ትሕትናን ከክርስቶስ መማር (ፊልጵስዩስ 2፡1-11) 

አንድ የካርቱን ፊልም ገጸ ባሕርይ እንዲህ አለ፥ «ለመውደዱ እንኳ መላውን የሰው ዘር እወድ ነበር፤ ሆኖም ሰዎችን በግል ልቀርባቸው አልሻም!» 

ሰዎች ደስታችንን ሊቀሙን ይችላሉ። ጳውሎስ ከሰዎች የተነሳ በሮም (1፡15-18) ችግር ገጥሞታል። በተለይም በፊልጵስዩስ ያሉት ነበሩ የበለጠ ችግር ያደረሱበት። አፍሮዲጡን ከፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጳውሎስ ብዙ ስጦታንና ስለ ጳውሎስ መልካም ወሬ አመጣ። በዚያውም መጠን በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ያለውን መከፋፈል የሚያረዳም ክፉ ወሬ ይዞ መጥቶ ነበር። የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት ከሁለት አቅጣጫ የተቃጣ ጥቃት በሥጋት ላይ የጣላት ይመስላል፤ ይኸውም ከውጭ የሚመጡ የስሕተት አስተማሪዎች (3፡1-3) እና በውስጥ ያሉት አባሎች አለመስማማት (4፡1-3) ነበር። ኤዎድያን («መዓዛ») እና ሲንጤኪ («ዕድለኛዋ») በምን የተነሣ እንደሚከራከሩ ጳውሎስ አልጠቀሰውም። ምናልባት ሁለቱም የሚፈልጉት የሴቶች ማኅበር ወይም የመዝሙር ቡድን ፕሬዚዳንት ለመሆን ይሆናል። 

ጳውሎስ የሚያውቀውን ያህል፥ በዛሬ ጊዜ የሚገኙት አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሠራተኞች አያውቁም። በአንድነትና በተመሳሳይነት መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን የማይረዱ ብዙዎች ናቸው። እውነተኛ መንፈሳዊ አንድነት ከውስጥ የሚመጣ ነው፤ ይኸውም ከልብ የሚመነጭ ነው። ተመሳሳይነት ከውጪ ከሚመጣ ጠላት የተነሣ የሚዳብር የአንድነት ስሜት ነው። ለዚህም ነው መግቢያ ጽሑፉን መንፈሳዊ መነቃቃትን ለማስገኘት ዓላማ ያዋለው (2፡1-4)። በፊልጵስዩስ ያሉ አማኞች «በክርስቶስ ውስጥ» የሚኖሩ እንደመሆናቸው ይህ በራሱ በመከፋፈልና በመፎካከር ምትክ በፍቅርና በአንድነት እንዲሠሩ ሊያበረታታቸውም በተገባ ነበር። ጳውሎስም አክብሮት በተሞላ መንገድ ለቤተ ክርስቲያኗ እንዲህ አለ፥ «የእናንተ አለመስማማት የሚያሳየው በኅብረታችሁ ውስጥ መንፈሳዊ ችግር እንዳለ ነው። ለዚህም በሕግ ወይም በማስፈራራት መፍትሔ ማግኘት አይቻልም። ለእነዚህ መፍትሔ ማግኘት የሚቻለው ልባችሁን ለክርስቶስ ስታስገዙና እርስ በርሳችሁ በፍቅር ስትተያዩ ነው» ። ጳውሎስ ለማሳየት የፈለገው ለችግሩ ዋናው ምክንያት ራስ ወዳድነት መሆኑን ነው። የራስ ወዳድነት መነሻው ኩራት ነው። በክርስትና ሕይወት ውስጥ ራስን ከሌሉች በላይ በማድረግ ምንም ደስታ ማግኘት አይቻልም። 

ተቃራኒ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙም ደስታን ለመቀዳጀት ምሥጢሩ በአንድ አሳብ መጽናት ብቻ ነው። ሰዎች ቢቃወሙንም አሁንም ደስታ የማግኛው ምሥጢር የአእምሮ ትሕትና ነው። ዋናው ጥቅስ፥ «ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር» ይላል (2፡3)። በምዕራፍ 1 «ክርስቶስ መጀመሪያ» እንደተደረገ ያየነው ሲሆን በምዕራፍ 2 «ሌሉች ሁለተኛ» መሆናቸውን እንመለከታለን። እንደዚሁም በምዕራፍ 1 ውስጥ የነፍሳት ማራኪ የነበረው ጳውሎስ በምዕራፍ 2 ውስጥ አገልጋይ ሆኖ እናገኘዋለን። 

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ትሕትና» ምን ማለት እንደሆነ መረዳቱ በጣም ጠቃሚ ነው። ትሑቱ ሰው ስለራሱ ብቻ የሚያስብ አይደለም፤ እንዳውም ስለእራሱ ጨርሶ አይጨነቅም። ትሕትና፥ አንድ ነገር እንዳለን እያወቅን፥ የለንም ለማለት የሚያስችለን ጸጋ ነው። በእውነቱ ትሑት የሆነ ሰው ራሱን ያውቃል፥ ደግሞም ራሱን ይቀበላል (ሮሜ 12፡3)። የክርስቶስ አገልጋይ አድርጎ ራሱን ይሰጣል፥ እርሱነቱንም ሆነ ያለውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሌሎችም ጥቅም ያውላል። በዚህ ምዕራፍ (ቁ. 3-4) ውስጥ «ሌሉች» የሚለው ዋና አሳብ ነው፤ የአማኞች ዓይን በራሳቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ በሌሎች ፍላጎት ላይ ያርፋል ማለት ነው። 

«ትሑት አእምሮ» የሚያመለክተው ሁሉም ሰው እንደፈለገ የሚያዘውን ወይም ሁሉም ሰው የሚጠቀምበትን «መንፈሰ ደካማ» የሆነ አማኝ አይደለም! አንዳንዶች ብዙ ጓደኞችን ለማፍራትና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ ሲሉ፥ ለማንኛውም ሰው ምኞትና ፍላጎት ተገዢዎች ይሆናሉ። ጳውሎስ እንደዚህ ዓይነት አሳብ በፍጹም አላቀረበም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የሰፈረው «ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን» (2ኛ ቆሮ. 4፡5) የሚል ነው። 

በምዕራፍ 1 ውስጥ በስፋት የተብራራው «አንድ አሳብ» እስካለን በምዕራፍ 2 ያለውን «ትሑት አእምሮ» ለማዳበር ችግር አይገጥመንም። 

ጳውሎስ ስለ ትሑት አእምሮ አራት ምሳሌዎችን ሰጥቶናል፡ እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ (ቁ. 1-11)፣ ጳውሎስ ራሱ (ቁ. 12-18)፥ ጢሞቴዎስ (ቁ. 19-24) እና አፍሮዲጡን (ቁ. 25-30) ናቸው። በእርግጥ ትልቁ ምሳሌ ኢየሱስ ሲሆን፥ ጳውሎስም የሚጀምረው በእርሱ ነው። ትሑት አእምሮ ያለው ሰው የሚኖሩት አራት ባሕርያት በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እንደሚከተለው ይንጸባረቃሉ። 

  1. ለሌሎች ያስባል፥ ለራሱ አይደለም (2፡5-6) 

የክርስቶስ «አሳብ» ማለት ክርስቶስ የሚያሳየው «ጠባይ» ማለት ነው። «በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አሳብ በእናንተም ዘንድ ደግሞ ይሁን» (ቁ. 5)። ያም ሆነ ይህ አመለካከታችን ውጤቱን ይወስናል። አመለካከታችን ራስ ወዳድነት ከሆነ ድርጊቶቻችን አውዳሚ ይሆናሉ። ያዕቆብ ይህንኑ ዓይነት ነገር ተናግሯል (ያዕ. 4፡1-10 ተመልከት)። 

እነዚህ በፊልጵስዩስ መልእክት ውስጥ ያሉት ጥቅሶች እኛን ወደ ቀድሞው ዘለዓለማዊነት ይወስዱናል። «የእግዚአብሔርን መልክ» በቅርጽ ወይም በመጠን ለመግለጽ አይቻልም። እግዚአብሔር መንፈስ ነው (ዮሐ. 4፡24)፥ እና እንደዚህ ያለውን አሳብ በሰው አነጋገር መግለጽ አይቻልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «የጌታ አይኖች» ወይም «የጌታ እጅ» የሚል ብንመለከትም፥ ይህ ግን እግዚአብሔር የሰው ቅርጽ አለው ማለት አይደለም። መለኮታዊ ሁኔታዎችን (የእግዚአብሔር ባሕርይ) እና ድርጊቶችን፥ በሰው አነጋገር ለመግለጽ የተደረገ ሙከራ ነው። «ምስል» የሚለው ቃል የውስጣዊውን ተፈጥሮ በውጭአዊ ገለጻ የሚያቀርብ ነው። ይህም ማለት በቀድሞው ዘላለማዊነት ውስጥ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ እግዚአብሔር ነበር ማለት ነው። ጳውሎስ እንደተናገረው እርሱ «ከእግዚአብሔር ጋር እኩል» ነው። በሌላ ጥቅሶች ላይ ደግሞ፥ ለምሳሌ በዮሐ. 1፡1-4፣ ቆላ. 1፡15 እና ዕብ. 1፡1-3፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር እንደሆነ በግልጥ ሰፍሯል። 

ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔርነቱ ምንም ነገር ባላስፈለገውም ነበር! ክብርና ምስጋና ሁሉ በሰማይ አለው። ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በዓለማት ላይ ይነግሣል። በቁጥር 6 ላይ እንደተጠቀሰው የሚያስደንቀው እውነት ከእግዚአብሔር ጋር መተካከሉን መግለጥ «እንደራስ ወዳድነት» እንዳይቆጠር በመፈለጉ አልተጠቀመበትም። ኢየሱስ ስለእራሱ አያስብም፤ የሚያስበው ለሌሎች ነው። የእርሱ አመለካከት (ፍላጎት) ለሌሎች ራስ ወዳድነት የሌለበት አሳቢነቱን ማሳየት ነው። እንግዲህ «የክርስተስ አሳብ» ማለት «ያለኝን መብቶች ለእራሴ ብቻ አልይዝም፥ የምጠቀምባቸውም ለሌሉች ነው። እና ይህን ለማድረግ በደስታ እነርሱን ትቼ የሚያስፈልገውን ዋጋ ሁሉ እከፍላለሁ» የሚል አስተሳሰብ ነው። 

አንድ ጋዜጠኛ፥ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን በየሙያቸው ለማስቀጠር ለቻሉ አንድ የሥራ አማካሪ ቃለ መጠይቅ አቅርቦላቸው ነበረ። እርሳቸውም የጠየቅከኝ ይህ እንዴት እንደተሳካልኝ እንዳብራራልህ ነው በማለት ሲገልጡ፥ «በእውነት አንድ ሠራተኛ ምን ይመስላል ብለህ ለማወቅ እስከፈለግህ፥ ኃላፊነትን ሳይሆን መብትን ስጠው። ብዙ ሰዎች ኃላፊነት የሚይዙት በቂ ገንዘብ ሲከፈላቸው ነው። ነገር ግን እውነተኛ መሪ መብቱን ለመያዝ ቅድሚያ ይሰጣል። መሪውም በመብቱ የሚጠቀመው ሌሎችን ለመርዳት፥ ድርጅቱን ለማስፋፋት ነው። አስተሳሰቡ አነስተኛ የሆነ ሰው ግን በሚያገኘው መብት ራሱን ለማበልጸግ ይሽቀዳደማል» በማለት ደምድመዋል። ኢየሱስም በሰማዩ መብቱ የሚጠቀመው ለሌሉች ማለትም እኛን ለመርዳት ነው። 

የክርስቶስን ሁኔታ ከሉሲፈር (ሰይጣን) (ኢሳ. 14፡12-15) ጋር እና ከአዳም (ዘፍ. 3፡1-7) ጋር ማነጻጸር የሚገባ አይደለም። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደሚያምኑት የሉሲፈር አወዳደቅ የሚገልጸው የሰይጣንን አወዳደቅ ነው። አንድ ጊዜ ከመላእክት ፍጥረት ሁሉ ታላቅ፥ ለእግዚአብሔር ዙፋን የቀረበ ነበር (ሕዝ. 28፡11-19)። ነገር ግን የእርሱ ፍላጎት በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ለመቀመጥ ሆነ። ሉሲፈር «አደርጋለሁ» ሲል በድፍረት ይናገራል፥ ኢየሱስ ግን «ፈቃድህ ይሁን …» ይላል። ሉሲፈር ፍጡር በመሆኑ አይረካም፤ እርሱ የሚፈልገው ፈጣሪ መሆን ነው። ኢየሱስ በፈቃዱ ሰው ሆነ እንጂ ፈጣሪ ነው። የክርስቶስ ትሕትና የሰይጣንን ኩራት ይገሥጸዋል። 

ሉሲፈር እራሱ ዐመፀኛ መሆኑ ስላላረካው ወደ ኤደን ገነት ጣልቃ በመግባት ሰውንም ዐመፀኛ እንዲሆን ገፋፋው። አዳም የሚያስፈልገው ሁሉ ነበረው፤ በእውነቱ እርሱ እግዚአብሔር በፈጠረው ላይ ሁሉ «ንጉሥ» ነበር («ይግዙ» ዘፍ. 1፡26 ይላል)፤ ነገር ግን ሰይጣን «እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ» አለ። ሰው በድንገት አሁን ከነበረበት ደረጃ በላይ የጨበጠ መሰለውእና ውጤቱም የሰውን ዘር በሙሉ ወደ ኃጢአትና ሞት ጣለ። አዳምና ሔዋን የሚያስቡት ለራሳቸው ብቻ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለሌሎች ያስባል። 

ያልዳኑ ሰዎች ራስ ወዳድና ስስታም ስለ መሆናቸው ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም፤ ሆኖም ግን የክርስቶስን ፍቅር ከተለማመዱና የመንፈስ ኅብረት (ፊልጵ. 2:1-2) ካላቸው ክርስቲያኖች ይህንን አንጠብቅም። በአዲስ ኪዳን ከሃያ ጊዜ በላይ «እርስ በርሳችን» ተፋቅረን እንድንኖር እግዚአብሔር አዝዞአል። እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ (ሮሜ 12፡10)፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ (1ኛ ተሰ. 5፡11) እና እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም (ገላ. 6፡2)። አንዱ በሌላው ላይ አይፍረድ (ሮሜ 14፡13) ግን እርስ በርሳችሁ ልትገሠጹ ትችላላችሁ (ሮሜ 15፡14)። ትሑት አእምሮ ላለው ክርስቲያን «ሌሉች» የሚለው ቃል ምንጊዜም ከሚጠቀምባቸው ቃላት ሁሉ የከበደ ነው። 

  1. ያገለግላል (2፡7)

«ሌሎች» የሚለውን ቃል በአሳብ ደረጃ ብቻ ማሰላሰል በቂ አይደለም። ይልቁኑ እውነተኛ አገልግሎት ለመስጠት ዝቅ በማለት ለመውረድ መቻል አለብን። አንድ የታወቀ ፈላስፋ ሕፃናትን ማስተማር ያለውን ጠቀሜታ በማስመልከት እጅግ የተዋበ ጽሑፍ አቅርቦ ነበር፤ ሆኖም ግን ፈላስፋው የራሱን ልጆች የትም የጣላቸው ነበረ። እንደርሱ ላለው ሰው ሕፃናትን በስሜት ደረጃ መውደዱ ከባድ አልነበረም። ግን ተግባራዊ ሊያደርገው አልቻለም ነበር። ኢየሱስ ለሌሎች በጎነት በማሰቡ ራሱን ዝቅ አድርጎ አገልጋይ ሆኗል። ጳውሎስ የክርስቶስን ትሕትና በመግለጽ በቅደም ተከተል አስፍሯል። 1) ራሱን ባዶ አደረገ፥ የራሱ በሆነው በእግዚአብሔር ባሕርይ መመራትን ተወ፤ 2) ከኃጢአት የጠራ ሰውነት ቢለብስም፥ ሆኖም ግን ለዘለዓለም ሰው ለመሆን ፈቀደ፤ 3) ያን ሰውነት ባሪያ እንዲሆን አደረገና፤ 4) ሰውነቱንም ወደ መሰቀል ወሰደ፥ ለመሞትም ፈቃደኛ ሆነ። 

ታዲያ ይህ ምን ዓይነት ጸጋ ነው! ከሰማይ ወደ ምድር፥ ከክብር ወደ ውርደት፡ ከጌትነት ወደ ባርነት፥ ከሕይወት ወደ ሞት፥ «የመስቀል ሞት እንኳን» እስከ መቀበል መድረስ ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ ክርስቶስ ምድርን የጎበኘው ለልዩ አገልግሎት ከመሆኑም (የዘፍጥረት 18 ፍሬ ነገሩ ይህ ነው) እነዚያ ጉብኝቶች ጊዜያዊ ነበሩ። ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ፥ ማምለጥ በማይችልበት ሁኔታ ከሰው ጋር አንድነትን መሠረተ። እኛን ለማንሳት ራሱን በፈቃደኝነት ዝቅ አደረገ። ጳውሎስ በጥቅሶቹ ላይ «መልክ» በሚለው ቃል ተጠቅሟል፤ ይህም «የውስጣዊውን ተፈጥሮ በውጥ መግለጽ» ለማለት ነው። ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን አላስመሰለም፥ እርሱ ዋናውን ሚና የሚጫወት ተዋናይም አልነበረም። በእውነት ግን አገልጋይ ነበር። ይህም እውነተኛ የውስጡን ተፈጥሮ የሚገልጽበት ነበር። እርሱ እግዚአብሔር ሰው ነበር፥ አምላክነቱንና ሰውነቱን በአንድ ላይ አዋህዶ እንደ አገልጋይ ሆኖ መጣ። 

ለመሆኑ አራቱን ወንጌሉች ስታነቡ፥ ኢየሱስ ሌሎችን አገለገለ እንጂ እነርሱ እርሱን አገለገሉት የሚል ቃል አስተውላችኋል? እሱ ማንኛውንም ዓይነት ሰው፥ ለምሳሌ አሳ አጥማጁን፥ ሴትኛ አዳሪዋን፥ ቀራጮችን ያዘኑትንና በሽተኞችን ሁሉ ይጠራ ነበር። «የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም» (ማቴ. 20፡28)። በላይኛው ክፍል ውስጥ ደቀመዛሙርቶቹ ለአገልግሎት እንቢ ወደማለቱ በተቃረቡበት ጊዜ ኢየሱስ ተነሣ፥ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻ ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፥ እናም እግራቸውን አጠበ (ዮሐ. 13)፥ እርሱም ዝቅተኛውን የባሪያን ቦታ ወሰደ። ይህ ለትሑቱ አእምሮው ድርጊታዊ ማረጋገጥ ነበር። እናም ኢየሱስ በዚህ አድራጎቱ ልዩ ደስታ ቢሰማው ሊያስገርመን አይችልም! 

በአሜሪካን የእርስ በርስ ጦርነት ጊዜ ጀኔራል ጆርጅ ቢ. ምክለላን የታላቁ የፓቶማክ ሠራዊት አዛዥ ሆኖ ነበረ፥ ለዚህም ምክንያቱ አብዛኛውን ጊዜ የጠቅላላው ሕዝብ አስተያየት ከእርሱ ጋር በመሆኑ ነበር። ራሱን ወደር የሌለው የጦር መሪ አድርጎ ስለሚቆጥር ሰዎች «ወጣቱ ናፖሊዮን» ብለው ሲጠሩት ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር። ነገር ግን የእርሱ አድራጎትና ታላቅነት ስሜት ቀስቃሽ እንጂ ዘላቂነት ያለው አልነበረውም። እርግጥ ፕሬዘዳንት ሊንከን እርሱን ዋና ጄኔራል አድርገው በመሾም ተጨባጭ ውጤት ያስገኛል የሚል ግምት ነበራቸው፤ ነገር ግን እርሱ «ነገ ዛሬ» በማለት ሲያወላውል ጊዜው እየኮበለለ ሄደ። አንድ ምሽት ሊንከን ከሁለቱ የጦር አማካሪዎቻቸው ጋር በመሆን ምክለላንን ለመጎብኘት ሄዱ። እርሱ ግን በዚያን ጊዜ አንድ የሠርግ ድግስ ላይ በመዝናናት ላይ ነበር። ሦስት ሰዎች ተቀምጠው ይጠብቁታል። ከአንድ ሰዓት በኋላ ጄኔራሉ እቤት ደረሰ። ፕሬዘዳንቱን ከምንም ሳይቆጥር ወደ ፎቅ ወጣ። ከዚያም አልተመለሰም። ግማሽ ሰዓት ከቆዩ በኋላ ሠራተኛውን ሰዎች እንደሚጠብቁት ንገረው ብለው ላኩት፥ ሠራተኛውም ተመልሶ እንደተኛ ነገራቸው። 

የጦር ጓደኞቹ በቁጣ ቢደብኑም ሊንከን ግን ዝም ብለው ተነሡና ወደ ራሳቸው ቤት ተመለሱ። «የአሁኑ ወቅት ክብራችን ተደፈረ ብለን የምንቆጭበት ወይም ሥነ-ምግባር ጎድሏል ብለን የምናወግዝበት ጊዜ አይደለም» ብለው ፕሬዘዳንቱ ከገለጹ በኋላ በመቀጠል «ምነው ምክለላን ድልን ባቀዳጀንና እኔ የፈረሱ ጠባቂ እንኳን ለመሆን ፈቃደኛነቴን በገለጥኩለት ኖሮ» ሲሉ ምኞታቸውን ገልጠዋል ይባላል። ሊንከንን ታላቅ ሰውና ታላቅ ፕሬዘዳንት ለመባል ያደረሳቸው ይኼ ትሕትናቸው ነው። ሌሉችን ለማገልገል ያስባሉ እንጂ ስለራሳቸው አይጨነቁም ነበር። ለትሑት አእምሮ፥ አገልግሉት ሁለተኛው ምልክቱ ነው።

  1. እራሱን መሥዋዕት አደረገ (2፡8) 

ብዙ ሰዎች የእነርሱን ጥቅም የማይነካ እስከሆነ ሌሉችን ለማገልገል ፈቃደኞች ናቸው። ነገር ግን ዋጋ የሚያስከፍል ከሆነ ወዲያውኑ ፍላጎታቸው ይጠፋል። ኢየሱስ «ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ» (ቁ. 8)። እሱ የሞተው የሰማዕታት ሞት አይደለም፤ ነገር ግን የአዳኝ ሞት ነበር። ለዚህ ዓለም ኃጢአት በፈቃደኝነት ሕይወቱን ከፈለ። 

ዶክተር ጄ.ኤች. ዶወት የተባሉት «ዋጋ የማይከፈልበት አገልግሎት ምንም ውጤት አይኖረውም» በማለት ተናግረዋል። ጥቂትም ቢሆን «በረከት» እንዲገኝ ጥቂት «ደም መፍሰስ» አለበት። ብራዚል ውስጥ በአንድ የሃይማኖት በዓል ላይ አንድ ወንጌላዊ እቃዎችን ለማየት ከአንዱ ዳስ ወደ ሌላው ይዘዋወር ነበር። በኣንደኛው ዳስ ላይ ግን «ርካሽ መስቀሎች» የሚል ምልክት በማየቱ ለራሱ እንዲህ ሲል አሰበ፤ «በአሁኑ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች የሚፈልጉት ርካሽ መስቀሎችን ነው። ሆኖም የጌታ መስቀል ግን ርካሽ አይደለም። ታዲያ የእኔስ መስቀል ለምን ርካሽ ይሆናል?» 

ትሑት አእምሮ ያለው ሰው መሥዋዕት ከመሆን አይሸሽም። እርሱ የሚኖረው ለእግዚአብሔር ክብር እና ለሌሎች ጥቅም ነው፤ ክርስቶስን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ዋጋ የምንከፍል ከሆነ፥ ጌታም ፈቃደኛ ሆኖ በውስጣችን ይሠራል። የጳውሎስም አመለካከት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ለመሆኑ (በቁ.17) በጢሞቴዎስ (ቁ.20) እና በአፍሮዲጡን (ቁ.30) ላይ ተገልጿል። መሥዋዕታችንና አገልግሎታችን አብሮ ከሄደ አገልግሎታችን እውነተኛ የክርስቲያን አገልግሎት ነው። 

«መስጠትና መምራት» በሚለው መጽሐፍ ውስጥ፥ ደግለስ ሃይድ፥ ኮሚኒስቶች እንዴት በሚነድፉት ዕቅድ መሠረት ስኬታማ እንደሚሆኑ ገልጿል። እራሱም ለ20 ዓመታት ያህል የኮሚኒስት ፓርቲው አባል ስለነበረ የአሠራራቸውን ዘዴ በጥልቀት ያውቀዋል። በእነርሱ ዘንድ ለአንድ ሰው «ልክስክስ ወይንም ዝቅተኛ» የሆነ ግዳጅ አይሰጠውም። ለግዳጅ የሚሠማራው ሕይወቱን እንኳን መሥዋዕት ሊያደርግ ለሚችልበት ተልዕኮ ነው። እነርሱ ታላላቅ ፍላጎቶች ያቀርባሉ። እናም የተዘጋጁ ምላሾች ያገኛሉ። ሚስተር ሃይድ ሲናገር፥ ለኮሚኒስት ፕሮግራም መሳካት ከሁሉም ጠቃሚ የሆነው «ለመሠዋት ፈቃደኛ መሆን» ነው። ወጣቶች እንኳን በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ለማጥናት፥ ለማገልገል፥ ለመታዘዝ ስለሚፈልጉ ይህን በሚያስተባብረው ድርጅት ሥር ለመታቀፍ ፈቃደኞች ነበሩ። 

የአንድ ቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ በዓመት «የወጣቶች እሁድ» ፕሮግራም እንዲኖር እቅድ አውጥቶ ነበር። አንዱም አባል፥ ወጣቶቹ በአስተናጋጅነት፥ በጸሎት መሪነትና በልዩ መዝሙር አቅራቢነት ተመድበው እንዲያገለግሉ አሳብ አቀረበ። አንዱ ወጣት ብድግ በማለት «ግልፁን ለመናገር ለምን እኛ ትንንሽ ነገሮችን ብቻ እንድንሠራ እንደምንጠየቅ አልገባኝም። እኛ በዚህ ዓመት መሥራት የምንፈልገው ከበድ ያለ ነገር ነው። ምናልባትም ሥራው ዓመቱን ሙሉ ይፈጅብን ይሆናል። እኛ ልጆች በሙሉ ስለዚህ ነገር ተነጋግረን ጸልየንበታል፥ እኛም ባለአደራዎቹ ከፈቀዱልን ምድር ቤቱን የመማሪያ ክፍል እንዲሆን ወስነናል። እንደገናም ልናድሰው እንፈልጋለን። ከዚህ በተጨማሪም በየሳምንቱ ሽማግሌዎቹን ለመጎብኘት እንፈልጋለን፥ ለዚህም በካሴት የተቀረፁ ስብከቶች ያስፈልጉናል። ተቃውሞ እስካልገጠመንም በየሳምንቱ እሁድ ከሰዓት በኋላ የምስክርነት ጊዜ በመናፈሻ ቦታ ውስጥ ማድረግ እንፈልጋለን። በዚህ ከእናንተ ጋር እንደምንስማማ ተስፋ እናደርጋለን» ብሎ ተናገረ። 

ወጣቱ ልጅ እንደተቀመጠ አዲሱ ጎልማሣ መጋቢ ለራሱ ፈገግ አለ። እርሱም ውስጥ ውስጡን ልጆቹን ዋጋ የሚያስከፍላቸው ነገር እንዲሠሩ ቅስቀሳ አካሂዶ ነበር። እነርሱም በጋለ ስሜት መለሱለት። መጋው ወደ እውነተኛ እድገትና አገልግሎት ለመሄድ መሥዋዕትነት እንደሚያስፈልግ በትክክል የተረዳ ሰው ነበር። 

ትሑት አእምሮ የሚፈተነው ፈቃደኛ ሆነን በምንቀበለው መከራ መጠን ሳይሆን ፈቃደኛ ሆነን በምንከፍለው መሥዋዕት መጠን ነው። አንድ መጋቢ መዘምራኑ የግጥሙን ስንኝ ጌታ ሆይ፥ ሕይወቴን ውሰደውና እንደ ፈቃድህ ይሳካልኝ» በማለት ምትክ «ሚስቴን ውሰዳት እና ሁሉም ይሳካልኝ» ብለው በመዘመራቸው በእጅጉ ተቆጥቶ ነበር። እነኝህ መዘምራን ስለ እነርሱ ሌሎች ሰዎች መሥዋዕት እንዲሆኑላቸው ፈለጉ እንጂ፥ እነርሱ ግን ለሌሎች መሥዋዕት ለመሆን ፈቃደኞች አልነበሩም። 

በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ አንድ ተፃራሪ አባባል አለ። ይኸውም እኛ በበለጠ በሰጠን መጠን አብልጠን መቀበላችንና፥ እኛ መሥዋዕት ባቀረብን ቁጥር እግዚአብሔር አብልጦ የሚባርከን መሆኑ ነው። ትሑት አእምሮም ወደ ደስታ የሚመራን ለዚህ ነው፤ እኛንም በይበልጥ ክርስቶስን እንድንመስል ያደርገናል። ይኸውም መከራውን በተካፈለንበት መጠን ደስታውንም እንካፈላለን ማለት ነው። እርግጥ፥ ፍቅር ምክንያት በሚሆንበት ጊዜ (2፡1)፥ መሥዋዕት ሊለካ ወይም ሊነገር አይችልም። አንድ ሰው ሳያቋርጥ ሁልጊዜ ስላደረገው መሥዋዕት የሚያወራ ከሆነ የሚገዛ ትሑት ኣእምሮ የለውም። 

እናንተስ ክርስቲያን ለመሆን የከፈላችሁት ነገር አለ? 

  1. እግዚአብሔርን አከበረ (2፡9-11) 

በእርግጥ፥ የሁላችንም ትልቁ ግባችን እግዚአብሔርን ለማክበር ነው። በቁጥር 3 ላይ ጳውሎስ «በከንቱ ውዳሴ» አንድም ነገር እንዳናደርግ ያስጠነቅቀናል። ክርስቲያንን ከክርስቲያን ጋር ኣገልግሎትን ከአገልግሎት ጋር የሚያጋጭ ፉክክርን የመሰለ ነገር መንፈሳዊ አይደለም፥ ወይንም አያረካም። ጨርሶም ከንቱና ባዶ ነገር ነው። ኢየሱስ ራሱን ለሌሉች ሲል ትሑት አደረገ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን በጣም ከፍ አደረገው፤ የእርሱ ከፍ መደረግ ለእግዚአብሔር ክብር ያመጣል። 

የእኛ ጌታ ከፍ መደረግ የጀመረው በትንሳኤ ጊዜ ነበር። ሰዎች የክርስቶስን አካል በቀበሩት ጊዜ፥ ያ በሰው እጅ የተደረገበት የመጨረሻው ነገር ነበር። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ሠራለት። ሰዎች በጣም የከፋ ነገር ቢያደርጉበትም እግዚአብሔር ግን ከፍ አደረገው፥ አከበረው። ሰዎች ስሙን መሳቂያና መሳለቂያ ቢያደርጉት፥ ስሙን ቢያጠፉትም፥ አባቱ ታላቅ የሆነ ስም ሰጠው። ልክ እንደ ትሕትናው «ኢየሱስ» የሚል ስም ሰጠው (ማቴ. 1፡21)፥ ከፍም በመደረጉ «ጌታ» የሚል ስም ተሰጠው (ቁ. 11፤ ሐዋ. 2፡32-36 ተመልከት)። ከሙታን ተነሣ፥ በድል ወደ ሰማይ ተመለሰ፥ በአባቱም ዙፋን ተቀመጠ። 

ከፍ በመደረጉ፥ በፍጥረት ሁሉ ላይ በሰማይ፥ በምድር እና ከምድር በታች ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን አለው። ሁሉም ለእርሱ ይሰግዳሉ (ኢሳ. 45፡23)። «ከምድር በታች» የሚለው የጠፉትን ሰዎች ለማመልከት ይመስለኛል። የእግዚአብሔር የሆኑት ወይ በሰማይ ወይ በምድር ናቸው (ኤፌ. 3፡14-15)። አንድ ቀን ሁሉም ይንበረከኩለታል፥ እርሱ ጌታ ነው ብለው ይመሰክራሉ። በእርግጥ ዛሬም ሰዎች ዝቅ ብለውና አምነው የደኅንነትን ስጦታ መቀበል ይችላሉ (ሮሜ 10፡9-10)። በአሁኑ ጊዜ በፊቱ ዝቅ ማለት ደኅንነት ሲሆን፥ በፍርድ ቀን ግን በፊቱ ዝቅ ማለት ይፈረድብሃል ማለት ነው። 

የክርስቶስ የመዋረዱም ሆነ ከፍ የመደረጉ ዓላማ እግዚአብሔር እንዲከብር ነው (ቁ. 11)። ኢየሱስ ለመስቀል ሞት ሲቀርብ፥ በአሳቡ ውስጥ የመጀመሪያውን ስፍራ የያዘው የአባቱ ክብር ነበር፥ «አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሷል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ ልጅህን አክብረው» (ዮሐ. 17:1)። በእውነቱ ለእርሱ የተሰጠውን ክብር ሰጥቶናል (ዮሐ. 17:22)፤ እንዲሁም አንድ ቀን ከእርሱ ጋር በሰማይ እንሆናለን (ዮሐ. 17፡24፥ ሮሜ 8፡28-30 ተመልከት)። ከአንድ ከጠፋ ነፍስ ደኅንነትም በላይ የደኅንነት ሥራ በጣም ትልቅ እና አስደናቂ ነገር ነው። የእኛ ደኅንነት የመጨረሻ ግቡ ለእግዚአብሔር ክብርን ማስገኘት ነው (ኤፌ. 1፡6፡ 12፥ 14)። 

አንድ ትሑት አእምሮ ያለው ሰው የሚኖረው ለሌሎች ነውና ስለዚህ መሥዋዕትነትና አገልግሉትን መጠበቅ አለበት፤ ነገር ግን በመጨረሻ ወደ ክብር ይደርሳል። «እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ» (1ኛ ጴጥ. 5:6)። ዮሴፍ ለ13 ዓመት አገለገለ መከራም ደረሰበት፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከፍ አደረገው፥ የግብጽም ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነ። ዳዊት በልጅነቱ የተቀባ ንጉሥ ነበር። እርሱም የመከራና የችግር ዓመታትን አሳልፏል፥ ግን በጊዜው እግዚአብሔር ከፍ አድርጎ የእስራኤል ንጉሥ አደረገው። 

ለትሑት አእምሮ ደስታ የሚሰማው ሌሎችን በመርዳት ወይም የክርስቶስን መከራ በመካፈሉ ብቻ ሳይሆን በተቀዳሚነት እግዚአብሔርን ለማክበር በመቻሉ ነው (ፊልጵ. 3፡10)። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችንን እንዲያከብሩ ብርሃናችን ይብራ (ማቴ. 5፡16)። ይህንን ክብር አሁን አናየውም፥ ነገር ግን ኢየሱስ ሲመጣ ለታማኝ አገልጋዮቹ ዋጋ (ሽልማት) ሲሰጥ እናየዋለን። 

ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ

Leave a Reply

%d bloggers like this: