ደስታችንን እንዴት እንጨምራለን (ፊልጵስዩስ 1፡1-11)

ኅብረት የሚለው ቃል ለብዙ ሰዎች የተለያየ ትርጉም ይሰጣል። ምናልባትም ለአንዳንድ ሰዎች ልክ እንደ አረጀ ሳንቲም ያህል፥ ማሳየት የሚገባውን እውነተኛ መልክ አጥቷአል ለማለት ይቻላል። እንዲህ ከሆነ የቃሉን ትክክለኛ ትርጉም ለማቆየት አንዳንድ እርምጃዎችን ብንወስድ ይሻላል። ለነገሩ፥ እንደ ኅብረት ያለው መልካም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመካከላችን ብዙ ጊዜ ሊዘወተር ይገባዋል። 

ጳውሎስ በሮም እስረኛ በነበረበት ጊዜ አስቸጋሪ አጋጣሚዎች ቢደርሱበትም ደስተኛ ነበር። የደስታውም ምሥጢር አንድ አሳብ ነው፤ እርሱ የሚኖረው ለክርስቶስ እና ለወንጌል ነው። (በምዕራፍ አንድ «ክርስቶስ» 18 ጊዜ እና «ወንጌል» ደግሞ 6 ጊዜ ተጠቅሷል)። «ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነውና» (ፊል. 2፡2)። ስለዚህ «አንድ አሳብ» ስንል ምን ማለት ነው? ለዚህ ትክክለኛው መልስ፥ «ክርስቶስ ይክበር፥ ወንጌል ለሌሉች ይዳረስ እንጂ በእኔ ላይ ምንም ቢደርስብኝም ለውጥ አያመጣም» የሚል ነው። ጳውሎስ በችግር ውስጥ ቢሆንም ደስተኛ ነው። ምክንያቱም ሁኔታዎቹ የወንጌል ኅብረትን አጠነከሩለት (1፡1-11)፥ ወንጌልን አስፋፋ (1፡12-26)እና የወንጌልንም እምነት ጠበቀ(1፡27-30)። 

ኅብረት የሚለው ቃል «በጋራ አለን» ማለት ነው። እውነተኛ የክርስቲያን ኅብረት አብሮ ከመብላትና ከመጠጣት፥ ከመጫወትም በላይ ሥር የሰደደ ነው። በጣም ብዙ ጊዜ «ኅብረት» የሚለው ቃል ለእኛ የሚያስታውሰን፥ ግንኙነትን (ትውውቅ) ወይም ጓደኝነትን ነው። ከአንድ ሰው ጋር በጋራ የምንካፈለው ከሌለን ኅብረት ማድረግ አንችልም፥ እናም ለክርስቲያኖች ኅብረት፡ ማለት የዘላለም ሕይወትን በልብ መያዝ ማለት 

ነው። አንድ ሰው ክርስቶስን እንደ አዳኙ ካልታመነ ስለ «ወንጌል የሆነ ኅብረት» ምንም አያውቅም። በፊልጵ. 2፡1 ውስጥ ጳውሎስ ስለ «መንፈስ የሆነ ኅብረት» ጽፏል። ምክንያቱም አንድ ሰው ዳግም በተወለደ ጊዜ የመንፈስን ስጦታ ይቀበላል (ሮሜ 8፡9)። ደግሞም «በመከራውም እንድንካፈል» የሚል ቃል አለ (ፊልጵ.3፡10)። ያለንን ከሌሎች ጋር በምንካፈልበት ጊዜ ይህም ደግሞ ኅብረት ነው (4፡15)። 

ስለዚህ፥ እውነተኛ የክርስቲያን ኅብረት በቤተ ክርስቲያን ስምን ከማስጠራትና በየጉባኤው ከመገኘት በብዙ የተለየ ነው። ሰዎችን በአካል አጠገባቸው ሆኖ በመንፈስ ግን ብዙ ኪሎ ሜትር መራቅ ይቻላል። አንደኛው የክርስቲያን የደስታ ምንጭ አማኞች በኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው ኅብረት ነው። ጳውሎስ በሮም ነበረ፥ ጓደኞቹም ደግሞ ብዙ ኪ.ሜ. ርቀው ፊልጵስዩስ ነበሩ፥ ነገር ግን መንፈሳዊ ኅብረታቸው ተጨባጭ እና የሚያረካ ነበረ። አንድ አሳብ በሚኖራችሁ ጊዜ፥ ስለ አጋጣሚዎች አታማርሩም፤ ምክንያቱም አስቸጋሪ አጋጣሚዎች የወንጌልን ኅብረት እንደሚያጠናክሩት ስለምታውቁ ነው። 

ጳውሎስ በ1፡1-11 ሦስት አሳቦችን ተጠቅሞ የክርስቲያንን እውነተኛ ኅብረት አስረዳ፡- አስታውሳችኋለሁ (ቁ. 3-6)፡ በልቤ ትኖራላችሁ (ቁ. 7-8) እጸልይላችኋለሁ (ቁ. 9-11)። 

  1. አስታውሳችኋለሁ (1፡3-6)

ጳውሎስ ስለራሱ ማሰብ ትቶ ለሌሎች ማሰቡ የሚያስደንቅ አይደለምን? ጳውሎስ በሮም ፍርዱን እየጠበቀ አሳቡን በፊልጵስዩስ ወዳሉት አማኞች በመመለስ እያንዳንዱ የሚያስታውሰው ነገር ደስታን ይሰጠው ነበር። የሐዋርያት ሥራ 16ን አንብቡ፤ ይህንን ስታነቡ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ከተማ ስለደረሰበት በደል ማወቅ ትችላላችሁ፥ ይህ ትውስታ ሐዘንን የሚፈጥር ነው። አግባብ ያልሆነ እስራትና ድብደባ ደረሰበት፥ ከግንድ ጋር አጣብቀው አስረውት ነበር፥ በሰዎችም ፊት ተዋርዶ ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን ሲያስታውስ እንኳን ለጳውሎስ ደስታ ይሰጠዋል፥ ምክንያቱም በዚህ መከራ ውስጥ በማለፍ ነበር የወህኒ ጠባቂው ክርስቶስን ለማግኘት የቻለው! ጳውሎስ ሊዲያንና ቤተሰቧን ያስታውሳል፥ በአጋንንት ተይዛ የነበረችውን ድሀ ልጅ፥ እንዲሁም በፊልጵስዩስ ያሉ ውድ ክርስቲያኖችን እና ሌሎችም የሚያስታውሳቸው ነገሮች የደስታው ምንጭ ነበሩ። (እንዲህ ብለን እራሳችን መጠየቅ የሚገባን ነው «ለመሆኑ መጋቢዩ ስለእኔ በሚያስብበት ጊዜ እውነተኛ ደስታን የማስገኝለት ዓይነት ክርስቲያን ነኝን?»)። 

ቁጥር 5 እነርሱ (የፊልጵስዩስ ሰዎች) ከጳውሎስ ጋር ስለነበራቸው ገንዘብ-ነክ ኅብረት ሊያወራ ይችላል፥ ይህን አርእስት በድጋሚ በ4:14-19 አንስቶታል። የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን የጳውሎስን አገልግሎት ለማገዝ ከጳውሎስ ጋር ኅብረት ያደረገች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። በቁጥር 6 ላይ «መልካም ሥራ» ብለን የምንመለከተው ያላቸውን ነገር እንደሚከፋፈሉ ነው፤ ይህም የተጀመረው በጌታ እንደመሆኑ ጳውሉስም ጌታ በዚሁ እንደሚቀጥልና ከፍጻሜ እንደሚያደርሰው እርግጠኛ ነበር። 

ነገር ግን እነዚህን ጥቅሶች ለድነታችንና (ለደኅንነታችንና) ለክርስቲያናዊ ኑሮአችን ዋስትና እንደሚያስገኙልን አድርገን መውሰዱ ወደ ስህተት ሊያመራን አይችልም። እኛ የዳንነው በመልካም ሥራችን አይደለም (ኤፌ. 2፡8-9)። ድነት (ደኅንነት) ማለት በልጁ ስናምን እግዚአብሔር በእኛ የሚሠራው መልካም ሥራ ነው። በፊል. 2፡12-13 እንደሚናገረን እግዚኣብሔር በእኛ የጀመረውን ሥራ በመንፈሱ በኩል ይቀጥላል በሌላ አነጋገር፥ ድነት በአጠቃላይ ሦስት አቅጣጫ ያለው ነው። 

– እግዚአብሔር ለእኛ የሠራው – መዋጀት 

– እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ የሚሠራው – መቀደስ 

– እግዚአብሔር በእኛ አማካኝነት የሚሠራው – አገልግሎት 

ይህ ሥራ ክርስቶስን እስከምናየው ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን ሥራው ይፈጸማል «ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን» (1ኛ ዮሐ. 3፡2)። 

እግዚአብሔር በፊልጵስዩስ ባሉ አማኝ ጓደኞቹ ሕይወት ውስጥ እስካሁን መሥራቱን ማወቅ ለጳውሎስ የደስታው ምንጭ ነበር። በእርግጥም እውነተኛ መሠረት ያለው ደስተኛ የክርስቲያን ኅብረት አለ ለማለት የምንችለው እግዚአብሔር በየቀኑ ኑሮአችን ውስጥ ሲሠራ ነው። 

  1. በልቤ ውስጥ ትኖራላችሁ (ፊል 1፡7-8)

አሁን ደግሞ ትንሽ ጠለቅ ወዳለ አስተሳሰብ እንተላለፍ፤ ሌሎችን በአእምሮአችን ልናስታውሳቸው ብንችልም እንደ እውነቱ ግን በልባችን ውስጥ ላይኖሩ ይችላሉ። (አንድ ሰው እንደ ታዘበው፥ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች፥ «አንጄቴን ቆርጠኃል!» በሚለው ገለጻ መጠቀማቸው የተለመደ ሆኗል።) ጳውሎስ ለጓደኞቹ ያለው ቅን የሆነ ፍቅር ግን የተሰወረ ወይም እንዳስመሳይ አልነበረም። 

የክርስቲያን ፍቅር «የሚያስተሳስር» ነው። ፍቅር ተድነታችን (የደኅንነታችን) ማስረጃ ነው «እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሸጋገርን እናውቃለን» (1ኛ ዮሐ. 3፡14)። ጨው አልጫ ውስጥ ቢገባ ወጡን እንደሚያጣፍጠው ሁሉ ፍቅር የማኅበራዊ ጉዳዮችን የኑሮ እንቅስቃሴ ያለምንም እንቅፋት በሰላማዊ መንገድ እንዲጓዝ ይረዳል። ጳውሎስ ሲጽፍ «ሁላችሁም» የሚለውን ሐረግ ብዙ ጊዜ እንደተጠቀመበት አስተውላችኋል? በዚህ መልእክት ቢያንስ ቢያንስ ዘጠኝ ጊዜ ጠቅሶት ነበር። ስለሁሉም ሰው በማሰብ አንድም ሰው እንኳን ቢሆን እንዲገለልበት አይፈልግም (አንዳንድ ትርጉሞች «እኔ በልብህ ውስጥ አለሁ» ይላሉ። ለምሳሌ በቁጥር 7 ውስጥ ተመልከት፤ ሆኖም ግን መሠረታዊው እውነት ኣንድ መሆኑን ልብ በል።) 

ጳውሎስ ፍቅሩን እንዴት ነበር ያሳያቸው? አንዱ ነገር፥ እርሱ ስለ እነርሱ መከራ ይቀበል ነበር። እስራቱም ፍቅሩን ያረጋግጣል። እርሱ «አሕዛብ ስለሆናችሁ ስለእናንተ የክርስቶስ እስረኛ ነበር» የተባለለት ሰው ነው (ኤፌ. 3፡1)። ጳውሎስ ለፍርድ በመቅረቡ ምክንያት፥ ክርስትና በሮም ባለሥልጣኖች ፊት በአግባቡ መታየት ጀመረ። ፊልጵስዩስ በሮም ቅኝ ግዛት ሥር ስለነበረች፥ በዚያ ያሉትን አማኞች ውሳኔው ጎድቷቸዋል። የጳውሎስ ፍቅር እንደው ለአፍ ያህል የሚናገረው ሳይሆን የተለማመደው ነገር ነበር። ለእርሱ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም፥ ዳሩ ግን ያንን አጋጣሚ ወንጌልን ለመጠበቅና እውነት መሆኑን ለማስረዳት ጥሩ ዕድል አድርጎ ቆጥሮታል። በዚህም በየቦታው ያሉት ወንድሞቹ ተጠቅመውበታል። 

ታዲያ ይህን ዓይነቱን ፍቅር ለመለማመድ ክርስቲያኖች እንዴት መማር ይችላሉ? «እኔ ካልዳኑት ዘመዶቼ ይልቅ ከዳኑት ጎረቤቶቼ ጋራ መኖር የበለጠ ይቀለኛል» ብሎ አንድ ሰው ለመጋቢው አጫወተውና በመቀጠልም «ምናልባትም አንድ ቢላዋ ስለት እንዲያወጣ በሌላ ቢላዋ መሞረድ ያሻዋል እንደሚሉት ዓይነት ለእኔም ተመሳሳይ እርዳታ ሳያስፈልገኝ አይቀርም» ሲል አከለበት። የክርስቲያን ፍቅር እኛ የምንሠራው ነገር ሳይሆን እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ እና በእኛም አማካይነት ለሌሉች የሚሠራው ነገር ነው። ጳውሎስ ከጓደኞቹ ተለያይቶ በመቆየቱ «በክርስቶስ ኢየሱስ እንደምናፍቃችሁ» ሲል ጽፏል (ቁ. 8)። ይህም ማለት የጳውሎስ ፍቅር በክርስቶስ አማካይነት ተገልጿል ማለት ሳይሆን፥ በዚያ ምትክ ግን የክርስቶስ ፍቅር በጳውሎስ አማካይነት ተላለፈ ማለት ነው። «በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ሞላ ተስፋው አያሳፍረንም» (ሮሜ 5፡5 አዲስ ትርጉም)። እግዚአብሔር «መልካሙን ሥራ» በእኛ ውስጥ እንዲያከናውን ስንፈቅድ፥ እርስ በርሳችን በፍቅር እናድጋለን። 

በእውነት ከሌላው ክርስቲያን ጋር በፍቅር መተሳሰራችንን እንዴት መናገር እንችላለን? አንደኛ ነገር፥ እኛ ለሌሎች ማሰባችን ነው። በፊልጵስዩስ ያሉ አማኞች ለጳውሎስ ስለሚያስቡ አፍሮዲጡን እንዲያገለግለው ላኩለት። ጳውሎስም ደግሞ በተለይ አፍሮዲጡን በህመሙ ምክንያት መልሶ ለመላክ ባቃተው ጊዜ (2፡25-28) በፊልጵስዩስ (ስላሉት) ወዳጆቹ በጣም ያስብ ነበር። «ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ» (1ኛ ዮሐ. 3፡18)። 

እርስ በርስ ይቅር ለመባባል ፈቃደኛ መሆን ሌላው የክርስቲያን ፍቅር መግለጫ ነው። «ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉም በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ(1ኛ ጴጥ. 4፡8)። 

ከዕለታት አንድ ቀን የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ለአንድ ሰው ቃለ መጠይቅ አቀረበለት፤ ያም ቃለ መጠይቅ እንዲህ የሚል ነበር፡- «ባለቤትህ የፈጸመችውን አንዳንድ ስሕተቶችን ልትነገረን ትችላለህን?» ብሉ ጠየቀው። 

«ምንም ነገር ማስታወስ አልችልም» ሲል ሰውየው መለሰለት። 

«ታዲያ፣ አንዳንዱን እንኳን ማስታወስ አያቅትህም» አለው የፕሮግራሙ አዘጋጅ። 

«አይ፥ በእውነቱ ማስታወስ አልችልም» አለ መልስ ሰጪው። «ባለቤቴን በጣም ስለምወዳት እንደዚህ ያለውን ነገር በትክክል አላስታውስም»። በ1ኛ ቆሮ. 13፡5 ውስጥ «ፍቅር በደልን አይቆጥርም» ተብሎ ተጠቅሷል።

  1. እጸልይላችኋለሁ (ፊል 1፡9-11) 

ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ላሉት ወዳጆቹ የሚያድግ ፍቅር ስለነበረው ሲያስታውሳቸው ደስተኛ ይሆናል። በጸሎት ወደ ጌታው የጸጋ ዙፋን በቀረበ ጊዜ ሁሉ እነርሱን በፊቱ እያስታወሰ ደስተኛ ነበር። በብሉይ ኪዳን ጊዜ ሊቀ ካህኑ በልቡ ላይ የሚደርበው ኤፉድ የተባለ ልዩ ልብስ ነበረው። በዚህም ላይ በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገዶች ስም በከበረ ድንጋይ የተቀረጹ አሥራ ሁለት ድንጋዮች ይገኛሉ (ዘጸ. 28፡15-29)። ጳውሎስም እንደሚያደርገው ሁሉ እርሱም በፍቅር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር በልቡ ይሸከም ነበረ። ምናልባትም በዚህ ሕይወታችን የምንለማመደው ከፍተኛው ክርስቲያናዊ ሕብረትና ደስታ የሚገኘው፥ ከጸጋ ዙፋኑ ሥር በፍቅር አብረን ስንጸልይና አንደኛችን ለሌላው ስንጸልይ ነው። 

ይህ ጸሎት አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብስለት እንዲያገኙ ነው፤ ጳውሎስ ይህንን የጀመረው በፍቅር ነው። ያም ሆነ ይህ የክርስቲያን ፍቅራችን እንደሚገባ ከሆነ የቀሩት ነገሮች ሁሉ ይከተሉናል። የሚለማመዱት ፍቅር የሞላ ፍቅርና ቀናዒ ፍቅር እንዲሆንላቸው ይጸልያል። የክርስቲያን ፍቅር እውር ፍቅር አይደለም! ልብና አሳብ አብረው ስለሚሠሩ ልንወደውና ልንጠላው የሚገባንን ለይተን እናውቃለን። ጳውሎስ ወዳጆቹ በዚህ ዓይነቱ ፍቅር በሙላት እንዲያድጉ ይፈልጋል፥ ይኸውም «የተለያዩ ነገሮችን መለየት» እንዲችሉ ነው። 

የመለየት ችሎታ የማደግ ምልክት ነው። አንድ ሕፃን ለመናገር በሚለማመድበት ጊዜ አራት እግር ያለውን እንሰሳ ሁሉ «ውው.. ውው» እያለ ይጣራል። በኋላ ግን ድመቶች፥ ውሾች፥ አይጦች፥ ላሞች እና ሌላ ባለአራት እግር ፍጥረቶች እንዳሉ ይገነዘባል። ለሕፃን ልጅ አንድ መኪና ከሌላው መኪና ጋር አንድ ነው፥ ግን ወደ ጎልማሣነቱ ሲቃረብ ወላጆቹ ከሚጠሩት የመኪና ስም ፈጥኖ የሞዴሉን ልዩነት እንኳን ይናገራል። እርግጠኛ የሆነ የማደግ ምልክቶች አንደኛው መለየት የሚችል ፍቅር ነው። 

ጳውሎስ ደግሞ ለክርስቲያኖች «ቅንና አለነውር» የሆነ ባሕርይ እንዲኖራቸው ይጸልያል። ከግሪክ ቃል የተተረጎመው ቅን የሚለው ቃል የተለያየ ትርጉም አለው። አንዳንዶቹ «በፀሐይ ብርሃን የተፈተነ» ብለው ይተረጉሙታል። ቅን የሆነ ክርስቲያን በብርሃን መቆም አይፈራም። አንድ ሰው ለታላቁ እንግሊዛዊ ሰባኪ፥ ለቻርልስ ስፐርጀን የሕይወት ታሪክህን ለመጻፍ እፈልጋለሁ ሲል ይነግረዋል። ስፐርጀን ግን «የእኔን ሕይወት ታሪክ በደመና ላይ መጻፍ ትችላለህ። ምንም የተደበቀ ነገር የለኝም» ሲል መልሶለታል። 

ሌሎች ደግሞ፥ ቅን ማለት «በወንፊት ውስጥ ተንገዋልሉ» መውጣትን ያመለክታል ይላሉ፡ ይህም አሳብ ገለባን ከማስወገድ ወይም ከማበራየት ዘዴ ጋር የተያያዘ ነው። በሁለቱም ትርጉሞች ላይ እውነቱ አንድ ነው፤ ጳውሎስ ለወዳጆቹ ፈተናን ማለፍ የሚችል የዚህ ዓይነቱ ባሕርይ እንዲኖራቸው ይጸልይላቸዋል። 

ጳውሎስ የሚጸልይላቸው የበሰለ የክርስቲያን ፍቅር እና ባሕርይ እንዲኖራቸው እና «ለክርስቶስ ቀን ያለ ነውር እንዲሆኑ» ነው (ቁ. 10)። ይህም ማለት የእኛ ሕይወት ለሌሉች መሰናከያ ምክንያት እንዳይሆንና ኢየሱስ ሲመለስ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ለመቅረብ ዝግጁ እንዲሆን ነው (2ኛ ቆሮ. 5:10 እና 1ኛ ዮሐ. 2:28 ተመልከት)። እኛ መንፈሳዊነትን መለየት እንድንለማመድ መከተል የሚገባን ሁለት መፈተኛ መንገዶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡- (1) ለሌሉች መሰናክል የሆንኩበት ጊዜ አለን? (2) ኢየሱስስ ሲመጣ አፍር ይሆንን? 

ከዚህ በተጨማሪም ጳውሎስ የበሰለ የክርስቲያን አገልግሎት እንዲኖራቸው ይጸልያል። ሕይወታቸው የጽድቅ ፍሬ የተሞላ እንዲሆን ይፈልጋል (ቁ. 11 አዲስ ትርጉም)። የእርሱ ፍላጎት «በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት» ውስጥ በምናደርገው ተሳትፎ የተወሰነ አይደለም፥ ግን ከክርስቶስ ጋር በምናደርገው ኅብረት በምናስገኘው የመንፈስ ፍሬ ዓይነት ላይ ጭምርም ነው። «በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም» (ዮሐ. 15፡4)። ብዙ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ከመኖር እና ፍሬን ለማግኘት ሕይወታቸውን ከመስጠት ይልቅ «ውጤት ለማግኘት» በራሳቸው ጥረት ይሞክራሉ። 

እግዚአብሔር በሕይወታችን ማየት የሚፈልገው «ፍሬ» ምንድን ነው? በእውነት እርሱ የሚፈልገው «የመንፈስ ፍሬ» (ገላ. 5፡22-23) ማስገኘታችንን ነው። የክርስቲያን ባሕርይ እግዚአብሔርን ያስከብራል። ጳውሎስ የጠፋውን ነፍስ ለክርስቶስ ማዳንን ፍሬ ከማፍራት ጋር ያመሳስለዋል (ሮሜ 1፡13)። እና «ቅድስናን» ደግሞ እንደ መንፈስ ፍሬ ይጠራዋል (ሮሜ 6፡22)። «በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ አፍሩ» (ቆላ. 1፡10) ብሎ አጥብቆ ያሳስባል። በዕብራውያን ላይ ደግሞ የእኛ ምስጋና «የከንፈራችን ፍሬ» (13፡15) መሆኑን ያስታውሰናል። የፍሬ ዛፍ ፍሬ በሚያፈራበት ጊዜ አንዳችም ዓይነት ጩኸት አያሰማም፤ ሕይወት በውስጡ እንዲሠራ ብቻ ይፈቅዳል፤ ውጤቱም ፍሬው ራሱ ነው። «እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል» ( ዮሐ. 15፡5)። 

በመንፈስ ፍሬ እና በሰው «የሃይማኖት አገልግሎት» መሀል ያለው ልዩነት ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር በሚያመጡት ፍሬ ላይ ነው። ምንጊዜም አንድን ነገር በራሳችን ኃይል ስንሠራ፥ እኛ ስለሠራነው የመመካት ፍላጎት ይኖረናል። እውነተኛ የመንፈስ ፍሬ እጅግ ያማረ እና ግሩም ነው። ክብሩ ወደ እግዚአብሔር ብቻ እንጂ ማንም ሰው ለራሱ «ዋጋ ይገባኛል» አይልም። 

እውነተኛ የክርስቲያን ኅብረት ከተራ ወዳጅነት ያለፈና ያለንን በጋራ ለመካፈል የሚያስችል ጥልቅ መተሳሰብ መሆን አለበት። «አስታውሳችኋለሁ … በልቤ ውስጥ ትኖራላችሁ … እጸልይላችኋለሁ አላቸው»። እንዲህ ዓይነት ኅብረት ደስታን ያስገኛል፥ ይህን ኅብረት ለማግኘት ደግሞ አንድ አሳብ መሆን ነው። 

አንድ ሰው ወደ ኒውዮርክ ከተማ ለልዩ ቀዶ ጥገና ሕክምና መሄድ ግድ ቢሆንበትም እርሱ ግን ርቆ መሔዱን አልወደደውም ነበር። «ለምንድን ነው የዚህ ዓይነቱ ሕክምና በአካባቢያችን የማይሰጠው?» ብሉ ሐኪሙን ጠየቀው። «በዚያ በግር ግር በተሞላ ታላቅ ከተማ ውስጥ አንድ ሰው እንኳ አላውቅም» አለው። ነገር ግን ባለቤቱና እርሱ ከሆስፒታሉ ሲደርሱ እነርሱን ለመገናኘት የመጣ አንድ መጋቢ አገኙ። ከተማውን እስኪለማመዱትም በእርሱ ቤት እንዲቀመጡ ጋበዛቸው። ቀዶ ጥገናው አስጊ ስለነበረ በሆስፒታሉ ውስጥ ለመቆየት የነበረው ዕድል ረጅምና አስቸጋሪ ነበር፤ ነገር ግን የባለቤቱና የመጋቢው ኅብረት ደስታን አስገኘለት። እኛም እነዚህን መሰሎቹ አጋጣሚዎች ለወንጌል ኅብረት ማጠናከር መንገድ እንደሚከፍቱ እስካመንበት ድረስ ሁኔታዎች ደስታችንን ሊነጥቁን እንደማይችሉ እርግጠኞች እንሆናለን። 

በተግባር ላይ እናውለው! 

እስቲ በዚህ ሳምንት ውስጥ ሁኔታዎች ሁሉ ወደ ክርስቲያን ወዳጆችህ እንድትቀርብ እንዲያደርጉህ ሞክር። አንድ አሳብ ብቻ ካለህ – ማለትም የምትኖረው ለክርስቶስና ለወንጌል እስከሆነ፥ ያለምንም ጥርጥር ከዚያ በኋላ መከራዎችህና ችግሮችህ የወንጌልን ኅብረትን እንደሚያጠነክሩ ትገነዘባለህ፥ ያም ኅብረት ከፍተኛ ደስታን ያጎናጽፍሃል። በ1966ዓ.ም፥ በሰዓት በ90 ማይል ፍጥነት የሚበር መኪና ገጭቶኝ በአስጊ ሁኔታ ላይ እገኝ ነበር። ሆኖም በዚያ ሳቢያ የመሠረትኩት መልካም ኅብረት ውጤት የደረሰብኝን ሕመምና ችግር ሁሉ የሚያስረሳ ነበር። ያም አጋጣሚ ነበር ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ እንድቀርብ ያስቻለኝ። 

«ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።» (1፡21)።

ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ

Leave a Reply

%d bloggers like this: