“እናንተን ባስታወስሁ ቍጥር አምላኬን አመሰግናለሁ። ዘወትር ስለ ሁላችሁ ስጸልይ፣ በደስታ እጸልያለሁ፤ ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስካሁን ድረስ በወንጌል አገልግሎት ተካፋይ ሆናችኋልና። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ።”
ጳውሎስ ስለራሱ ማሰብ ትቶ ለሌሎች ማሰቡ የሚያስደንቅ አይደለምን? ጳውሎስ በሮም ፍርዱን እየጠበቀ አሳቡን በፊልጵስዩስ ወዳሉት አማኞች በመመለስ እያንዳንዱ የሚያስታውሰው ነገር ደስታን ይሰጠው ነበር። የሐዋርያት ሥራ 16ን አንብቡ፤ ይህንን ስታነቡ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ከተማ ስለደረሰበት በደል ማወቅ ትችላላችሁ፥ ይህ ትውስታ ሐዘንን የሚፈጥር ነው። አግባብ ያልሆነ እስራትና ድብደባ ደረሰበት፥ ከግንድ ጋር አጣብቀው አስረውት ነበር፥ በሰዎችም ፊት ተዋርዶ ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን ሲያስታውስ እንኳን ለጳውሎስ ደስታ ይሰጠዋል፥ ምክንያቱም በዚህ መከራ ውስጥ በማለፍ ነበር የወህኒ ጠባቂው ክርስቶስን ለማግኘት የቻለው! ጳውሎስ ሊዲያንና ቤተሰቧን ያስታውሳል፥ በአጋንንት ተይዛ የነበረችውን ድሀ ልጅ፥ እንዲሁም በፊልጵስዩስ ያሉ ውድ ክርስቲያኖችን እና ሌሎችም የሚያስታውሳቸው ነገሮች የደስታው ምንጭ ነበሩ። (እንዲህ ብለን እራሳችን መጠየቅ የሚገባን ነው «ለመሆኑ መጋቢዩ ስለእኔ በሚያስብበት ጊዜ እውነተኛ ደስታን የማስገኝለት ዓይነት ክርስቲያን ነኝን?»)።
ቁጥር 5 እነርሱ (የፊልጵስዩስ ሰዎች) ከጳውሎስ ጋር ስለነበራቸው ገንዘብ-ነክ ኅብረት ሊያወራ ይችላል፥ ይህን አርእስት በድጋሚ በ4:14-19 አንስቶታል። የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን የጳውሎስን አገልግሎት ለማገዝ ከጳውሎስ ጋር ኅብረት ያደረገች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። በቁጥር 6 ላይ «መልካም ሥራ» ብለን የምንመለከተው ያላቸውን ነገር እንደሚከፋፈሉ ነው፤ ይህም የተጀመረው በጌታ እንደመሆኑ ጳውሉስም ጌታ በዚሁ እንደሚቀጥልና ከፍጻሜ እንደሚያደርሰው እርግጠኛ ነበር።
ነገር ግን እነዚህን ጥቅሶች ለድነታችንና (ለደኅንነታችንና) ለክርስቲያናዊ ኑሮአችን ዋስትና እንደሚያስገኙልን አድርገን መውሰዱ ወደ ስህተት ሊያመራን አይችልም። እኛ የዳንነው በመልካም ሥራችን አይደለም (ኤፌ. 2፡8-9)። ድነት (ደኅንነት) ማለት በልጁ ስናምን እግዚአብሔር በእኛ የሚሠራው መልካም ሥራ ነው። በፊል. 2፡12-13 እንደሚናገረን እግዚኣብሔር በእኛ የጀመረውን ሥራ በመንፈሱ በኩል ይቀጥላል በሌላ አነጋገር፥ ድነት በአጠቃላይ ሦስት አቅጣጫ ያለው ነው።
– እግዚአብሔር ለእኛ የሠራው – መዋጀት
– እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ የሚሠራው – መቀደስ
– እግዚአብሔር በእኛ አማካኝነት የሚሠራው – አገልግሎት
ይህ ሥራ ክርስቶስን እስከምናየው ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን ሥራው ይፈጸማል «ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን» (1ኛ ዮሐ. 3፡2)።
እግዚአብሔር በፊልጵስዩስ ባሉ አማኝ ጓደኞቹ ሕይወት ውስጥ እስካሁን መሥራቱን ማወቅ ለጳውሎስ የደስታው ምንጭ ነበር። በእርግጥም እውነተኛ መሠረት ያለው ደስተኛ የክርስቲያን ኅብረት አለ ለማለት የምንችለው እግዚአብሔር በየቀኑ ኑሮአችን ውስጥ ሲሠራ ነው።
ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ