ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል (ፊልጵስዩስ 1፡27-30) 

የክርስቲያን ሕይወት የጨዋታ ሜዳ ሳይሆን የጦር ሜዳ ነው። እኛ በወንጌል አንድነት ደስ የሚለን የአንድ ቤተሰብ ልጆች ነን (1፡1-11)። እኛ ወንጌልን ለማስፋፋት የተሰማራን አገልጋዮች ነን (1፡12-26)። ከሁሉም በላይ ደግሞ እኛ የወንጌልን እምነት የምንጠብቅ ወታደሮች ነን፥ እና በአንድ አሳብ የሚመሩ አማኞች በጦርነት መሃል ቢሆኑ እንኳን የመንፈስ ቅዱስ ደስታ ይኖራቸዋል። 

«የወንጌል እምነት» ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መለኮታዊ እውነት ነው። ይሁዳ በመልእክቱ ላይ «ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ» (ቁ. 3) ብሉ ይጠራዋል። ጳውሎስ በ1ኛ ጢሞ. 4፡1 ላይ «በኋለኛው ዘመናት አንዳንዶች ሃይማኖትን ይክዳሉ» ብሎ ያስጠነቅቃል። እግዚአብሔር ለጳውሎስ ይህን መንፈሳዊ ሀብት አደራ ሰጥቶታል (1ኛ ጢሞ. 1፡1)። እና እሱም በተራው ለጢሞቴዎስ እንደሰጠው ሁሉ አደራውን ለሌሎችም አስተላልፏል (1ኛ ጢሞ. 6፡20)። የእርሱም ኃላፊነት ከጳውሎስ የተማረውን ለሌሎች ማስተላለፍ ነው (2ኛ ጢሞ. 2፡2)። ቤተ ክርስቲያንም በማስተማር አገልግሎት የተሰማራችው ለዚህ ነው፥ ይኸውም የእያንዳንዱ የአዲስ ትውልድ አማኞች የእምነታቸውን ቅርስ በማወቅ፥ እንዲወዱትና እንዲጠቀሙበት ለማስቻል ነው። 

ነገር ግን ጠላት የከበረውን ነገር ከእግዚአብሔር ሕዝብ ሊሰርቅ በደጅ ነው። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ጠላቱን አግኝቶታል፥ አሁንም በሮም አግኝቶት ነበር። ሰይጣን የአማኞችን የክርስትና እምነት ለመስረቅ እስከቻለ፥ የእነርሱም የሆኑትን የሥነ መለኮት ሕግጋት ለመቀማት እስከደፈረ፥ የወንጌልን አገልግሎት ለማሰናከልና ድል ለማድረግ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች «ትክክለኛ ሕይወት እስከመራ ድረስ፥ ስለሰውየው እምነት ግድ የለኝም» ብለው ሲናገሩ መስማት ምንኛ ያሳዝናል። እንደ እውነቱ ግን እንዴት እንደምንኖር የሚወስነው እምነታችን ነው። የተሳሳተ እምነት ውሎ አድሮ ኑሮአችንን ማበላሸቱ የማይቀር ነው። ሰይጣን በተለይ ወጣቶችን ከእምነት ለማራቅ ያለማቋረጥ ትግል ማካሄዱ ሊያስገርመን አይችልም። 

ክርስቲያኖች እንዴት ይህንን ጠላት መዋጋት ይችላሉ? «የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና» (2ኛ ቆሮ. 10፡4)። በአትክልት ስፍራ ጴጥሮስ ሰይፉን መዘዘ፥ ኢየሱስ ግን ገሠጸው (ዮሐ. 18፡10-11)። እኛ የምንጠቀመው በመንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው። እነርሱም የእግዚአብሔር ቃል እና ጸሉት ናቸው (ዕብ. 4፡12፤ ኤፌ. 6፡11-18)። የሚያስፈልገንን ኃይል እንዲሰጠን በመንፈስ ቅዱስ መተማመን አለብን፤ ነገር ግን ጦርነቱን አንድ ላይ ነው መዋጋት ያለብን። ለዚህም ነው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ላሉ ወዳጆቹ ኅብረታቸውን እንዲያጠነክሩ አስጠንቅቆ የላከው። በዚህም አንቀጽ ላይ ውጊያውን ድል ለማድረግና «እምነትን» ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሦስት ጠቃሚ ነገሮች ማስፈሩን እንመለከታለን። 

  1. አሳበ ጽኑነት (1፡27) 

«እንግዲህ በጣም አስፈላጊው ነገር ሕይወታችሁ የክርስቶስን የምሥራች ቃል ዋጋ ያለው እንዲያደርግ ነው» (አዲሱ ትርጉም)። ጠላትን ለመቃወም በጣም ጠቃሚው የጦር ዕቃችን ቀስቃሽ ስብከት ወይም ኃይለኛ መጽሐፍ አይደለም፤ ግን አሳበ ጽኑ የሆነ የአማኝ ኑሮ ነው። 

ጳውሎስ የተጠቀመበት ግሥ እኛ ፖለቲካ ከምንለው ቃል ጋር የተገናኘ ነው። እርሱ የሚለን ዜጎች መሆን እንደሚገባቸው መንገድ ሁኑ» ነው። እኔና ሚስቴ ለንደንን እየጎበኘን እያለን አንድ ቀን አራዊቶች ወደሚጠበቁበት ቦታ ለመሄድ ወሰንን። በጉዞው ለመደሰት ስንል በአውቶቡስ ተሳፍረን ከኋላ ተቀመጥን። ታዲያ ከፊታችን ካሉት ተሳፋሪዎች ጩኸትና ያልታረመ ንግግር የተነሳ መደሰት አልቻልንም። ለክፋቱ ደግሞ ሁሉም አሜሪካኖች ነበሩ። በእኛ አካባቢ ያሉት እንግሊዛውያኖችን ስናያቸው በትዝብት እየተመለከቷቸውና እራሳቸውን እየነቀነቁ «አዎን፥ እነዚህ ከአሜሪካ የመጡ መሆን አለባቸው!» በማለት በሆዳቸው ያሟቸዋል። እኛ አፈርን፥ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች እንደ አሜሪካዊ ዜግነታቸው በእውነቱ ጥሩ ሥነ ምግባር አላሳዩም። 

ጳውሎስ እንደሚያስበው እኛ ክርስቲያኖች ሰማያዊ ዜጎች ነን። በመሆኑም በምድር ላይ በምንኖርበት ጊዜ እንኳን ሕይወታችንን እንደ ሰማያዊ ዜጎች መምራት አለብን። ይህን አሳብ በ3፡20 ላይ በድጋሚ አንስቶታል። ይህ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጣም ትርጉም ያለው አባባል ነው። ምክንያቱም ፊልጵስዩስ በሮም ቅኝ ግዛት ሥር የምትገኝ፥ ነዋሪዎችዋም የሮም ዜግነት ያላቸውና መብታቸውም በሮማ ሕግ የተጠበቀላቸው ነበሩ። ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ ያለ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅኝ ግዛት ነው። ስለዚህ እኛም እራሳችንን እንደ ሰማያዊ ዜጎች መቁጠር አለብን። 

«እኔ ተገቢ በሆነው በወንጌል ሥርዓት መሠረት ራሴን መርቻለሁን?» የሚለውን ጥሩ ጥያቄ ዘወትር ራሳችንን መጠየቅ አለብን። «እኛ በክርስቶስ ያለን እንደተጠራንበት መጠራት በሚገባ መመላለስ …» አለብን (ኤፌ. 4፡ 1)። መመላለስ ማለት «እንደ ጌታ ፈቃድ በመኖር በሁሉ ነገር ጌታን ታስደስታላችሁ» ማለት ነው (ቆላ. 1፡10)። እንደዚህ የምንሆነው ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ስንል አይደለም ምክንያቱም በመልካም ሥራችን አልዳንንም። ግን እንደዚህ የምንሆነው አስቀድሞ ስማችን በመንግሥተ ሰማይ ስለተጻፈ እና ዜግነታችን ሰማያዊ ስለሆነ ነው። 

እዚህ ላይ በሚገባ ማስታወስ ያለብን፥ በዙሪያችን ያለው ዓለም የሚያውቀው፥ እኛ በምድራዊ ሕይወታችን የምናንፀባርቀውን ወንጌል መሆኑን ነው። 

በምትሠራው ሥራ፥ በአነጋገርህ 

አንድ ምዕራፍ ወንጌል በቀን መጻፍህ 

እንዳይዘነጋህ፥ እንዳይረሳህ፤ 

ሰዎች ያነቡታል ያንን የጻፍከውን 

በእምነት ጸንተህ እንደሁ ለእውነት መቆምህን 

ወንጌልህ ያሳይ ዘንድ፥ ብቃት ያለው ይሁን! 

(ጸሐፊው ማን እንደሆነ አይታወቅም።) 

«ወንጌል» ማለት የምሥራች ቃል ማለት ሲሆን፥ ይኸውም ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን መሞቱን፥ መቀበሩንና ከሞት መነሣቱን የሚያበስረን ነው (1ኛ ቆሮ. 15፡1-8)። ለድነታችን (ለደኅንነታችን) መንገድ «የምሥራቹ ቃል» ብቻ ሲሆን፥ ማንኛውም ሌላ መልእክት ውሸት ነው (ገላ. 1፡6-10)። የወንጌል መልእክት ግን የምሥራች ቃል ነው። የሚያበስርልን መልካም ዜናም ኃጢአተኞች በኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ልጅ በማመን እነርሱም የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን የመቻላቸውን ተስፋ ነው (ዮሐ. 3፡16)። በወንጌል ላይ አንዳች መጨመር ኃይሉን መቀነስ ነው። እኛ ከኃጢአታችን የዳንነው በክርስቶስ በማመን ላይ ሌላ ነገር ጨምረን አይደለም። እኛ የዳንነው በክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። 

«ከጎረቤቶቼ አንዳንዶቹ በሐሰተኛ ወንጌል የሚያምኑ ናቸው» ሲል አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል የሆነ ሰው ለመጋቢው ነግሮት፥ እግረ መንገዱንም «ልሰጣቸው የምችለው የተጻፈ ነገር አለህን?» በማለት ጠየቀው። መጋቢውም መጽሐፍ ቅዱሱን በማውጣት ከ2ኛ ቆሮ. 3፡2 ላይ፥ «ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባቸው የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ» የሚለውን አነበበለት። በመቀጠልም «በዓለም ውስጥ ካለው ምርጥ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ አንዱም እንኳን የአንተን ሕይወት መተካት አይችልም። በአንተ ባሕርይ ውስጥ ክርስቶስ እንዳለ አሳያቸው፥ እና ይህ በራሱ የክርስቶስን ወንጌል እንድታካፍላቸው እድል ይከፍትልሃል» በማለት መከረው። 

ሰይጣንን ለመቃወም ታላቁ የጦር ዕቃ እግዚአብሔርን እየመሰሉ መኖር ነው፤ ስለዚህ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ይህንን እውነት ከተለማመዱ፥ «የሚያምኑትን ይሆናሉ»። ይህ ደግሞ ጠላትን ድል ያደርጋል። በዚህም ውጊያ ላይ ድል ለማድረግ የመጀመሪያው ጠቃሚ ነገር ይኼው ብቻ ነው። 

  1. መተባበር (1፡27) 

ጳውሎስ አሁን የሚያብራራውን ከፖለቲካ ወደ ሩጫ ለውጦታል። (በጋራ መታገል) የሚለው ሲተረጎም (የሩጫ ውድድር) «አትሌቲክስ» የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ይሰጣል። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን የሳለው በቡድን መስሉ ሲሆን፥ በዚህም ተባብሮ በመሥራት ድል እንደሚገኝ ያሳስባቸዋል። 

በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈል እንደ ነበረ በአሳባችሁ ያዙት። አንደኛ ነገር፥ ሁለት ሴቶች በአንድ ላይ ተስማምተው ሊኖሩ አልቻሉም (4፡2)። የኅብረቱ አባሉችም ወገን የለዩ ይመስላል፥ ጉዳዩ ለብዙ ጊዜ በዚሁ ሁኔታ ቀጠለ፤ እናም የመከፋፈሉ ውጤት የቤተ ክርስቲያኑን ሥራ እንዲደናቀፍ አደረገ። ጠላት በአገልግሎት ውስጥ ያለውን መከፋፈል እያየ ሁልጊዜ ይደሰታል። «ከፋፍል እና ግዛ» የእርሱ መመሪያ ነው። ይህም ዘዴው ብዙ ጊዜ ያዋጣዋል። ሆኖም አማኞች በአንድ ላይ በመቆም ክፉውን ማስወገድ ይችላሉ። 

በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ዳር እስከ ዳር ድረስ ጳውሎስ የአንድነትን ጥቅም በማጉላት አስደናቂ በሆነ መንገድ አቅርቦታል። በግሪክ ቋንቋ የአንድ ቃል መነሻው «ሰን» ከሆነ፥ ትርጉሙ «ጋር» ወይንም «በአንድነት» መሆንን ያመለክታል። ከሌላ ቃል ጋር አብረን በምንጠቀምበት ጊዜ የመተባበርንና አንድ ግንባር የመመሥረትን አሳብ ያጠናክራል። (ይህም እኛ «አብሮ» በማለት ከምንጠቀምበት መነሻ ጋር ይመሳሰላል)። ጳውሎስ ይህንን መነሻ ቃል በፊልጵስዩስ መልእክት ውስጥ ቢያንስ 16 ጊዜ ተጠቅሞበታል። አንባቢዎች መልእክቱን ሊያጡት አይችሉም! በ1፡27 ውስጥ በግሪክ ቃል ሰን አቴሊዮ የሚለው «ለማሸነፍ አብሮ መታገል» ማለት ነው። 

ጄሪ በልምምዱ በመሰላቸቱ፥ ለአሰልጣኙ ምን እንደሚሰማው ሊነግረው ወስኗል። «ከአሁን በኋላ ወጥቼ ለመለማመድ ምንም ስሜት የለኝም። ምክንያቱም ማይክ እራሱን እንደ አንድ ቡድን ስለሚቆጥር፥ የእኛ ከእርሱ ጋር መሰለፍ የሚያስፈልግ ባለመሆኑ ነው» ሲል አማረረ። 

አሰልጣኙ ጋርድነር ግን ችግሩን በማወቅ «እባክህ ጄሪ ተመልከት! ማይክ ግብን ለማስገባት ብዙ እድል አገኘ ማለት የቀራችሁት አታስፈልጉም ማለት አይደለም። አንዱ ከሌላው ጋር ተጋግዘ ኳሱን ወደ ግብ አካባቢ ማድረስ አለበት። እናንተም የምታስፈልጉት እዚህ ላይ ነው» በማለት አጽናናው። 

አንዳንድ ጊዜ በአንድ ቡድን ውስጥ ሙገሳውን ሁሉ ለግሉ አሰባስቦ የሚወስድ «የታደለ» ተጫዋች ሊኖር ይችላል። ይህም አብዛኛውን ጊዜ በተቀሩት የቡድኑ አባላት ዘንድ ቅሬታን ይፈጥራል። ምንም እንኳን ሁሉም በእኩል ደረጃ ይጫወታሉ ለማለት ባይቻልም፥ ሆኖም ግን ሙገሳው የሚደራረበው ለአንዱ ተጫዋች ብቻ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ይህ ቅሬታ ለሽንፈት ምክንያት ይሆናል። ለክፋቱ፥ በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ አንዳንድ «ክብር አሳዳጆች» አሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ዲዮጥራጢስ ሲናገር «ዋናቸው ሊሆን የሚወድ» ይለዋል (3ኛ ዮሐ. 9)። ሐዋርያቶቹ ያዕቆብና ዮሐንስም እንኳን ልዩ ዙፋን እንዲኖራቸው ጠይቀዋል (ማቴ. 20፡20-28)። ጠቃሚው ቃል አንድ ላይ የሚለው ነው፤ በአንድ መንፈስ ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆም፥ በአንድ ላይ ታግሉ ጠላትን መቃወም ማለት በአንድ አሳብና ልብ መሥራት ማለት ነው። 

አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሯጭ ቡድን አድርገን በመቁጠር፥ በዚህ አሳብ በስፋት ለመጠቀም እንችላለን። እያንዳንዱ ሥራውን በትክክል ከሠራ፥ ሌሉቹን በሙሉ ይረዳል። ሁሉም ሰው መሪ ወይም ግብ ጠባቂ ሊሆን አይችልም። ቡድኑ ሕጎችን መከተል አለበት፥ የእግዚአብሔር ቃል ለእኛ «የመምሪያ-መጽሐፍ» ነው። አንድ ግብ አለ፤ እርሱም ክርስቶስን ለማክበር እና የእርሱን ፈቃድ መሥራት ነው። ሁላችንም አንድ ላይ ከሠራን ወደ ግቡ ደርሰን ሽልማትን እናገኛለን፥ ጌታንም እናከብራለን (ለክርስቲያን ሕይወት ሥነ-ሥርዓት መጠበቅ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን ለሕጉ ባለመታዘዝ ካፈነገጥን፥ ልምምዳችንን ካቋረጥን ወይንም ክብርን ብንፈልግ ተባብሮ መሥራት ይጠፋና በምትኩ መከፋፈልና መፎካከር ይነግሣል። 

በሌላ አነጋገር፥ ጳውሎስ እንደገና የሚያስታውሰን የአንድ አሳብ አስፈላጊነቱን ነው። ከጠላት ጋር ውጊያ ቢኖርም እንኳን በእኛ ኑሮ ውስጥ ደስታ አለ። ለክርስቶስና ለወንጌል ከኖርን «ከክርስቲያን ጋር መተባበርን» እንለማመዳለን። እርግጥ ነው፥ አብረናቸው ልንሠራ የማንችለው አንዳንድ ሰዎች አሉ። (2ኛ ቆሮ. 6፡14-18፤ ኤፌ. 5፡1)፥ ነገር ግን አብረናቸው ልንሠራ የምንችለውና፥ ልናገላቸው የማይገባን ብዙዎች አሉ። 

እኛ ሰማያዊ ዜጎች ስለሆንን አሳባችንን ጽኑ አድርገን መጓዝ አለብን። እኛ «የአንድ ቡድን» አባሎች ስለሆንን ተባብረን መሥራት ይገባናል። ነገር ግን ጠላትን ስንገጥም ውጤቱን ለማቃናት የሚረዳን ሌላም ሦስተኛ ጠቃሚ የሆነ መሣሪያ አለን። ይኸውም በራሳችን ላይ ያለን መተማመን ነው። 

  1. በእግዚአብሔር ላይ መተማመን (1፡28-30) 

«ከተቃዋሚዎቻችሁ የተነሣ አትደንግጡ!» ጳውሎስ ይህን ቃል ሲጠቀም በውጊያ ላይ በደነበረ ፈረስ በማስመሰል ነው። በእርግጥ ማንም ሰው አይኑን ጨፍኖ ወደ ጦርነት ፍልሚያ ውስጥ አይገባም። ነገር ግን ማንም እውነተኛ አማኝ ሆን ብሉ ጠላትን መጋፈጥን ማስወገድ አይችልም። በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ጳውሎስ በውጊያ ላይ እምነት እንዲኖረን በርካታ ማበረታቻዎች ሰጥቶናል። 

መጀመሪያ፥ እነዚህ ውጊያዎች ለመዳናችን ማረጋገጫ ናቸው (ቁ. 29)። እኛ በክርስቶስ ማመን ብቻ ሳይሆን ስለእርሱም መከራ መቀበል አለብን። ጳውሎስ ይህንን «በመከራም እንድንካፈል» ይለዋል (3፡10)። በአንዳንድ ምክንያቶች ለብዙ አዲስ አማኞች በክርስቶስ መታመን የውጊያ መጨረሻ ማለት ነው ይላሉ። እውነቱ ግን የአዲስ ውጊያ መጀመሪያ ማለት ነው። «በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ» (ዮሐ. 16፡33)። «በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ» (2ኛ ጢሞ. 3፡12)። 

በሌላ ጎኑ ደግሞ የቅራኔ መኖርም አንድ እራሱን የቻለ ዕድል ነው፤ እኛ መከራ የምንቀበለው «ስለ እርሱ» ነው። እንዲያውም፥ ጳውሎስ እንደነገረን ይህ የቅራኔዎች መኖር ለእኛ እንደልዩ «ስጦታ» ሊቆጠር የሚገባው ነው። ለእራሳችን መከራን ብንቀበል፥ ምንም ዕድል የለውም። እኛ ለክርስቶስና ከክርስቶስ ጋር መከራን ብንቀበል ትልቅና የተቀደሰ ክብር እናገኛለን። መቼም እሱ መከራን ለእኛ ከተቀበለልን፥ እኛም ለእርሱ ፍቅራችንን ለማሳየትና ለምስጋና ስንል በፈቃደኛነት መከራን ብንቀበል የሚበዛብን አይሆንም። 

ሦስተኛው ማበረታቻው የሚከተለው ነው፤ «ሌሎቹም አንድ ዓይነት መጋደል ተለማምደዋል» (ቁ. 30)። ሰይጣን በውጊያ ጊዜ ብቻችንን እንደሆንን እንድናስብ፥ ችግሮቻችንንም ከሌሉቹ የተለዩ አድርገን እንድንመለከታቸው ይፈልጋል። እውነታው ግን እንደዚህ አይደለም። ጳውሎስ ያለው በሮም ውስጥ ቢሆንም፥ ከእርሱ በብዙ ኪሎሜትር ርቀው በፊልጵስዩስ ከሚገኙት ወዳጆቹ ጋር ተመሳሳይ ችግር በማሳለፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። የመልክአ ምድር ለውጥ አብዛኛውን ጊዜ ለመንፈሳዊ ችግር መፍትሔ አይሆንም። ምክንያቱም የትም ብንሄድ የሰው ተፈጥሮ አንድ በመሆኑ ነው። ደግሞም ጠላት በሁሉ ቦታ አለ። የሚያምኑ ወዳጆቼ በውጊያው ላይ መካፈላቸውን ማወቄ ለእኔ ማበረታቻ ነው። እንዲሁም ለእኔ እንደምጸልይ ለእነርሱም መጸለዩን እቀጥላለሁ። 

በእውነቱ በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ማለፍ ወደ ክርስቶስ የማደጊያ አንደኛው መንገድ ነው። እግዚአብሔር ጠላትን አጥብቀን እንድንቃወም የሚያስፈልገንን ኃይል ሰጥቶናል። ይህም በእርሱ ላይ የመተማመን ስሜታችን የሚያረጋግጠው የእኛን ከአሸናፊዎች ወገን መሰለፍ ነው (ቁ. 28)። የፊልጵስዩስ ሰዎች ጳውሎስ ከእነርሱ ጋር በነበረ ጊዜ በዚህ ውጊያ ውስጥ እንዳለፈ አይተዋል (ሐዋ. 16፡19 ጀምሮ አንብብ)፥ እና ከጌታ ጋር መጣበቁን አስመስክሯል። «ውጊያ» የሚለው ቃል ስለ ጣር ያሳስበናል። ይህም በአትክልት ሥፍራ የክርስቶስን ጣር ለመግለጽ ከሰፈረው ቃል ጋር አንድ ዓይነት ትርጉም ያለው ነው (ሉቃ. 22፡44)። በጌታ ተደግፈን ጠላታችንን ስንገጥም እሱም ለውጊያ የሚያስፈልገንን ኃይል ሁሉ ይሰጠናል። ጠላትም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰጠንን መተማመን ሲያይ ይፈራል። 

በአንድ አሳብ የጸናን መሆናችን በውጊያ መሀል ውስጥ ሆነን እንኳ ደስታን እንድናገኝ ያስችለናል፥ ምክንያቱም በእኛ ውስጥ አሳበ ጽኑነትን፥ መተባበርን፥ መተማመንን እንድናገኝ ስለሚያስችለን ነው። የወንጌልን እምነት ለማጠናከር በመጣጣራችን «በመንፈስ ተባብሮ የመሥራትን» ደስታ እንለማመዳለን። 

ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ

1 thought on “ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል (ፊልጵስዩስ 1፡27-30) ”

Leave a Reply

%d