መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስራት ምን ይላል? ክርስቲያን አስራት ማውጣት አለበት?

ብዙ ክርስቲያኖች በአስራት ማውጣት እና አለማውጣት ጉዳይ ሲከራከሩ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሁለት ጽንፎች ይስተዋላሉ፡፡ አንደኛው ጽንፍ፣ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንደሚታየው ገንዘብ መስጠት ከፍተኛ ትኩረት ማግኘቱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ክርስቲያኖች ገንዘባቸውን ለጌታ ስራ መስጠትን አስመልክቶ ለመጽሐፍ ቅዱስ ማሳሰቢያዎች ለመገዛት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው፡፡ መስጠት ደስታ እና በረከትን ይዞ እንዲመጣ የታቀደ እንጂ ቀድሞም የሸክም ዓላማ አልነበረውም። ሆኖም፣ ይህ እውነት በሁሉ አማኝ ዘንድ አለመገኘቱ አሳዛኝ ነው፡፡

አስራት የብሉይ ኪዳን ጽንሰ-ሀሳብ ነው። እስራኤላውያን ዘርተው ካበቀሉት እህልና ከሚያረቡት እንስሣት ሁሉ ለቤተ መቅደሱ 10 ከመቶውን እጅ በአስራት መልክ እንዲያወጡ ሕጉ ያዝ ነበር  (ዘሌዋውያን 27:30፣ ዘኁልቁ 18: 18-26፣ 2ኛ ዜና 31:5)፡፡ እንዳውም፣ የብሉይ ኪዳኑ ሕግ እስራኤላውያን ከአንድ በላይ አስራትን እንዲያወጡ ያዛል፡፡ እነዚህ አስራቶች ለሌዋውያን፣ ለቤተ መቅደስና ለበዓላት እና ለምድሪቱ ድሆች የሚሰጡ ነበር፡፡ ይህም የአስራቱን መጠን በጠቅላላው ወደ 23.3 ከመቶ ያደርሰዋል፡፡ አንዳንዶች የብሉይ ኪዳንን አስራት በመሠዊያው ስርዓት ውስጥ ለካህናቱ እና ለሌዋውያኑ ፍላጎቶች እንዲውል የሚቀርብ የግብር ዘዴ እንደ ሆነ ይገነዘባሉ፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ሕጉን ከፈጸመ በኋላ፣ በአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች በአንድም ስፍራ ለብሉዩ አስራት ስርዓት እንዲገዙ ሲታዘዙ አይታይም፡፡ አዲስ ኪዳን በየትኛውም ቦታ አንድ አማኝ ሊሰጥ የሚገባውን ገቢ በመቶኛ ስርዓት አስልቶ አይገልጽም፡፡ ሆኖም ግን ስጦታዎችን “እያንዳንዱ እንደ ገቢው መጠን” እንዲሰጥ ያዛል (1ኛ ቆሮንቶስ 16:2)። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ከመቶ 10 እጅ የሚለውን የብሉይ ኪዳን የአሥራት ሥራዓት በመውሰድ ክርስቲያኖች ሊሰጡት እንደሚገባቸው “ዝቅተኛ የመጠን መመዘኛ” አድርገው ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡

አዲስ ኪዳን ስለ መስጠት አስፈላጊነት እና ጥቅሞች ይናገራል፡፡ መስጠት የምንችለውን ያህል መስጠት አለብን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህ መጠን ከገቢያችን 10 በመቶ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከ10 በመቶ ገቢያችን ያነሰ ሊሆን ይችላል፡፡ የስጦታችን መጠን፣ በመስጠት አቅማችን (1ኛ ቆሮንቶስ 16:2) እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ፍላጎት ይወሰናል፡፡ የስጦታችንን መጠን ለመወሰን እያንዳንዱ ክርስቲያን በትጋት መጸለይ እና የእግዚአብሔርን ጥበብ መፈለግ ይኖርበታል (ያዕ. 1:5)። ከሁሉም በላይ፣ ማንኛውም ስጦታዎቻችን በንጹህ ውስጣዊ ግፊት፣ ለእግዚአብሔር አምልኮ እና ለክርስቶስ አካል አገልግሎት ሲባል መሰጠታቸው ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል፡፡ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” (2ኛ ቆሮንቶስ 9:7)።

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ

4 thoughts on “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስራት ምን ይላል? ክርስቲያን አስራት ማውጣት አለበት?”

  1. Daniel ketema from Ethiopia

    በጣም ተባረኩ በጣም እኔ የ3 አመት የቲዎለጂ ተማሪ ነኝ እና የምታነሱዋቸው ሀሳቦች ስፈልጋቸው የነበሩ ሀሳቦች ነበሩ በጣም ደስ ብሎኛል ..በጣም …..እግዚአብሔር ፀሎታችሁን ይስማችሁ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading