በልቤ ውስጥ ትኖራላችሁ (ፊል 1፡7-8) 

በልቤ ውስጥ ትኖራላችሁ (ፊል 1፡7-8) 

“በልቤ ስላላችሁ፣ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው፤ በእስራቴም ሆነ ለወንጌል ስመክትና ሳጸናው ሁላችሁም ከእኔ ጋር የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ናችሁና። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያህል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው።”

አሁን ደግሞ ትንሽ ጠለቅ ወዳለ አስተሳሰብ እንተላለፍ፤ ሌሎችን በአእምሮአችን ልናስታውሳቸው ብንችልም እንደ እውነቱ ግን በልባችን ውስጥ ላይኖሩ ይችላሉ። (አንድ ሰው እንደ ታዘበው፥ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች፥ «አንጄቴን ቆርጠኃል!» በሚለው ገለጻ መጠቀማቸው የተለመደ ሆኗል።) ጳውሎስ ለጓደኞቹ ያለው ቅን የሆነ ፍቅር ግን የተሰወረ ወይም እንዳስመሳይ አልነበረም። 

የክርስቲያን ፍቅር «የሚያስተሳስር» ነው። ፍቅር ተድነታችን (የደኅንነታችን) ማስረጃ ነው «እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሸጋገርን እናውቃለን» (1ኛ ዮሐ. 3፡14)። ጨው አልጫ ውስጥ ቢገባ ወጡን እንደሚያጣፍጠው ሁሉ ፍቅር የማኅበራዊ ጉዳዮችን የኑሮ እንቅስቃሴ ያለምንም እንቅፋት በሰላማዊ መንገድ እንዲጓዝ ይረዳል። ጳውሎስ ሲጽፍ «ሁላችሁም» የሚለውን ሐረግ ብዙ ጊዜ እንደተጠቀመበት አስተውላችኋል? በዚህ መልእክት ቢያንስ ቢያንስ ዘጠኝ ጊዜ ጠቅሶት ነበር። ስለሁሉም ሰው በማሰብ አንድም ሰው እንኳን ቢሆን እንዲገለልበት አይፈልግም (አንዳንድ ትርጉሞች «እኔ በልብህ ውስጥ አለሁ» ይላሉ። ለምሳሌ በቁጥር 7 ውስጥ ተመልከት፤ ሆኖም ግን መሠረታዊው እውነት ኣንድ መሆኑን ልብ በል።) 

ጳውሎስ ፍቅሩን እንዴት ነበር ያሳያቸው? አንዱ ነገር፥ እርሱ ስለ እነርሱ መከራ ይቀበል ነበር። እስራቱም ፍቅሩን ያረጋግጣል። እርሱ «አሕዛብ ስለሆናችሁ ስለእናንተ የክርስቶስ እስረኛ ነበር» የተባለለት ሰው ነው (ኤፌ. 3፡1)። ጳውሎስ ለፍርድ በመቅረቡ ምክንያት፥ ክርስትና በሮም ባለሥልጣኖች ፊት በአግባቡ መታየት ጀመረ። ፊልጵስዩስ በሮም ቅኝ ግዛት ሥር ስለነበረች፥ በዚያ ያሉትን አማኞች ውሳኔው ጎድቷቸዋል። የጳውሎስ ፍቅር እንደው ለአፍ ያህል የሚናገረው ሳይሆን የተለማመደው ነገር ነበር። ለእርሱ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም፥ ዳሩ ግን ያንን አጋጣሚ ወንጌልን ለመጠበቅና እውነት መሆኑን ለማስረዳት ጥሩ ዕድል አድርጎ ቆጥሮታል። በዚህም በየቦታው ያሉት ወንድሞቹ ተጠቅመውበታል። 

ታዲያ ይህን ዓይነቱን ፍቅር ለመለማመድ ክርስቲያኖች እንዴት መማር ይችላሉ? «እኔ ካልዳኑት ዘመዶቼ ይልቅ ከዳኑት ጎረቤቶቼ ጋራ መኖር የበለጠ ይቀለኛል» ብሎ አንድ ሰው ለመጋቢው አጫወተውና በመቀጠልም «ምናልባትም አንድ ቢላዋ ስለት እንዲያወጣ በሌላ ቢላዋ መሞረድ ያሻዋል እንደሚሉት ዓይነት ለእኔም ተመሳሳይ እርዳታ ሳያስፈልገኝ አይቀርም» ሲል አከለበት። የክርስቲያን ፍቅር እኛ የምንሠራው ነገር ሳይሆን እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ እና በእኛም አማካይነት ለሌሉች የሚሠራው ነገር ነው። ጳውሎስ ከጓደኞቹ ተለያይቶ በመቆየቱ «በክርስቶስ ኢየሱስ እንደምናፍቃችሁ» ሲል ጽፏል (ቁ. 8)። ይህም ማለት የጳውሎስ ፍቅር በክርስቶስ አማካይነት ተገልጿል ማለት ሳይሆን፥ በዚያ ምትክ ግን የክርስቶስ ፍቅር በጳውሎስ አማካይነት ተላለፈ ማለት ነው። «በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ሞላ ተስፋው አያሳፍረንም» (ሮሜ 5፡5 አዲስ ትርጉም)። እግዚአብሔር «መልካሙን ሥራ» በእኛ ውስጥ እንዲያከናውን ስንፈቅድ፥ እርስ በርሳችን በፍቅር እናድጋለን። 

በእውነት ከሌላው ክርስቲያን ጋር በፍቅር መተሳሰራችንን እንዴት መናገር እንችላለን? አንደኛ ነገር፥ እኛ ለሌሎች ማሰባችን ነው። በፊልጵስዩስ ያሉ አማኞች ለጳውሎስ ስለሚያስቡ አፍሮዲጡን እንዲያገለግለው ላኩለት። ጳውሎስም ደግሞ በተለይ አፍሮዲጡን በህመሙ ምክንያት መልሶ ለመላክ ባቃተው ጊዜ (2፡25-28) በፊልጵስዩስ (ስላሉት) ወዳጆቹ በጣም ያስብ ነበር። «ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ» (1ኛ ዮሐ. 3፡18)። 

እርስ በርስ ይቅር ለመባባል ፈቃደኛ መሆን ሌላው የክርስቲያን ፍቅር መግለጫ ነው። «ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉም በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ(1ኛ ጴጥ. 4፡8)። 

ከዕለታት አንድ ቀን የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ለአንድ ሰው ቃለ መጠይቅ አቀረበለት፤ ያም ቃለ መጠይቅ እንዲህ የሚል ነበር፡- «ባለቤትህ የፈጸመችውን አንዳንድ ስሕተቶችን ልትነገረን ትችላለህን?» ብሉ ጠየቀው። 

«ምንም ነገር ማስታወስ አልችልም» ሲል ሰውየው መለሰለት። 

«ታዲያ፣ አንዳንዱን እንኳን ማስታወስ አያቅትህም» አለው የፕሮግራሙ አዘጋጅ። 

«አይ፥ በእውነቱ ማስታወስ አልችልም» አለ መልስ ሰጪው። «ባለቤቴን በጣም ስለምወዳት እንደዚህ ያለውን ነገር በትክክል አላስታውስም»። በ1ኛ ቆሮ. 13፡5 ውስጥ «ፍቅር በደልን አይቆጥርም» ተብሎ ተጠቅሷል። 

በፍቅር የሚሠሩ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ደስታን ይለማመዳሉ፥ ሁለቱም የአንድ መንፈስ መገኘት ውጤት ነው። «የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፥ ደስታ … ነው» (ገላ. 5፡22)።

ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading