Site icon

በክርስቲያናዊ ሕይወቴ ደስታን እንዴት ማግኘት እችላለሁ?

ደስታ ሁላችንም ሊኖረን የምንፈልገው ነገር ቢሆንም በተግባር ለመለማመድ ግን ቀላል ሲሆን አይታይም፡፡ ደስታን ማጣጣም ወይም በጥቅሉ ደስተኛ መሆን ከእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ይጠበቃል። ደስተኛ ሕይወት መምራት፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፈቃድ ከመሆኑ ባሻገር እርሱ ራሱ በውስጣችን የሚሰራው የመንፈሱ ፍሬ ነው፡፡ 

በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሳል የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ደስታ አልባ የሆነ ሕይወት ያሳለፉበት ጊዚያት እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ፣ ኢዮብ መፈጠሩን ጠልቶ ነበር (ኢዮብ 3፣11)። ዳዊት ደግሞ የገጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ ወደማያይበት ስፍራ እንዲወሰድ ጸልዮ ነበር (መዝሙር 55፣6-8)። ኤልያስ በበኩሉ 450 የበኣልን ነቢያት ካሸነፈና እሳትን ከሰማይ መጥራት ከቻለ በኋላ እንኳ (1ኛ ነገሥትት 18:16–46) ወደ ምድረ በዳ ሸሽቶ ነፍሱ ከስጋው እንድትለይ እግዚአብሔርን ጠይቆ ነበር (1ኛ ነገሥትት 19:3-5)። ታዲያ፣ እነዚህ ታላላቅ ሰዎች እንዲህ ባሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈው እንዲህ አይነቶቹን ምኞቶችና ጸሎቶች ካደረጉ እኛ እንዴት የማያቋርጥ ደስታን መለማመድ እንችላለን?

የመጀመሪያው ቁም ነገር፣ ደስታ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን መገንዘብ ነው፡፡ ደስታ የሚለው ቃል በግሪክ ስረወ ቃሉ ቻራ (chara) ሲሆን በትርጉሙ ቻሪስ (charis) ከሚለው የግሪክ ቃል ጋር አቻ ነው፡፡ ቻሪስ (charis)፣ ጸጋ ከሚለው ቃል ጋር ተቀራራቢ ፍቺ አለው፡፡ ደስታ የሚለው ቃል የእግዚአብሔር ስጦታን እና ለዚህ ስጦታ የምንመልሰውን ምላሽ አካቶ ይይዛል፡፡ ደስታን የምንለማመደው ስለእግዚአብሔር ጸጋ ስናውቅ ባቻ ሳይሆን በእኛ ውስጥ እንዲፈስ ስንፈቅድም ጭምር ነው።

ይህንን እውነት በአእምሯችን ይዘን ስንነጋገር፣ ደስታን የምንለማመድበት አንዱ መንገድ በእግዚአብሔር ላይ ያተኮረ ሕይወት ስንመራ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ትኩረታችንን ከችግሮቻችን ወይም ደስታችንን ከሚሰርቁት ጉዳዮች ላይ አንስተን በአምላካችን ላይ የማረፍ ሕይወት መለማመድ እንችላለን። ይህ ማለት ግን የሚሰሙንን አሉታዊ ስሜቶች ሁሉ በውስጣችን መኖራቸው እንክዳለን ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ፣ የብዙዎቹን የመዝሙራት ጸሃፊዎች ምሳሌ በመከተል፣ ልባችንን በእግዚአብሔር ፊት ማፍሰስ እንችላለን። ይህ ማለት የሚያሳዝኑንን እና የሚያሳምሙንን የነፍስ ሸክሞች እንደሌሉ ከመቁጠር ወይም ከመካድ ይልቅ በጸሎት በእግሩ ስር ማኖር መለማመድ ማለት ነው። ከዚያም ነገሮቹን ለእርሱ በማስገዛትና እርሱ ማን እንደ ሆነ በማስታወስ በእርሱ ደሳችንን እናገኛለን (መዝሙር 3፣ 13፣ 18፣ 43 እና 103 ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው)።

ምንም እንኳን ጳውሎስ ከእስር ቤት የጻፈው ደብዳቤው ቢሆንም የፊልጵስዩስ መጽሐፍ ስለ ደስታ ብዙ ይላል፡፡ ፊልጵስዩስ 4፣4-8 በክርስቲያን ሕይወት ደስታ ለማግኘት የሚረዱ አንዳንድ መመሪያዎችን ይሰጣል:- “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤” በዚህ ጥቅስ ውስጥ፣ እግዚአብሔርን የማመስገን አስፈላጊነትን፣ ቅርብ መሆኑን የማስታወስ ጠቃሚነትን፣ ስለሚያስጨንቁን ጉዳዮች የመጸለይ አስፈላጊነትንና፣ አእምሮአችን በእግዚአብሔር መልካም ነገሮች ላይ ትኩረት የማድረግ ውጤትን እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔርን ሆን ብለን በማመስገን ደስታን መለማመድ ይቻላል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ማሰላሰል (ማጥናት) ደስታ ሊያስገኝልን እንደሚችል ዳዊት በመዝሙሩ ጽፏል (መዝሙር 19፣8)። በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር መነጋገራችንም ደስታን ይሰጠናል። እንዲሁም ትኩረታችንን ከአስቸጋሪ ሁኔታዎቻችን ላይ በማንሳትና በእግዚአብሔር መልካምነት ላይ በማድረግ ደስታን ልናጣጥም እንችላለን፡፡

ኢየሱስ ደስታን አስመልክቶ የተወሰኑ መመሪያዎችን ሰጥቷል፡፡ በዮሐንስ 15 ውስጥ በእርሱ ስለ መኖር እና መታዘዝ ተናግሯል:- “አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ” (ዮሐ. 15፥ 9-11)። ለደስታ ቁልፍ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መኖር ነው፡፡

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ደስታን የምንለማመድበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ በቅዱሳን ሕብረት ውስጥ በመሳተፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለኤልያስ ረዳቱ እንዲሆን ኤልሳዕን ልኮለት ነበር (1 ነገሥት 19:19-21)፡፡ እኛም ጉዳቶቻችንን እና ህመሞቻችንን የምናጋራቸው ጓደኞች ያስፈልጉናል (መክብብ 4፥ 9-12)። ዕብራውያን 10:19-25  (አ.መ.ት) እንዲህ ይላል:- “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ …እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ”፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር በተቀበልነው ፀጋ ምክንያት በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንደምንችል እናውቃለን (ዕብ. 10፣19)። በክርስቶስ ደም ከኃጢያታችን እንደነጻንም እናውቃለን (ዕብ 10፣22)። ከዚህ የተነሳ፣ ወደ አዲስ ማህበረሰብ ማለትም የአማኞች ቤተሰብ ውስጥ ገብተናል፡፡ ስለዚህም፣ ከእምነት ወንድሞቻችን ጋር፣ በእግዚአብሔር ባሕርይ ላይ በመታመን እምነታችንን አጥብቀን መያዝንን መለማመድ ይኖርብናል፡፡ አንዳችን ሌላውን ልናበረታታም ይገባናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕይወት ብቸኝነት እንዲሰማን ሊያደርገን እና ተስፋ አስቆራጭም ሊሆን ይችላል። በዚህ ወቅት፣ ከቅዱሳን የምናገኘው እርዳታ (ገላትያ 6:10 ፤ ቆላስይስ 3 12 እስከ 14)፣ በዚህ ሕብረት መካከል እግዚአብሔር ያስቀመጠውን ደስታ እንድናጣጥም እድል ይሰጠናል፡፡

ደስታ አማኝ የሚለይበት የሕይወት ምልክቱ ሊሆን ይገባል፡፡ ደስታ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እና የእግዚአብሔር ስጦታ እንደመሆኑ በእግዚአብሔር ማንነት ላይ ስናተኩር፣ በጸሎት ከእርሱ ጋር ስንነጋገር እና እርሱ በሰጠው የአማኞች ሕብረት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ስናደርግ ይህንን ስጦታ በተሻለ መንገድ መለማመድ እንጀምራለን፡፡

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ

Exit mobile version