን ማለት ነው? ጳውሎስ አማኞች ባልተቋረጠ ጭንቀት እና ፍርሃት ውስጥ እንዲኖሩ እየመከረ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ያ፣ በድነታችን ጀማሪና ፈጻሚ በሆነው በእግዚአብሔር ላይ እምነት፣ ድፍረትን እና መተማመን እንዲኖረን ከሚመክሩት ሌሎች በርካታ ማሳሰቢያዎቹ ጋር ይጋጫልና፡፡ በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ ውስጥ “ፍርሃት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል “ማክበር” ወይም “ከማክበር የሚመነጭ ፍርሃት” ከሚሉት ሃሳቦች ጋር አቻ ነው፡፡ ጳውሎስ ይህንኑ ሃረግ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ቲቶን ከተቀበለችበት የአክብሮትና የትህትና አቀባበል ጋር በተያያዘ እንዲህ ሲል ተጠቅሟል፣ “ስለዚህም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደተቀበላችሁት፥ የሁላችሁን መታዘዝ እያሰበ ፍቅሩ በእናንተ ላይ እጅግ በዝቶአል (2ኛ ቆሮንቶስ 7:15)።” ጳውሎስ ራሱ ወደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ ታማኝ ተደርጎ የተቆጠረበትን የወንጌል አገልግሎት ታላቅነትና ክብር በማሰብ፣ “…በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤ (1 ቆሮ. 2:3)” ሲል ሃረጉን ይጠቀማል።

ድነታችንን በመንቀጥቀጥና በፍርሃት መፈጸም በሚለው ሃሳብ ሁለት ነጥቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ነጥብ፣ “ፈጽሙ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ግስ ሲሆን ይህ ቃል “አንድ ነገር ወደ ፍጻሜ ወይም ፍሬ ለማምጣት ያለማቋረጥ መሥራትን” ያሳያል፡፡ ይህንንም ጳውሎስ በቀጣዩ የፊልጵስዩስ ምዕራፍ ውስጥ እንደሚያብራራው ቀጣይነት ባለው የመቀደስ (progressive sanctification) ጉዟችን ውስጥ ለእግዚአብሔር ታዛዥነታችንን በማሳየት እንገልጻለን፡፡ ይህን ጉዳይ ጳውሎስ፣ ክርስቶስን ለመምሰል “እዘረጋለሁ” እና “እፈጥናለሁ” (ፊልጵስዩስ 3፡13-14) በማለት  ይገልጸዋል። ጳውሎስ የሚለው “መንቀጥቀጥ” ክርስቲያኖች ይህንን ግብ (ማለትም ክርስቶስን መምሰልን) ለማሳካት ሊኖራቸው የሚገባውን የልብ ዝንባሌ ያመለክታል፡፡ ይህም፣ እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ ላለማሳዘን እና ለታላቅነቱና ለቅድስናው ሊኖረን የሚገባ አክብሮታዊ ፍርሃት ነው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ፣ “መንቀጥቀጥ” የሚለው ሲሆን ይህ ቃል አንድን ነገር ለማድረግ አቅም ከማጣት ጋር በተያያዘ ሊታይ ይችላል፡፡ ይህ አይነቱ መንቀጥቀጥ ወደ እግዚአብሔር ጥገኛነት የሚያደርስ ላቅ ያለ ግብ ስላለው ጥቅሙ እጅግ ከፍተኛ ነው። የምንፈራውን እና የምናከብረውን አምላካችንን መታዘዛችን እና ለእርሱ መገዛታችን “ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችን” ነው (ሮሜ 12፡1-2)፡፡ ይህም ታላቅ ደስታን ያስገኝልናል። ይህን ጉዳይ መዝሙር 2:11፣ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።” ሲል ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፡፡ በአክብሮትና በአድናቆት መንፈስ በመቅረብ፣ ልባችንን እና አእምሯችንን ወደምናድስበት ወደ መዳን ምንጭ ወደ እግዚአብሔር ቃል በመሄድ መዳናችንን በመንቀጥቀጥና በፍርሃት እንፈጽማለን (ሮሜ 12፡1-2)፡፡

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ

1 thought on “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳንን መፈጸም ማለት ምን ማለት ነው (ፊልጵስዩስ 2:12)?”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading