የእግዚአብሔር ሉአላዊነትና የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ

ስለ አንድ ነገር ያለን እውቀት ጉዳዩን አስመልክቶ በምንወስደው ማንኛውም ውሳኔ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ትክክለኛ እውቀት ወደ ትክክለኛ ውሳኔ እንደሚያመራን ሁሉ የተሳሳተ ወይም የተዛባ እውቀት ደግሞ ተቃራኒውን መንገድ እንድንከተል ምክንያት ይሆነናል፡፡ በተለይ ውሳኔው የሞት ሽረት ከሆነ፣ ስለጉዳዩ ትክክለኛ እውቀት መያዝ ግዴታ እንጂ ምርጫ አይሆንም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊነትና ስለ ሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀት መያዝ የሞት ሽረት ያህል ከባድ የሚሆንበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል የተረዳሁት በዚህ እውቀት መዛባት ምክንያት ራሱን ያጠፋ መጋቢ መኖሩን በአንድ ጽሑፍ ውስጥ ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡

የሚገባኝን ባለማድረጌ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተጓጉላለሁ ወይ? እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያለው የዘላለም እቅድ፣ እኔ የድርሻዬን ባለመወጣቴ ምክንያት ሳይሳካ ይቀራል ወይ? ከእግዚአብሔር ሉአላዊነት አንጻር የእኔ ድርሻ ምንድን ነው? እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት ውስጥ ያለውን እቅድ ከማሳካት አኳያ ከእኔ የሚጠብቀው ምንድን ነው? እግዚአብሔር ያለ እኔ ተሳታፊነት በእኔ ውስጥ ሊያደርጋቸው የሚችላቸው ነገሮችና ያለ እኔ ደግሞ ሊያደርጋቸው የማይችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ይህን ርዕሰ ጉዳይ በአግባቡ ካለመረዳት ሊመነጩ ይችላሉ፡፡ 

የሰው ልጅ ካለው ውሱን እውቀት እና በሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች ጥያቄዎቹን ሁሉ እንደ ነጭና ጥቁር ቀለማትን የመለየት ያህል በማያሻማ ሁኔታ መመለስ ባይቻልም፣ ነፍስን አስጨንቆ ሕይወትን እስከማጥፋት ደረጃ የሚደርስ ውሳኔ ውስጥ ላለመግባት የሚያስችል መርህ ግን  መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ይገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡    

ከእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ሃሳብ እንጀምር፡፡ ለመሆኑ፣ የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ምን ማለት ነው? በአጭሩ፣ ሉዓላዊነት ማለት “ሉዓላዊ ገዥ” ያለው ነገር ሁሉ ማለታችን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት፣ ማለትም አጽናፈ ዓለሙን እና በውስጡ ያሉትን ሁሉ ያለማንም ተቀናቃኝነት መቆጣጠሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ አስተምሕሮ ነው:- 

 • “አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፥ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው።” (1 ዜና 29:11-12)።
 • “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች የሚመልሳትስ ማን ነው?” (ኢሳ 14:27)
 • “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ።” (ኢዮብ 42:2)
 • “እግዚአብሔርን ለመቋቋም የሚያስችል፣ አንዳችም ጥበብ ማስተዋልና ዕቅድ የለም።” (ምሳ 21:30 አ.መ.ት.) 
 • “…የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘላለም ይኖራል፥ የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው።” (መዝ 33:11)
 • “በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል።” (ምሳ 19:21)

እግዚአብሔር በአጽናፈ አለሙ ውስጥ ያለውን ሁሉ እንደሚገዛ እና ያሰበውን ከማድረግ የሚያግደው አንዳች ሃይል እንደሌለ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከዳር ስንመረምር የምናገኘው ሃቅ ነው፡፡ የሰው ልጅ፣ ሰይጣን እና ቅዱሳን መላእክት ሳይቀሩ በአንድነትም ሆነ በተናጥል ከእግዚአብሔር ሃሳብ በተቃራኒ በመቆም እቅዱን ማሰናከል ከቶ አይችሉም፡፡ ሆኖም ግን ይህ አስተምሕሮ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ከተቀመጠ ሌላ ርእሰ ጉዳይ (ማለትም ከሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ሃሳብ) ጋር በተዛምዶ ካልታየ፣  የሰውን ልጅ ሃላፊነትንና ግዴታን ከጨዋታው ውጪ በማድረግ ጥፋት የሚያስከትል ዋልታ ረገጥ ሃሳብ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለ ሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ስናወራ ምን እያልን ነው? የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ማለት አንድን ነገር ያለ ተጽእኖ የመምረጥ አቅምን ይመለከታል፡፡ የሰውን ነጻ የመምረጥ ችሎታን ስናወራ ከውድቀት በፊትና በኋላ ያሉትን ማንነቶች ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ ከውድቀት በፊት የሰው ልጅ የክፉና የመልካም እውቀት ስለሌለው (ዘፍ. 3:22) ያለምንም ውስጣዊ መልካም ተጽዕኖ – መልካሙን፣ ያለምንም ውስጣዊ ክፉ ተጽዕኖ ደግሞ- ክፉዉን የመምረጥ ችሎታ ነበረው፡፡ ከውድቀት በኋላ ግን የሰው ልጅ መልካም የማድረግ (የመምረጥ) ችሎታውን በማጣት የሚያደርገውን የማያውቅ፤ የሚጠላውን የሚያደርግ እና የሚወደውን የማያደርግ ሆነ (ሮሜ. 7:15)። ይህ ማለት የሰው ልጅ የነበረውን ነጻ ፈቃድ አጥቶ ፈቃዱ በባርነት ስር ወደቀ ማለት ነው (ሮሜ. 6:16-20፣ ሮሜ. 7:20፣ ዮሐ. 8:34)፡፡ በዳግም ልደት (ማለትም ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛችን በተቀበልን ወቅት) ክፉውን ያለምርጫችን የማድረግ ባርነት ከላያችን ተገፎ ቀድሞ የነበረንን በነጻ የመምረጥ ችሎታ መልሰን ተጎናጽፈናል (ሮሜ. 6:17-19)፡፡ ኢየሱስን እንደግል አዳኛቸው ያልተቀበሉ ሰዎች ጥቅል የሆነው መልካሙን የመምረጥ ነጻነታቸው በባርነት ውስጥ ቢሆንም እንኳ፣ በእግዚአብሔር ምሕረት ምክንያት የድነትን ወንጌል ለመቀበል መምረጥ እንዲችሉ ነጻነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚሁ ባርነት ውስጥም ሆነው እንኳን እጅግ በተትረፈረፈው የእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ቢያንስ  አንድ ምርጫን ያለባርነት (በነጻነት) የማድረግ እድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም፣ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ በኩል ያቀረበላቸውን የድነት ጥሪ መቀበል ወይም አለመቀበል ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ ኢየሱስን ለመቀበል ሰዎች እንዲያደርጉት የሚቀርብላቸው የምርጫ ጥያቄ ትርጉም አልባ ይሆን ነበር፡፡ ሰው ነጻ ምርጫ የሌለው ሮቦት ቢሆን ኖሮ፣ አማራጭ ሃሳቦች ቀርበውለት እንዲወስን መጠየቅም ሆነ በውሳኔውና በተግባሩ ተጠያቂ መደረግ አይገባውም፡፡ እናም፣ ጌታን እንደግል አዳኙ ያልተቀበለ ሰው ጥቅል የሆነ ነጻ ፈቃድ ባይኖረውም እንኳ ለሃሳቡና ድርጊቱ ተጠያቂ ላለመሆን ማመካኛ አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ባርነት የመውጫ መንገድ በኢየሱስ ቤዛነት በኩል ተዘጋጅቶለታልና፡፡ 

ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ፣ ይህ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ትምሕርት፣ እንደ እግዚአብሔር ሉዓላው አስተምህሮ ሁሉ ተለጥጦ አጥፊ እውቀት ሊሆን የሚችልበት አደጋም አለው፡፡ የዚህ አስተምሕሮ ጽንፈኞች፣ “በነጻ ፈቃዳችን በመጠቀም ልንወስን በማሰብ ላይ ያለነው ነገር ለእግዚአብሔር የተሰወረ ነው፤ እንዳውም ውሳኔያችንን ለማወቅ እግዚአብሔር በጉጉት ይጠባበቃል፤” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እግዚአብሔር ወደፊት ስለሚሆነው ነገር እውቀት ከሌለው፣ ወደፊት ምን ሊገጥመን እንደሚችል በማሰብ በትልቅ ጭንቀት ውስጥ ልንወድቅ ይገባል፡፡ እውነታው ግን ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው፣ በሰው ልብ (አእምሮ) ውስጥ የሚመላለሰውንም ሆነ ገና ያልታሰበውን ሃሳባችን ሳይቀር ያውቃል:-

 • “እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።” (ኢሳ 46:9-10)
 • “እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣ እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ።” (መዝ 139:4 አ.መ.ት.) 
 • “እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ። መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤ መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል።” (መዝ 139:1-3 አ.መ.ት.) 
 • “እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ፥ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።” መዝ 139:15-16
 • “አንተም፥ ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና፥ የአባትህን አምላክ እወቅ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው ብትፈልገው ታገኘዋለህ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል።” 1ዜና 28:9
 • “እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።” ዕብ 4:13
 • “…እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል።” 1ዮሐ 3:20

እናም፣ እውነቱ ያለው በእነዚህ ሁለት ጽንፎች መካከል መሆን አለበት፡፡ የሰው ልጆች (የጌታ ኢየሱስን አዳኝነት የተቀበሉቱ) እግዚአብሔር እንዲያስቡ፣ እንዲናገሩና እንዲያደርጉ ያዘዛቸውን ሁሉ ለማሰብ፣ ለመናገርና ለማድረግ ነጻ ፈቃድ አላቸው፡፡ ይህ ነጻነት ስላላቸውም እንዲያስቡት፣ እንዲናገሩትና እንዲያደርጉት የሚጠበቅባቸው ሃላፊነቶች ይኖሩባቸዋል፡፡ ሁሉ ነገር አስቀድሞ በተወሰነለት ኡደት በራሱ መንገድ የሚሆን እንደሆነ ማሰብም ሆነ ነገሮችን ሁሉ ያለ እኛ ተሳትፎ እግዚአብሔር ከሉዓላዊነቱ በመነሳት እንደሚፈጽማቸው ማሰብ ሁለቱን ትምሕርቶች (የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነትና የሰውን ልጅ ነጻ ፈቃድ) ያለሚዛን ከመገንዘብ የሚመጣ ስህተት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ የሚወጣ ምንም ነገር እንደሌለ እንደምናውቀው ሁሉ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የምርጫ ነጻነት ሲሰጥም ያለምክንያት እንደሆነ ማሰብ የለብንም፡፡ ያለነጻ ፈቃድ ተጠያቂነትን ለማስፈን ማሰብ እግሩን ያሰርነውን ሰው ለምን እንዳልሮጠ መጠየቅ ማለት ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ለፈጠረው ጭንቅላት ግልጽ ከሆነ ከዚህ ያነሰ ከእግዚአብሔር መጠበቅ እርሱን አለማወቅ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሔር የድርሻዬን እንድወጣ በጠየቀኝ ቦታ የእሱን ድርሻ መጠበቀም ሆነ የእርሱ ድርሻ እንደሆነ በነገረኝ ነገር ውስጥ የእኔን እጅ ማስገባት ሁለቱም ስህተቶች ናቸው፡፡ የእኔ ድርሻ ምንድር ነው? የሚል ጥያቄ አንስተህ ከሆነ፣ ለአብነት እንሆ:- “ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” (ሚክ 6:8)፡፡ እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ ሁሉን ማድረግ የሚችል ቢሆንም፣ እኛ እንድናደርገው የሚጠብቀው ነገርም አለው፣ “እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራ እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን” (ኤፌ 2:10)። እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለወሰነው እቅድ ተናግሮ ሲያበቃ፣ በወሰነው በዚሁ እቅዱ ውስጥ ያንተን ድርሻ ካሳየህ፣ የሁለቱ ሃሳቦች ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ባይገባህም እንኳ የተጠየከውን አድርግ፡፡ ባለማድረግህ የሚጎድልብህ ሊኖር ቢችልም በማድረግህ የምትጠቀመው እንጂ የምትጎዳው ነገር አይኖርምና፡፡ 

ጸሐፊ፤ አዳነው ዲሮ

1 thought on “የእግዚአብሔር ሉአላዊነትና የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ”

 1. ጠቃሚ መረጃ ነው፣ ነገሩን በስፋት ባያብራራም ግልጽ የሆነ ጭብጥ አለው፡፡ አመሰግናለሁ

Leave a Reply

%d bloggers like this: