ለዚህ ጥያቄ በቂና ሙሉ ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱሳችን ክፉ ወይም አስቸጋሪ ነገሮች እንዲደርሱብን ለምን እግዚአብሔር እንደሚፈቅድ መጠነኛ ፍንጮች ይሰጠናል፡፡ ከእስራኤል ሕዝብ ጉዞ አንጻር ይህን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር፡፡ አጭርና ጥቂት ቀናት ብቻ የሚፈጅ መንገድ እያለ እግዚአብሔር እስራኤላውያን ለምን ለ40 አመታት በምድረበዳ መራቸው? መልሱ እነሆ፣ “አምላክህ እግዚአብሔር ትእዛዞቹን መጠበቅህንና በልብህ ያለውን ለማወቅ፣ ትሑት ሊያደርግህና ሊፈትንህ በእነዚህ አርባ ዓመታት በዚህ ምድረ በዳ ጒዞህ ሁሉ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ።ዘዳ 8፡2”
እውነተኛውን ማንነታችንን የምናውቀው (ማለትም ድካማንንን/ጥንካሬያችንን፣ ወዘተ) በአስቸጋሪ ወይም ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ስናልፍ ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ ማንነታችንን ማወቃችን ደግሞ የሚያስፈልገንን/የጎደለንን አውቀን እውነተኛ የእርዳታ ጥሪ ለማቅረብ ያስችለናል፡፡ ውድቀት/ሃጢአት አይኖቻችንን አሳውሮታል፣ ሕሊናችንን አደንዝዞታል፣ እውቀታችንን በክሎታል፣ ወዘተ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ስለራሳችን ያለን ግንዛቤ የተዛባ ቢሆን አያስገርምም፡፡ እናም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስናልፍ ከተኛንበት መንፈሳዊ እንቅልፍ እንነቃለን፣ እውነተኛ የልብ ሃሳቦቻችንን፣ አነሳሽ ምክንያቶቻችንን፣ ዝንባሌዎቻችንን እና ፍላጎቶቻችንን እናውቃለን፣ የጎደለንን እንረዳለን፣ ድካማችንን እናስተውላለን፣ እርዳታ ወደምናገኝበት ስፍራ እንጠጋለን፣ መፍትሄውን/መድሃኒቱን ለማግኘት እውነተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡
ፈተናዎች ወይም አስቸጋሪ ነገሮች ያለንበትን እውነተኛ ሁኔታ ከማሳበቃቸው በተጨማሪ ለመፍትሄው እንድንተጋም ያነሳሱናል፡፡ ለአብነት፣ በራሱ አይንና መመዘኛ ትሁት የሆነ የመሰለው ሰው፣ ትህትናውን በሚፈትን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፍ ተደርጎ ትህትናው የውሸት እንደሆነ መረዳት ቢችል፣ በመጀመሪያ እውነተኛ ማንነቱን ያውቃል (የሃሰት ጭንብሉን ይወልቃል) በመቀጠልም ትህትናን ሊሰጥ የሚችለውን አምላክ በብርቱ ፍላጎትና እንባ ይጠይቃል፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሉሃል ይህ ነው፡፡ አንድ ሰው ትሕትናን በሚፈትኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲያልፍ ሳይደረግ ስለትህትናው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ትህትናን ሳይቀበል ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋ በሙላት ማግኘት አይችልም (ያዕ 4፡6፣ 1ጴጥ 5፡5፣ ምሳሌ 3፡34)፡፡ እግዚአብሔርን “ለምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንድንገባ ፈቀድክ?” የምንለው ብዙውን ጊዜ ከአስቸጋሪዎቹ ሁኔታዎቹ በስተጀርባ ያሉትን እነዚህን ስጦታዎች ማስተዋል ስለማንችል ነው፡፡ አንድ ሕጻን የአባቱን ቅጣት እንደሚያማርር ማለት ነው፡፡ ልጁ በሕጻንነቱ ዘመን ያላስተዋለውን የቅጣት አስፈላጊነት ሲጎለምስ እንደሚያስተውለው ሁሉ እኛም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንድናልፍ ለምን እግዚአብሔር እንደፈቀደ የምናስተውለው ብዙ ጊዜ ዘግይተን ነው፤ ምናልባትም ጭራሽ ላናስተውለውም እንችላለን፡፡
አይምሮአዊ እውቀት በራሱ ተግባራዊ እውቀት ሊሆን እንደማይችል ሁሉ ያልተፈተነ መታዘዝ፣ እውነተኛ መታዘዝ ሊባል አይችልም፡፡ አብርሃም ልጁን ለእግዚአብሔር መሰዋት አድርጎ ለማቅረብ “እሺ” ማለቱ ብቻ በቂ አልነበረም፡፡ ያ “እሺታ” በተግባር መፈተን ነበረበት፡፡ ያ ፈተና ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ እና አስጨናቂ መሆኑን ማንም ወላጅ የሆነ ሰው ሁሉ መገመት ይችላል፡፡ አብርሃም ልጁ ላይ ቢላ እስኪያነሳ ድረስ እግዚአብሔር ዝም ያለው በአብርሃም ልብ ውስጥ ያለው መታዘዝ (እግዚአብሔርን መፍራት) በግልጽ ይታወቅ ዘንድ ነበር፡፡ “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ (ዘፍ 22፡12)”፡፡ እግዚአብሔርን መታዘዛችንን ሳይፈትን፣ መታዘዛችን ከእውቀት ያለፈ ስለመሆኑ ሊረጋገጥ አይቻልም፡፡ የፈተና አይነቶቹ ደግሞ ብዙ መልክ ሊኖራቸው ይችላል፣ (ሥቃይ፣ የጓደኞችና ጎረቤቶች መሳለቂያ መሆን፣ እስራት፣ ሞት፣ ድህነት፣ ወዘተ)፡፡
አዳነው ዲሮ