በጳውሎስ እስራት ወንጌል መስፋፋቱ  (ፊልጵስዩስ 1፡12-26) 

ከሁሉም በላይ፥ የጳውሎስ ፍላጎት በታላቁ የንጉሠ ነገሥት ግዛት እምብርት በሆነችው በሮም ከተማ ወንጌልን በመስበክ ለማገልገል ነበር። በጳውሎስ አጀንዳ ላይ ልዩ ትኩረት የተሰጠውና በአንገብጋቢነት የተመዘገበው የሮምን ከተማ ለክርስቶስ በማሸነፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን በድነት (በደኅንነት) መልእክት መድረስ ነበር። ለዚህም ነው «እዚያ (ኢየሩሳሌም) ከደረስኩ በኋላ ወደ ሮም መሄድ አለብኝ» ሲል ባለማወላወል የተናገረው (የሐዋ. 19፡21)። በቆሮንቶስ ከተማ ሳለ በጻፈላቸው መልእክት ውስጥ «በሚቻለኝ መጠን በሮም ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቻለሁ» በማለት አቋሙን አሳውቋል (ሮሜ 1፡15)። 

ጳውሎስ ወደ ሮም ሰባኪ ሆኖ ለመሄድ ያቅድ እንጂ፥ ዳሩ ግን እስረኛ ሆኖ ነበር የመጣው። በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ረጅም ደብዳቤ ለመጻፍ በቻለም ነበር። በምትኩ ግን ነገሩን ሁሉ በማጠቃለል፥ «ይህ የደረሰብኝ» በማለት ያልፈዋል (ፊልጵ. 1፡12)። የዚህ ታሪክ በሐዋርያት ሥራ 21፡17-28፥ 31 ላይ ይገኛል። የሚጀምረው ከጳውሎስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ መታሰር ነው። የአይሁድም አስተሳሰብ አሕዛብን ወደ ቤተ መቅደስ እያመጣ ቤተ መቅደሱን ያረክሳል የሚል ሲሆን፥ በሮማውያን በኩል ደግሞ ስሙ «በጣም-ተፈላጊ» ከሆኑት ግብፃውያን አመፀኞች ዝርዝር ውስጥ አለ በሚል ሰበብ ነው። ስለዚህ ጳውሎስ ከሁለት አቅጣጫ፥ ማለትም በፖለቲካውም፥ በሃይማኖቱም መሪዎች ዘንድ ሴረኛ ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር። በዚህም የተነሣ በቄሣሪያ ለሁለት ዓመታት ታስሮ ቆይቷል። በመጨረሻ ጊዜ ግን ለቄሣር ይግባኝ በማለቱ (የእያንዳንዱ የሮማ ዜጋ መብት ነውና) ወደ ሮም ተላከ። በመንገድም ላይ፥ መርከቡ በአውሎንፋስ ምክንያት ተሰባበረ። በዚያን ወቅት ጳውሎስ ያሳየው ጉብዝናና የእምነት ጥንካሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሠፈሩት አስደናቂ ታሪኮች አንዱ ለመሆን አብቅቶታል (ሐዋ. 27)። በመላጥያ ደሴት ሦስት ወር ከቆየ በኋላ ባቀረበው አቤቱታ መሠረት ቄሣር ፊት ለመቅረብ በመርከብ ተሳፍሮ ወደ ሮም ሄደ። 

ይህ በብዙዎች ዘንድ እንደ ውድቀት ይታይ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ሰው «በአንድ አሳብ» እና ዓላማ በመመራት፥ ምኞቱ የክርስቶስን ወንጌል ማካፈል ስለነበረ፥ ውድቀት አይደለም። ጳውሎስ ደስታን ያገኘው ሌሎችን ለክርስቶስ በመማረክ እንጂ አመቺ በሆነ ሁኔታ አይደለም። ሆኖም ለእርሱ እነዚያ ሁኔታዎች ሁሉ ወንጌልን ለማስፋፋት አመቺ ገጠመኞች ሆነውለት ነበር። ማስፋፋት ማለት «ወደፊት ገፍቶ ማቅናት» ነው። ይህ የግሪክ ወታደራዊ ቃል የሚያሳየን የጦር መሐንዲሶች (ዕቅድ አውጪዎች) ከወታደሮች በፊት ሄደው ለአገሩ አዲስ መንገድ መክፈታቸውን ነው። እንደዚያው ሁሉ ጳውሎስ ራሱን እንደ እስረኛ ከመወሰን ይልቅ ሁኔታዎቹ አዲስ የአገልግሎት ዕድል እንደሚከፍቱለት ተማምኖ ነበረ። 

እያንዳንዱ ሰው ስለታዋቂው ሰባኪ ቻርልስ ሂደን ስፐርጀን ሰምቷል፥ ጥቂቶችም ብቻ ስለባለቤቱ ሱዛና ያውቃሉ። ገና እንደተጋቡ፥ ሚስዝ ስፐርጀን አካለ ስንኩል ሆነች። ከዚያ በኋላ የእርሷ አገልግሎት ባሏን በማበረታታት፥ ለእርሱ ሥራ በመጸለይ ብቻ የተገታ የመሰላቸው ነበሩ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የባሏን መጻሕፍት መግዛት ለማይችሉ መጋቢዎች መጻሕፍቱን በማከፋፈል እንድታገለግላቸው ሌላ የሥራ ድርሻ ሰጣት። ይህ ኃላፊነቷ «የመጽሐፍ መዋጮ» ወደማሰባሰብ አመራ። በእምነት ሥራ አራማጅነቱ ይህ «የመጽሐፍ መዋጮ» በሺህ ለሚቆጠሩ መጋቢዎች ከፍተኛ እርዳታ ሰጪ ሆነ፡፡ ይህን ሁሉ ሚስዝ ስፐርጀን በቤቷ ሆና ትቆጣጠር ነበር። የእርሷም አርአያነት፥ ከአቅኚዎች መሀል ቀዳሚነት የያዘ አገልግሎት ነው። 

እግዚአብሔር አሁንም ልጆቹ አቅኚዎች ሆነው ወንጌልን ወደ አዲስ ስፍራ እንዲወስዱ ይፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች አቅኚዎች ብቻ እንድንሆን ይወስኑናል። እንዲያውም፥ ጳውሎስ በመጀመሪያ ወደ ፊልጵስዩስ ለመግባት የቻለው እግዚአብሔር ደጋግሞ ሌላውን በር ስለዘጋበት ነው (ሐዋ. 16፡6-10)። እንደእርሱ ፍላጎት ከሆነ ወደ ሌላ ግዛት በሄደም ነበረ። ጳውሎስ መልእክቱን በምሥራቁ አቅጣጫ ለማስፋፋት ቢያቅድም፥ እግዚአብሔር ግን በምዕራብ በኩል ወደ  አውሮፓ እንዲሄድ መራው። ጳውሎስ የራሱን ፈቃድ ቢከተል ኖሮ በሰው ልጆች ታሪክ ምን ያህል ልዩነት ባመጣ ነበር! 

እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ወንጌልን ለማስቀደም እንዲረዳን እንግዳ በሆኑ መሣሪያዎች ይጠቀማል። ጳውሎስን በተመለከተ፥ ወንጌልን የሮማ ኅብረተሰብ ቁንጮ በሆኑት የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘቦች (ፕሬቶሪያን ጋርድዝ) መሀል ለመዝራት ያስቻሉት ሦስት መሣሪያዎች ነበሩ። እነኝህም ሰንሰለቱ (ቁ. 12-14)፥ ነቃፊዎቹና (ቁ. 15-19)፥ ያጋጠሙት አስጊ ሁኔታዎች (ቁ. 20-26) ናቸው። 

  1. የጳውሎስ ሰንሰለቶች (1፡12-14) 

እግዚአብሔር በሙሴ በትር፥ በጌዴዎን ማሰሮዎች፥ እና በዳዊት ወንጭፍ እንደተጠቀመው ሁሉ በጳውሎስም ሰንሰለት ተጠቅሟል። ሮማውያኖቹ በጥቂቱ እንደተረዱት በእጁ ላይ ያኖሩት ሰንሰለት ጳውሎስን ፈታው እንጂ አላሰረውም። እሱም እስር ቤት በነበረበት ጊዜ እንደጻፈው «እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራን እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም» (2ኛ ጢሞ. 2፡9)። እነርሱ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲሰጡ እንጂ ስለመታሰሩ አማርሮ አያውቅም። እግዚአብሔርንም በእነርሱ አማካይነት ወደፊት ወንጌል እንዲሰራጭ እንዲጠቀምባቸው ከልቡ ጠይቆ ነበር። እግዚአብሔርም ጸሎቱን መለሰለት። 

ስለዚህ ይህ ሰንሰለት ጳውሎስን ከጠፉ ነፍሳት ጋር ግንኙነት እንዲኖረው ረድቶታል። ጳውሎስ ከአንድ የሮማ ወታደር ጋር ለ24 ሰዓት ተቆራኝቶ መቆየት ሲኖርበት፥ ወታደሮቹ ግን በየ 6 ሰዓቱ ይቀያየሩ ነበር። ይህ እስራቱ ከጠፉት ሰዎች ጋር እንዲገናኝ አድርጎታል። ይህም ማለት ጳውሎስ በየቀኑ ቢያንስ ለአራት ሰው ይመሰክር ነበር። እስቲ ራሳችሁን እንደ አንዱ ወታደር አድርጋችሁ አስቡ! «አለማቋረጥ» የሚጸልይ እስረኛ፥ ሳያቋርጥ ሰዎችን ስለመንፈሳዊ ሁኔታቸው የሚጠይቅ ሰው፥ በመላው የሮም ግዛት ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖችና ቤተ ክርስቲያናት፥ ደብዳቤ የሚጽፈው ጳውሎስ በየዕለቱ ያጋጥማችሁ ነበር ማለት ነው። አንዳንዶቹ ወታደሮች እምነታቸውን በክርስቶስ ለማድረግ ረጅም ጊዜ አልወሰደባቸውም። ጳውሎስ በክብር ዘበኞቹ ሹማምንት መካከል ወንጌልን ለማድረስ ችሏል። ይህን ደግሞ ነፃ ሰው ቢሆን ኖሮ ሊያደርገው ባልቻለም ነበር። 

የጳውሎስ ሰንሰለት የሌላ መደብ አባላት ከሆኑት ከቄሣር ባለሥልጣናት ጋር ለመገናኘት አስችሉታል። በሮም በነበረበት ጊዜ ጉዳዩ ከፍተኛ ተደርጎ ስለሚቆጠር እሱንም እንደ ከባድ እስረኛ ያዩት ነበረ። የሮማ መንግሥት ለአዲሱ «የክርስትና» እምነት አቋሙን በይፋ የሚያሳውቅበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ለመሆኑ ክርስትና የአይሁድ ሃይማኖት አንድ ዘርፍ ነው? ወይስ አዲስ እምነትና አደገኛ ነው? ይህን ለመወሰን ባለሥልጣኖቹ የክርስትናን እምነት ሳይወዱ በግድ ማጥናት ስለነበረባቸው፥ በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እንዴት እንደሚደሰት አስቡ! 

እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ወዳልሰሙት የወንጌልን ስርጭት እንዲያካሂዱ የራሱን ሕዝብ ወደ «እስራት» ይከታል። በተለይ በሌላ መንገድ የማይቻለውን በዚህ እንዲከናወን ያደርጋል። ወጣት የሆኑ እናቶች በቤት ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን ሲንከባከቡ የታሰሩ እንደሚመስላቸው ሁሉ፥ እግዚአብሔርም የደኅንነትን መልእክት በሰዎች ዘንድ ለማድረስ እንዲሁ በ«እስራት» ይጠቀማል። ሱዛና ዌዝሌ 19 ልጆችዋን ያሳደገችው የልጆች ማሳደጊያና መንከባከቢያ እንዳሁኑ ባልሠለጠነበት ወይንም ባልተፈለሰፈበት ወቅት ነበር። ሆኖም ከዚህ ከትልቅ ቤተሰብ ውስጥ የወጡት ጆን እና ቻርልስ ዌስሊ በመተባበር መላው የእንግሊዝ ደሴቶችን ያንቀሳቀሰ አገልግሎት አበረከቱ። ፈኒ ክሮስቢ በ6 ሳምንት እድሜዋ ታውራ ነበር፥ ግን ገና ወጣት ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ በጨለማ እንዳትታሰር ወሰነች። ከጊዜም በኋላ በዝማሬዋና በወንጌል መዝሙሮችዋ በኩል የእግዚአብሔርን ታላቅ ኃይል የምትገልጽ ሆነች። 

ምሥጢሩ ይህ ነው:- አንድ አሳብ በሚኖረን ጊዜ አጋጣሚዎችን የምንመለከታቸው እግዚአብሔር ወንጌልን ለማስፋፋት እንደሰጠን ዕድል አድርገን በመቁጠር ነው፤ እና እግዚአብሔር ባደረገልን ነገር ከምናማርር ይልቅ በሠራው ነገር እንደሰታለን። 

የጳውሎስ እስራት የጠፉትን መገናኘት ብቻ ሳይሆን፥ የዳኑትንም ደግሞ ማበረታታት ነው። ብዙዎቹ በሮም ያሉት አማኞች የጳውሎስን እምነትና ቆራጥነት ሲያዩ እንደ አዲስ ይበረቱ ነበር፤ (ቁ. 14)፥ እነርሱም «በይበልጥ ደፍረው ቃሉን ያለፍርሃት ለመናገር» ይችሉ ነበር። መናገር የሚለው ቃል መስበክ ማለት አይደለም። እንዲያውም «የዘወትር ንግግር» ማለት ነው። ያለጥርጥር ብዙዎች ሮማዊያን የጳውሉስን ጉዳይ ይነጋገሩበታል። ምክንያቱም እንደዚህ ያለ የሕግ ጉዳይ፥ የዚህን በሕጋዊነቱ የሚኩራራው መንግሥት አትኩሮት ከሚስቡት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ በመሆኑ ነው። እና በሮም ያሉ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ስላዘኑለት በንግግራቸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥሩ ቃልን ለማውራት መልካም ዕድል አጋጠማቸው። ተስፋ በመቁረጥ የመስፋፋቱን ያህል፥ የተስፋም መለምለም ያንኑ ያህል ታዳጊ ነው። በጳውሎስ ደስተኛ ሁኔታ ምክንያት በሮም ውስጥ ያሉ አማኞች አዲስ የሆነ መበረታታት ስላገኙ ስለ ክርስቶስ በድፍረት ለመመስከር ቻሉ። 

ከደረሰብኝ አስጊ የመኪና አደጋ በኋላ ሆስፒታል ገብቼ በማገገም ላይ እንዳለሁኝ፣ ከአንድ ፍጹም ከማላውቀው እንግዳ ሰው፥ ወደ ብርሃን የመራኝ ደብዳቤ ደረሰኝ። ከዚያም ከዚሁ ሰው በተከታታይ ብዙ ደብዳቤዎቹ ደረሱኝ። የሚገርመው አንዱ ከሌላው የሚሻል መሆኑ ነው። ታዲያ ከዚያ ከሰውዩ ጋር መዘዋወር በምችልበት ጊዜ ተገናኘን። እጅግ የተደነቅኩት ሰውዬው እውር፥ የስኳር በሽተኛና እንዲሁም አንድ እግሩ የተቆረጠ አካለ ስንኩል በመሆኑ ነበር (እና ከዚያ ወዲያም ሌላኛው እግሩ ተቆርጧል። ሆኖም ይህ ሰው የሚኖረው በእድሜ የገፋ እናቱን እየረዳ ነበር። እንግዲህ ከዚህ ሰው ይብስ እግር ከወርች በሰንሰለት የታሠረ ሰው አለ ለማለት አይቻልም! በዚያ መጠን ደግሞ ወንጌልን ለማሰራጨት ነፃነት ያስፈልጋል ከተባለ አሁንም እንደእርሱ ነፃ የሆነ ሰው አልነበረም። በአገልግሎት ሰጪ ቡድኖች ፊት፥ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጉባኤዎች ውስጥ ስለ ክርስቶስ ይመሰክር ነበር። እናም ለተሾሙ አገልጋዮች ብቻ በሚፈቀዱ የባለሙያዎች ስብሰባ ላይ በመገኘት ገንቢ አስተያየቶች የሚያካፍል ሰው ነበር። ጓደኛዬ ለክርስቶስና ለወንጌል ስለሚኖር ያለው አንድ አሳብ ብቻ ነበረ። ከዚህም የተነሣ ወንጌልን በማስፋፋት በሚገኘው ደስታ ተቋዳሽ ነበር። 

የእኛ እስራት አስደናቂ ወይም አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል። ያ ማለት ግን እግዚአብሔር በአንድ በሆነ መንገድ አይጠቀምብንም ማለት አይደለም። 

  1. የጳውሎስ ነቃፊዎች (1፡15-19) 

ጳውሎስን የሚቃወመው ሰው አለ ቢባል ለማመን ያስቸግራል፤ ይህንን ግን በሮም ውስጥ የነበሩ አማኞች ፈጽመውት ነበር። በእዚያ ያሉ ቤተ ክርስቲያኖች ተከፋፍለዋል። አንዳንዶቹ፣ ሰዎች እንዲድኑ ስለሚፈልጉ ክርስቶስን በቅንንነት ይሰብካሉ፥ አንዳንዶቹ ግን በጳውሎስ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ለመፍጠር ክርስቶስን በተጣመመ መንገድ እያስተዋወቁ ነበር። የኋለኛው ወገን በወንጌል ይጠቀም የነበረው የግል ፍላጎትና ምቾቱን ለማደላደል ነበር። ምናልባትም እነዚህ ወገኖች አንድም የጳውሎስን ለአሕዛብ ያለውን አገልግሎት የሚቃወሙ፥ ወይንም ለሙሴ ሕግጋት በመታዘዝ ምትክ ለእግዚአብሔር ጸጋ የሰጠውን ተቀዳሚነት የማይቀበሉ የቤተ ክርስቲያን ወግ አጥባቂ ክንፍ አባሎች ሊሆኑ ይችላሉ። ፍቅርና አንድነት አብሮ የመሄዱን ያህል፤ ቅናትና ክርክርም በዚያው መጠን አብሮ ይሄዳል። 

ጳውሎስ በቁጥር 16 ላይ «ቅንዓት» በሚል አስደናቂ ቃል ተጠቅሟል። ይህም «ለሥልጣን መሯሯጥና ደጋፊዎችን ለማብዛት መሽቀዳደም» እንደ ማለት ነው። የጳውሎስ ዓላማ ክርስቶስን ለማክበርና እርሱን የሚከተሉ ሰዎች ለማግኘት ነው፥ ነቃፊዎቹ ግን ዓላማቸው ራሳቸውን ለማስከበርና የራሳቸውን ተከታዮች ለማግኘት ነው። «ክርስቶስን አምነኸዋል?» ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ «የማን ወገን ነህ – የእኛ ወይስ የጳውሎስ?» ብለው መጠየቁን የሚያስቀድሙ ነበሩ። ክፋቱ እንዲህ ዓይነቱ «የሃይማኖት ፖለቲካ» በአሁኑም ጊዜ እንኳን መታየቱ ነው። ይህንን የሚለማመዱ ሰዎች ራሳቸውን ብቻ እንደሚጎዱ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። 

እኛ አንድ አሳብ ብቻ ያለን እስከሆንን ድረስ የሚነቅፉንን የምንመለከተው እንደ ሌላ ወንጌል የማስፋፊያ እድል በመቁጠር ነው። ጳውሎስ እንደ ታማኝ ወታደር «ለወንጌል መመከቻ (የተወሰነ)» ነበር (ቁ 17)። በነቃፊዎቹ ራስ መውደድ ሳይሆን ክርስቶስን በመስበኩ ሊደሰት ችሏል። በጳውሎስ ልብ ውስጥ ቅናት አልነበረም። አንዳንዶች ከእርሱ ጋር ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ይቃወሙታል። ከሁሉም አስፈላጊው የክርስቶስ የኢየሱስን ወንጌል መስበክ ነው። 

ከታሪክ ማስታወሻ ላይ እንደምናገኘው ሁለቱ ታላላቅ የእንግሊዝ ወንጌላዊያን፥ ጆን ዌስሊ እና ጆርጅ ውትፊልድ፥ በሥነ- መለኮት ጉዳዮች ላይ አይስማሙም ነበር። ሁለቱም በሺህ ለሚቆጠር ሕዝብ እጅግ የተሳካ ስብከት ሰብከው በጣም ብዙዎችም ወደ ክርስቶስ ሲመለሱ በዓይናቸው ያዩ ናቸው። ታዲያ አንድ ሰው ዌስሊን፥ ውትፊልድን በመንግስተ ሰማይ የምትገናኘው ይመስልሃል? ሲል ጠይቆት እንደነበረ ይወራል። ወንጌላዊውም ሲመልስ «አይ፥ አይመስለኝም» አለው። «አንተ እንደምታስበው ውትፊልድ የተለወጠ ሰው አይመስልህም?» 

ዌስሊም «እርግጥ ነው የተለወጠ ሰው ነው» ካለ በኋላ በመቀጠል፥ «ግን በመንግሥተ ሰማይ እርሱን አያለሁ ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም እርሱ ለእግዚአብሔር ዙፋን በጣም የቀረበ ስለሚሆንና እኔ ደግሞ በጣም ስለምርቅ ችዩ የማየው አይመስለኝም» በማለት መልሶለታል። እርሱና ወንድሙ ውትፊልድ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ቢለያዩም፥ ዌስሊ ግን በልቡ ምንም ቅናት አድሮበት አያውቅም። የውትፊልድንም አገልግሎት መቃወም አይፈልግም። የመቃወምም ፍላጎት አልነበረውም። 

አብዛኛውን ጊዜ ነቀፌታን ለመቀበል ያስቸግራል፥ በተለይም ጳውሎስ እንደነበረበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ግን ሐዋርያው የተለያዩ ነቃፊዎች እየገጠሙት እንኳን እንዴት ሊደሰት ቻለ? ለዚህ መልሱ በአንድ አሳብ ብቻ የሚመራ በመሆኑ ነው። ቁጥር 19 እንደሚያመለክተው ጉዳዩን በአሸናፊነት እንደሚወጣው (ስደኅንነት) ያውቀው ነበር። ለዚህም ምክንያቱ በወዳጆቹ ድሎችና በእግዚአብሔር መንፈስ እርዳታ ሙሉ በሙሉ በመተማመኑ ነው። «እርዳታ» የሚለው ቃል በእንግሊዘኛው ቃል የመዘምራን ጓድ የሚለውን ይሰጠናል። በግሪክ ከተማ ውስጥ ልዩ በዓል ለማሳየት ምንጊዜም አንድ ሰው ለዘፋኞቹና ለደናሾቹ ልዩ እርዳታ ወይንም ስጦታ ማድረግ ነበረበት። ዝግጅቱም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነበር። ከዚህም በመነሣት ቃሉ «የሚያስፈልገውን ሁሉ በልግሥና መስጠትና ማሟላት» የሚለውን አስተሳሰብ የሚወክል ለመሆን ቻለ። ጳውሎስ እየመነመነ በሚሄደው በራሱ ሀብት የሚተማመን ሳይሆን ሙሉ እምነቱ በመንፈስ ቅዱስ ስሚከናወነው ቸር የእግዚአብሔር ልግሥና ምንጭ ላይ ነበር። 

ጳውሎስ በሮም እንደቀዳሚ አቅኚነቱ በእስራቱና በነቀፌታው በኩል ወንጌልን አካፍሏል፥ ግን ሌላ የተጠቀመበት ሦስተኛም መሣሪያ ነበረው። 

  1. የጳውሎስ ችግር (1፡20-26) 

በእስራቱ ምክንያት ክርስቶስ ታውቆ ነበር (ቁ. 13)፥ እና በመነቀፉም ምክንያት ክርስቶስ ተሰብኮ ነበር (ቁ. 18)። ስለዚህ በጳውሎስ ችግር ምክንያት ክርስቶስ ጎልቶ ታይቶ ነበር (ቁ. 20)። ጳውሎስ ለሮም ከዳተኛ ሆኖ ከተገኘ በኋላ የሞት ቅጣት ሊደርስበት ይችል ነበር። ጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ለጳውሎስ የሚያሠጋው አልመሰለም ነበር። የመጨረሻው ፍርድ ግን፥ ገና ወደፊት የሚመጣ ነበር። ያም ሆኖ ለጳውሎስ ሰውነቱ እንኳን የራሱ አልነበረም። ብቸኛው ፍላጎቱም (ምክንያቱም አንድ አሳብ ስላለው) ክርስቶስን በሰውነቱ ማጉላት ነበር። 

ግን ክርስቶስን ማጉላት ያስፈልጋል ወይ? ደግሞስ እንዴት የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ልጅ አጉልቶ ለማሳየት ይችላል? ታዲያ፥ ከዋክብቶች አጉልቶ ከሚያሳያቸው መሣሪያ (ቴሌስኮፕ) ይልቅ በጣም ትልቅ ናቸው፤ ሆኖም ግን ቴሌስኮፑ ያጎላቸዋል፥ እንዲሁም ያቀርባቸዋል። የአማኞች አካል ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሰዎች አጉልቶና አቅርቦ እንደሚያሳይ መሣሪያ ነው። በተራው ሰው ዘንድ ክርስቶስ ከዘመናት በፊት የኖረና፥ በታሪካዊ ሰውነቱም የጭጋግ ያህል ርቆና ደብዝዞ የሚታይ ነው። ሆኖም ግን የአማኙን ሰው በችግሮች መፈተንና በጽናትም ሲወጣቸው`ማየት፥ ላላመኑት ክርስቶስን አጉልቶና አቅርቦ ያሳያቸዋል። አንድ አሳብ ብቻ ላለው ክርስቲያን፥ ክርስቶስ አሁንም ከእኛ ጋር አብሮን ያለ ነው። 

ቴሌስኮፕ ነገሮችን ያቀርባል፥ ማይክሮስኮፕ ደግሞ ትንንሽ የሆኑ ነገሮችን በትልቁ ያሳየናል። አማኝ ላልሆኑ ሰዎች ኢየሱስ በጣም ትልቅ አይደለም። ለእነርሱ እጅግ ትልቅ መስለው የሚታዩዋቸው ሌሎች ሰዎችና ሌሉች ነገሮች ናቸው፤ ነገር ግን ክርስቲያኖች እንዴት የተለያዩ ችግሮችን እንደሚቋቋሙና እንደሚያሳልፉ ሲያዩ፥ በእውነትም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት ትልቅ የቱን ያህል ኃያል እንደሆነ ይገነዘባሉ። የአማኞች አካል እንደማጉያ መስታወት (ሌንስ) ነው። «ትንሹን ክርስቶስን» ትልቅ አድርጎ ያሳያል፥ እንዲሁም «ሩቁን ክርስቶስን» በጣም ቅርብ ያደርገዋል። 

ጳውሎስ ሕይወትንም ሆነ ሞትን አይፈራም ነበር! በሁለቱም መንገድ ክርስቶስን በሰውነቱ ማጉላት ይፈልጋል። ደስታም ቢኖረው አያስደንቅም! 

ጳውሎስ፥ ከቁርጥ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ስለመቸገሩ እራሱም ያምናል። በሕይወት መቆየቱ በፊልጵስዩስ ላሉ አማኞች ጠቀሜታ ቢኖረውም፥ ዳሩ ግን ከእነርሱ በመለየት ከክርስቶስ ጋር መኖሩ በለጠበት። ሆኖም ጳውሎስ ክርስቶስ እንደሚያቆየው ያውቀው ነበር። ይኸውም «ወንጌልን ለማስፋት» (ቁ. 12) ብቻ ሳይሆን «የእምነታቸውን ደስታ ለማስፋት» (ቁ. 25) ጭምር ነበር። አዲስ መንፈሳዊ እድገት ወደታየባቸው አካባቢዎች አንዳንዶችን «በግንባር ቀደም አቅኚነት» የማሰማራት ፍላጎት ነበረው። (በነገራችን ላይ፥ ጳውሎስ ወጣቱን መጋቢ ጢሞቴዎስን በሕይወትህና በአገልግሎትህ አዲስ መንፈሳዊ አገርን ለማቅናት እርግጠኛ ሁን ሲል ምክርና ማስጠንቀቂያ ሰጥቶት ነበር። በ 1ኛ ጢሞ. 4፡ 15 ውስጥ «ማደግ» ለሚለው ቃል «ግንባር ቀደም አቅኚ» የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል)። 

ጳውሎስ እንዴት ዓይነት ድንቅ ሰው ነው! የክርስቲያኖችን እድገት ለመርዳት ሲል ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚሄድበትን ጊዜ ለማራዘም ፈቃደኛ ነበር። በመሆኑም የጠፉትን ወደ ክርስቶስ ለማምጣት ወደ ሲዖል ለመሄድ ፈቃደኛ ሆነ (ሮሜ 9፡1-3)። 

በእርግጥ፥ ጳውሎስን ሞት አላስፈራራውም። ሞት በቀላሉ «መለየት» ማለት ነው። በዚህ ቃል የሚጠቀሙበት ወታደሮች ነበሩ፥ ይህም ማለት «ድንኳንህን ጠቅልልና ወደፊት ሂድ» ማለት ነው። ይህም የክርስቲያን ሞት ምን እንደሆነ ያሳየናል። በምንሞትበት ጊዜ እንኖርበት የነበረው «ድንኳን» ተጠቅልሎ ይወሰዳል። መንፈሳችን ግን ከክርስቶስ ጋር በዘለቄታ ወደሚኖርበት መንግሥተ ሰማይ ያመራል። (2ኛ ቆሮ. 5፡1-8 አንብብ)። መርከበኛም «የመርከቡን መልሕቅ ለማላቀቅና መርከቡን ለማነቃነቅ» በዚሁ ቃል ይጠቀማል። እንደዚሁም እርድ ቴንሰን «መሰናክሉን ለማለፍ» በሚለው እጅግ ዝነኛ ግጥማቸው ውስጥ የሞትን ምንነት ለማሳየት በዚሁ ቃል ተጠቅመውበት ነበር። 

በሌላ በኩል ደግሞ ይኸው «መለየት» የሚለው ቃል የፖለቲካ አነጋገር በመሆን የእስረኛን ነፃ መለቅቅ ለማሳየት ጠቀሜታ ላይ የሚውልበት ጊዜ አለ። የእግዚአብሔር ሰዎች በእስር ላይ ያሉ ናቸው። ምክንያቱም በአካላዊ እንቅፋቶችና በሥጋዊ ፈተናዎች የታሰሩ በመሆናቸው ሲሆን፥ ሞት ግን ነፃ ያወጣቸዋል ወይንም ከመሞታቸው በፊት የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከተከሰተ በዚያ ነፃ ይወጣሉ (ሮሜ 8፡18-23)። በመጨረሻም፥ መለየት የሚለውን ቃል ገበሬዎች የሚጠቀሙበት ነው። ይኸውም «የተጠመዱ በሬዎችን» በማላቀቅ ጊዜ ነው። ጳውሎስ ለመሸከም ቀላል የሆነውን የክርስቶስን ቀንበር ወስዷል (ማቴ. 11፡28-30)፥ ነገር ግን ስንት ሸክሞችን በአገልግሎቱ ተሸክሟል! (ለማስታወስ ከፈለግህ፥ 2ኛ ቆሮ. 11፡22-12፡10 አንብብ)። ከክርስቶስ ጋር ለመሆን መለየት ማለት ሸክማችንን ማራገፍ ወይም ምድራዊ ሥራችንን መጨረስ ማለት ነው። 

በየትኛውም አቅጣጫ ብንመለከተውም፥ የአንድ አሳብ ባለቤት እስከሆንን ደስታችንን ማንም ሊሰርቀን አይችልም። «ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና» (ቁ. 21)። ማልቲቢ ባብኮክ «ይኼ የአባቴ ዓለም ነው» በሚለው መጽሐፉ ውስጥ «ሕይወት ማለት የምንኖርለት ዓላማ ነው» በማለት ጽፏል። እኔና ሚስቴ ለገበያ በምንወጣበት ጊዜ ሁሉ እኔ ወደ ልብስ መደብሮች አካባቢ መሄዱ ደስ አይለኝም። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ባለቤቴ ጨርቃጨርቅ ማየት ስለሚያስደስታት ለእርሷ ስል እሄዳለሁ። ዳሩ ግን በዚያ መንገድ ላይ አንድ የመጽሐፍ መደብር እንኳ ቢያጋጥመኝ ወዲያውኑ ነፍስ በመዝራት ሕይወቴ ይለወጣል። እኛን የሚያስደስተን ነገር እና «በሕይወታችን የሚያበራልን» ነገር፥ ያ ለኛ «ሕይወት» ነው። ጳውሎስን በተመለከተ ክርስቶስ ሕይወቱ ነበር። ክርስቶስ አስደስቶታል እና ሕይወቱንም ዋጋ ያለው ኑሮ አድርጎለታል። 

በቁጥር 21 ውስጥ የሚከተለውን ለሕይወታችን ጠቃሚ የሆነ ፈተና እናገኝበታለን። «ለእኔ ሕይወቴ———፥ ሞትም——- ነውና»። ራስህ በጎደለው መስመር ላይ ሙላ። 

«ለእኔ ሕይወት ማለት ገንዘብ ሲሆን፥ ሞት ደግሞ ሁሉንም ወደኋላ መተው ነውና»። 

«ለእኔ ሕይወት ዝና ሲሆን፥ ሞትም መረሳት ነውና»። 

«ለእኔ ሕይወት ኃይል ሲሆን፥ ሞትም ሁሉንም ማጣት ነውና»። 

ይህ ሁሉ ትክክለኛ አባባል አይደለም፤ እኛ የጳውሎስን የጸና እምነት ማስተጋባት አለብን። ሁኔታዎች ቢኖሩም እኛ የምንደሰት ከሆነ እና እኛ ወንጌልን በማስፋፋት የምንካፈል ከሆነ፥ «ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሲሆን፥ ሞትም ጥቅም ነውና» ለማለት መቻል አለብን።

ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ

Leave a Reply

%d bloggers like this: